Saturday, 26 April 2014 12:20

የኢህአዴግ 1 ለ 5 አደረጃጀት፣ ቀጣዩ ምርጫ እና የተቃዋሚዎች ስጋት

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)

“በልማት ሰበብ አፈና የሚፈፀምበት መዋቅር ነው” - መኢአድ
“1ለ5 አደረጃጀት ለምርጫው ስጋት አይሆንም”  - አንድነት
“ፓርቲያችን፤ ህዝቡ የመዋቅሩ ሰለባ እንዳይሆን የማጋለጥ ሥራ ያከናውናል”  - መድረክ
“ተቃዋሚዎችም እንደ ኢህአዴግ የፈለጉትን አደረጃጀት መፍጠር ይችላሉ”  - መኢአብ
“ኢህአዴግ አፋኝ ሚሊሻ አድርጎ ያዘጋጃቸው ናቸው” - ኢዴፓ
“አደረጃጀቱን ለምርጫ ይጠቀማል የተባለው የሃሰት ውንጀላ ነው”  - ኢህአዴግ

መንግስት 1 ለ 5 የተሰኘውን አደረጃጀት ለፈጣን ልማታዊ እድገት እየተጠቀመበት እንደሆነ ይናገራል፡፡ በገጠር ይሄንኑ አደረጃጀት ለጤና ኤክስቴንሽን ሠራተኞች ተጠቅሞበት ባስገኘው ውጤት፣ ከኢትዮጵያ አልፎ ለአፍሪካ አገራት ምሳሌ ለመሆን መብቃቱንም በኩራት ይጠቅሳል፡፡ ተቃዋሚዎች በበኩላቸው፤ አደረጃጀቱ ፖለቲካዊ ግብን ያነገበ የስለላ መዋቅር ነው፣ የገዥው ፓርቲ የምርጫ ማስፈፀሚያና መቆጣጠሪያ መዋቅር ነው ሲሉ ይተቻሉ፡፡
ኢህአዴግ በ1 ለ 5  አደረጃጀት በመላው ሃገሪቱ የልማት እንቅስቃሴዎችን በማፋጠን ረገድ ስኬታማ እየሆንኩ ነው ቢልም ተቃዋሚዎች ግን ለአፈና እየተጠቀመበት ነው ይላሉ፡፡ “ከክልል ክልል፣ ከወረዳ ወረዳ ተዘዋውረን ህዝብን በአላማችን ስር ማሰለፍና ማደራጀት ቸግሮናል፣ አባላቶቻችንና ደጋፊዎቻችን እስራትና ድብደባን ጨምሮ ለብዙ እንግልት እየተዳረጉ ነው፣ እንኳንስ ሰፊ ህዝባዊ መሰረት ያለው አደረጃጀት ልንፈጥር በአንድ ወረዳ ውስጥ እንኳን  ፅ/ቤት መክፈት አቅቶናል፣ ከአዲስ አበባ ህዝብ የማደራጀት ተልዕኮ ተሰጥቷቸው የተሸኙ አመራሮች፣ የወረዳ ሹማምንት ሰለባ ይሆናሉ” የሚሉት ተቃዋሚ ፓርቲዎች፤ ገበሬው 1 ለ 5 ካልተጠረነፈ፣ ማዳበሪያና ምርጥ ዘር የመሳሰሉ የግብርና ግብአቶችን ማግኘት አይችልም ሲሉ ችግሮችን ይዘረዝራሉ፡፡
ኢህአዴግ 1ለ5 አደረጃጀትን ከምንም በላይ ለምርጫ ማስፈፀሚያነት ነው የሚፈልገው ሲሉ የሚከራከሩት ተቃዋሚዎች፤ በምሳሌነትም ያለፉትን ሁለት ምርጫዎች ይጠቅሳሉ፡፡ በ2002 ዓ.ም አገራዊ ምርጫ “ሊግ” እና “ፎረም” ኢህአዴግን በማስመረጥ ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል የሚሉት ተቃዋሚዎች፤ በ2005 ዓ.ም የአካባቢና ማሟያ ምርጫ ደግሞ የመንግስት ሰራተኛ የሆኑ የጤና ኤክስቴንሽንና የግብርና ባለሙያዎችን ጨምሮ በ1 ለ 5 አደረጃጀት በሚገባ ተጠቅሞባቸዋል ይላሉ፡፡ 12 ወራት ብቻ ለቀሩት ቀጣዩ ብሄራዊ ምርጫም ገዥው ፓርቲ እነዚህን የመንግስት መዋቅሮችና የህዝብ አደረጃጀቶች እንዲሁም ሌሎች አዳዲስ የአደረጃጀት ስልቶችን ለምርጫ ቅስቀሳ እና ድጋፍ ማሰባሰቢያ መጠቀሙ ፈጽሞ አያጠራጥርም፤ ምክንያቱም ከዚህ በፊትም አድርጐታል በማለት ሽንጣቸውን ገትረው ይከራከራሉ - ተቃዋሚዎች፡፡
“የገዥው ፓርቲ የጨዋታ ህግ 1 ለ 5፣ 1 ለ 40 እና 1 ለ 100 መሆኑን ደርሰንበታል” ያሉት የመላ ኢትዮጵያውያን አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ሊቀመንበር አቶ አበባው መሃሪ፤ “በልማት ሰበብ አፈና የሚፈፀምበት መዋቅር ነው” በማለት 1ለ5 አደረጃጀትን ይከሳሉ፡፡ ኢህአዴግ እንደሚለው ለልማት ብቻ ቢሆን ኖሮ፤ ተማሪዎች በ1 ለ5 ባልተደራጁ ነበር የሚሉት ሊቀመንበሩ፤ መዋቅሩ ገበሬውንና ነዋሪውን እንዲሁም የመንግስት ሰራተኛውን ከገዥው ፓርቲ አስተሳሰብ ውጪ እንዳይንቀሳቀሱ የሚያስር እንደሆነ ጠቅሰው፤ በመዋቅር ወደታች ከሚወርደው አስተሳሰብ ያፈነገጠም ቅጣት ይጣልበታል ብለዋል፡፡ “በገጠር የ1 ለ 5 አደረጃጀት አባል ያልሆነ ገበሬ፤  ማዳበሪያና የግብርና ግብአቶች እንዳያገኝ ከመከልከሉም ባሻገር ከሌላው የህብረተሰብ ክፍልም እንዲገለል ይደረጋል፡፡ መንግስት ይህን በማድረጉ አፈናውን አጠናክሮ መቀጠል ይችል ይሆናል፤ የህዝብ ተወዳጅነትንና ቅቡልነት ማግኘት ግን አይችልም፡፡” እንዲህ ዓይነቱ ሴራ ኢህአዴግን በ2007 ምርጫ ከመሸነፍ አይታደገውም የሚሉት አቶ አበባው፤ ይሁን እንጂ አደረጃጀቱ በመራጩ ህዝብ ላይ በነፃነት የፈለገውን እንዳይመርጥ ስጋት ማሳደሩ አይቀርም ባይ ናቸው፡፡ ምንም እንኳን ኢህአዴግ በአፉ ግልጽና ፍትሃዊ ምርጫ እንደሚካሄድ በተለያዩ አጋጣሚዎች ሲናገር ቢደመጥም፤ ይሄ አደረጃጀት ግን ትክክለኛ ምርጫ እንዳይካሄድ የአፈና መዋቅር መዘርጋቱን የሚያረጋግጥ ነው ብለዋል፤ አቶ አበባው፡፡ ይህን አስጊ መዋቅር ለመበጣጠስና ለማክሸፍ መፍትሄው በምርጫው ተሳታፊ የሆኑ ፓርቲዎች ሁሉ ህብረት ፈጥረው በጋራ መቆማቸው ነው ያሉት አቶ አበባው፤ መኢአድ የጉዳዩን አሳሳቢነት ከግምት ውስጥ በማስገባት ለሰብአዊ መብት ኮሚሽን፣ ለፍትህ ሚኒስቴር እና ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት የአቤቱታ ደብዳቤ ማቅረቡን ገልፀዋል፡፡
የአንድነት ፓርቲ የድርጅት ጉዳይ ኃላፊ አቶ ዳንኤል ተፈራ በበኩላቸው፤ ፓርቲያቸው እስካሁን ህዝብን ለማደራጀት ባደረጋቸው እንቅስቃሴዎች በርካታ የአፈና ተግባራት እንደተፈፀሙበት ጠቅሰው፤ የ1 ለ 5 አደረጃጀት በምርጫው ላይ የሚፈጥረው ስጋት እምብዛም ነው ሲሉ ያቃልሉታል - መንግስትን መቀየር የፈለገ ህዝብ፣ የአፈና መዋቅር ሊገድበው እንደማይችል በመግለፅ፡፡ በአሁን ወቅት ፓርቲያቸው ከ34 በላይ በሚሆኑ የሀገሪቱ ዞኖች ቢሮዎችን በማደራጀት፣ ወደ ወረዳዎች ወርዶ  ለህዝቡ ተደራሽ ለመሆን እየጣረ መሆኑን የጠቆሙት ኃላፊው፤ በነዚህ ሂደቶች ውስጥ የወረዳ ሹማምንት የሚፈፅሙት ወከባና እንግልት ከአቅም በላይ እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡ በአዲስ አበባ አዳዲስ አባላት ፎርም ሞልተው ከፓርቲው ጽ/ቤት ሲወጡ ፀጉረ ልውጥ ግለሰቦች ክትትል ያደርጉባቸዋል የሚሉት አቶ ዳንኤል፤ ይሄም የአፈና መዋቅሩ ይበልጥ መጠናከሩን ይጠቁማል ባይ ናቸው፡፡  እንዲያም ሆኖ ግን ይህ ለፓርቲያችን ፈታኝ ጉዳይ ተብሎ ሊጠቀስ አይችልም ያሉት ኃላፊው፤ ህዝቡ ጋ ቁርጠኝነት መኖሩን በተለያዩ አጋጣሚዎች ስለተረዳን፣ ገዥው ፓርቲ 1 ለ 5ን ጨምሮ የተለያዩ መዋቅሮችን ዘርግቶ ዲሞክራሲያዊ እንቅስቃሴዎችን ለመገደብ እየሞከረ ቢሆንም፣ በምርጫው ለማሸነፍ የሚደረገውን ትግል አጠናክረን ከመቀጠል ወደ ኋላ አንልም ብለዋል፡፡
ኢህአዴግ ኃላፊነት የሚሰማውና ለመድብለ ፓርቲ መጐልበት የሚጨነቅ ፓርቲ አይደለም ሲሉ የተቹት አቶ ዳንኤል፤ ሁሌም ምርጫን ህገወጥ በሆኑ አደረጃጀቶች ለማሸነፍ ሲታትር ነው የሚታየው ብለዋል፡፡ የ1 ለ 5 አደረጃጀት፤ በዲሞክራሲ ግንባታ ሂደት ላይ ነኝ ከሚል መንግስት የማይጠበቅ ኢ-ዲሞክራሲያዊ የሆነ አደረጃጀት ነው ያሉት ሃላፊው፤ ይሄም ሳያንሰው በገጠሩ የሃገሪቱ ክፍል ሴፍቲኔት፣ ጤና ኤክስቴንሽንና የግብርና ኤክስቴንሽን የመሳሰሉ የመንግስት መዋቅሮችን ፓርቲው ለግል ጥቅሙ ያውላል ሲሉ ይከሳሉ፡፡ አሁን ደግሞ “የህዝብ ክንፍ” በሚባል አደረጃጀት እድሮችን፣ እቁቦችንና የመሳሰሉ ማህበራዊ ተቋማትን ለመቆጣጠር እየተሞከረ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ዳንኤል፤ ፓርቲያቸው እነዚህን መዋቅሮችና አደረጃጀቶች ለመስበር የተለያዩ ስልቶችን ነድፎ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ የፓርቲው አባላት በአደረጃጀቱ ውስጥ ሰርገው እንዲገቡ በማድረግ መንግስት ለልማት በሚል የዘረጋውን መዋቅር፣ ለፖለቲካ አላማ እንዳያውል ቁጥጥር መጀመራቸውን ጠቁመዋል፡፡ በዚህም ተልዕኦ አባላቶቻቸው ውጤታማ የሆነ ተግባር እያከናወኑ እንደሆነ አቶ ዳንኤል አክለው ገልፀዋል፡፡
ምርጫ የገዥም የተቃዋሚ ፓርቲም አይደለም፤ ህዝብ የራሱን ውሳኔና አቅሙን የሚያሳይበት ነው የሚሉት የአንድነት ሃላፊ፤ “በሃገሪቱ ካለው ከፍተኛ የሆነ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ቀውስ አንፃር ገዥው ፓርቲ ያደራጀውን መዋቅር ፈርቶ ህዝቡ የምርጫ ካርዱን የማይገባ ቦታ አይጥልም” ሲሉ ይሟገታሉ፡፡ አቶ ዳንኤል ሃሳባቸውን ሲያጠቃልሉም፤ ፓርቲያቸው በተለያዩ የንቅናቄ መንገዶች ህብረተሰቡን ለማንቃት እየተጋ በመሆኑ፣ የ1 ለ 5 አደረጃጀት ለምርጫው ስጋት አይሆንም ብለዋል፡፡
“ገዥው ፓርቲ በተጨባጭ በ2002 ምርጫ  የ1 ለ 5 አደረጃጀትን ‘የምርጫ ሰራዊት’ ብሎ ለምርጫ አላማ እንደተጠቀመበት እናውቃለን” የሚሉት ደግሞ የመድረክ ሥራ አስፈፃሚ አባል አቶ ጥላሁን እንደሻው ናቸው፡፡ መድረክ እነዚህ አደረጃጀቶች በምርጫ ሂደት ውስጥ እንዳይገቡ በሚል እንደመደራደሪያ ያቀረበው ጥያቄ እስከዛሬ መልስ አለማግኘቱን የጠቆሙት አቶ ጥላሁን፤  በቀጣዩ ምርጫም የ1 ለ 5 አደረጃጀት ተፅዕኖ ላለማድረጉ ምንም ዋስትና የለም ሲሉ ስጋታቸውን ገልፀዋል፡፡ “በአደረጃጀቱ ውስጥ ጠርናፊ የሆነው ግለሰብ፣ ዋና ተግባሩ ሌሎች በስሩ ያሉ ግለሰቦችን እንቅስቃሴ መከታተል ነው” ያሉት አቶ ጥላሁን፤ ድርጊቱ የግለሰቦችን ነፃነት የሚፃረርና ኢ-ዲሞክራሲያዊ ነው ሲሉ ይነቅፋሉ፡፡
መዋቅሩ በዲሞክራሲ ስርአት ግንባታ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ የሚያሳርፍ እንደሆነ የተናገሩት የመድረክ ሥራ አስፈፃሚ አባል፤ ፓርቲያቸው አሰራሩን በጥብቅ እየተቃወመ፣ ህብረተሰቡ የመዋቅሩ ሰለባ እንዳይሆን በተለያዩ መንገዶች የማጋለጥ ስራ ያከናውናል ብለዋል፡፡
አረና ትግራይ ለሉአላዊነት ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ጎይቶም ፀጋዬ በበኩላቸው፤ የ1 ለ 5 አደረጃጀት ለምርጫው እንቅፋት ሊሆን ይችላል የሚል ስጋት አላቸው፡፡ “ፍትሐዊና ሚዛናዊ ምርጫ ይካሄዳል የሚባል ከሆነ፣ የምርጫ ቦርድም ሆነ ገዥው ፓርቲ በዚህ ጉዳይ ላይ ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር ድርድር ሊያደርጉ ይገባል” ባይ ናቸው፡፡ ኢህአዴግ አውራ ፓርቲ ሆኖ ለመቀጠል እነዚህን መዋቅሮች እየተጠቀመ ነው የሚሉት አቶ ጎይቶም፤ በልማት ስም የተዋቀረውን አደረጃጀት ለፖለቲካ አላማ ሊጠቀምበት እንደሚችል ጠቅሰው፤ አደረጃጀቱ በህዝቡ ዘንድ ተቀባይነት  እንዳይኖረው ማስገንዘብ ከፓርቲዎች ይጠበቃል ይላሉ፡፡
ኢህአዴግን ጨምሮ የተወሰኑ ተቃዋሚዎች የተካተቱበት የፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አባል የሆነው የመላው ኢትዮጵያውያን ብሄራዊ ንቅናቄ (መኢአብ) ሊቀመንበር አቶ መሳፍንት ሽፈራው ግን የሌሎቹን ተቃዋሚ ፓርቲዎች ሃሳብና ስጋት አይጋሩም፡፡ እንደውም ተቃዋሚዎቹን ይወቅሳሉ፡፡ የማደራጀት መብት ለኢህዴግ ብቻ አልተሰጠም ያሉት ሊቀመንበሩ፤ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ይህን መብት የመጠቀም የቤት ስራቸውን በአግባቡ ስላልተወጡ ነው የተበለጡት ይላሉ፡፡ ተቃዋሚዎችም እንደ ኢህአዴግ የፈለጉትን አደረጃጀት መፍጠር ይችላሉ የሚሉት አቶ መሳፍንት፤ የ1 ለ 5 አደረጃጀት ችግር ሊፈጥር የሚችለው ለልማት ተብሎ የተቀየሰው መዋቅር ለፖለቲካ አላማ ከዋለ ነው ሲሉ ወደ ተቃዋሚዎች ሃሳብ ይመለሳሉ፡፡ ፓርቲያቸው ጉዳዩን ለመገምገም እየተዘጋጀ መሆኑን በመጠቆምም ከግምገማው በኋላ መግለጫ እንደሚሰጡበት ተናግረዋል - ሊቀመንበሩ፡፡
የኢትዮጵያውያን ዲሞክራቲክ ፓርቲ (ኢዴፓ) ሊቀመንር አቶ ጫኔ ከበደ በበኩላቸው፤ ጉዳዩን ቁጭ ብለው እንደገመገሙት  ይናገራሉ፡፡ “መንግስት የልማት ቡድን ነው ይላል፤ ኢህአዴግ እንደ ፓርቲ ደግሞ ዴሞክራሲያዊ ስርአት በዚህች ሃገር እንዳይሰፍን የአፈና ሚሊሻ አድርጎ ያዘጋጃቸው ናቸው በሚል ነው በግምገማችን የፈረጅናቸው” ያሉት ሊቀመንበሩ፤ መዋቅሩ በቀጣይ ምርጫ ችግር ፈጣሪ እንቅፋት ይሆናል የሚል ስጋት አለን ይላሉ፡፡ የማደራጀት መብት የተቃዋሚ ፓርቲዎችም ነው የሚለው አባባል አያስማማንም የሚሉት አቶ ጫኔ፤ እንኳንስ በህዝቡ ውስጥ ዘልቆ አጀንዳን ለማስረፅ ይቅርና ሦስትና አራት ሆኖ የተሰበሰበም በጥርጣሬ የሚታይበት ሃገር ላይ ነው ያለነው ሲሉ ችግሩን ያስረዳሉ፡፡ ኢዴፓ አፈናውን ለመቋቋም ሚስጥራዊ አደረጃጀቶችን ይጠቀማል ያሉት ሊቀመንበሩ፤ መዋቅሩን ፓርቲያቸው እንደማይቀበለውና ድርጊቱንም “አፋኝ ሚሊሻዎችን እንደማደራጀት” እንደሚቆጥረው ተናግረዋል፡፡
ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ አንድ የፖለቲካ ምሁር እንደሚሉት፤ ገና ከአሁኑ የተነሳው ውዝግብ በምርጫ ማግስት ለሚከሰቱ ቅራኔዎችና አለመግባባቶች ትልቅ ሰበብ ሊሆን ስለሚችል፣ ኢህአዴግን ጨምሮ ፓርቲዎቹ ሁሉ በጉዳዩ ላይ በሰለጠነ መንገድ ተወያይተው መግባባት ላይ መድረስ አለባቸው፡፡
በአንድ ክልል ከተማ ስለ 1ለ5 አደረጃጀት ግንዛቤ ለማስጨበጥ የተበተነ ሠነድ፣ አደረጃጀቱ በኢኮኖሚ ከበለፀገችው የጃፓን መንግስት የሚጠቀመው እንደሆነና ከዚያም እንደተኮረጀ ይጠቁማል፡፡ አላማውም የልማት ሠራዊት በመገንባት ዜጐችን በየተሠማሩበት ዘርፍ ብቁና ውጤታማ ለማድረግ እንደሆነ  ሰነዱ ያብራራል፡፡
በትምህርት ሚኒስቴር ተዘጋጅቶ የቀረበ ስለ አደረጃጀቶች የሚተነትን ሌላ ሰነድ ደግሞ ተማሪዎችን 1ለ5 ማደራጀት፣ ተማሪዎች በየትምህርታቸው ውጤታማ ሆነው እንዲጨርሱና የትምህርት ብክነትን ለመቀነስ ዋነኛ መፍትሔ መሆኑን ይገልፃል፡፡ የየቡድኑ ሃላፊነት እና ተግባርም የክፍሉ ተማሪዎች ውጤትና ስነምግባር ተቀራራቢ ደረጃ እንዲደርስ፣ የተሻሉ ተማሪዎች ሌሎችን እንዲረዱ፣ የተማሪዎች የመተጋገዝና የመረዳዳት ባህል እንዲዳብር፣ ያለአግባብ የትምህርት ክፍለጊዜ እንዳይባክን ማድረግና ሌሎችንም ይዘረዝራል፡፡
ያነጋገርናቸው የ1ለ5 አደረጃጀት ተሣታፊዎች በበኩላቸው፤ የስለላ አይነት መዋቅር ነው በማለት የተቃዋሚ  ፓርቲ መሪዎችን ሃሳብ ይጋራሉ፡፡ ስማቸው እንዳይገለፅ የጠየቁ የአንድ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ሠራተኛ እንደሚሉት፤ የአደረጃጀቱ አላማ በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ውስጥ ያሉ የሥራ ክፍሎች፣ በየዘርፋቸው ውጤታማ እንዲሆኑ  ምክክርና ውይይቶች የሚካሄድበት ቢሆንም የውይይቱ ፍሬ ሃሳብ ለበላይ አደረጃጀቶች ሪፖርት ሲደረግ፣ ተቃራኒ ሃሳብ ያንፀባረቁትን ግለሰቦች ለፖለቲካዊ ጥቃት ይዳርጋል፡፡ በመስሪያ ቤታቸው ውስጥ ያሉት አደረጃጀቶች በሙሉ በኢህአዴግ አባልነታቸው በሚታሙ ግለሰቦች እንደሚመሩ የገለፁት እኚሁ አስተያየት ሰጪ፤ ብዙውን ጊዜ በውይይትና በምክክር ወቅት ስለአብዮታዊ ዲሞክራሲና ስለልማት ትልሞቹ ገቢራዊነት በስፋት ይደመጣል ይላሉ፡፡ ይህም አደረጃጀቱ ከፖለቲካ ነፃ አለመሆኑን ያሳያል ባይ ናቸው አስተያየት ሠጪው፡፡ በስልጣን ላይ ያለው መንግስት ከሚከተለው ርዕዮተ አለም ውጪም ሌላ ሃሳብ ማራመድ እንደማይቻል አክለው ገልፀዋል፡፡
በዚሁ መስሪያ ቤት ውስጥ ያለው የ1 ለ5 አደረጃጀት ተዋረዳዊ ሲሆን ከስር ያለው የ1 ለ 5 አደረጃጀት መሪ ከሌሎች አደረጃጀቶች መሪዎች ጋር እንደገና 1ለ5 ይደራጃል፤ እንደዚያ እያለ እስከ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች ይደርሳል፡፡ ከላይ የሚቀመጠው ደግሞ የመንግስት ሹመኛ የሆነ ግለሰብ ነው ብሏል፡፡
በጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት የህዝብ ተሣትፎና አደረጃጀት ሚኒስትር ዲኤታ አቶ ደስታ ተስፋው፤ መንግስት ስለዘረጋው 1 ለ5 አደረጃጀት ሲያብራሩ፤ “አደረጃጀቱን በርካታ የእስያ ሃገሮችን ጨምሮ በአፍሪካ ውስጥም ታንዛንያን የመሳሰሉ ሀገሮች እየተጠቀሙበት ውጤታማ እየሆኑ ነው፤አደረጃጀቱ ህዝብን ለልማትና ለመልካም አስተዳደር አደራጅቶ ተግባራዊ ለማድረግ የተፈጠረ ነው፡፡ የህዝብን ጉልበት አስተባብሮ፣ በጋራ ተደራጅቶ ያሉበትን የአፈፃፀም ችግሮች በጋራ ቀርፎ እቅድ ላይም ተወያይቶ በጋራ የሚሠራበት አደረጃጀት ነው” ይላሉ፡፡ በዚህ ሂደትም ግቦቹ ሲሳኩ ተጠቃሚ የሚሆነው ራሱ ህብረተሰቡ ነው ይላሉ፤ አቶ ደስታው፡፡
ከላይ ጀምሮ እስከታች ያለው አደረጃጀት ዋና አላማው፣ በልማት ሠራዊት ተደራጅቶ እንዲንቀሳቀስ ማድረግ ነው የሚሉት ሃላፊው፤ የልማት ሠራዊት ሲባልም የተመጣጠነ ክህሎትና አስተሳሰብ በመፍጠር፣ ለልማትና ለመልካም አስተዳደር ማዋል ነው፣ በዚህ መንገድም የልማት ሠራዊቱ ትልቅ ለውጥ እያመጣ ነው ባይ ናቸው፡፡ በማስረጃነትም በተፈጥሮ ሃብት ጥበቃና በመስኖ ልማት የመጡትን ለውጦች ይጠቅሳሉ፡፡ እነዚህ ለውጦች ዝም ብለው የመጡ ሳይሆን ህዝቡና የመንግስት አደረጃጀቶች ተቀናጅተው ያመጧቸው እንደሆኑ በአጽንኦት የሚገልፁት ሃላፊው፤ በ1 ለ5 አደረጃጀት ውስጥ የሚሳተፍ ሁሉ የኢህአዴግ አባል ነው ማለት አይደለም ይላሉ፡፡  “የኢህአዴግ አደረጃጀት የተለየ ነው፡፡ ከላይ ጀምሮ መሠረታዊ ድርጅት፣ ህዋስ እያለ እስከታች ይወርዳል፡፡ ይሄኛው ግን የተቃዋሚ ደጋፊና አባል ጭምር የሚሳተፍበት የመላው ህዝብ አደረጃጀት ነው፡፡ የተቃዋሚ አባል በመሆኑ በአደረጃጀቱ አትገባም አይባልም” የሚሉት አቶ ደስታ፤ የኢህአዴግ አባል የሆኑትም  ከድርጅቱ መዋቅር ባሻገር በዚህ አደረጃጀት ውስጥም መሳተፍ ይችላሉ ብለዋል፡፡
የ1 ለ5 አደረጃጀት የኢህአዴግ አባላት ብቻ የተደራጁበት ነው ተብሎ የሚገለፀው ስህተት ነው ያሉት አቶ ደስታ፤ ለልማት ህዝቡ ቢደራጅ ምንድን ነው ክፋቱ ሲሉ ይጠይቃሉ፡፡ ኢህአዴግ አደረጃጀቱን ለምርጫ ይጠቀማል የተባለውም የሃሰት ውንጀላ ነው የሚሉት ሃላፊው፤ ”ምርጫ የህዝብ ጉዳይ ነው፣ ነገር ግን ምርጫው ሠላማዊና ፍትሐዊ እንዲሆን፣ ለምርጫ ምዝገባና ተሳትፎ ህዝብ እንዲወጣ ለማድረግ ተመሳሳይ አደረጃጀቶችን መጠቀም ሃጢያት አይደለም፣ ህዝብ የሚመርጠው ግን የሚቀርብለትን የፖሊሲ አማራጭ መሠረት አድርጐ ነው” ብለዋል፡፡ 

Read 7299 times