Saturday, 19 April 2014 11:57

እንኳን ለቀለም አብዮተኞች ለፋሽስት ኢጣልያም እጅ አልሰጠንም!

Written by  ኤልያስ
Rate this item
(15 votes)

ኒዮሊበራሎች ያሴሩት “የቀለም አብዮት” ቦሌ ኤርፖርት ከሸፈ  
የቀለም አብዮት ፍቱን መድሃኒት- የህዝብ ፍቅር ነው!
ሰኞ እለት ምሽት ይመስለኛል። እቃ ለመሸመት ወደ አንድ ሱቅ ጎራ ብዬ ሳለሁ ነው የሰማሁት - የሬዲዮ የቀጥታ የስልክ ውይይቱን። በየትኛው ጣቢያ እንደነበር ግን አላወቅሁም። ደዋይዋ  ተማሪ ናት። ከጋዜጠኛዋ ጋር ሰላምታ ከተለዋወጡ በኋላ፣ ሰፈራቸው ውሃ ጠፍቶ በጣም እንደደበራት በምሬት  ተናገረች - ተማሪዋ። ጋዜጠኛዋ የውሃው መጥፋት የተከሰተው እየተከናወነ ባለው የልማት ሥራ የተነሳ በመሆኑ ብዙም  ልትማረር እንደማይገባት  አስረግጣ ነገረቻት። (የእድገት ምስቅልቅል ነው ማለቷ እኮ ነው!) ደዋይዋ ግን የጋዜጠኛዋ መልስ  የተዋጠላት አትመስልም። “ኮብልስቶን ሲሰሩ እኮ ነው ---” ስትል አከለችላት። (“አውቀው ነው እንጂ “ውሃችን ሳትጠፋ ኮብልስቶኑን መስራት ያቅታቸዋል?!” የሚል ሃሳብ ውስጧ የቀረ ይመስላል)  
 ጋዜጠኛዋ በፍጥነት መለሰችላት “እንደውም ሰምተሽ ከሆነ --- አገራችን በኮብልስቶን  ዓለም አቀፍ ሽልማት አግኝታለች ----እና ለልማት የሚከፈል መስዋዕትነት ነው”  
“ቢሆንም  ይሄ እኮ መሠረታዊ ፍላጎት ነው” አለቻት ተማሪዋ ድምጿን መረር አድርጋ።
“ መሠረታዊ ፍላጎት ቢሆንም ለልማት ሲባል አንድ ሁለት ቀን ብትታገሽ ምንም አይደለም --- አየሽ እኛ መስዋዕትነት ከፍለን ለመጪው ትውልድ ያደገች አገር ማስረከብ አለብን”   
“እኛንም ይመለከታል  ማለት ነው?” ጠየቀች ደዋይዋ ተማሪ። (“መስዋዕትነቱ ለኛ አይደለም ወይ?” የምትል ትመስላለች!)
“እየቀለድሽ ነው አይደል---እናንተ ኢትዮጵያውያን አይደላችሁም  እንዴ? ይሄ እኮ  ሁሉንም ኢትዮጵያዊ የሚመለከት ጉዳይ  ነው” በመገረም በተሞላ ቅላፄ መለሰችላት።
ከደዋይዋ ድምፀት እንደተረዳሁት የጋዜጠኛዋ ምላሽ ያረካት አትመስልም። ለነገሩ እንኳን ታዳጊዋን  እኔንም አላረካኝም። አረ እንደውም አናዶኛል። (“ልማት ላይ ስለሆንን አንድ ሁለት ቀን ውሃ ባትጠጪ ምን ትሆኛለሽ” ማለት እኮ ነው የቀራት!) በነገራችሁ ይሄ “ልማት” ---- ለብዙ ዳተኞች ተመችቷቸዋል። (የሆነውንም ያልሆነውንም በልማቱ እያሳበቡ ለሽ ይላሉ!)
እስቲ አሁን ደሞ ከሬዲዮ ወጥተን ወደ ቴሌቪዥን እንግባ።  
  ባለፈው ሳምንት ኢቴቪ “የቀለም አብዮት ሰለባዎች” በሚል ርዕስ የተዘጋጀ  ዶክመንታሪ በቅዳሜ ምሽት ፕሮግራሙ እንደሚያቀርብ ደጋግሞ ሲያስተዋውቅ፣ አንድ ለየት ያለ መረጃ ወይም ፍንጭ እጁ እንደገባ እርግጠኛ ነበርኩ። ለምን መሰላችሁ? ኢቴቪ ከመሬት ተነስቶ  ዶክመንተሪ አይሰራማ። አንድም ለማጋለጥ ነው አሊያም ለማስጠንቀቅ። (በ“አንድነት” ላይ ያነጣጠረው አኬልዳማ  ትዝ አይላችሁም?) በነገራችሁ ላይ---ኢቴቪ  በአኬልዳማ  ሳቢያ  ፈፅሞ ያላሰበው ጣጣ ውስጥ ገብቷል። አንድነት የተባለ ተቃዋሚ  ፓርቲ፣ በስም ማጥፋት ወንጀል ፍርድ ቤት ይገትረኛል ብሎ አስቦም አልሞም አያውቅም። (ህጉን አያውቅም  እንዴ?) ከተከሰሰም በኋላ  ቢሆን  ይፈረድብኛል ብሎ አላሰበም። ለምን መሰላችሁ ? ራሱን እንደ “ንጉስ” ነበር የሚቆጥረዋ (“ንጉስ አይከሰስ ሠማይ አይታረስ አሉ!”)
ኢቴቪን በቅርብ የሚያውቁት እንደሚናገሩት፤ ይሄን የመታበይ ስሜት ለመጀመርያ ጊዜ የፈጠሩበት ንጉሱ ናቸው። በደርግም ንጉስ በሌለበት እንደንጉስ ያደርገው ነበር -ኢቴቪ። ብቻ የአገሪቱ መንግስታት ሁሉ   እንደ አያት አቅብጠው ነው ያሳደጉት! ዘንድሮ ግን ከባድ ፈተና ገጠመው። በአንድነት የተከሰሰው ኢቴቪ፤ ስምና ክብር አጉድፈሃል ተብሎ የጎደፈውን ስምና ክብር የሚመልስ ማስተባበያ እንዲያስተናግድ በፍርድ ቤት ተወስኗል። ምንም እንኳን ይግባኝ እጠይቃለሁ ቢልም። እርግጠኛ ነኝ ከዚህ በኋላ ያለአስተማማኝ መረጃ የሰው ስም አያጠፋም። (The hard way እኮ ነው የተማረው!) መቼም ኢህአዴግም ይሁን መንግስት የሰው ስምና ክብር እንዲያጎድፍ አያስቸግሩትም። (ቢያስቸግሩትም በጄ ማለት የለበትም!)   
 እናላችሁ ---ቅዳሜ ደርሶ “የቀለም አብዮት ሰለባዎች” የተሰኘውን ዶክመንታሪ ለማየት ቸኩዬም ጓጉቼም ነበር። እንደማይደርስ የለም ቀኑ ደረሰ፤ እንደጠበቅሁት ግን  አልነበረም። (አይረባም አልወጣኝም!) ከዚህ በፊት የማይታወቅ ምስጢር ወይም ፍንጭ አልሰጠኝም ማለቴ ነው። በእርግጥ ለብዙዎች ስለቀለም አብዮት አፈጣጠርና ምንነት ደህና ግንዛቤ ያስጨብጣል። እናንተ---ይሄ የቀለም አብዮት ቀላል ኢንቨስትመንት መሰላችሁ! የቢሊዮን  ዶላር ፕሮጀክት እኮ ነው። አሜሪካ በዩክሬን ለተካሄደው ብርቱካናማው አብዮት ስንት እንደመደበች ታውቃላችሁ? 5 ቢሊዮን  ዶላር! (ለአንድ አብዮት ብቻ?)
        የቀለም አብዮት ላይ ያነጣጠረው ዶክመንታሪ፤ በአብዛኛው በቀለም አብዮት እየተቀጣጠለች ባለችው ዩክሬን ላይ የሚያተኩር ሲሆን በሦስት ባለሙያዎች አስተያየት ተደግፎ የቀረበ ነው። “የቀለም አብዮት ተንታኞች” ብያቸዋለሁ። እኔ የምላችሁ----- ይሄ የቀለም አብዮት ስንት ስም ነው ያለው! በነገራችሁ ላይ የቀድሞው ጠ/ሚኒስትር መለስ ዜናዊ  (ነፍሳቸውን ይማረውና!) ብርቱካናማውን አብዮት “የአትክልትና ፍራፍሬ አብዮት” ሲሉ ተሳልቀውበት ነበር። እንዲያም ሆኖ ግን የዩክሬንን ብርቱካናማ አብዮት ለመድገም አስበዋል የተባሉትን ተቃዋሚ ፓርቲዎች “ብትሞክሯት ውርድ ከራሴ በሉ” እንዳሏቸው ምንጮች  ይጠቁማሉ።
“የቀለም አብዮት” ሰለባዎች በሚለው ዶክመንተሪ ላይ  አስተያየት የሰጡት ተንታኞች እንደሚሉት፣ ምዕራባውያን በ97 ምርጫ  በጦቢያችን  ላይ የቀለም  አብዮት የማቀጣጠል እቅድ የነበራቸው ቢሆንም አልተሳካላቸውም።
እስካሁን በዓለም የተለያዩ አገራት በርካታ  የቀለም አብዮቶች መካሄዳቸውን  ያወሱት ተንታኞቹ፤ የምዕራባውያኑ ዓላማ አልታዘዝ ያሏቸውን መንግስታት በህዝባዊ አመፅ ከሥልጣን በማውረድ  ርዕዮተ ዓለማቸውን የሚያስከብርላቸውን  የትሮይ ፈረስ ቤተመንግስት ማስገባት  ነው ብለዋል። የቀለም አብዮት የማይሳካበት አገር ብቸኛዋ  ቬኔዝዌላ እንደሆነች የገለፁት አንዱ ተንታኝ ፤ እ.ኤ.አ ከ1999 ጀምሮ አገሪቱን የመሩት ሁጎ ቻቬዝ በህዝብ ዘንድ ተወዳጅ ስለነበሩ በቀለም አብዮት ከሥልጣን እንዲወርዱ ቢደረግም ህዝቡ አብዮቱን በማክሸፍ ወደ ሥልጣን መልሷቸዋል ብሏል። (የቀለም አብዮት ፍቱን መድሃኒት- የህዝብ ፍቅር ነው!)
ምዕራባውያን ኢትዮጵያን በቀለም አብዮት ለማፈራረስ ይሞክሩ  ይሆን? በሚል ለቀረበው ጥያቄ ተንታኞቹ  ሁለት የተለያዩ ምላሾች ሰጥተዋል። ሊሞክሩ ይችላሉና አይሞክሩም በሚል። ኢትዮጵያ ከምዕራባውያን ጋር በሚያስማሟት ጉዳዮች ላይ ተባብራ  እየሰራች መሆኑን የገለፁት ተንታኙ፤አገሪቱን በቀለም አብዮት ለማፈራረስ  የሚፈልጉበት ምክንያት የለም ይላሉ። ምዕራባውያን የማይፈልጓቸውን መንግስታት የሚቀጡት የልማት እርዳታ  በመከልከል መሆኑን በመጠቆምም፤ በእኛ አገር ሁኔታ ግን የልማት እርዳታ  በየጊዜው እየጨመረ መምጣቱን ገልፀዋል። (“ብሩህ ተስፈኛ” ብያቸዋለሁ!)  ሌላኛው የቀለም አብዮት ተንታኝ በበኩላቸው፤ ምእራባውያኑ በጦቢያ ላይ የቀለም አብዮት ሊያቀጣጥሉ ይችላሉ ባይ ናቸው። ለዚህ ዋና ሰበቡም የርዕዮተ ዓለም ልዩነት መሆኑን ይናገራሉ። ኢህአዴግ መራሹ መንግስት አስፈላጊ በሆኑ የኢኮኖሚ ዘርፎች ላይ ጣልቃ መግባት ይፈልጋል (ቁጭ ብሎማ አይመለከትም!) ምዕራባውያኑ ግን  መንግስት ሁሉን ነገር ለውጭ ኢንቨስተር ክፍት እንዲያደርግ ነው የሚፈልጉት።  (የግል ባለሃብት መጫወቻ ሊያደርጉት እኮ ነው!) ይሄ ቅራኔ ብቻ ነው ለቀለም አብዮት መሠረታዊ ምክንያት የሚሆነው ብለዋል -ተንታኙ። በተረፈ ግን ሁሉም ሙሉ ሁሉም ዝግጁ ስለሆነ ጦቢያን የቀለም አብዮት አያሰጋትም  ባይ ናቸው።
ከዚሁ ከቀለም አብዮት ሳንወጣ ባሳለፍነው ሳምንት በኢቴቪ የሰማሁትን አንድ አስደንጋጭ ዜና ልንገራችሁ - ላልሰማችሁ። ከሦስቱ አንጋፋ የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች ማህበራት የአንዱ ፕሬዚዳንት ለኢቴቪ እንደተናገሩት፤ የቀለም አብዮት ለማቀጣጠል የመጡ አርቲክል 19 የተባለ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ድርጅት ተወካይ ወደ አገር ውስጥ ሳይገቡ እንዲመለሱ ተደርገዋል - ከቦሌ አየር ማረፍያ። ተወካዩ ወደ ኢትዮጵያ የመጡት ለጋዜጠኞች ሥልጠና ለመስጠት እንደነበር ውስጥ አዋቂ ምንጮች  ቢናገሩም፣ የጋዜጠኛ ማህበሩ ፕሬዚዳንት ግን  በዚህ አይስማሙም። ሰውየውም ሰልጣኞቹም  ህገወጥ ናቸው ብለዋል- ፕሬዚዳንቱ። እናም  በኒዮሊበራሎች  የታቀደው “የቀለም አብዮት” ቦሌ አየር ማረፍያ ላይ ከሽፏል።
 እኔ የምለው ግን ----የቀለም አብዮት ትፈራላችሁ እንዴ? (ይሄማ የጦቢያን ልጆች ታሪክ መርሳት ነው!)  እንኳንስ ለቀለም አብዮተኞች ለፋሺስት ኢጣልያም እጅ አልሰጠንም እኮ! አያችሁ ---- ኢህአዴግም ሆነ   መንግስት መፍራት ያለባቸው ህዝብን እንጂ የቀለም አብዮተኞችን አይደለም።
ሥልጣን የሚሰጥም የሚነሳም ህዝብ  ነው! (የ97ቱን ምርጫ ልብ ይሏል!) እናም  ህዝብ የሚወደው መንግስት የቀለምም ይሁን የፍራፍሬ አብዮት ጨርሶ አያስፈራውም (“ህዝብ የሚወደው መንግስት” እንዴት ያለ ነው?) እናላችሁ----ኢህአዴግ ነፍሴ ከመስጋት ይልቅ ብልህ መሆን ነው የሚያዋጣው። ከልማት ሥራው ጎን ለጎን በመብራት፣ በውሃ፣ በኔትዎርክ፣ በትራንስፖርት፣ በዳቦ ወዘተ-- እጥረትና መጥፋት ለሚሰቃየው ህዝብ፤ዛሬ ነገ ሳይል አፋጣኝ መፍትሄ ይዘይድ።
መንገዱ ወጣ ገባና ኮረኮንች ቢበዛውም “አገር ውስጥ ሰላማዊ ትግል ማካሄድ ይቻላል” ብለው በህጋዊነት  የሚንቀሳቀሱ  ተቃዋሚዎችን አትላወሱም ብሎ ማዋከብ፣ትርፉ የጠላትን ቁጥር ማብዛት ብቻ  ነው።  እናም በዶክመንታሪው ላይ አንዱ ተንታኝ እንዳሉት፣ የቀለም አብዮትን ለመከላከል የቤት ሥራን አጥርቶ መስራት የግድ ይላል።
መልካም የትንሳኤ በዓል ይሁንላችሁ!! 

Read 7103 times