Saturday, 10 December 2011 10:20

ራስህን እንዴት ትሸጣለህ?

Written by  ኢዮብ ካሣ
Rate this item
(2 votes)

ሂላሪ ክሊንተን በአንድ ጋዜጣዊ መግለጫ 19 ጊዜ “You know”ን ደጋግመዋል…  
ሬጋን ሁለቴ ምርጫ ያሸነፉት ትክክለኛ ማንነታቸውን ይዘው ስለቀረቡ ነው …
ምንም ቢሆን ከማንወደው ነጋዴ እቃ አንሸምትም …
ዛሬም ከስኬት የራቀ ጉዳይ አይደለም የምናወጋው፡፡ በእርግጥ ከሌላው ጊዜ በተለየ መንገድ ነው ስኬትን የምንዳስሰው፡፡ በኮሙኒኬሽን (ተግባቦት) ወይም ራስን በመሸጥ (Selling oneself) በሚሉ ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ ያጠነጥናል - የዛሬው የስኬት ወጋችን፡፡ ለዚህ ፅሁፌ ምክንያት የሆነኝ ደግሞ ሰሞኑን ጥሞኝ ያነበብኩት የአሜሪካዊው ፀሃፊ አርች ሉስቶበርግ “How to sell yourself” መፅሃፍ ነው፡፡ ለመንደርደርያ ይሄን ያህል ካልን ወደ ዋናው ጉዳይ እንዝለቅ፡፡


ሁልጊዜ ለመናገር አፋችንን ስንከፍት ራሳችንን እየሸጥን ነው ይለናል ፀሃፊው፡፡ ምን ማለቱ ነው? ለሰው ሰላምታ ስንሰጥ፣ ስልክ ስናነሳ፣ ከወዳጅ ዘመድ ጋር ስናወራ፣ ስብሰባ ላይ ስንናገር፣ ለሥራ ኢንተርቪው ስንደረግ፣ ለምርጫ ስንወዳደር፣ ፍ/ቤት ምስክር ሆነን ስንቀርብ፣ ስናስተምር፣ ስንሰብክ፣ ስንደራደር … ሁሉም ራስን የመሸጥ አካል ናቸው፡፡ ራስን መሸጥ ማለት ሌላ ሳይሆን ለምንፈልገው ወገን መልዕክታችንን ወይም ሃሳባችንን በትክክል ማድረስ ማለት ነው፡፡ በእኛና በሌላው ሰው መካከል ተግባቦት (Communication) እንዲፈጠር የምንሻ ከሆነ ራሳችንን በትክክል መሸጥ አለብን፡፡ ራሳችንን ካልሸጥን ግን ተግባቦት እውን አይሆንም፡፡ ራሳችንን ስንሸጥ የምንፈልገው መልዕክት ሳይዛባ በትክክል የምንፈልገው ወገን ጋ ይደርሳል፡፡ ሁሌም ሽያጭ የሚለውን ቃል የምናያይዘው ምርት ተኮር ከሆኑ ነገሮች ጋር ነው፡፡ ይሄ ግን የሽያጭ አንዱ ገፅታ ብቻ ነው፡፡ የምርት ሽያጭን በተመለከተ ዋናዎቹ ጉዳዮች የሽያጭ ባለሙያውና የምርቱ ዋጋ ሲሆኑ ራሳችንን ስንሸጥ ግን ሃሳባችን ወይም መልዕክታችንና ያንን የምናቀርብበት መንገድ ነው ዋናው ጉዳይ፡፡ ማናቸውም የምናደርጋቸው ነገሮች ለተመልካቹ ወይም ለአድማጩ አንድ ምልክት (ትርጉም) ይሰጣሉ፡፡ ሌላውን ሰው የምትመለከቱበት መንገድ፣ እጃችሁን የምትጠቀሙበት ሁኔታ፣ አቀማመጣችሁ ወይም አቋቋማችሁ፣ የድምፃችሁ ቃና፣ ለአድማጩ የሚሰጡት ትርጉም አላቸው፡፡ እነዚህን በማየት ብቻ ስለናንተ የሆነ ድምዳሜ ላይ እንደሚደርስም ይታወቃል፡፡
ከእዚህ በመነሳትም አድማጩ ወይም ተመልካቹ ስለኛ ብቃት፣ ደካማነት፣ መልካምነት፣ ተወዳጅነት ወዘተ አቋም ሊይዝ ይችላል ማለት ነው፡፡
ራሳችንን ለመሸጥ ስናስብ ሦስት ነገሮች ያስፈልጉናል የሚለን “How to sell yourself” የተሰኘው መፅሃፍ፤ እነሱም ብቃት፣ ተወዳጅነትና እድል ናቸው ይላል፡፡ የመጀመሪያዎቹ ሁለቱ ካሉን ሦስተኛውን እነሱ ያመጡታል፡፡ ነገር ግን ብቃትና ተወዳጅነት ብቻ በቂ አይደሉም፡፡ እነዚህ ነገሮች አብዛኞቻችን ዘንድ አሉ፡፡ ሆኖም ሰዎች ያንን አምነው እንዲቀበሉ ማድረግ አለብን፡፡ ይሄንን የምናደርገው ግን ሰዎችን በማሳሳት ወይም በማጭበርበር አይደለም፡፡ እሱ የፕሮፌሽናል አጭበርባሪዎች ተግባር ነው፡፡ እንደኔና እንደናንተ ያሉ እውነተኛ ሰዎች እውነተኛ ራሳችንን ለመሆን የሚያስችሉንን ጥቂት መሰረታዊ ዘዴዎች መማር አለብን ይላል - አርች ሉስትበርግ፡፡ የችግሩ ሥር ያለው እዚህ ጋ ነው - ራሳችንን መሆን!
በ1977 እ.ኤ.አ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ሽያጭ ያስመዘገበው “The Book of Lists” የተሰኘው መፅሃፍ “14ቱ የሰው ልጅ አስከፊ ፍርሃቶች” በሚል ከዘረዘሯቸው ጉዳዮች፣ በአንደኛ ደረጃ የተቀመጠው ሰዎች ፊት ንግግር ማድረግ ሲሆን “ሞት” 6ኛ ደረጃ ላይ ሰፍሯል፡፡ ከሞት ይልቅ ሰዎች ፊት መናገር ያስፈራናል ማለት ነው?
ግን ለምንድነው ይሄን ያህል ሰዎች ፊት መናገር የሚያስፈራን? “How to sell yourself” የተባለው መፅሃፍ ጥቂት ምክንያቶችን ይጠቅሳል፡፡ አንደኛው ፍርሃት ነው፡፡ ከመደበኛ የንግግር ድባብ ጋር አለመተዋወቅ፣ ውጥረትና ጭንቀት፤ እንዲሁም “ይሄ ሁሉ ሰው እየተመለከተኝ ነው፤ ዛሬ መሳቂያ መሳለቂያ እንዳልሆን” የሚለው ሃሳብ ሰዎች ፊት ቆሞ መናገርን እንድንፈራ ያደርገናል፡፡ እነዚህ ስሜቶች ደግሞ እውነተኛ ማንነታችንን ቀይረን አዲስ ገፀባህርይ እንድንላበስ ያደርጉናል - ፕሮፌሽናል መስለን ለመታየት እንጥራለን፡፡ በሌላ አነጋገር አክተሮች እንሆናለን፡፡ የተዋጣለት አክተር መሆን ደግም የአባት ነው፡፡ ግን ያልተዋጣለት አክተር ነው የምንሆነው፡፡
ለዚህ ስህተት የሚዳርገን ምን መሰላችሁ? አድማጩ ከኛ ይጠብቃል ብለን የምናስበው የተሳሳተ ግምት ነው፡፡ አድማጩ ብቁና የበሰለ ባለሙያ ማየት ይፈልጋል እንልና የመምሰል ትወናችንን ወይም “Acting” እንጀምራለን፡፡ ግን እኮ እኛ የቀረብነው ብቁና የበሰለ ባለሙያ በመሆናችን ነበር፡፡ ሆኖም ያንን ዘንግተነዋል፡፡
አድማጩ ወይም ተመልካቹ የሚፈልገው ነው ብለን ያሰብነውን ለመሆን “Acting” ስንጀምር የራሳችንን ማንነት እንቀይርና ካርቱን መስለን እንቀርባለን፡፡ ገፅታችን፣ የአነጋገር ስታይላችን፣ ፈገግታችን፣ የቃላት አመራረጣችን ወዘተ ከኛ ፍፁም የራቀ ይሆናል፡፡ ምናልባት ሞዴላችን ብለን ከወሰድነው መጥፎ ተናጋሪ የተኮረጀ ሊሆን ይችላል፡፡ ይሄ ሁሉ ጭንቀት ግን ለምን? እንል ይሆናል፡፡ መልሱ ቀላል ነው፡፡ ይሄን ያህል የምንጨነቀውና የምንጠበበው አድማጩን ለማስደነቅ ወይም ለማስደመም ነው፡፡ ተወደደም ተጠላም ይሄ መጃጃል እንጂ ሌላ ስም ሊሰጠው አይችልም ይላል -ፀሃፊው፡፡ ለምን ቢባል? የእኛ ዓላማ ማስደመም ሳይሆን መልዕክታችንን በትክክል ማድረስ ነው፡፡ የተግባቦቱ (communication) ዓላማ ራሳችንን (ሃሳባችንን) መግለፅ ነው፡፡
ሰዎች ካሜራ ፊት ሲቀመጡ እንዴት ተፈጥሮአዊ ገፅታቸውን እንደሚያጡ አስተውላችኋል? ሳቅና ጨዋታቸውን ገትተው ካሜራው ላይ ፍጥጥ ይላሉ - ኤሌክትሪክ እንደያዘው ሰው፡፡ ምናልባት ጥሩ ፎቶግራፍ እንዲወጣላቸው አስበው ይሆናል፡፡ ግን ተፈጥሮአዊ የሆነውን የፊታቸውን ገፅታ አያገኙትም፡፡ ለመምሰል የሞከሩትን እንጂ፡፡
የተዋጣለት ተናጋሪ ለመሆን የምንፈልግ ከሆነ ዘና ማለት ይጠበቅብናል፡፡ ለጥቂት ሰዎችም ይሁን በመቶዎች ለሚቆጠሩ ታዳሚዎች ስልቱ ተመሳሳይ ነው፡፡ ከጓደኛችን ጋር የግል ወሬ እንደምናወራው ባለ ድባብ ንግግራችንንን ማቅረብ አለብን ይላሉ፡፡ ያለመታደል ሆኖ ግን ጥሩ ሞዴል የሆኑ ብዙ ተናጋሪዎች የሉንም የሚለው ሉስትበርግ፤ አብዛኞቹ የዛሬ ተናጋሪዎች ከሌሎች በአርአያነት ከማይጠቀሱ ተናጋሪዎች ያዩትን ነው የሚገለብጡት ብሏል፡፡ “አድማጩን አስደምመው ዘንድ ፕሮፌሽናል መምሰል አለብኝ” ብለን እናስባለን፡፡ ይሄ ግን ትልቅ ስህተት ነው፡፡ እስቲ ለምርጫ የሚወዳደሩ እጩዎችን ወይም በቲቪ አስተያየትና ሙያዊ ትንተና የሚሰጡ “ባለሙያዎች”ን አሊያም መምህራንን ወይም ደግሞ ስብሰባ ላይ ንግግር የሚያደርጉ ተናጋሪዎችን እዩዋቸው - ከማንኛውም የእንቅልፍ ክኒን የበለጠ እንቅልፍ የሚያመጡ ወይም የሚያስተኙን ናቸው ሲል ይተቻል - ሊስትበርግ፡፡
ይሄን እንኳን እኛም አሳምረን እናውቀዋለን፡፡ ፓርላማ ውስጥ የተቀመጡ ተወካዮች ስለህይወታችን ዋና ጉዳዮች እንደሚወስኑ ብናውቅም የፓርላማ ስብሰባን ብዙ ሰው በትኩረት አይከታተለውም፡፡ ለምን? እስካሁን ደራሲው የሚለንን ከተከተልን ሰዎቹ ራሳቸውን ሆነው ስለማይቀርቡ ሊሆን ይችላል፡፡ በቲቪ የምናያቸው የባለሙያዎች ኢንተርቪዎች በአብዛኛው አሰልቺ እንደሆኑም እናውቃለን፡፡ መልዕክታቸውን ለማድረስ ሳይሆን ተመልካቹን ለማስደመም ስለሚጨነቁ ይሆን? የሆኖ ሆኖ ግን እኛ ፈፅም እነሱን መምሰል የለብንም ሲል ይመክራል የ”How to Sell yourself” ደራሲ፡፡
ራስህን መሆን ነው ያለብህ - ትክክለኛ አንተነትህን ይላል - ሉስትበርግ፡፡
ሁላችንም ትክክለኛ ራሳችንን ይዘን መቅረብን መማር አለብን - እውነተኛ እኛነታችንን፡፡ መምህራን ይሄን መማር አለባቸው፡፡ ሰባኪዎች ይሄን መማር አለባቸው፡፡ ጠበቃዎችና መስካሪዎች ይሄን መማር አለባቸው፡፡ በየትኛውም የህይወት ዘርፍ የተሰማሩ ሰዎች ይሄን መማር አለባቸው፡፡
እኔና እናንተም ስኬታማ ለመሆን ይሄን መማር አለብን፤ ይለናል - ፀሃፊው፡፡
ራስን ስለመሸጥ ስንናገር የአቀራረብ ስታይላችን የምንናገረውን ፍሬ ሃሳብ ያህል ፋይዳ እንዳለው መገንዘብ ተገቢ ነው፡፡ ተወዳጅነት ደግም ከብቃት የበለጠም አስፈላጊ ነው - ራስን በመሸጥ ጥበብ፡፡ እቺን ትንሽ ማብራራት ሳያስፈልግ አይቀርም፡፡ ሁለት መደብሮች አሉ እንበል፡፡ ሁለቱም በመስተንግዶና በአቅርቦት ደረጃ እኩል ናቸው፡፡ የአንደኛውን መደብር ባለቤት ግን አትወዱትም (ምናልባት ትዕቢተኛ በመሆኑ) የሁለተኛው መደብር ባለቤት ደግሞ ትሁት ስለሆነ ተወዳጅ ነው፡፡ ሸቀጥ ለመሸመት የምትመርጡት የትኛውን መደብር ነው? እርግጠኛ ነኝ ሁለተኛውን መደብር ነው፡፡ ለምን? ባለቤቱ ተወዳጅ ስለሆነ፡፡ ፀሃፊው ይሄን “Likeability” ይለዋል፡፡ ራሳችን ብቃት እንዳለን ብቻ ማወቃችን ወይም ማሰባችን ብቻውን ምንም አይፈይድልንም፡፡ ሰዎች እንደዚያ መሆናችንን አምነው እንዲቀበሉ ማድረግ ነው ራስን የመሸጥ ዋና ግቡ፡፡ ራስን የመሸጥ ችሎታም ይሄው ነው፡፡ የምናወራቸው ሰዎች እኛ አለን ብለን የምናስበውን ተወዳጅነትና ብቃት እንዲቀበሉት ማድረግ፡፡ ሰዎች ካልወደዱንና ብቁ አይደሉም ብለው ካሰቡን አለቀልን፡፡ መልዕክታችን ጆሮአቸው ጋ አይደርስም፡፡ ተግባቦቱ አይሳካም፡፡
የማንወደውና ብቃት እንዳለው የማናምንበት እጩ የምርጫ ተወዳዳሪ ግብር እንደሚቀንስና የተሻለ አገልግሎት እንደሚሰጥ ቢለፈልፍ ነገሬ አንለውም፡፡ እንደውም “ዋሾ” ብለነው እናርፋለን፡፡ ተመሳሳይ ቃል ከምንወደውና ብቃት አለው ብለን ከተቀበልነው እጩ ተወዳዳሪ ቢመጣስ? ምንም ሳናቅማማ እንመርጠዋለን፡፡ አጀንዳዎችና ርዕሰ ጉዳዮች በሚታመንና በሚወደድ መልኩ ካልቀረቡ ትርጉም የላቸውም - የደራሲው መደምደሚያ፡፡ ፖለቲከኞቻችንን በማየት ብቻ ስለዚህ ጉዳይ መማር እንችላለን ይላል ፀሃፊው፡፡ እኛስ?
ራስን በመሸጥ ጥበብ ሰዎች እንዴት ይቀበሉናል የሚለውን በምሳሌ ለማሳየት እ.ኤ.አ በ1996 ዓ.ም የተካሄደውን የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ውጤት ፀሃፊው ይጠቅሳል፡፡ ቢል ክሊንተን በታማኝነት ከፍተኛ ነጥብ አላስመዘገቡም ነበር፡፡ ነገር ግን ተፎካካሪያቸው ቦብ ዶሌ ቅንጣት ታህል ተወዳጅነት አልነበራቸውም፡፡ እንደውም እሳቸው የተወዳጅነት መርፌ በደም ስራቸው ሊሰጣቸው የሚገቡ ተፎካካሪ ነበሩ፡፡ የእሳቸው ተወዳጅ አለመሆን ግን ቢል ክሊንተንን አሸናፊ አደረጋቸው፡፡ አፍን ሞልቶ ክሊንተን አሸነፉ ማለት አይቻልም - ዶሌ ግን በደንብ ተሸንፈዋል፡፡ በእርግጥ ዶሌ የተወሰነ ያህል ድምፅ አግኝተው ነበር፡፡ ድምፁን ያገኙት ግን ቢል ክሊንተንን ከሚጠሉ ኦርቶዶክስ ሪፐብሊካኖች ነው፡፡ ከዚህኛው ምርጫ በፊት በነበሩ ሁለት ምርጫዎችም ተመሳሳይ ሁኔታ ተከስቷል፡፡
ቢል ክሊንተን አላሸነፉም - ጆርጅ ቡሽ ተሸንፈዋል፡፡
በ1988 ምርጫ ቡሽ አላሸነፉም - ማይክል ዱካኪስ ተሸንፈዋል፡፡
ሮናልድ ሬገን ደግሞ ሁለት ጊዜ አሸንፈዋል፡፡ ለምን? አዘወትረው ድምፅ በማይሰጡ አብላጫ መራጮች ተወዳጅ ስለነበሩ ነው፡፡ ነገሩ ይሄን ያህል ቀላልና እውነት ነው፡፡ ሁልጊዜም የበለጠ የምንወደውን ወይም ከሌላው ያነሰ የምጠላውን እንመርጣለን፡፡
ደራሲው ጆርጅ ደብሊው ቡሽና አልጐር ተወዳድረው አቻ ውጤት ያስመዘገቡበትን የ2000 ዓ.ም ምርጫም በምሳሌነት ይጠቅሳል፡፡ ቡሽ ለምን በቀላሉ እንዳላሸነፉ ሲያስረዳም፤ በምርጫ ክርክር ወቅት የፕሬዚዳንትነት ወይም የመሪነት ጭምብል አጥልቀው መቅረባቸዉን እንደ ዋነኛ ችግር ያነሳል፡፡
ቡሽ ሚስታቸውን ባርባራን ወይም ልጆቻቸውን አሊያም ጓደኞቻቸውን በሚያነጋግሩበት (በሚያወሩበት) መንገድ ህዝቡን ቢቀርቡና ቢያነጋግሩ ኖሮ በቀላሉ ያሸንፉ እንደነበር አርች ሉስትበርግ ይናገራል፡፡
የጆርጅ ቡሽን ፀጉር የሚያስተካክለውና የአሜሪካ ፕሬዚዳንቶችን ፀጉር በማስተካከል የሚታወቀው ሚልተን ፒትስ የእሱም ደንበኛ እንደሆነ የጠቀሰው ፀሃፊው፤ ቡሽ ጨዋታ አዋቂና መልካም ሰው እንደሆኑ ነግሮኛል፤ ሌሎች የቅርብ ወዳጆቻቸውም ቡሽ ቀልደኛ እንደሆኑ አጫውተውኛል፤ ይሄንን ግን በ2000 ምርጫ ለመራጩ ህዝብ አላሳዩትም ይላል፡፡
ፀሃፊው የጠቀሳቸው በአንድ ወቅት ተፎካካሪ የነበሩ ሰዎች በሙሉ በግል ግንኙነታቸው ችግር እንደሌለባቸው የሚያወሳው ሉስትበርግ፤ በምርጫ ውድድሩ ስኬት እንዳያገኙ ያደረጋቸው እራሳቸውን ሆነው አለመቅረባቸው ነው ይላል፡፡ ከዚህ በተቃራኒ በሁለት ምርጫ ያሸነፉትን ሮናልድ ሬገን እናገኛቸዋለን፡፡ የእሳቸውን የአሸናፊነት ምስጢር የሚያብራራው ሉስትበርግ፤ ምስጢሩ ሰውየው ራሳቸውን የመሆን ጥበብ መካናቸው ነው ይለናል፡፡ ሬጋን ህዝብ ፊት ሲቀርቡ እውነተኛ ማንነታቸውን ይዘው አይደለም፤ እያስመሰሉ ወይም እየተወኑ ነው የሚሉ አንዳንድ ወገኖች ቢኖሩም ፀሃፊው ግን ትችቱን አይቀበልም፡፡ የካሊፎርኒያ ገዢና የአሜሪካ ፕሬዚዳንት በመሆን ድንቅ ጊዜን አሳልፈዋል፤ ትወና የሚያስፈልጋቸው ሰው አልነበሩም ሲል ይከራከራል - ሁልጊዜም ዘናና ፈታ ብለው እንዲሁም ራሳቸውን ተቆጣጥረው እንደሚታዩና በራስ መተማመን የሚንፀባረቅባቸው ሰው እንደነበሩ በመጥቀስ፡፡ ይሄም ነው ለተወዳጅነታቸው ምክንያቱ፡፡ በአዕምሮ ብቃት የትናየት የሚበልጧቸውን ሁለት ተፎካካሪዎች አሸንፈው ፕሬዚዳንት የሆኑት ራሳቸውን ሆነው በመቅረብ በተቀዳጁት ተወዳጅነት የተነሳ እንደነበርም ያወሳል፡፡

ብቃትን መሸጥ
ለመሆኑ ብቃታችንን ለሌላው ሰው የምናሳየው ወይም የምንሸጠው እንዴት ነው? “Selling Yourself” የሚለው መፅሃፍ እያንዳንዳችን አራት የተግባቦት (Communication) መሳሪያዎች እንዳሉን ይገልፃል - አዕምሮአችን፣ ፊታችን፣ አካላችንና ድምፃችን፡፡ አድማጩ ወይም ተመልካቹ አንድ ሰው ብቃት አለው ወይም የለውም ብሎ የሚወስነው የዚያን ሰው የአዕምሮ አጠቃቀም በመመልከት ሲሆን የቀሩት ፊታችን፣ አካላችንና ድምፃችን የተወዳጅነታችን ሁኔታ የሚመዘንባቸው ናቸው፡፡ አዕምሮአችንን “ፍሬ ጉዳይን” ሲወክል ፊታችን፣ አካላችንና ድምፃችን ደግም “ስታይል”ን ይወክላሉ፡፡ የምንናገረውን ጉዳይ የሚመለከተው አዕምሮአችን፤ የምንናገርበትን (የምናቀርብበት ስታይል) መንገድ ደግም የቀሩት ሦስቱ ይመለከታቸዋል እንደ ማለት ነው፡፡ አድማጩ ብቃታችንን እንዴት እንደሚቀበለው ማወቅ ብቃታችንን አውጥቶ ለማሳየት ወሳኝ ነው፡፡ ብቃታችን የሚንፀባረቀው በአዕምሮ አጠቃቀማችን ነው፡፡ ሃሳቦችን እንዴት አደራጅተን እናቀርባለን፣ የሚለው ብቃታችንን ለሌላው ሰው የምናሳይበት መንገድ፡፡
እንግዲህ ብቃታችንን ለመሸጥ ስንነሳ ተመልካቹ ወይም አድማጩ አስተማማኝ ብቃትና ችሎታ (አቅም) በትክክል እንዳለን እንዲገነዘብ ልናግዘው ይገባል፡፡ ቀደም ብለን እንደጠቀስነው ስለብቃታችን እኛ ብቻ ማወቃችን ምንም የሚፈይደው ነገር የለም፡፡ ዋና ዓላማችን ሌላው ሰው ያንን ብቃት አውቆ እንዲገዛን፤ እንድንሸጥለት ማድረግ ነው፡፡
ይሄንን እንዴት ማድረግ ይቻለናል ለሚለው “Selling yourself” ጥቂት ዘዴዎችን ይጠቁመናል፡፡ አንደኛው ብቃታችንን ለሌሎች ለመሸጥ ከመቅረባችን በፊት በቂ ዝግጅት ማድረግ ነው፡፡ ሌላው የእኛን የተለየ ጥንካሬ ማወቅ፡፡ እኛ ብቻ ይበልጥ የምናውቃቸው (የተካንባቸው) የተወሰኑ ጉዳዮች እንዳሉ ማወቅ ብልህነት ነው፡፡ ሰዎች ፊት ቀርበን ስንናገር ወይም አስቸጋሪ ጥያቄዎች ሲቀርቡልን ረዥም ፋታ መውሰድ ተረጋግቶ ለማሰብ ወሳኝ እንደሆነ ማወቅ ተገቢ ነው፡፡ ብዙዎቻችን መልስ ለመስጠት ረዥም ፋታ መውሰድ በአድማጩ ዘንድ ዝቅ ያለ ግምት ያሰጠናል በሚል እየተደነቃቀፍንም ቢሆን በጥድፍያ እንመልሳለን፤ የሚለን ፀሃፊው፤ ይሄ ግን ሽንፈትን እንጂ ድልን አያቀዳጀንም ባይ ነው፡፡ “እንግዲህ … ኧ … ነገሩን ከኢኮኖሚ አንፃር …ኧ ከተመለከትነው … ኧ … ጠቀሜታው … ኧ … ከፍተኛ …. ኧ … እንደሆነ … ኧ … ግልፅ ነው” የዚህ ዓይነት የተደነቃቀፈ ንግግር የተናጋሪውን ብቃት ጥያቄ ውስጥ ከማስገባቱም ባሻገር መልዕክቱን በትክክል እንዳንረዳ ያደርገናል፡፡ የሚገርመው ደግሞ ፕሮፌሽናሎች ሳይቀሩ እንዲህ ዓይነቱን ስህተት መፈፀማቸው ነው፡፡ ለምሳሌ የቲቪ ሪፖርተሮች ዘገባቸውን ከስክሪፕት ላይ ማንበብ በማይችሉበት የሰበር ዜና (Breaking news) ዘገባ ላይ እንዴት እንደሚደነባበሩ ተመልከቱ ይለናል - የአንድ ሰበር ዜና ምሳሌ በማቅረብ፡፡
“The … uh … Fire is … uh reported to … uh …. Have broken out at … uh … just after … uh … midnight.”
ሂላሪ ክሊንተን ሴኔት ሆነው እንደተመረጡ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ባለቤታቸው ስለተሰጣቸው “ፕሬዚዳንታዊ ምህረት” ተጠይቀው ሲመልሱ በአጠቃላይ 19 ጊዜ “you know” የሚለውን ቃል መደጋገማቸውን እንደ እንከን የጠቀሰው ፀሃፊው፤ ይሄንኑ ቃል በአንድ ዓ.ነገር ሦስት ጊዜ እንደደጋገሙና በጣም ብዙ ጊዜ “uhs” ማለታቸውን አስታውሷል፡፡ እናም እንዲህ ያሉ ተናጋሪዎችን አትኮርጁ ሲል መክሯል፡፡
ተወዳጅነትን መሸጥ
መቼም አንድ ሃሳብ፣ መልዕክት ወይም ምርት መሸጥ ወይም ለፈላጊው ማድረስ የሚፈልግ ማንኛውም ሰው የተወዳጅነትን ፋይዳ በቅጡ ሊገነዘብ ይገባል፡፡ አንድ ዓለማዊ መምህር ወይም ሃይማኖታዊ ሰባኪ ትምህርቱን በአግባቡ ለማስተማር እስከጣረ ድረስ ባይወደድ ምን ችግር አለው? ሊባል ይችላል፡፡ ግን ከባድ ችግር አለው ይላሉ በዘርፉ ጥናት ያደረጉ ባለሙያዋች፡፡ ለምሳሌ ንግግር ስናደርግ አድማጩ የሚጠላን ከሆነ በከንቱ ነው የምንለፈልፈው፡፡ ለምን ቢባል ስለማይወደን ለምንናገረው ጉዳይ ትኩረት ሰጥቶ አይሰማንማ! አዳራሹ የተሞላው ተናጋሪውን በሚወዱ ሰዎች ከሆነ ግን ተናጋሪው ተሳክቶለታል - በትኩረት ስለሚያዳምጡት መልዕክቱ በሚገባ ለአድማጮቹ ይደርስታል፡፡ አድማጩ ለእኛ ግድ የሌለው ቢሆንስ? የማይወደንም የማይጠላንም እንደማለት፡፡ እነሱ ደግሞ ምነው ባልመጣን ኖሮ ብለው የሚያስቡ ናቸው - እናም የተናጋሪው መልዕክት ፈፅሞ አጠገባቸዉ አይደርስም፡፡
ከማንወደው ነጋዴ ፈፅም አንገዛም
የምር ከምንጠላቸው ሰዎች ጋር የቅርብ ጓደኞች አንሆንም
ያልወደድነውን የስራ አመልካች አንቀጥረውም
ለማንወደው ሰው የሥራ ዕድገት አንሰጠውም
የምንወደውና የሚወደን አስተማሪ ስናገኝ የተሻለ ትምህርት እንቀስማለን
በጣም ለምንጠላው እጩ ተወዳዳሪ ድምፅ አንሰጥም - የተሻለ ሥራ ሊሰራ እንደሚችል ብናውቅም እንኳን እንደውም ወደ ምርጫ ጣቢያ ሁሉ ላንሄድ እንችላለን፡፡
እዚህ ላይ አንድ ጥያቄ ሊነሳ ይችላል፡፡ እኛ ስለፈለግን ብቻ በሌሎች ተወዳጅ ልንሆን እንችላለን? ተወዳጅነት በእኛ ቁጥጥር ሥር ያለ ጉዳይስ ነውን? የ “Selling yourself” ደራሲ አርች ሉስትበርግ፤ በሁሉም ሰዎች መወደድ የሚባል ነገር የለም ይላል፡፡ ራሳችንን ለመሸጥ ስንነሳ ግን ዓላማችን ሊሆን የሚገባው በአብዛኛው አድማጭ ዘንድ ተወዳጅነትን ማትረፍ ነው፡፡ ለዚህም ነው የተወዳጅነታችን ቁልፎች በሚል ርዕስ ፊታችንን፣ ሰውነታችንን፣ ድምፃችንን አጠቃቀማችን የተወዳጅነት ቁልፎች እንደሆኑ የሚገልፀው፡፡ ንግግር ለማድረግ ሰዎች ፊት ስንቀርብ የምናሳየው የፊት ገፅታ ለተወዳጅነታችንም ሆነ ላለመወደዳችን ትልቅ ሚና ይጫወታል፡፡ ዘና ፈታ ብለን ነው ወይስ ተጨናንቀንና ተወጣጥረን የቀረብነው? ተደስተን ነው ተቆጥተን የታየነው?
የፊታችን ገፅታ በፈገግታ የተመላ ነበር ወይስ በመረበሽና በመጨነቅ? ከእዚህ በመነሳት ነው ታዳሚው የሚወደንም ሆነ የሚጠላን አሊያም ከጉዳዩ የማይጥፈን፡፡ አንድ ተናጋሪ ለታዳሚው ዝግ ፊት ሲያሳይ ታዳሚውን የማይወደው መስሎ ነው የሚታየው፡፡ ታዳሚውም አፀፋው ተመሳሳይ ይሆናል - ተናጋሪውን አይወደውም፡፡ በደስታና በፈገግት ተሞልቶ የቀረበ ተናጋሪስ? ታዳሚው ይሄን ተናጋሪ ከመውደድ ውጭ ሌላ አማራጭ የለውም፡፡ ሁልጊዜም አትዘንጉ - ተወዳጅነት በማናቸውም ግንኙነት ውስጥ አሸናፊነትን ያጐናፅፋል፡፡ ተወዳጅነት የስኬትም ቁልፍ ነው፡፡
ዝግ ፊት
የተናደደ ወይም የተበሳጨ ሰው የሚያሳየው ፊት ነው፡፡ ጭንቀት የሚታይበት ፊት፡፡ ጆርጅ ደብሊው ቡሽ በ2000 ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ የተጠቀሙበት የፊት ገፅታ ሲሆን ከሽንፈት የተረፉት ለትንሽ ነበር፡፡
የታከተ ፊት
አብዛኞቹ የቴሌቪዥን ቃለመጠይቅ ተደራጊዎችና ንግግር አቅራቢዎች የሚታይባቸው የፊት ገፅታ ነው፡፡ የታከተ ወይም የሞተ ሰው ፊት ሊባል ይችላል፡፡ በ2002 ምርጫ አልጐርን ድል ያሳጣቸው ፊት ይሄ ነበር፡፡
የበራ ፊት
ንቁና የጋለ ስሜት የሚንፀባረቅበት ፊት ነው፡፡ ሰዎች ምስጢር ሲያወሩ ወይም ሃሜት ላይ ሲሆኑ የሚያሳዩት ፊት ይሄን ይመስላል፡፡

 

ት (Communication) እንዲፈጠር የምንሻ ከሆነ ራሳችንን በትክክል መሸጥ አለብን፡፡ ራሳችንን ካልሸጥን ግን ተግባቦት እውን አይሆንም፡፡ ራሳችንን ስንሸጥ የምንፈልገው መልዕክት ሳይዛባ በትክክል የምንፈልገው ወገን ጋ ይደርሳል፡፡ ሁሌም ሽያጭ የሚለውን ቃል የምናያይዘው ምርት ተኮር ከሆኑ ነገሮች ጋር ነው፡፡ ይሄ ግን የሽያጭ አንዱ ገፅታ ብቻ ነው፡፡ የምርት ሽያጭን በተመለከተ ዋናዎቹ ጉዳዮች የሽያጭ ባለሙያውና የምርቱ ዋጋ ሲሆኑ ራሳችንን ስንሸጥ ግን ሃሳባችን ወይም መልዕክታችንና ያንን የምናቀርብበት መንገድ ነው ዋናው ጉዳይ፡፡ ማናቸውም የምናደርጋቸው ነገሮች ለተመልካቹ ወይም ለአድማጩ አንድ ምልክት (ትርጉም) ይሰጣሉ፡፡ ሌላውን ሰው የምትመለከቱበት መንገድ፣ እጃችሁን የምትጠቀሙበት ሁኔታ፣ አቀማመጣችሁ ወይም አቋቋማችሁ፣ የድምፃችሁ ቃና፣ ለአድማጩ የሚሰጡት ትርጉም አላቸው፡፡ እነዚህን በማየት ብቻ ስለናንተ የሆነ ድምዳሜ ላይ እንደሚደርስም ይታወቃል፡፡

Read 10104 times Last modified on Saturday, 10 December 2011 12:44