Saturday, 10 December 2011 10:18

ምርጥ የዓለም ከተሞች፤ የበሽታ መፈልፈያ “ቆሼ”

Written by  መንግሰቱ አበበ
Rate this item
(0 votes)

ዛሬ ዛሬ፤ ከተሞችንና ከተማነትን በማንቋሸሽ ኋላቀር የገጠር ኑሮን ማዳነቅ፤ ብዙ አላዋቂዎችን የሚያስፈነድቅ ፈሊጥ ሆኗል፡፡ በጭስ የታፈነ፤ በከብቶች እበት የተጨማለቀ ጨለማ ጎጆ ውስጥ መኖር የሚያስቀና ምቹ ኑሮ ይመስል፤ ከተሞችን ያጣጥላሉ፡፡ የተፋፈጉ ቆሼ ሰፈሮችን፤ የተወታተፉ ኩታራ መንደሮችን እያሳዩ ከተማነትን ይኮንናሉ፡፡ ነገር ግን ስልጣኔንና ብልፅግናን መፍጠር የሚቻለው በከተሞች እድገት ነው፡፡ ለነገሩም የዛሬዎቹ ዘመናዊና ምርጥ፣ ውብና ማራኪ ከተሞች ከመቶ አመት በፊት በቆሼ ሰፈር የተሞሉ ነበሩ፡፡ የስልጣኔና የብልፅግና ምልክት የሆኑትን ትልልቅ ከተሞች መጥራት እንችላለን … ኒውዮርክ፣ ለንደን፣ ፓሪስ፣ ሲንጋፖር፣ ቶኪዮ፣ እያልን፡፡

አገር የሚያክሉ ከተሞች  
በነዋሪዎች ብዛት ቶኪዮን የሚስተካከላት የለም - 37ሚ. ገደማ ሕዝብ ይኖርባታል፡፡ ከጃፓን ህዝብ መካከል 30 በመቶ ያህሉ በቶኪዮ ከትሟል፡፡ የሕንድ ዋና ከተማ ዴልሂ ደግሞ 22 ሚ. ሰዎች ይርመሰመሱባታል፡፡ ሳኦፖሎና ሙምባይ በ20 ሚ ተከታዩን ስፍራ ይዘዋል፡፡ ሜክሲኮ እና ኒውዮርክ ከተሞች እያንዳንዳቸው ከ19ሚ. በላይ፤ ሻንጋይ ከ16ሚ. በላይ፤ ካልካታ ከ15ሚ. በላይ፤ የባንግላዲሽ ዋና ከተማ ዳካ ከ14ሚ. በላይ፤ ካራቺ 13ሚ ሕዝብ በመያዝ እስከ 10 ያለውን ደረጃ ይዘዋል፡፡
እንዴት ነው ይኼ ሁሉ ሕዝብ ለምን ይሆን እነዚህን ከተሞች ለመኖሪያነት የመረጣቸው? መልሱ ቀላል ነው፣ ከተሞቹ ከሁሉም በላይ የንግድ፣ የምርት፣ የሥራ ማዕከል ናቸው፡፡ ለምሳሌ የብራዚሏ ሳኦፖሎ የአገሪቱ 10 በመቶ ያህል ህዝብ እየኖረባት፤ ከአገሪቱ ጠቅላላ ምርት 50% ያህል ይመረትባታል፡፡ የስራና የቢዝነስ እድል ፍለጋ ሰዎች ይጎርፉባታል፡፡ ከተሞቹ ለስራ ተስማሚ ለኑሮ ምቹ ስለሆኑ ብዙ ሰዎች ይመርጧቸዋል ይባል ይሆናል፡፡ እንደ ኒውዮርክና ሎስ አንጀለስ ያሉ ከተሞች የመኖሪያ፤ የንፅህና፤ የትራንስፖርትና የኮሙኒኬሽን አቅርቦት የተሟላላቸው እስከሆነ ድረስ ነዋሪ ቢበዛባቸው አይገርምም፡፡ ግን ሁሉም ትልልቅ ከተሞች የምቾት ደሴቶች አይደሉም፡፡ እንዲያውም፤ የሙምባይና የካራቺ፣ የናይሮቢና የአቡጃን፣ የአዲስ አበባም ሳይቀር፤ የተፋፈጉ “ኩታራ” መንደሮችንና “ቆሼ” ሰፈሮችን በማየት፤ ከተሞችንና ከተሜነትን የሚያንቋሽሹ ጥቂት አይደሉም፡፡ ከስልሳ አመት በፊት የአዲስ አበባ ግማሽ ያህል የነበረችው የህንዷ ደልሂ ከተማ፤ ዛሬ ከ15 እጥፍ በላይ ሰፍታ 22ሜ. ነዋሪዎችን ይዛለች፡፡ በዚያው መጠን “ኩታራ” ሰፈሮች በአምስት እጥፍ ጨምረዋል፡፡ እንዲያም ሆኖ፤ በጥቃቅን የገጠር ከተሞች ውስጥ ከመኖር ይልቅ፤ ደልሂ መግባት የተሻለ ነው - ሰፊ የስራና የቢዝነስ እድል ያስገኛል፡፡ ለነገሩ የዛሬዎቹ ዘመናዊና ማራኪ የአለማችን ከተሞችም፤ ንፁህና ምቹ ሆነው አልተፈጠሩም፡፡
ታዲያ፤ በኩታራና በቆሼ ሰፈሮች ምክንያት ከተሞችን ማጣጣል እና ብዙ ህዝብ ወደ ከተማ መፍሰሱን መቃወም ተገቢ ነው፡፡ “ከዚህ የባሰ ጎስቋላና አስቀያሚ ወይም ከዚህ የባሰ ቆሻሻ አካባቢ አይቶ አያውቅም፡፡ መንገዱ ጠባብ እና በቆሻሻ የጨቀየ ነው፡፡ ከዋናው መንገድ ወዲህና ወዲያ የሚያስገቡ ቅያሶችና ቀጫጭን የውስጥ ለውስጥ መንገዶች ግራና ቀኝ እርስ በርስ በተወታተፉ ጥቃቅን ቤቶች ተጨናንቀዋል፡፡ በፍሳሽና በግማት በጨቀየው መንገድ ላይ፣ ሰካራም ወንዶችና ሴቶች እየወደቁ ይንከባለላሉ፤ ይጨማለቃሉ” …. የአፍሪካን ኩታራ ሰፈሮችን ለመግለፅ የተፃፈ አይደለም፡፡
ከ170 አመታት በፊት የለንደንን መስፋፋት በሚያጥላላ መንገድ የተፃፈ ነው - በቻርልስ ዲከንስ፡፡ በእርግጥ የዛሬዎቹ ምርጥ ከተሞች፤ ያኔ ውሃ እና መፀዳጃ ያልነበራቸው ተወታትፈውና ተደጋግፈው በተሠሩ የካርቶን ቤቶች ውስጥ ሰው ተጠጋግቶና ተጨናንቆ የሚኖርባቸው፣ የበሽታ መናኸሪያ፣ ጐስቋላና ቆሼ ሰፈር የበዛባቸው አስቀያሚ ከተሞች እንደነበሩ ያውቃሉ? ጥቂቱን ላጫውታችሁ፡፡
አንትወርፕ - በተደጋጋሚ የኮሌራ ወረርሽኝ የምትታወቅ የቤልጅዬም ከተማ
በ19ኛው ክፍለዘመን በአንትወርፕና በአብዛኞቹ የቤልጅየም ከተሞች፤ በቅጥር ስራ የሚተዳደሩ ቤተሰቦች በ”ኩታራ” መንደር ውስጥ ነበር ኑሯቸውን የሚገፉት፡፡ ተፋፍገው የተሰሩ ጐስቋላ ቤቶች በሚበዙበት ቆሼ ሰፈር ውስጥ፤ ለአንድ ቤተሰብ የግል መፀዳጃ እና የግል የውሃ አቅርቦት የሚባል ነገር አይታወቅም፡፡ በዚህ ሳቢያ የተከሰቱ ሦስት የኮሌራ ወረርሽኞች በነዋሪዎች ላይ ያደረሱት ጉዳት እጅግ ከባድ፣ እጅግ አሰቃቂ ነበር፡፡
አንትወርፕ ዛሬ የብልጽግና ከተማ ነች፡፡ ከአውሮፓ ትልቅ የወደብ አገልግሎቶች መካከል አንዱ በአንትወርፕ የሚገኘው ወደብ ነው፡፡ ወደ ግማሽ ሚሊዮን የሚጠጋ ነዋሪዎችን የያዘችው አንትወርፕ፤ የቤልጅዬም ሁለተኛ ከተማ ከመሆኗም በተጨማሪ በዘመናዊ የኢንዱስትሪ ምርቶች ትታወቃለች - የመርከብ ፋብሪካ፣ የመኪኖች ግንባታ፣ የኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎች፣ የማሽኖችና የኬሚካሎች ምርት ማመንጫ ሆናለች - አንትወርፕ፡፡
ባልቲሞር - በወባና በታይፎይድ በሽታዎች የምትታወቅ የአሜሪካ ከተማ
ለባህር ትራንስፖርት አመቺ ከሚባሉ የአለማችን ትልልቅ ከተሞች አንዷ የሆነችው ባልቲሞር፤ የ350 አመት ታሪክ አላት፡፡ አብዛኛው ታሪኳ ግን በወባ እና በታይፎይድ ወረርሽኞች የተበከለ ነው፡፡ ከመቶ አመት በፊት ገደማ የነበረውን ታሪክ ለመግለጽ ተብሎ የተፃፈውን ተመልከቱ፡፡
“የባልቲሞር ድሆች መጀመሪያ የሰፈሩት ከባህሩ ዳር ነበር፡፡ የቢጫ ወባና የኮሌራ፣ እንዲሁም የታይፎይድ ወረርሽኞች፣ በየጊዜው እየተፈራረቁ ከተማዋን እንደ ማዕበል ያናውጣታል፡፡ በ1797 ዓ.ም የቢጫ ወባ ወረርሽኝ የተነሳው፤ የታጀለ ውሃ ከሚገኝበት ረባዳ የመኖሪያ ስፍራ ነው፡፡ ከዚያ ከፍ ብሎ ዳገቱ ላይ ወዳለው ሰፈር ተዛመተ፡፡ በጐስቋላ ጐጆዎች ከተጨናነቀው ቆሻሻ ሰፈር ባሻገርም፤ በጠባብ ቦይ ወረርሽኙ እስከ ኮረብታው ግርጌ መንደሮች ተስፋፋ፡፡ መንደሮቹ በካርቱንና በቁርጥራጭ ቆርቆሮዎች ተጠባብቀው በተሰሩ ኩታራ ቤቶች የተሞሉ ናቸው፡፡
በ1890 ገደማም በርካታ ክፍሎች የያዙ ቤቶች ቢገነቡም መንደሮቹ ከቆሼ ሰፈርነት አልተላቀቁም፡፡ በአንድ መኖሪያ ቤት ውስጥ እስከ ስምንት ያህል ቤተሰብ ይኖርበታል - እንደ ቤተሰብ፡፡ በአንድ ክፍል መንደሮቹ፤ ለሚያያቸው… አስጠሊታ የቆሻሻ ክምር፣ ክፍት የፍሳሽ መውረጃ፣ በረዣዥም አረሞች የተሞላ ረግረግ፣ በአመድና በቆሻሻ የተሞላ ጠባብ የውሃ መውረጃ፣ ጠቋቁሮ በሚገማ ውሃ የተሞላ ምድር ቤት፤ ኖራ ወይም ብሩሽ ነክቷቸው የማያውቁ እጅግ የነተቡ ቤቶች፤ ለወራት ውሃና ሳሙና ነክቶት የማያውቅ ገላ፣ በአጠቃላይ አሳማ አሳማ የሚሸት ከተማ ነው” ዛሬ ባልቲሞር እንደዚያ አይደችም፡፡ በባህር ብቻ ሳይሆን በባቡር፣ በአስፋልት መንገድና በአውሮፕላን ትራንስፖርት በጣም ምቹ ከመሆኗ የተነሳ፣ ከፍተኛ የቢዝነስ ማዕከል ሆናለች፡፡ በተለይ በህክምና መሳሪያዎችና ቁሳቁሶች እንዲሁም በመድሀኒት ምርምርና ምርት ጐልታ ትታወቃለች፡፡ 2.6 ሚ ሰው በሚኖሩባት በባልቲሞር ከተማ፤ ከ10 በላይ ታዋቂ ዩኒቨርሲዎችና ከመቶ የሚበልጡ የተራቀቁ የምርምር ላብራቶሪዎች ይገኙባታል፡፡ ንፁህ እንዲሁም ከከተማ ስፋት ውስጥ አስር በመቶው በአረንጓዴ ልምላሜ የተሸፈነች የፋብሪካዎችና የሰማይ ጠቀስ ህንፃዎች ከተማ ነች፡፡
ደብሊን እና ግላስኮ - በአውሮፓ ወደር የለሽ ቆሼ ከተሞች
ድሮ፣ የደብሊን የዛጉና የቆሸሹ ‹ቆሼ› ሰፈሮች፣ እጅግ ከመነቸኩት አስቀያሚ የአውሮፓ ከተሞች ሁሉ የባሱ ከመሆናቸው የተነሳ፤ ከግላስጐ “ቆሼ”ዎች በስተቀር የሚወዳደራቸው አልነበረም፡፡ መጀመሪያ ላይ ለ18ኛው ክ.ዘመን ሀብታሞች የተሠሩት ረዣዥምና ውብ ማራኪ የከተማ ቤቶች፣ ከከተማዋ መስፋፋትና ከሰራተኞች መብዛት ጋር ድሆች በደባልነት ተፋፍገው የሚኖሩባቸው ቆሻሻ ቤቶች ለመሆን ጊዜ አልፈጀባቸውም፡፡
በአሳዛኝ መልኩ ሁኔታዎች ከመቅጽበት መለወጥ ጀመሩ፡፡ በርካታ የካርቶን ቤቶች እየተደጋገፉና እየተወታተፉ ተሠርተው ከተማዋን አጨናነቋት” እንዲህ የከተማ መስፋፋትን በሚያንቋሽሽ መልክ የተፃፈላቸው ደብሊንና ግላስኮ፤ ዛሬ የብልጽግና ማዕከላት ናቸው፡፡ ግማሽ ሚሊዮን ነዋሪዎች ያሏት ደብሊን፤ ዋነኛ የንግድና የትራንስፖርት፣ የኢንዱስትሪና የዘመናዊ ቴክኖሎጂ መነ ኀሪያ ስትሆን፣ ግላስኮም ስሟ ከሳይንስና ከቴክኖሎጂ ጋር የተቆራኘ ሆኗል፡፡
የእንግሊዝ ከተሞችን በሚያጥላላ መንገድ የቀረበውን የታሪክ ጽሑፍ ተመልከቱ፡፡ “በወጣ ገባ ዳርቻዎች በኩል፣ ክምር ቆሻሻዎች አጠገብ፤ በአጥሮችና በልብስ ማጠቢያው መሃል ያለፈ ሰው የተመሰቃቀሉና የተጐሳቆሉ ባለ አንድ ፎቅና ባለአንድ ክፍል ጐጆ ቤቶች ያገኛል፡፡ ሳሎን፣ መኝታ ክፍል፣ ምግብ ማብሰያ የሚባል ነገር የላቸውም፡፡ ሁሉም አንድ ላይ ነው፡፡ አንድ ሜትር ተኩል ቁመትና አንድ ሜትር ከ82 ሳ.ሜ ስፋት ባለው እስር ቤት የመሰለ ክፍል ውስጥ፣ ሁለት አልጋዎች፣ ፎቅ መውጫ መሰላል፤ የጭስ መውጫ እና ቅራቅንቦ ክፍሉን ከአፍ እስከ ገደፉ ሞልተውታል”
ከተሞቹ ግን አድገውና በልጽገው፤ ሰልጥነውና ተውበው በአለም የሚታወቁ ሆነዋል፡፡ ሜልቦርን - በቆሻሻ የተዝረከረከች
የሜልቦርን ስመ ጥፉ “ቆሼ” ከተማ - ሊትል ቡረክ ስትሪት ይባላል - በ1880ዎቹ፡፡ የመንገዱ ጠርዞች በሙሉ በሁሉም ዓይነት ቆሻሻ የተሞሉ ናቸው፡፡ የቆሻሻ ማጠራቀሚያዎች ጢም ብለው ሞልተው ያፈስሳሉ፡፡
መጥፎ ጠረን የፈጠረ አትክልት ወይም ሞቶ የበሰበሰበ እንስሳ፤ የእህል ገለባ፣ የቤት ጥራጊ፣ ያረጁ ጨርቆች… ምን አለፋችሁ የቆሻሻ ዘር ሁሉ ይዝረከረካል፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ የበሰበሰበው የቆሻሻ ክምር የሚፈጥረው እጅግ የሚሰነፍጥ መጥፎ ጠረን በዚያ ማለፍን አስቸጋሪ አድርጐ ነበር፡፡ የዛሬ ሜልቦርን፤ የአውስትራሊያ ውብ የብልጽግና ከተማ ነች፡፡ በዘመናዊ ቢዝነስና በታላላቅ ዩኒቨርሲቲዎች የምትታወቀው ሜልቦርን፤ 3ሚ ነዋሪዎች አሏት፡፡
ኒውዮርክ ማንሃተን
በኒውዮርክ ማንሃተን ከ200 ዓመት በፊት በሁለት ሄክታር ላይ የተንጣለለ “ኮሌክት” የተባለ ተወዳጅ ሐይቅ ነበር፡፡ በ1750ዎቹ ገደማ በሐይቁ ዙሪያ የተቋቋሙ ቄራዎችና የቆዳ ፋብሪካዎች፤ ለበርካታ ሰዎች የስራ ዕድልን፤ ለበርካታ ነዋሪዎች ጠቃሚ ምርቶችን የሚያቀርቡ ቢሆንም ሃይቁን ማበላሸቱ አልቀረም - ቆሻሻ፡፡
ከጊዜ ወደ ጊዜ ከየቦታውና ከየቤቱ እየመጣ ወደ ሃይቁ የሚገባ ቆሻሻ እየጨመረ ስለመጣ፤ ሃይቅነቱ እየጠፋ መጣ፡፡ ቆሻሻዎች ማራገፊያ የሆነው ሃይቅ፤ በሩቅ የሚሰነፍጥ ኃይለኛ መጥፎ ሽታ ያመነጫል፡፡ በ1810 ገደማ ሙሉ በሙሉ በቆሻሻ ሞላ፡፡ በ1825 ዓ.ም ሐይቁ በነበረበት ስፍራ፣ በዓይነቱ አዲስ የሆነ ነገር ቆሞ ተገኘ - የመጀመሪያው የቆሻሻ ክምር”
በቆሻሻው ምክንያት ከተሜነትን በማጥላላትና ገጠሬነትን በማዳነቅ የኒውዮርክን እድገት ለመቅጨት አለመቻሉ በጀ፡፡ ዛሬ፤ ኒውዮርክ የብልጽግናና የስልጣኔ ፋና ነች፡፡
ስለ ድሮዋ ፓሪስ የተፃፈውንም እዩ፡፡
በ“ቆሼ” የፓሪስ መንደሮች የሚያድጉ ብዙ ልጆች፣ ውሃ ስለማያገኙ ገላቸውን አይታጠቡም፡፡ ቆሻሻው እላያቸው ላይ ተጋግሮ አካላቸውን ይሰነጣጥቀዋል፡፡ ጀርም የያዘ አቧራ በየስንጥቆቹ ገብቶ ኢንፌክሽን ፈጥሮ ስለሚያቆስል፣ ከሰውነታቸው መግል ይፈስ ነበር”
ዛሬ ግን ውቢቷ የብርሃን ከተማ እየተባለች ትጠራለች - ፓሪስ፡፡
ቶኪዮ - የጃፓን ዋና ከተማና ትልቋ ከተማ ናት፡፡ ቶኪዮ በፋይናንስ፣ በኢንዱስትሪ፣ በንግድ፣ በትምህርትና ባህል ማዕከልነት እያገለገለች ሲሆን፤ በዓለማችን እጅግ ብዙ ሕዝብ በመያዝ ቀዳሚ ናት - 36.7 ሚሊዮን ሕዝብ ይኖርባታል፡፡
ቶኪዮ ውስጥ በ1920ዎቹ የነበሩት ጐስቋላና ቀሽም (ጌቶ) መንደሮች፣ የቶኪዮ የከተሜነት ልማትና የጃፓን ዘመናዊ ኢኮኖሚ ዕድገት ውጤት ነበሩ፡፡ እነዚያ ተደጋግፈው

የቆሙ ጐስቋላና ደካማ የካርቶን ቤቶች መጠን፣ አስገራሚ ነበር፡፡ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ፤ በሁሉም የቶኪዮ አካባቢዎችና በአሮጌው የቶኪዮ እምብርት ሁሉ ሳይቀር በየኪዮስክ ቦታዎች የሚሠሩት “ቆሼ” የድሀ ቤቶች እንደገና እንደ አሸን ፈሉ፡፡ የትላንቶቹ ውትፍትፍ “ቆሼ” መንደሮች፣ ዛሬ የዓለማችን ምርጥ ከተሞች ናቸው፡፡

 

Read 6040 times Last modified on Saturday, 10 December 2011 12:41