Monday, 14 April 2014 09:44

በስድሳዎቹ ላይ የተላለፈው አሳዛኝ ውሳኔ

Written by  ኤልያስ
Rate this item
(40 votes)

ከአዘጋጁ-
ከዚህ በታች የቀረበው ፅሁፍ በደርግ መንግስት ጠ/ሚኒስትር በነበሩት ሻምበል ፍቅረስላሴ ወግደረስ ተፅፎ በቅርቡ ለንባብ ከበቃው “እኛና አብዮቱ” የተሰኘ መፅሐፍ የተወሰደ ነው፡፡ በተለይ መጽሐፉን አግኝተው የማንበብ ዕድል ላላገኙ አንባብያን የመጽሐፉን መንፈስ እንዲያገኙት በማሰብ ጥቂት ገፆችን ቀንጭበን አቅርበናል፡፡

ሻለቃ መንግሥቱ በተቀሰቀሰው ስሜት በማዘንና በመተከዝ፣ በመናደድና በመቆጣት ስሜት እየተቀያየሩ በቴፕ በተሰማው ንግግር ላይ በመመርኮዝ ሰፊ ገለጣ አደረጉ፡፡ “የእናንተ ስሜት እንዳይጐዳ እያልን ብዙ ነገር ከመናገር እንቆጠባለን እንጅ የጄነራል አማን እቅድ በጣም ሰፊና አደገኛ ነው” ብለው ንግግራቸውን በመቀጠል “የደርግ አባላትን ወደመጡበት ክፍል መልሶ ደርግን በማፍረስ ከደርግ አባላት ሰባት፣ ከውጭ ደግሞ ሰባት መኮንኖችን ያቀፈ ወታደራዊ ካውንስል በእሳቸው መሪነት እንዲቋቋም ጠይቀውኝ የማልስማማ መሆኔን ነግሬአቸዋለሁ፡፡ ይህ ሃሳባቸው ተቀባይነት ሲያጣ፣ የጦር አዛዦችን በማሰባሰብ መፈንቅለ መንግሥት በማድረግ ሕዝቡ ሆ ብሎ ከሥልጣን ያወረድናቸውን የኃይለሥላሴ መንግሥት ባለሥልጣናትን ከእሥር ቤት በማስወጣት መልሰው በሥልጣን ላይ ለማስቀመጥ እቅድ እንዳላቸው በመረጃ ደርሰንበታል፡፡ ለዚህም ካስፈለገ መረጃውን እናቀርባለን” ብለው ለአጭር ጊዜ ዝም ሲሉ የአዳራሹ ፀጥታ እንደገና ደፈረሰ፡፡ ጉምጉምታና የመገረም ስሜት መሰማት ጀመረ፡፡
ሻለቃ መንግሥቱ በሰጡን መግለጫና በሰማነው የቴፕ ንግግር ሁላችንም ስሜታችን ተነክቷል፡፡ ኃዘንም፣ ፍርሃትም፣ ድንጋጤም፣ ንዴትም በእያንዳንዳችን አዕምሮ ይመላለሳል፡፡ በማንኛውም ሰዓት ልንመታ እንደምንችል ስጋት አደረብን፡፡ ይህንን ስሜታችንን በሚገባ ያጤኑት ሻለቃ መንግሥቱ፤ “አስጊ ሁኔታ ውስጥ ነው የምንገኘው” አሉ፡፡ “ጦሩ ብዙ ጊዜ “የኃይለሥላሴን ባለሥልጣናት አሥራችሁ ትቀልባላችሁ” እያለ ወቀሳ ሰንዝሮብናል ብለው ዝም አሉ፡፡
በከፍተኛ ስሜት ለመገፋፋት ጥቂት የደርግ አባላት እየተነሱ ንግግር ማድረግ ጀመሩ፡፡ “እኛን ለማጥፋት ከተነሱ የኢትዮጵያን ሕዝብ የበደሉትን ማጥፋት አለብን! ካልቀደምናቸው ይቀድሙናል” በማለት ሥጋታቸውን ገለጡ፡፡ እያንዳንዱን ተናጋሪ በመከተል “ትክክል ነው! እርምጃ መውሰድ አለብን! አደገኛውን እንቅስቃሴ ማክሸፍ የምንችለው ቆራጥ እርምጃ በመውሰድ ብቻ ነው” እያሉ አንገታቸውን እየነቀነቁ ድጋፍ የሚሰጡ ነበሩ፡፡ በዚህ ሁኔታ ቅስቀሳው ተፋፋመ፡፡ አንድ ውሳኔ የምንሰጥበት ደረጃ ላይ መድረሳችን ግልጽ እየሆነ መጣ፡፡ ተናጋሪዎች ሁሉ በንግግራቸው መጨረሻ በታሠሩት ሰዎች ላይ እርምጃ እንዲወሰድ አሳሰቡ፡፡ አብዛኛው ይህን አስተያየት የተቀበለው መስሎ ታየ፡፡ በመጨረሻ ስብሰባውን የሚመሩት ሻለቃ መንግሥቱ፤ ከዚህ በፊት ሲያደርጉት እንደነበረው አሁን እያነሳችሁት ያላችሁት ጉዳይ ዛሬ ከተሰበሰብንበት አጀንዳ ውጭ ስለሆነ አስፈላጊ ከሆነ ወደፊት አጀንዳ ይዘን እንነጋገርበታለን ብለው ማስቆም ሲችሉ ውሳኔ ወደማሰጠት ተሸጋገሩ፡፡
“በእኛ ላይ እያንዣበበ ያለውን አደጋ በስፋት አስተውለናል፡፡ ከዚህ አደጋም ለመውጣት የምንችለው ፈጣንና ቆራጥ እርምጃ ስንወስድ ብቻ እንደሆነ ብዙዎቻችሁ ተናግራችኋል፡፡ ስለሆነም ከታሠሩት የቀድሞ ባለሥልጣናት በተወሰኑት ላይ የመጨረሻውን እርምጃ እንድንወስድ በድምጽ ብልጫ እንወስን” አሉ፡፡ የተቃወመ አልነበረም፡፡ ብዙዎቻችን አንገታችንን በማወዛወዝ የቀረበውን ሃሳብ በምልክት ደገፍን፡፡ ደርግ በስሜት ተገፋፍቶ አንድ አቋም በያዘበት ወቅት አንድ ግለሰብ ለመቃወም ወይም የተለየ አስተያየት ለመስጠት ቢሞክር ከባድ ቅጣት እንደሚደርስበት ስለሚታወቅ፣ ይህን ጉዳይ አስመልክቶ ተቃዋሚ እንኳን ቢሆን ተቃውሞውን ከዝምታ ውጭ በግልጽ ያሰማ አልነበረም፡፡ ይህም ሆኖ ግን የሕግ ባለሙያ ስለሆነ ሊሆን ይችላል ሻለቃ ብርሃኑ ባይህ ብቻ ተነስቶ “በሕግ የተያዘ ጉዳይ ስለሆነ በሕግ ለምን አንጨርሰውም” አለ፡፡ የደገፈው ግን አልነበረም፡፡
ተሰብሳቢው ወደ አንድ አቅጣጫ ማዘንበሉን የተገነዘቡት ሻለቃ መንግሥቱ፤ “የተወሰኑት የቀድሞ ባለሥልጣናት በሞት እንዲቀጡ የምትሰማሙ እጃችሁን አውጡ” አሉ፡፡ ከደርግ አባላት በተጨማሪ የንዑስ ደርግ አባላትና ሌሎችም ተሳታፊዎች በሙሉ ድምፅ የመስጠት መብት ስለተሰጣቸው አብዛኞቹ የቀረበውን የውሳኔ ሃሳብ በመደገፍ እጃቸውን አወጡ፡፡ በጣም ጥቂት የደርግ አባላት እጃቸውን ያላወጡ ቢኖሩም “የምትቃወሙ ወይም ድምጽ የማትሰጡ እጃችሁን አውጡ” ተብለው ሲጠየቁ፣ ከፍርሃት የተነሳ ዝም ብለው አደፈጡ፡፡ በመጨረሻ “በሞት እንዲቀጡ” የሚለው ሃሳብ በሙሉ ድምጽ ተደግፏል ተብሎ ተመዘገበ፡፡ ይህ ውሳኔ እንደተሰጠ ሻለቃ መንግሥቱ ሻለቃ ጌታቸው ሺበሺን በስም ጠርተው “የእሥረኞችን የሥም ዝርዝር የያዘውን መዝገብ አምጣ” ብለው አዘዙት፡፡ መዝገቡም ቀረበ፡
ሻለቃ መንግሥቱ “መረጃ አለ” ብለው ውጥረቱን ረገብ በማድረግ “ጄነራል አማን እጃቸውን እንዲሰጡ ብንጠይቃቸው ፈቃደኛ ሆነው ባለመገኘታቸው ቤታቸው ተከቧል፡፡ ከዚህ በኋላ ማባበሉና መለማመጡ ጥቅም ስለሌለው በሰላም እጃቸውን የማይሰጡ ከሆነ” ብለው በስብሰባው ተሳታፊ የነበሩትን ኮሎኔል ዳንኤል አስፋውን በስም በመጥራት “በሰላም እጃቸውን እንዲሰጡ፡፡ ይህ ካልሆነ ግን እንዲደመሰሱ” የሚል ትዕዛዝ ሰጧቸው፡፡ ኮሎኔሉም ትዕዛዙን ተቀብለው ለማስፈፀም ከስብስባው አዳራሽ ወጥተው ሄዱ፡፡
አሳዛኙ ውሳኔ ከተላለፈ በኋላ “በእያንዳንዱ እስረኛ ላይ እየተነጋገርን ውሳኔ የምንሰጠው ከምሳ በኋላ ይሆናል፡፡ ምሳ ተዘጋጅቶ እዚህ ስለሚመጣ ማንም ሰው ወደ ቤቱ ወይም ወደ ሌላ ቦታ ሊዘዋወር አይፈቀድለትም” ተብሎ ስለተነገረን፣ ደርግ መሰብሰቢያ አዳራሽ ዙሪያ በሚገኙ ክፍሎች ውስጥ ተዘጋጅቶ የሚጠብቀንን እንጀራ በልተን ሻይና ቡናም ጠጣን፡፡ እርስ በርሳችን በቅርብ ስለማንተዋወቅ ምሳ ላይ ሳለን ቀድሞ ያሳለፍነውን ውሳኔ አስመልክቶ ምንም ውይይት አላደረግንም፤ ዝም ማለቱና በሌላ ጉዳይ ላይ መወያየቱ ለሁላችንም የተሻለ አማራጭ ነበር፡፡
ከሰዓት በኋላ በሰባት ሰዓት ሁላችንም በስብሰባው አዳራሽ ጠቅለን ነበር፡፡ ሁለቱም ምክትል ሊቀመናብርትም ተከታትለው ገቡ፡፡ ሻለቃ መንግሥቱ አንድ ትልቅ መዝገብ ይዘዋል፡፡ ወንበራቸው ላይ እንደተቀመጡ መዝገቡን ጠረጴዛቸው ላይ አኖሩት፡፡ አዳራሹ ፀጥታ ሰፍኖበታል፡፡ ድንጋጤና ፍርሃት አስጨንቆናል፡፡ የምናሳልፈው ከባድ ወሳኔ አሳስቦናል፡፡ ሳናስበውና ሳንፈልገው በሁካታ እንድንወስን መገፋፋታችንን የተወሰኑ የደርግ አባላት ተገንዝበውታል፡፡
“ከምሳ በፊት በተስማማንበት መሠረት የእስረኞቹን ስም ዝርዝር በቅደም ተከተል አነባለሁ፡፡ የእያንዳንዱ እስረኛ የሚታወቅ ጥፋቱ ይነገራል፡፡ በመጨረሻ በድምጽ ውሳኔ እንሰጣለን” ብለው ሻለቃ መንግሥቱ የባሕር መዝገቡን ከፈቱ፡፡ ከኪሳቸውም ምልክት ማድረጊያ እስክሪፕቶ አውጥተው ያዙ፡፡ ማንም የተለየ አስተያየት አልነበረውም፡፡ “በአንድ እስረኛ ላይ እዚህ ከተሰበሰብነው ሃምሳ ከመቶ በላይ በሞት ይቀጣ ብሎ እጅ ከወጣበት ይቀጣል፡፡ ከሃምሳ በመቶ በታች ከሆነ ግን ይድናል” ብለው ስለአወሳሰኑ ማብራሪያ ሰጡን፡፡
ከዚህ በኋላ ስም መጥራቱ ተጀመረ፡፡ በመጀመሪያ የአቶ አክሊሉ ሃብተወልድ ስም ተጠራ፡፡ ሁሉም ያውቃቸዋል፡፡ ለረጅም ጊዜ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው አገልግለዋል፡፡ ለኢትዮጵያ ኋላቀርነት፣ ለሕዝቡ ድህነት፣ በወሎ ለደረሰው ረሃብና እልቂት ተጠያቂ እንደሆኑ ከተሰብሳቢዎቹ ውስጥ የተወሰኑት እየተነሱ ተጨባጭ ማስረጃ ይኑረው አይኑረው የማይታወቅ ወንጀል ደረደሩባቸው፡፡ ከዚያ “በሞት እንዲቀጡ የምትስማሙ እጃችሁን አውጡ” ተባለ፡፡ አብዛኛው ተሰብሳቢ እጁን አወጣ፡፡ ከሃምሳ ከመቶ በላይ መሆኑ በቆጠራ ተረጋገጠ፡፡ “በሞት እንዲቀጡ ተወስኗል” ብለው ሻለቃ መንግሥቱ ምልክት አደረጉ፡፡ በዚህ ዓይነት ፍርድ መስጠቱ እስከምሽቱ አንድ ሰዓት ድረስ ቀጠለ፡፡
***
ኢህአፓና ወጣቱ የኅብረተሰብ ክፍል
ኢሕአፓ የተመሠረተው፣ ከላይ እስከታች የተዋቀረውም በአብዛኛው በወጣቶች ነበር፡፡ ከሠራተኛው ከመምህራንና ከተማረው ኅብረተሰብ ክፍል ወጣቶች ተመልምለው በኢሕአፓ በተደራጁ የሙያ ማህበራት ውስጥ በአመራር ሰጭነትና በተራ አባልነት ያሰማራቸው የነበሩት ወጣት ተማሪዎች ነበሩ፡፡ ወጣት ተማሪዎች ምን ዓይነት ለውጥ እንደተደረገ እንኳን በደንብ ሳይረዱ “ለውጡን ያቀጣጠልን የለውጥ ሐዋሪያ ነን” ብለው ስለሚያምኑ፣ ግምባር ቀደም ኃይል ነን ብለው ስለሚገምቱ፤ ሞትን እንኳን ሳይፈሩ ከማንኛውም አደገኛ ኃይል ጋር በጀብደኝነት ፊት ለፊት ይጋፈጣሉ፡፡ የወጣት ተማሪዎችን መሠረታዊ ድክመት ብዙም ጥያቄ የማያቀርቡና ማብራሪያም የማይፈልጉ በመሆናቸው፣ በድርጅታዊ ዲሲፕሊን ሽፋን የድርጅት መመሪያ ነው አድርጉ ወይም ፈጽሙ ተብሎ የሚመጣላቸውን ትዕዛዝ ባለማወላወል ተግባራዊ ስለሚያደርጉ ኢሕአፓ ፍላጐቱን ለማሟላት ምቹ መሣሪያ ሆነው አገኛቸው፡፡
ደርግ “ለሕዝቡ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት አስተዋጽኦ ያደርጋል” ብሎ የሚወስደውን ማንኛውንም እርምጃ ኢሕአፓ አቃቂር በማውጣትና በማጥላላት የወጣቱን ስሜት የሚቀሰቅሱና የሚስቡ መፈክሮች በማንሳት፣ ወጣት ተማሪዎችን በከፍተኛ ደረጃ ለመመልመል በቃ፡፡ አብዛኛውን ወጣት ተማሪ ለመመልመል የቻለው በዕድገት በኅብረት የዕውቀትና የሥራ ዘመቻ ወቅት የከተማ ቦታና ትርፍ ቤቶች እንዲወረሱ የሚደነግገው አዋጅ ከወጣ በኋላ ነው፡፡
ኢሕአፓ ወጣቱን አባልና ደጋፊ ለማድረግ የበቃው በማሳመንና በፈቃደኝነት ብቻ አልነበረም፡፡ በማንኛውም ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ተሳታፊ ለመሆን ፍላጐት ያልነበረው ማንኛውም ወጣት፤ ኢሕአፓ ለሚያካሂደው እንቅስቃሴ ጠቃሚ መስሎ ከታያቸው በማስገደድ ወይም በማስፈራራት ወይም ስም በማጥፋት ሳይወድ በግድ አባል ያደርጉታል ወይም የሚሰጡትን ሥራ እንዲፈጽም ያስገድዱታል፡፡

Read 6687 times