Monday, 14 April 2014 09:40

እንዴት ያገሳ ይሆን ያሉት በሬ እምቧ ይላል (ዋን ጣገኔ ጊዶ ህምባ ጌስ) የወላይታ ተረት

Written by 
Rate this item
(5 votes)

 አንድ የህንድ አፈ-ታሪክ እንዲህ ይላል፡፡ ከዕለታት አንድ ቀን ወደ አመሻሹ ላይ አንድ የህንድ የመንደር አለቃ በድንገት ሴት ልጁ ወደምትተኛበት ድንኳን ጥልቅ ይላል፡፡ ለካ ሴት ልጁ ከሰፈሩ ቆንጆ ጎረምሣ ጋር ተቃቅፋ ተኝታ ኖሯል፡፡ ያ ጎረምሣ በሰፈሩ ዝነኛ ጀግና በመባል የሚታወቅም ነው፡፡ “እንግዲህ” አለ አባትዬው “ልጄን አቅፈህ እስከ መተኛት ከደረስህ በሥርዐቱ ልታገባት ይገባል፡፡ ሆኖም በሥርዓቱ እንድታገባትም ብፈቅድልህ እንዲሁ አልሰጥህም”
ጎረምሣው ጀግናም፤
“ምን ማድረግ አለብኝ ጌታዬ?” ሲል ጠየቀ፡
አባትየው፤
“ፈተና እሰጥሃለሁ፡፡ ያንን ፈተና ካለፍክ ልጄን እድርልሃለሁ”
ጎረምሣው ጀግና፤
“ለእሷ ፍቅር ስል ማናቸውንም ፈተና እቀበላለሁ!” አለ በሙሉ ልብ፡፡
አባትየውና ጎረምሣው ጀግና ተያይዘው መንደሩ ውስጥ ወደሚገኘው ሐይቅ ሄዱ፡፡ ክረምት ስለገባ ብርዱ እጅ ይቆርጣል፡፡ ቅዝቃዜው በድን ያደርጋል፡፡ ሁለቱም ደራርበው ለብሰዋል፡፡ ከፊታቸው በስተቀር የሚታይ ሰውነት የለም፡፡
ያ ሀይቅ ረግቶ በረዶ ሰርቷል፡፡ ጠርዙ ላይ ቆሙ፡፡
አባትየው፤
“ይህን በረዶ ከስክሰህ ገብተህ፣ ወደዚያኛው የሐይቁ ዳርቻ ዋኝተህ፣ ሁለቱን ኪሎ ሜትር ጨርሰህ፣ እዚህ ተመልሰህ ትመጣለህ፡፡ ስትመለስ ታላቅ ፌሽታ አደርግልሃለሁ፡፡ ከዛ ልጄን በሠርግ ታገባታለህ” ይለዋል፡፡
ጎረምሣው ጀግናም፤
“ለእሷ ያለኝ ፍቅር ይህንን ወንድነቴን (manhood) የሚፈታተነውን ፈተና እንዳልፍ እንደሚያበረታታኝ አልጠራጠርም” አለ፡፡
ከዚያም በረዶውን እየከሰከሰ ቆፍሮ በበረዶው ውሃ ውስጥ ዋና ጀመረ፡፡ ከሶስት ሰዓት በኋላ የጎረምሳው ጀግና ወሬ ደብዛው ጠፋ፡፡ እምጥ ይግባ ስምጥ የሚያቅ ሰውም ጠፋ፡፡ በስምምነታቸው መሠረት አባትየው ምሽቱ ዐይን እስኪይዝ ድረስ  ጠበቀው፡፡ ለአንዴም ለሁሌም እንደሄደ፤ እንዳበቃለት አወቀ፡፡ ያን ቅዝቃዜ ተቋቁሞ ያ ጎረምሣ ለፍቅረኛው አልደረሰላትም፡፡
የመንደሩ አለቃ፤ ለዚያ ጎረምሳ፣ ለልጁ እጮኛ ማስታወሻ ይሆን ዘንድ ሐይቁ ስም እንዲወጣለት አደረገ፡፡
ይኸው እስከዛሬ ያ ሐይቅ፤
“ደደቡ ሐይቅ” በመባል ይታወቃል፡፡
*       *      *
ደደቡ ሐይቅ ላለመባል ግራና ቀኝ ማየት፤ አርቆ ማስተዋል፤ ግትር አለመሆን ይጠበቅብናል፡፡ አንድና አንድ ነገር ላይ ብቻ አተኩረን፣ እሱም ላይ ግትር ሆነን አንችለውም፡፡ ምክንያቱም ከየአቅጣጫው የሚቦረቡሩንን ችግሮች ስራዬ ብለን ስለማናያቸው አወዳደቃችን አያምርምና ነው፡፡ የምናደንቀውና የምናወራለት ነገር ሳናስበው ከወደቀ “ወርቅ ከዛገ ብረት ምን ሊሆን ነው?” እንዳለው ቻውሰር፤ “ያመኑት ፈረስ ጣለ በደንደስ” ይሆንብናል፡፡
በድህነት ላይ ሙስና ተጨምሮ የት እንደሚያደርስ ማንም ጅል አይስተውም፡፡ “በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ” ነው፡፡
“ከተማ ኢኮኖሚዋን በኮንትሮባንድ ላይ ከመሰረተች፤ አይዟችሁ፤ የጉምሩክም ሰራተኞች የደምቡን ጉርሻ ብቻ ነው የሚወስዱት” እያለ ይሳለቃል የአሜሪካው ተጓዥ ፀሀፊ ፒተር ማቴይሶን፡፡ ድርሻ ድርሻችንን ከወሰድን በኋላ፤ አገራችን እያደገች ነው ብሎ መለፈፍ ምን ያህል ቀላል እንደሚሆን መተማመን አያዳግትም፡፡ ትላልቆቹ አሳዎች የበሉትን በልተው ትናንሾቹ አሳዎች ላይ ቢላክኩ፤ የ “አይጥ በበላ ዳዋ ተመታ” ታሪክ ያህል አስገራሚ ነው፡፡ (እርግጥ ትናንሾቹ አሳዎችም ትርፍራፊ አልለቃቀሙም ማለት አይደለም፡፡) ህዝብም ያንን አይቶ “ወይ አገሬ!” የሚል ቁጭት ቢያሰማ አይገርምም፡፡ ቁጭቱን ሲለማመደው ግን “እገሌ ከበላው፣ እገሌ የበላው ይበልጣል፤ እንወራረድ!” እያለ የዕለት ኑሮ ያደርገዋል፡፡
የፈረንሳዩ ፀሀፊ ዣን ዣክ ሩሶ፤
“በፈጣሪ እጅ የተሰራው ፍፁም ነበር፡፡ እሰው እጅ ሲገባ ይነክታል ይነትባል” ይለናል፡፡ ወይም በእኛ ቋንቋ “ይቸከላል!”፤ ወይም የድሮው መሪ እንዳሉት “ብታምኑም ባታምኑም ሞተናል!” ያሉት ዓይነት ነገር ይሆናል፡፡
“ቀይ የመንገደኛ መብራት ሲበራ ማለፍ ክልክል ነው” የሚል የእንስት ድምፅ በየመንታ መንገዱ መብራቶች ዙሪያ ይሰማል፡፡ ማንም ባለመኪና ባይሰማውም የሴትየዋ ድምጽ፤ ከመንገዱ መብራት ጋር ብቅ ይልና እንደማንኛውም የድምፅ የአየር ብክለት፤ ማለትም እንደጡሩምባው፣ እንደ ጩኸቱ፣ እንደ አውቶብሱ ገዝጋዥ ድምፅ ወዘተ መወትወቱን ይቀጥላል፡፡ ባለመኪናውም አይሰማም፤ እግረኛውም አይሰማም፡፡ መንገዱም አይሰማም፡፡ በማይሰማ ማህበረሰብ መካከል የቴክኖሎጂ ፋይዳ ምን ያህል እንደሆነ ሳይጠቁመን አይቀርም፡፡
ሙስና ቁመቱና ዐርቡ እንዲሁም ስፋቱ አህጉራችንን ያጥለቀለቀ ነው፡፡ እንደተስቦ ድንበርተኞቹን አገሮች ያዳርሳል፡፡ የእኛ ውስጥ ውስጡን በተምችም፣ በምችም፣ በምሥጥም ጀምሮ አሁን አሁን መስረቅም ሆነ መንጠቅ አሊያም መዝረፍ፤ ወደ ብዝበዛ ተሸጋግሮ እንደ ናይጄሪያና ኬንያ ዐይን-ያወጣ የሆነበት ደረጃ ለመድረስ አንድ ሐሙስ የቀረን ይመስላል፡፡
ኦባፌሚ አዎሎዎ የተባለው የናይጄሪያ ጠበቃና ፖለቲከኛ፣ “ብዙዎቻችን የምንስማማበት አንድ ነገር አለ፡፡ ይኸውም በአፍሪካ ማህበረሰብ ሙስናን ማጥፋት አዳጋች ሥራ መሆኑ ብቻ አይደለም፡፡ ይልቁንም ዋናው ጣጣ፤ የማይቻል ዓላማ ማለማችን ነው፡፡ ለዚህ ምክንያቱ የታችኛውን ሌባ የሚያስረው የላይኛው ሌባ መሆኑ ነው” ይለናል፡፡ እንግሊዞቹ who guards the guards እንደሚሉት መሆኑ ነው (ጠባቂዎቹን ማን ይጠብቃቸዋል እንደማለት ነው፡፡) ሥርዓቱ የፈቀደውን ሌብነት ያካሂዱ ዘንድ ዕድሉን አትከልክሏቸው፡፡ የሁላችንም የጋራ ሀብት ሌብነት ነውና ብንልም ያስኬዳል፡፡
ዛሬ መታሰርም እየቀለለ መጥቷል ይባላል፡፡ አንድ የአሥር ዓመት ፍርደኛ ያሉት ነገር እዚህ ላይ ተጠቃሽ ነው፡፡ “አይዟችሁ ብትታሠሩም የሰረቃችሁት ገንዘብ ያኖራችኋል፡፡” አንድ የዱሮ ባለሥልጣን እሥር ቤት ሲጎበኙ፤ “ይህ እሥር ቤት መታደስም፣ መስፋፋትም ይገባዋል፡፡ የወደፊት ቤታችን‘ኮ ነው!” አሉ፤ አሉ፡፡ አሉ ነዋ ነገራችን ሁሉ፡፡
The Strongest Poison ever known
Came from Caesar’s Laurel Crown
(auguries of Innocence)
“በዓለም ከታወቁት መርዞች፣ እጅግ በልጦ የተገኘው
ከቄሣር የወይራ ጉንጉን፣ ከዘውዱ የሚመጣው ነው” የሚለው ይሄ የዊሊያም ብሌክ ግጥም፤ የዓሳ ግማቱ ከጭንቅላቱ” ከሚለው የአማርኛ ተረት ጋር አብሮ-አደግ ነው፡፡ እኛ ስለዕድገት፣ ስለልማት ጧት ማታ እያወራን፣ ስለመልካም አስተዳደርና የሕግ የበላይነት እያወራን፤ ላይና ታች ሳይባል በየዕለቱ የሚሰማው የሙስና ጀብድ፤ አሳዛኝም አስደንጋጭም እየሆነ ነው፡፡ በከፍተኛ ደረጃ የሚወሳለት ዕድገት በዚህ ሁሉ ሙስና ማህል አቋርጦ እንዴት እንደሚሸጋገር አሳሳቢ ነው፡፡ እንዴት ያገሳ ይሆን ያሉት በሬ እምቧ ይላል፤ እንደሚባለው እንዳይሆን ዐይናችንን ገልጠን እንይ!

Read 6625 times