Monday, 07 April 2014 15:52

የአለቃ ተክለ ኢየሱስ የታሪክ ማጣፈጫ ግጥሞች ሲፈተሹ

Written by  ጵርስፎራ ዘዋሽራ
Rate this item
(5 votes)

ከተድላ ሞት በኋላ ልጁጅ ደስታ ተድላ ወደ ሥልጣን መጣ፤ ራስ ደስታ ልክ እንደ ብሩ ጎሹ የኃይለኛነት ጠባይ ነበረው፤ በዚህ የተነሣ በወዲህ ምኒልክን በወዲያ ተክለ ጊዮርጊስን ግራ አጋባ፡፡ በድንገት ዓባይን ተሻግሮ፣ ሸዋን ስለወረረ በሁኔታው ግራ የተጋባው ምኒልክ፤ “እዘን ሸዋ” ሲል አስለፈፈ፡፡ ተክለ ጊዮርጊስ በበኩሉ፤ የደስታን ጥጋብ በጋብቻ ለማቀዝቀዝ አስቦ፣ ልጁን እንዲያገባ ጋበዘው፡፡ ሆኖም በሀገራችን የጋብቻ ሕግ መሠረት፤ ሙሽራው ሄዶ ሙሽራዋን መውሰድ ሲገባ፣ ደስታ በተቃራኒው ሙሽራዋ እንድትላክለት ጠየቀ፡፡

    የታሪክ ጸሐፍት በአንድ ሀገር ላይ የተከሰተውን ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ሕይወት መሠረት አድርገው ታሪክ በሚጽፉበት ጊዜ፣ ወቅቱን ተከትለው በሕዝብ ዘንድ የተፈጠሩ ግጥሞችንና ምርጥ አባባሎችን ለሥራቸው ማጣፈጫ አድርገው ያቀርቧቸዋል፡፡ ታዋቂ ሠዓሊና ታሪክ ጸሐፌ የነበሩት አለቃ ተክለ ኢየሱስ ዋቅጅራም ያደረጉት ይህንኑ ነው፡፡
የምዕራብ ወለጋ ተወላጅ የሆኑት አለቃ ተክለ ኢየሱስ ዋቅጅራ ከዘመነ ኦሪት እስከ ዘመነ መሳፍንትና እስከ ዓፄ ዮሐንስ፣ ዓፄ ምኒልክና ንጉሥ ተክለ ሃይማኖት (ንጉሠ ጎጃም ወከፉ) ድረስ የነበረውን ታሪክ የጻፉት በየዘመኑ ከተከሰጹ ታሪካዊ ሂደጾች ጋር የሚዛመዱ ሕዝባዊ ግጥሞችንና ምርጥ አባባሎችን እንደ ታሪኩ ቅደም ተከተል በመጽሐፋቸው ላይ በማስፈር ነው። ጸሐፌ ታሪክ ተክለ ጻድቅ መኩሪያም በርካታ የታሪክ መጻሕፍትን የጻፉት በዚሁ ስልት ነው፡፡
ግጥሞቹ የሚገኙት በመጀመሪያ አለቃ ተክለ ኢየሱስ ዋቅጅራ “የጎጃም ታሪክ” ብለው በእጅ ከጻፉትና ዶ/ር ሥርግው ገላው፤ “የኢትዮጵያ ታሪክ ከአለቃ ተክለ ኢየሱስ ሐተታ” ብለው በ2002 ዓ.ም በአሳተሙት መጽሐፍ ላይ ነው፡፡ በሰንሳ መገን በቀረርቶ፣ በፉከራ፣ በበገና፣ በወረብ፣ በለቅሶ ዘፈን መልክ የተጻፉት ግጥሞቹ በርካታዎች ሲሆኑ በዚህ ጽሑፍ የቀረቡት በተመጠነ መልኩ ነው፡፡
በጎጃሙ ገዥ በራስ መርዕድ ኃይሉና በጎንደሩ ጦረኛ በራስ ወልደ ገብርኤል መካከል ብርቱ ጠብ ተነሥቶ በሽማግሌ ከታረቁ በኋላ፤ ራስ መርዕድ ስለአገረሸበት ጫን ፈረሴን ብሎ ወልደ ገብርኤልን ለመዋጋት ወደ ጎንደር ሄደ፡፡ “መጣሁብህ” ቢለው ጊዜ ራስ ወልደገብርኤል
“…ኧረ ምነው ይሆን እርቁ የፈረሰ፣
የሚሞት ሰው አለ ቀኑ የደረሰ፡፡” ብሎ ለራስ መርዕድ ኃይሉ ልኮበታል፡፡
ራስ መርዕድ ኃይሉ የታላቁ ራስ ኃይሉ ዮሴዴቅ ልጅ ሲሆን በሕይወት የቆየው ለ26 ዓመት ብቻ ነው፡፡ የራስ ኃይሉ ዮሴዴቅ ልጆችም ራስ መርዕድን ጨምሮ ፋሲል፣ ድንቅነሽና ወለተ ጊዮርጊስ ናቸው፡፡ ራስ መርዕድ ሲሞት ልጁ ደጃዝማች ጓሉ የ10 ዓመት ልጅ ስለነበር የጎጃም፣ የዳሞትና የይባባ ግዛት በወ/ሮ ድንቅነሽ ኃይሉ ባለ ቤት በደጃች ዘውዴ እጅ ገባ። ደጃች ዘውዴ ሥልጣንን በእጁ ከአስገባ በኋላ፣ በሚያዚያ 1796 ዓ.ም ወደ አገው ዘምቶ ድልን ስለተቀዳጀ፤
“ከሩቅ አገር ምድር ከአካኮ ገሥግሶ፣
እንደ ፋሲል ፈጀው ከአፋፉ ላይ ደርሶ፡፡”  ተብሎ ተገጠመለት፡፡
ደጃች ዘውዴ ሲሞት ልጆቹ ደጃች ጎሹና ልጅ ብሩ ጎሹ ወደ አገዛዙ መድረክ መጡ፡፡ የራስ መርዕድ ልጅ ደጃች ጓሉ ምሥራቅ ጎጃምን በመግዛት ላይ ስለነበር፣ ጓሉና ጎሹ የሥልጣን ባላንጣዎች ሆኑ፡፡ በሌላ በኩልም ጎሹ ለጓሉ የአክስቱ የወ/ሮ ድንቅነሽ ልጅ ነው፡፡ ደጃች ጓሉ በጦርነት ላይ በነበረበት ጊዜ ጎሹ ለጥንቃቄ ሲባል ወደ አባቱ ዘመዶች አገር ወደ አማሮ /ወለጋ/ ተላከ፡፡ በተለይ የደጃች ጎሹ ዘውዴ ልጅ ብሩ ጎሹ ኃይልና ጉልበት ስለተሰማው፤ በአባቱ በጎሹ ዘውዴ ረዳትነት ወደ ወገራና ደንቢያ ዘልቆ፣ የደጃዝማትች ክንፉን ግዛት ስለተቆጣጠረ፣ በድርጊቱ የተበሳጩት ከጎንደር ወጥቶ ወደ ጎጃም እንዲሄድ አደረጉ፡፡ ብሩም ጎጃም ሲደርስ በሁለቱ ላይ ዐመፀ፡፡
በወቅቱ ራስ አሊና እቴጌ መነን የጎጃምና የዳሞት ዐመፀኞችን ብሩንና አባቱን ጎሹን ለማንበርከክ፣ ሥዩም በቃኸኝን ከብዙ ጦር ጋር ወደ ጎጃም ላኩት፤ ሹም ሽርም ተደርጎ በጎጃምና በዳሞት እነ መሸሻ ባቡ እና አደየ ባቡና እነ ሥዩም በቃኸኝ ተሾሙ። እነዚህ አዳዲስ ሹሞች በዳሞት አድርገው ደረቤ ሲገቡ፣ አባትና ልጅ ጎሹ ዘውዴና ብሩ ጎሹ፣ ስኩት ከተባለው ቦታ ላይ ጦርነት ከፍተው ደመሰሷቸው። በጊዜው ቤጌምድሬው ሥዩም በቃኸኝ፤ መልካም አድርጎ ስለተዋጋ በፈጸመው ጀብዱ የተደነቁት ጎጃሞች፡-
“ሥዩም በቃኸኝ የሞተበቱ፣
ሣር አልበቀለም ስኩት መሬቱ፡፡
ስኩት መሬቱ ሣሩ ለምለም ነው፤
የውሃ አይደለም የሥዩም ደም ነው፡፡
ሥዩም በቃኸኝ የወረደበት፤
አምስት መቶ ላም የተነዳበት፡፡” ብለው ዘፍነውለታል፡፡
ጓሉ መርዕድ ተድላ፤ ጓሉን የወለደ ሲሆን ተድላ ጓሉ በብሩ ጊዜ በአልጋ ባላንጣነት ምክንያት ብዙ እንግልትና ስደት ደርሶበታል፡፡ ጓሉ /ደጃች/ የኖረው ከ1845-1860 ሲሆን በዓፄ ቴዎድሮስ ዘመን ደጃች ብሩ ጎሹ እንደተያዘ፣ ከተደበቀበት ከደጀን ወጥቶ ለዓፄ ቴዎድሮስ ገባ፡፡ ቴዎድሮስም የደጃች ጓሉ ልጅ መሆኑን ተረድቶ፣ በጎጃም ላይ ሾመው፡፡ ይሁን እንጂ ተድላም ለቴዎድሮስ ለመታጠቅ ፈቃደኛ አልሆነም። በዚህን ጊዜ አንድ የጎጃም አዝማሪ ከተድላ ጓሉ ሠፈር ገብቶ፡-
“እናንት የጎጃም መኳንንት፣
ጭቃ አይነካችሁ በክረምት፡፡
በአገራችሁ በወንዛችሁ፣
ወየው ወየው በራችሁ፡፡
አልተከልሁ እንኳ ከጓሮየ፣
ዱባ ለመከራየ፡፡” ብሎ በመዝፈኑ ተድላ ተጠርጥሮ፣ ከቴዎድሮስ ሠፈር በሌሊት ጠፋ። ደጃዝማች ተድላ ጓሉ ጎጃምን ለአሥራ ሁለት ዓመታት ገዝቶ፣ በሕመም ምክንያት ኅዳር 6 ቀን 1860 ዓ.ም ዐርፎ የውሽ ቅዱስ ሚካኤል ከተባለ ቦታ ተቀበረ፡፡
በወቅቱ ዓፄ ቴዎድሮስ ሊመጣ ይችላል ተብሎ ስለተሰጋ፣ ደጃካች ተድላ የተቀበረው በቶሎ ነው። ዓፄ ቴዎድሮስም የተድላን ሞት ሰምቶ በእጅጉ አዘነ፡፡ ምክንያቱም ተድላ ከሞተ አንተም ተከትለህ ትሞታለህ ብሎ መነኩሴ ለቴዎድሮስ ነግሮት ስለነበር ነው፡፡
ደጃች ተድላ በሕይወት በነበረበት ጊዜ ድግስ እየደገሰ፣ ድሃውን ሁሉ በየሳምንቱ እሑድ ቤተክርስቲያን ውስጥ ያበላና ያጠጣም ስለነበር፡-
“አልሞተም ይሉናል ደጃዝማች ተድላን፣
አሁን እሑድ ሲቀር የምናውቀውን፡፡
የውሽ ወስደው ጣሉት ደጃዝማት ተድላን፣
ይነሣ ነበረ አብማ ቢሆን፡፡
አጭር ቀድደው ወጡ ነውረኛ መስለው፤
እረኛ ሳይሰጡት ለዚህ ሁሉ ሰው፡፡
ከእንግዲህስ ወዲህ የልቤን ልናገር፣
አባ መልአክ ተድላ ጠጁ ውሀ ነበር፡፡
በሸዋ ተላከ ጥናው ሊመጣ ነው፣
በትግሬ ተላከ ጥናው ሊመጣ ነው፣
በጎንደር ተላከ ጥናው ሊመጣ ነው፣
ተድላ ጓሎ ሞቶ ጎጃም ሊፈታ ነው፡፡
እሺ እሺ ነው እንጂ የእስራኤልን ሞት፣
እንዲያልቅሰው ተድላን ለምን ቀበሩት፡፡
የንጉሥ አሽከር ጠፍቶ ሲፈለግ ሌሊት፣
ቀን ከተድላ ጋራ ሲሄድ አየሁት፡፡”
“ለደጃች ተድላ የተገጠመውየለቅሶ ግጥም ብዙ ነው፡፡ መልካም ጌታ ከሞተ በኋላም ይለቀስለታል፤ ክፉ ጌታ ግን በቁመና ያስለቅሳል” ይላሉ አለቃ ተክለ ኢሲየሱስ ዋቅጅራ፡፡
ከተድላ ሞት በኋላ ልጁጅ ደስታ ተድላ ወደ ሥልጣን መጣ፤ ራስ ደስታ ልክ እንደ ብሩ ጎሹ የኃይለኛነት ጠባይ ነበረው፤ በዚህ የተነሣ በወዲህ ምኒልክን በወዲያ ተክለ ጊዮርጊስን ግራ አጋባ። በድንገት ዓባይን ተሻግሮ፣ ሸዋን ስለወረረ በሁኔታው ግራ የተጋባው ምኒልክ፤ “እዘን ሸዋ” ሲል አስለፈፈ። ተክለ ጊዮርጊስ በበኩሉ፤ የደስታን ጥጋብ በጋብቻ ለማቀዝቀዝ አስቦ፣ ልጁን እንዲያገባ ጋበዘው፡፡ ሆኖም በሀገራችን የጋብቻ ሕግ መሠረት፤ ሙሽራው ሄዶ ሙሽራዋን መውሰድ ሲገባ፣ ደስታ በተቃራኒው ሙሽራዋ እንድትላክለት ጠየቀ፡፡ በዚህ ጊዜ
“አባ ቀማው ደሴ ሁልጊዜ ትቢት፣
አልጋውን በጉልበት ሚስቱን በመልእክት” ተብሎ ተዘፈነለት፡፡
አለቃ ቀጸላ፤ የዲማ ጊዮርጊስን ቤተክርስቲያን ከሣሉት ጥበበኞች ውስጥ አንደኛው ነው፡፡ አለቃ ቀጸላ ዲማን ሲሥል “ዐረቄ፣ ጎድን ተዳቢት፣ ወተት አቅርቡልኝ፣ ከሴት ጣይቱ ዓይናሚትን ጥሩልኝ” እያለ ያስቸግር ነበር፡፡ ሲሥል የበረደው እንደ ሆነና ጣይቱ ትሙቀኝ ልሂድ” ይልና ውልቅ ይላል። ያን ጊዜ ጣይቱ ባለባል ነበረች፡፡ ባለቤቷም ግልቱ ይባል ነበር፡፡ ግልቱ አለቃ ቀጸላን በዘፈን እንዲህ ብሎ ሰደበው፡-
“ሳላይ ነው እንጂ በድንገት፣
ሳይን በወሰዳት፡፡” አለ
አለቃ ቀጸላ ይህንን ስድብ በሰማ ጊዜም፡-
“እስቲ አታድርገኝ የሰው ሞኝ፣
ብሥል ሰው እንጂ ነች፡፡” ብሎ መለሰለት፡፡
ራስ መርዕድ ለወታደሮቹ ብዙም ፍቅር አልነበረውም፤ በአንጻሩ ግን ባላገሩን ይወድድና ይንከባከብ ነበር፡፡ በተቃራኒው ልጁ ደጃች ጓሉ ወታደር ይወድድ ነበርና በየባላገሩ ቤት እንዲፋንን፣ ሚስቱንም እየቀማ እንዲወሰልት ስለአደረገውና እርጎ እየደፋ፣ በግና ዶሮ እያረደ፣ ሚስቱን እየቀማ ወታደሩ በሚቀናጣበት ጊዜ እንዲህ ብሎ ዘፈነ (ወታደሩ)
“እንዴት ነሽ እርጎ፣
የመርዕድ ማደጎ፡፡
እንዴት ነሽ ዶሮ፣
የመርዕድ ወይዘሮ፡፡”
ደጃች ዘውዴና ደጃዝማች ኤልያስ በተጣሉ ጊዜ፣ ዘውዴ የኦሮሞ ፈረስ ይዞ ገሥግሶ ገብቶ የደጃች ኤልያስን ጦር ፈጀው፤ ደጃች ኤልያስም ተማረከ፡፡ ዘውዴ ጉልበት ተሰምቶት ደጃች ጓሉን ለመውጋት ሲነሣ፣ ጓሉ የጎጃምን ጦር በብላታ ኩላሊት እግር አስገብቶና ደንበጫ ላይ ሌሊት ገብቶ ዘውዴን ወጋው፡፡ ባለቤቱን ወይዘሮ ድንቅነሽንም (አክስቱን) አስከድቶ በወሰደበት ጊዜ ጓሉ፤
“ቀርባችሁ ሙቁ የበረዳችሁ፤
ዘውዴ ነደደላችሁ፡፡
የማቅ ፈታየ የደሜ ልጅ፣
እደርስ እደርስ ሲል ገደለው እንጅ፡፡” ብሎ ደጃች ዘውዴን በመሰንቆ ሰደበው፡፡
ዘውዴ የባለቤቱን የወይዘሮ ድንቅነሽን ተይዛ መሄድ በሰማ ጊዜ ጎጃምን ሊወጋ ገሠገሠ፤ ያን ጊዜ ብላታ ኩላሊት ወ/ሮ ድንቅነሽን ይዞ ወደ ቤጌምድር ወደ ራስ ጉግሣ ከተማ ደብረ ታቦር ሸሸ፡፡ ብላታ ኩላሊትም ድንቅነሽን በውሽምነት ለምዶ ነበር ስለተባለ አዝማሪ
“ሥጋ ብሰድለት ጎድን ተዳቢት፣
አልበላም አለችኝ አለ ኩላሊት” ብሎ ተጫወተ።
ደጃች ዘውዴም ብላታ ኩላሊት፣ ባለቤቱን ወ/ሮ ድንቅነሽን ይዞ ወደ ጎንደር የወሰዳት መሆኑን በሰማ ጊዜ አዝማሪ አሰልፎ፤
“ጦር ግድግዳ ሆኖ በሾተል ቢማገር፣
ሳላየው አልቀርም የድንቂቱን አገር…
መኮንንስ ቢሆን ከቤቱ ባልወጣ፣”
ብሎ ግጥም ጀምሮ ሳይደፋው ሳይጨርሰው ወደራስ ጉግሣ ደብዳቤ ጽፎ ላከ፡፡
ጉግሣም ቃሉን ሰምቶ፣ ብላታ ኩላሊትንና ወ/ሮ ድንቅነሽን አስጠርቶ፣ ጌታህ የሰደደውን ደብዳቤ እይና ትርጓሜውን ንገረኝ አለው፡፡ ብላታ ኩላሊትም የባሏን ንግግር ራስዋ ትወቀው እንጂ እኔ ምን አውቃለሁ አለ፤ ወ/ሮ ድንቅነሽ ቃሉን ሰምታ ባሏ ዘውዴ የጀመረውን ግጥም ሞላቺው፤
“መኮንንስ ቢሆን ከቤቱም ባልወጣ፣
ንጉሥ የመሰለ ዘውዴ ጫነ መጣ” ብላ
ዘውዴ መምጣቱ ነውና ይታጠቁ ብላ ለራስ ጉግሣ ብትነግረው፣ በጌምድር ሽብር ሆነ። “ፊታውራሪ ገለታና ፊታውራሪ ባሪያ” የተባሉ ጀግኖች የደጃች ጎሹ ሹማምንት ነበሩ፡፡ ተይዘው በታሰሩበት ጊዜ አንዲት ገረድ፤
“ከተያዘ ገለታ፣
እስቲ ደመወዜን የኔታ፡፡
ከተያዘ ባሪያው፣
እስቲ አገሬን ልየው”
ብላ ዘፈነች የራስ አሊ እናት እቴጌ መነን፣ ልጅ ካሣን በኋላ ዓፄ ቴዎድሮስን ለማስያዝ ጦር በላከችበት ጊዜ ድል አደረገ፡፡ እርስዋም ወደ አለበት በመሄድ ጦርነት በገጠመችው ጊዜ ጭኗን በጦር ወጋና ያዛት። ራስ አሊ ያን ጊዜ ብሩን ለመያዝ ጎጃም ነበርና የእናቱን መያዝ በሰማ ጊዜ፣ የጎጃም ጦር በደጃች ብሩ ጎሹ እየታዘዘ፣ ወደ ጎንደር ሄዶ እንዲዋጋ ዝግጅት በሚያደርግበት ሰዓት የደጃች ጎሹ አዝማሪ እንዲህ ብሎ ዘፈነ፤
“አያችሁልኝ ወይ ይህን የእኛን ዕብድ፣
አምስት ጋሞች ይዞ ጉራምባ ሲወርድ፡፡
ያንዣብባል እንጂ መች ይዋጋል ካሣ፤
ወርደህ ጥመድበት ከሽምብራው ማሳ፡፡
ወዶ፣ ወዶ፣
በሴቶቹ በነጉንጭት ለምዶ፡፡”
በኋላ በደጃች ካሣዬ ጦርና በደጃች ጎሹ ጦር ጉራምባ ላይ በተደረገ ውጊያ ደጃች ጎሹ ኅዳር 10 ቀን ሞተ፡፡ የደጃች ካሣ ሎሌም በጦርነት ላይ ወድቆ ያገኘውን የጎሹን አሽከር አፍንጫውን በድንጊያ ደብድቦ ገደለው፡፡ የደጃች ጎሹም ሞት በተሰማ ጊዜ፣ አንዲት የጎጃም ሴት እንዲህ አለች፡-
“ጎሹ እንደ ኦርዮ፤ ዓሊ እንደ ዳዊት፣
የጥንት አይደለም ወይ ተልኮ መሞት፡፡”
ዓፄ ቴዎድሮስ ሰው ለሞተ ዘመዱ እንዳያለቅስ አዋጅ አስነግሮ ሲኖር፣ በድንገት የባለቤቱ የእቴጌ ጥሩወርቅ አባት ደጃች ውቤ ይሞታሉ፡፡ ለእኒህ ትልቅ ጀግና ለቅሶ እንዲለቀስላቸው ቴዎድሮስ በፈቀደበት ጊዜ ዕንባውን ቋጥሮ የኖረው ሁሉ እንደልቡ አለቀሰ። ያን ጊዜ የቤጌምድር አልቃሽ “ጌታው ደጃች ውቤ ሁልጊዜ ደግነት
ዛሬ እንኳን ለድሀው ዕንባ አተረፉለት፡፡” ብላ ሕዝቡን አስለቀሰች፡፡
ወሰን ቢሰውር የተባለ አንድ የሜጫ መኮንን ከቴዎድሮስ ጋር በሚዋጋበት ጊዜ ተከብቦ ጦሩ በምግብና በውሀ ጥም ሲሰቃይ፣ ወሰን ቢሰውር ወደ ዓፄ ቴዎድሮስ ቀርቦ
“ንጉሥ ሆይ፤ አምስት መቶ ብር ልስጥና ውሃ ይስጡን ቢላቸው እምቢ አሉት፡፡ ወሰንም እንደለፈለፈ፣ እንደተጠማ ሞተ፡፡ በዚህ ጊዜ ሚስቱ ስታለቅስ እንዲህ አለች፤
“ጌታው የጌታው ልጅ ወሰን ቢሰውር፣
ውሀ ልግዛ ይላል በአምስት መቶ ብር፡፡”
ዓፄ ቴዎድሮስ ጎጃ ዘምተው ሕዝቡን በዘረፉበት ጊዜ ጉዳት የደረሰባት አንዲት ሴት እንዲህ ብላ አለቀሰች፡፡
“ልብሴንም ገፈፈው፤ ለበሰው እርዘኛ፤
በሬየንም ነዳው አረደው ነፍጠኛ፤
እህሌን ዘረፈው በላው ቀለብተኛ፤
ንጉሥ የቀረዎ ጥቂት አማርኛ፣
ምነው ሆድ አይዘርፉ አርፌ እንድተኛ፡፡
አገሬን ዘረፈው እያለው ደስደስ፣
ሞኙ በጌምድሬ ፈንታው እስቲደርስ፡፡”
ንጉሥ ተክለ ሃይማኖት በሞተበት ሰዓት፣ ልጁ ራስ በዛብህ በዓፄ ምኒልክ ትእዛዝ አፍቀራ ታስሮ ነበርና የአባቱን ሞት እንደሰማ እንዲህ ብሎ አለቀሰ፡-
“ጎጃም ንጉሥ ሞቶ ሸዋ ተሸበረ፤
እግሬ ባይታሰር ለቅሶየ ነበረ፡፡
እንዲያ እንደፍቅራችን፣
እንዲያ እንደወትሮአችን፤
የሚሆን እንዲሆን፤
ንጉሥ በሬ ይግዙ እኔም ዐፈር ልሁን፡፡”
ንጉሥ ምኒልክ አንድ ወቅት ከሐረሪ ነጫጭ ርግቦችን በቀፎ፣ ዥንጉርጉር ውሾን በሰንሰለት ይዞ በመጣበት ጊዜ አንዲት ገምቦኛ እንዲህ ብላ ዘፈነች፡-
“የምኒልክ ነገር ይመስለኛል ተረት፣
አሞራው በቀፎ ውሻው በሰንሰለት፡፡”
ራስ ኃይሉ በዘመኑ የጎጃምን ሕዝብ (የኔ ቢጤ ደሀን ለማኙን ሳይቀር) “ግብር ክፈል” እያለ በአስጨነቀበት ወቅት ሕዝቡ እንዲህ ብሎ ስሜቱን ገለጠ፡፡
“ጎመኑን ቀርድጄ ጥሬውን በላሁት፣
እንዳላበስለውም የጭሱን ፈራሁት፡፡”
ራስ ኃይሉ ጭስ የሚጨስባትን እያንዳንዷን ጎጆ እያስቆጠሩ፣ ግብር ያስከፍሉ ስለነበር በጎጃም ሚስት ያገቡ ወጣቶች ጎጆ አይወጡም ነበር፤ ትልቁ ቤት እየተዘረጠጠ በታዛ ውስጥ ይኖሩ እንደነበር አባቶቻችን ይናገራሉ፤     
ዓፄ ዮሐንስ ወደ መተማ ሲሄድ ከብቷን የተዘረፈች፤ ልብስዋን የተገፈፈች የጎጃም ሴት እንዲህ ብላ አለቀሰች፡-
“ዘንድሮ ንጉሡ ደህና ቢመለሱ፣
ጎልድፏል ማለት ነው ጎጃሜ ምላሱ፡፡” የታሪክ ማጣፈጫ ጥሞች ለዛሬው በዚህ መልክ ተሰናብተዋል፡፡

Read 5092 times