Monday, 07 April 2014 15:48

ጌድዮንን አንፈልገውም እንዴ?

Written by 
Rate this item
(10 votes)

      የ17 ዓመቱ ፕሮፌሽናል እግር ኳስ ተጨዋች ጌድዮን ዘላለም በብሔራዊ ቡድን ደረጃ ለየትኛው አገር መጫወት እንደሚፈልግ ለመወሰን ቢያንስ እስከ 3 ዓመት ሊዘገይ እንደሚችል ዘገባዎች አመለከቱ፡፡ ጌድዮን ከወር በፊት በታላቁ የእንግሊዝ ክለብ አርሰናል እስከ ከ2017 ለመቆየት የኮንትራት ማራዘሚያ ውል የፈረመ ሲሆን ጀርመን፤ በወላጆቹ ዘር ግንድ ከኢትዮጵያ፤ በተወለደበት አገር ጀርመን እና ለስምንት ዓመታት በኖረበት አሜሪካ  በብሄራዊ ቡድን ደረጃ እንዲጫወት ይፈልጋል፡፡  በብሔራዊ ቡድናቸው እንዲጫወትላቸው በተለይ አሜሪካ እና ጀርመን በየአቅጣጫው ጥረት እያደረጉ መሆናቸውን ያወሱ ዘገባዎች፤ ከ2 ሳምንት በፊት ወጣቱ በጀርመን ሀ- 17 ቡድን እንዲሰለፍ የቀረበለትን ጥሪ ሳይቀበል ከቀረ በኋላ  ጉዳዩ ማነጋገር መጀመሩን ያወሳው የኢኤስፒኤን ነው፡፡ አንዳንድ የጀርመን ሚዲያዎች ጌድዮን በጀርመን ብሄራዊ ቡድን የሚጫወትበትን እድል ማበላሸቱ ለወደፊት የእግር ኳስ ህይወቱ መጥፎ ጠባሳ መሆኑን በማውሳት እንደ ባየር ሙኒክ አይነት ክለቦች ውስጥ ለመጫወት ያለውን ተስፋ እንደሚያደበዝዘው እየገለፁ ናቸው፡፡ በሌላ በኩል ጌድዮን በጀርመን ሀ -17 ቡድን  እንዲሰለፍ የቀረበለትን ጥሪ ወደ ጐን ገሸሽ ማድረጉን ተከትሎ በርካታ የአሜሪካ ስፖርት ሚዲያዎች እና የብሄራዊ ቡድን ደጋፊዎች አጋጣሚውን ለመጠቀም ተሯሩጠዋል፡፡ እንደ ኢኤስፒኤን  ዘገባ ጌድዮን ዘላለም፤ አሜሪካዊ ዜግነቱን በአፋጣኝ አግኝቶ ከወራት በኋላ ብራዚል በምታስተናግደው 20ኛው ዓለም ዋንጫ  በሚሳተፈው የአሜሪካ ብሔራዊ ቡድን  እንዲካተት ፊርማ በማሰባሰብ  እና ለፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ግልፅ ደብዳቤ በማስገባት  ዘመቻ ማድረግ ቀጥለዋል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ በኢትዮጵያ እግር ኳስ አፍቃሪዎች ከፍተኛ ድጋፍ እና ክትትል ባለው የእንግሊዙ ክለብ አርሰናል የሚጫወተው ጌድዮን ዘላለም ከዋልያዎቹ ጎን እንዲሰለፍ ከወራት በፊት ተፈጥሮ የነበረው ፍላጎት የተቀዛቀዘ መስሏል፡፡
ኢትዮጵያና የትዊተር ምልልሱ
ጌድዮን በአርሰናል ክለብ በታቀፈበት ወቅት የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ከ31 ዓመታት መራቅ በኋላ ደቡብ አፍሪካ ላይ በ29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ መሳተፍ ላይ ነበር፡፡ ከዚያም በኋላ ዋልያዎቹ በ20ኛው ዓለም ዋንጫ የምድብ ማጣርያ ስኬታማ ጉዞ  ነበራቸው፡፡ በዚሁ ጊዜ ጌድዮን ዘላለም ወደ እናት አባቱ አገር ኢትዮጵያ መጥቶ  ለብሄራዊ ቡድን እንዲጫወት  ከስፖርት አፍቃሪው ጋር ፍላጐት ያሳዩ ግለሰቦች ነበሩ፡፡ እነሱም የቀድሞው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አቶ ቴዎድሮስ አድሃኖም ነበሩ፡፡
አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው ስለወጣቱ የተናገሩት በጋዜጣዊ መግለጫዎች ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በመደገፍ የቅርብ ክትትል የሚያደርጉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ደግሞ የማህበረሰብ ድረገፆችን ተጠቅመዋል፡፡
ከወራት በፊት በዓለም ዋንጫ ጥሎ ማለፍ የመጀመርያ ጨዋታ ኢትዮጵያ ከናይጄርያ  አዲስ አበባ ላይ ሲጫወቱ  ጌድዮን ዘላለም በትዊተር ድረ-ገጹ ሁለት መልክቶችን በመፃፍ አስነብቦ እንደነበር ይታወሳል፡፡ በወቅቱ የመጀመርያው ጎል በኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ሲመዘገብ ደስታውን ለመግለፅ “ጎልልልልልልልልል......” ብሎ በመፃፍ አስነበበ፤ ጨዋታዉ በናይጄርያ 2ለ1 አሸናፊነት ከተጠናቀቀ በኋላ ደግሞ “ ...አሁንም ኮርቻለሁ ” የሚል አስተያየቱን በማስፈር ለዋልያዎቹ ብቃት አድናቆቱን ሲገልፅ አገሩን በቅርብ ርቀት እንደሚከታተል አረጋግጦ ነበር፡፡
ይህንን ተከትሎም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቴዎድሮስ አድሀኖም ጌድዮን ዘላለም ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን እንዲጫወት በትዊተር ድረገፃቸው መልዕክታቸውን በማስፈር ያደረጉት ማግባባት ትኩረት ስቦ ነበር፡፡ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ለጌድዮን ባደረሱት ፈጣን መልዕክት “ ሃይ ጌድዮን…. ያንተን ሃሳብ መስማቱ  ጥሩ ነው፡፡ በቶሎ ለኢትዮጵያ መጫወትህን ተስፋ አድረጋለሁ”  ብለዋል፡፡ ጌድዮን ዘላለም ለዚህ ምላሽ አልሰጠም፤ ከዚያን በኋላ ኢትዮጵያ ተጨዋቹን ወደ ብሄራዊ ቡድን ለመቀላቀል የነበራት ፍላጎት እንደተቀዛቀዘ ቀርቷል፡፡
ምላሽ የተነፈገው የጀርመን ጥሪ
የቀድሞው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አቶ ቴዎድሮስ አድሃኖም ለጌድዮን ዘላለም ወደ አገሩ መምጣት የነበራቸው ፍላጐት ለወር ያህል በይፋ ሲያነጋግር ሰንብቶ ለወጣቱ የጀርመን እግር ኳስ ፌደሬሽን ጥሪ ቀረበለት፤ በሀ-17  ቡድን በመካተት ከስፔን ጋር በሚደረገው የወዳጅነት ጨዋታ እንዲሳተፍ ነበር፡፡ በዜግነት ሁኔታው ላይ የሚፈጥረው ችግር ስላልነበር ጌድዮን ጥሪውን በመቀበል ተጫወተ፡፡
ከዚሀ የጨዋታ ልምድ ከ4 ወራት በኋላ ግን ሌላ ጥሪውን የጀርመን እግር ኳስ ፌደሬሽን አቀረበ፡፡ ከሁለት ሳምንት በፊት ማለት ነው፡፡ ጌድዮን ዘላለም በአውሮፓ ደረጃ በሚደረገው የሀ-17 አህጉራዊ የምድብ ማጣሪያ ጨዋታ በሚሳተፈው የጀርመን ሀ-17 ቡድን እንዲቀላቀል የቀረበ ጥያቄ ነበር፡፡ ይህን ጥሪ ግን ጌድዮን ሳይቀበለው ቀረ፡፡ በምን ምክንያት እንደሆነ በይፋ የታወቀ ነገር የለም፡፡ አንዳንድ መረጃዎች እንደገለፁት ግን ጌድዮን ዘላለም ጥሪውን በመቀበል በዚሁ አህጉራዊ ሻምፒዮና ላይ ለጀርመን ሀ-17 ቡድን  ተሰልፎ ቢጫወት ኖሮ በተለይ ለአሜሪካ ብሔራዊ ቡድን ዜግነቱን ቀይሮ በዓለም አቀፍ ውድድሮች መሳተፍ የሚችልበትን ሁኔታ ያበላሽ ነበር ብለዋል፡፡
የአሜሪካውያን የፊርማ ማሰባሰብ ዘመቻ
ጌድዮን ከ2 ሳምንት በፊት በጀርመን ሀ-17 ቡድን  የቀረበለትን ጥሪ ገሸሽ ማድረጉ ግን በአሜሪካ ያለውን ፍላጎት ቆስቁሶታል፡፡ የአሜሪካ ሚዲያዎችና ደጋፊዎች ለጌድዮን በአስቸኳይ ዜግነት ተሰጥቶት ለብሄራዊ ቡድን እንዲጫወት ሰፊ ዘመቻ ጀምረዋል። ጌድዮን ዘላለም ለ8 ዓመታት በአሜሪካ በመኖር በእግር ኳስ ልምምድና ጨዋታ በሶስት አማተር ክለቦች ልምድ ስለነበረው ፍላጎቱ እንዲጠናከር ምክንያት ሆኗል፡፡
ጌድዮን ዘላለም የአሜሪካ ዜግነት፤ የመኖርያ እና የስራ ፈቃዶች የሉትም፡፡ በአሜሪካ እግር ኳስ  ሰፊ ልምድ ነበረው፡፡ ግን መቼም ቢሆን በዚያ አገር ብሔራዊ ቡድን ተሰልፎ ለመጫወት እንደሚፈልግ የሚያመላክት አስተያየት የሰጠበት ሁኔታ አላጋጠመም፡፡  የእሱን ፍላጎት ባይሰሙም የአሜሪካ ሚዲያዎችና የብሄራዊ ቡድን ደጋፊዎች ዘመቻቸውን ፊርማ በማሰባሰብ እና ለፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ ይድረስ ብለው የፃፉት ግልፅ ደብዳቤ  እየጣሩ ናቸው፡፡ እነዚህ አካላት ጌድዮን ለአሜሪካ ብሄራዊ ቡድን እንዲሰለፍ ፅፈውታል የተባለው ደብዳቤ  ከዚህ በታች የቀረበው ነው፡፡
“አገራችንን በመምራት ያላችሁን ታላቅ ኃላፊነቱ እናከብራለን፡፡ በትህትና የምንጠይቀው ጌድዮን ዘላለም ለአሜሪካ ብሔራዊ ቡድን እንዲጫወት የሚቻለው ሁሉ እንዲደረግ ነው፡፡ የማይቻል ከሆነ የሌላ አገር ማልያ ይለብሳል - ምናልባትም የኮሚኒስቶችን”
የአሜሪካ  ሚዲያዎችና ብሄራዊ ቡድን ደጋፊዎች በዚህ ዘመቻቸው  ተስፋ የቆረጡ አይመስሉም፡፡ በጥቂት ሳምንታት ውስጥ የጌድዮን ዘላለም ጉዳይ እልባት አግኝቶ ወጣቱ  በብራዚል በሚደረገው 20ኛው ዓለም ዋንጫ ከብሄራዊ ቡድን ጋር እንዲሳተፍ ግፊት ማድረጋቸውን ቀጥለዋል። የወቅቱ የአሜሪካ ብሄራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ የሆነው ጀርመናዊው የርገን ክሊስማን ይህን ፍላጎት በማጤን በተጨዋቹ ላይ የቅርብ ክትትል ማድረግ መጀመሩን ሰሞኑን የገለፀው ደግሞ የኢኤስፒኤን ዘገባ ነው፡፡
በመጨረሻስ የማንን ማልያ ይለብሳል?
የ17 ዓመቱን ጌድዮን ዘላለምን ወደ ብሄራዊ ቡድናቸው ለመቀላቀል ጀርመንና አሜሪካ ከፍተኛ ፍላጎታቸውን በማሳየት ያለፈውን አንድ አመት በትኩረት ተከታትለውታል፡፡ በኢትዮጵያ በኩል የነበረው ፍላጎት ከአራት ወራት በፊት በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ቴዎድሮስ አድናሆም እና በቀድሞው የዋልያዎቹ አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው ከተንፀባረቀ ወዲህ ብዙም እንቅስቃሴ  እየተስተዋለ አይደለም። በተለያዩ ድረገፆች ስለ ጌድዮን ዘላለም በቀረቡ መረጃዎች ወጣቱ የኢትዮጵያ እና የጀርመን ዜግነት እንዳለው ይጠቀሳል፡፡ ስለ አሜሪካዊ ዜግነቱ የሚገለፅ መረጃ ግን የለም፡፡ በእርግጥ ጌድዮን የሚፈልግ ከሆነ በጀርመን ፓስፖርቱ ላይ ተጨማሪ የዜግነት እና የስራ ፈቃድ በመያዝ በአሜሪካ ብሄራዊ ቡድን የመጫወት እድል አለው፡፡ በአንፃሩ ግን በኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ለመጫወት ሁለት ዜግነት መያዝ አይፈቀድለትም፡፡ በኢትዮጵያ  ህግ መሰረት አንድ ሰው የሁለት አገራት ዜግነት እንዲኖረው አይፈቀድም፡፡
በአርሰናል ክለብ እስከ 2017 እኤአ የኮንትራቱን ማራዘሚያ ውል  ከወር በፊት የፈፀመው ጌድዮን ዘላለም አሁን ትኩረቱ በክለቡ መጫወት ብቻ እንጂ በብሄራዊ ቡድን ደረጃ የየትኛውን አገር ማልያ ለብሶ እንደሚጫወት መግለፅ እንደማይፈልግ ከአርሰናል ክለብ የቅርብ ምንጮች የተገኙ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ጌድዮን ዘላለም ዜግነቱን ሰጥቶ የሚጫወትበትን ብሄራዊ ቡድን ለመወሰን ቢያንስ 3 ቢበዛ 5 ዓመታት ሊዘገይ እንደሚችል ያወሱ መረጃዎች ወቅታዊ ፍላጎቱ በአርሰናል ክለብ ማደግ እና በአውሮፓ እግር ኳስ ከፍተኛ ልምድ ማካበት እንደሆነ ይገልፃሉ፡፡ ተጨዋቹ በብሄራዊ ቡድን ደረጃ ለመጫወት የሚያስብ ከሆነ በ2018 እኤአ ራሽያ ላይ እንዲሁም በ2022 እኤአ በኳታር የሚደረጉትን 21ኛው እና 22ኛው የዓለም ዋንጫዎች መጠበቅ ግድ እንደሚሆንም ያስገነዝባሉ፡፡

Read 5332 times