Monday, 07 April 2014 15:47

“በእጆቹ የሚሮጠው፤ ታምሩ ፀጋዬ እና አስገራሚ ሪከርዱ!

Written by 
Rate this item
(2 votes)
  • 100 ሜትር በ56 ሰከንድ በክራንቾቹ ሮጧል፡፡
  • ሪከርዱ ገና በጊነስ መዝገብ እውቅና በማግኘት አልሰፈረም፡፡
  • የዩሲያን ቦልት አድናቂ ነው፡፡ ሊያገኘውም ይፈልጋል፡፡
  • በጀርመን ለመኖር የጥገኝነት ጥያቄ አቅርቧል፡፡
  • ከዓመት በፊት ስለህይወት ውጣውረዱና ሪከርድ ስለማስመዝገብ  አላማው ከአዲስ አድማስ ጋር ባደረገው ቃለምልልስ ተናግሮ ነበር፡፡

   ከሳምንት በፊት “ፋርዝ” በተባለችና በሰሜን በቫርያ በምትገኝ የጀርመን ከተማ የ32 ዓመቱ ታምሩ ፀጋዬ በክራንቾቹ 100 ሜትርን በ56 ሴኮንዶች  በመሮጥ ባስመዘገበው ልዩ የዓለም ሪከርድ አነጋጋሪ ሆኗል፡፡ ታዋቂው የእንግሊዝ ታብሎይድ ጋዜጣ ዴይልሜል በፃፈው ዘገባ  አካል ጉዳተኛው  ታምሩ ፀጋዬ በክራንቾቹ ተጠቅሞ 100 ሜትሩን በመሮጥ ያሳየው አስደናቂ ስፖርታዊ ብቃት ለመላው የሰው ልጆች ከፍተኛ የሞራል መነቃቃት የሚፈጥር ልዩ ስኬት ነው ብሎ አድንቆታል፡፡
የታምሩ ፀጋዬ  ልዩና አስገራሚ ሪከርድ በጊኒስ የሪከርዶች መዝገብ ገና አለመስፈሩን የዘገበው ጨምሮ የዘገበው ዴይሊ ሜል፤ በአጭር ጊዜ እውቅና ማግኘቱ እንደማይቀር ገልፆ፤ ሪከርዱን ያስመዘገበበት ትእይንት በአገሪቱ ብሄራዊ የቴሌቭዥን ጣቢያ ሽፋን ማግኘቱን አውስቷል፡፡ አካል ጉዳተኛ ሆኖ ለመንቀሳቀስ በሚጠቀምባቸው ክራንቾች አስገራሚና ልዩ ክብረወሰኖችን በማስመዝገብ የተሳካለትን እንግሊዛዊውን  ጆን ሳንድ ፎርድ የጠቀሰው የዴይሊ ሜል ዘገባ ታምሩ ለእነዚህ ክብረወሰኖች ተቀናቃኝ መሆን እንደሚችልም ጠቁሟል፡፡ እንግሊዛዊው አካል ጉዳተኛበክራንቾቹ በመታገዝ ሁለት የዓለም ክብረወሰኖችን በማሳካት በጊነስ የሪኮርዶች መዝገብ ሰፍሯል፡፡  ጆን ሳንድ ፎርድ  በ2009 እ.ኤ.አ ላይ የኪሊማንጀሮ ተራራን በ4 ቀናት ከ20 ሰዓታት እና ከ30 ደቂቃዎች የወጣ ሲሆን፤ በ2011 እ.ኤ.አ ላይ ደግሞ በለንደን ማራቶን በመሳተፍ 42.195 ኪ.ሜ ርቀትን በ6 ሰዓት ከ24 ደቂቃዎች ከ48 ሰኮንዶች ጨርሶ በእነዚህ ሁለት ልዩ ክብረወሰኖች በጊነስ የሪከርዶች መዝገብ ለመስፈር በቅቷል፡፡  ታምሩ ፀጋዬ በጀርመኗ ፋርዝ ከተማ ካስመዘገበው ልዩ የዓለም ሪከርድ በኋላ  “አንድ በአንድ ህልሞቼን እያሳካሁ ነኝ፡፡ በህይወቴ ብዙ ውጣውረዶችን አሳልፌያለሁ፤ አካል ጉዳተኛ ብሆንም ብዙ ነገር ማድረግ እችላለሁ። በስፖርታዊ ብቃቴ እና አስደናቂ ተሰጥኦዎቼ ሌሎችን ሪኮርዶችን በማስመዝገብ መላው ዓለምን ማስደነቅ እፈልጋለሁ” ብሏል፡፡  ለዓለማችን ፈጣን የአጭር ርቀት ሯጭ ዮሴያን ቦልተ ከፍተኛ አድናቆት እንዳለው መናገሩን የጠቀሰው የዴይል ሜል ዘገባ “ዮሲያን ቦልትን እንደተምሳሌት የምመለከተው ጀግና ነው፡፡ እኔም ምርጥ ስፖርተኛ ነኝ፡፡ እሱ በፈጣን እግሮቹ እንደተሳካለት በጠንካራ እጆቼ በክራንቾቼ በመሮጥ ሪከርድ አስመዝግቢያለሁ፡፡ የሰራሁትን ታሪክ ቢያይልኝና ባገኘውገኘውም ደስ ይለኛል” ብሎ መናገሩንም አውስቷል፡፡
በሌላ በኩል ታምሩ ፀጋዬ ባለፉት ጥቂት ወራት በመላው አውሮፓ ከሚታወቀው እና “ሲርኪዊ ዲ ሶሊል” ከተባለ የሰርከስ ቡድን ጋር  እየሰራ እንደሚገኝ ያመለከተው አንድ የጀርመን ሚዲያ፤ በተለያዩ የጀርመን ከተሞች በመዘዋወር ትርኢቶችን ማቅረቡን  እንደሚቀጥል ቢገልፅም ወደ አገሩ ለመመለስ ፍላጐት እንደሌለውና በጀርመን አገር ለመኖር የጥገኝነት ማመልከቻ ማስገባቱን ጎን ለጎን ዘግቧል፡፡
በአዲስ አድማስ ያደረገው ቃለምልልስ
ታምሩ ፀጋዬ ለአስራ አምስት ዓመት እግሮቹ መራመድ ስለማይችሉ እጁን እንደ እግር በመጠቀም እየተሳበ ነበር የሚጓዘው፡፡ እናትና አባቱ አግልለውታል፡፡ ከቤተሰብ፣ ከማህበረሰብና ከጓደኞች ብዙ ተፅዕኖ፣ ብዙ ንቀትና ጥላቻ ደርሶበታል፡፡ ማደርያ አጥቶ ጐዳና አድሯል፤ ሊስትሮነትም ሰርቷል፡፡ ግን ሁሌም ትልቅ ታሪክ የመስራት ሪከርድ የማስመዝገብ ህልም እንደነበረው ከዓመት በፊት የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ከሆነችው አበባየሁ ገበያው ጋር ባደረገው ቃለምምልስ ተናግሮ ነበር፡፡  ታምሩ በክራንች በመታገዝ መንቀሳቀስ የቻለበትን ከፍተኛ የቀዶ ጥገና ህክምና ያገኘው በአጋጣሚ ነው፡፡ “ተዓምር” ከሚመስል ህክምናው በኋላ በእግሩ መሄድ ጀመረና በ16 ዓመቱ አንደኛ ክፍል ገባ፡፡ እስከ ኮሌጅ ዘለቀ፡፡ ከዛም ወደ ስፖርት ገባ፡፡ ሪከርድ ለማስመዝገብ አለመ፡፡ ይህንንም ፊልም የሚመስለው አስገራሚ የህይወት ታሪኩን በወቅቱ ከጋዜጣው ጋር ባደረገው ቃለምልልስ በስፋት ሲያወጋ ሁሉንም የህይወት ተሞክሮውን በማጠቃለል ሲናገር ወደቅሁ፤ ተጋጋጥኩ፤ ግን ተሳካልኝ  ብሎ ነበር፡፡ ታምሩ ፀጋዬ ከሳምንት በፊት ካስመዘገበው ልዩ የዓለም ሪከርድ በኋላ ከዓመት በፊት ከአዲስ አድማስ ጋር ካደረገው ቃለምልልስ አንዳንድ ምላሾቹን ለትውስታ እንዲህ ይቀርባሉ፡፡
‹‹ስወለድ አፈጣጠሬ የሚያስደንቅ ስለነበረ ፈቃዱ ዘገዬ አሉኝ፡፡ “እሱ እንደፈቀደ፣ እንደፈጠረው የሚያደርገውን ያድርገው” ለማለት ይመስለኛል፡፡ ታምሩ የሚለው ግን የቆሎ ት/ቤት እያለሁ የወጣልኝ ስም ነው፡፡ ይሄም ተመሳሳይ ትርጉም አለው፡፡ ሁለቱም እግሮቼ ስወለድ ወደ ኋላ ተቆልምመው ነው የተወለድኩት፡፡ አካል ጉዳተኛ ሆኜ ማለት ነው፤… የተወለድኩት ከላሊበላ 60 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ባለች የገጠር ሰፈር (ምዢ ማርያም በምትባል ቦታ) ነው፡፡ እናቴ፤ አያቴ ቤት  በቤት ሠራተኝነት ታገለግል ነበር፡፡ እኔ የተረገዝኩት አባቴ ከእናቴ ጋር በነበረው የምስጢር ግንኙነት ነው፡፡ አባቴ ሊዳር ሁለት ወር ሲቀረው እኔ ተወለድኩ፡፡›› በማለት ለአዲስ አድማስ ጋዜጣ የልጅነት ታሪኩን አጫውቷል፡፡
ስትወለድ በቤት ውስጥ የነበረው ስሜት እንዴት ነበር፤ ካደግህ በኋላ ስትሰማ ምን ስሜት ተፈጠረብህ በሚል ጥያቄ ቀርቦለት ነበር፡፡ ታምሩ ፀጋዬ ምላሹን ሲሰጥ‹‹ ለእናቴም ለእኔም መጥፎ እንደነበር ዛሬ ዛሬ እሰማለሁ፡፡ አካል ጉዳተኛ ሆኜ በመወለዴ የአባቴ ቤተሰቦች ‹‹ይሄ ልጅ ከእኛ ዘር አይደለም፤ ዘር አሰዳቢ ነው›› ይሉ ነበር፡፡ እናቴ መረራትና ጥላኝ ጠፋች፡፡  ለ3 ወር ብቻ ጡት አጥብታኝና ከተማ ገባች፡፡ ሴት አያቴ ደረቅ ጡቷን ታጠባኝ ነበር፡፡ እናቴ  ካደግሁ በኋላ አልፎ አልፎ ቤተሰብ ለመጠየቅ ትመጣ ነበር፡፡ እኔን ያሳደገኝ አያቴ ነው፡፡ እስከ አምስት አመቴ ድረስ ከቤት መውጣት አልችልም ነበር፡፡ አፈና ተደርጐብኝ ሳይሆን በቃ መራመድ አልችልም፡፡ እንደ እባብ ነበር የምሳበው፤ በእጄ እየተራመድኩ፣ እጄን እንደ እግር እየተጠቀምኩ ማለት ነው፡፡ ሰው ስለሚያገለኝ ብቻዬን አወራለሁ፤ ብቻዬን እጫወታለሁ፡፡ አያቴ ቄስ ትምህርት ቤት እንድማር ይፈልግ ነበር…ያኔ በየደብሩ ቄስ ትምህርት ቤት አለ፡፡ እኔ ግን ፍላጐቴ ጨዋታ ብቻ ነው፡፡ በእጄ እየተሳብኩ …በሩጫም እንኳን የሚቀድመኝ አልነበረም፡፡ አያቴ የትምህርት ፍላጐት እንደሌለኝ ሲረዳ ከብት ጠባቂ አደረገኝ፡፡›› በማለት ያሳለፈውን የህይወት ውጣውረድ ገልፆታል፡፡
እንዴት የስፖርት እንቅስቃሴዎችን ማድረግ እንደጀመረ ሲናገር ደግሞ ‹‹ብቻዬን፡፡ አንድ ጓደኛዬ ነበር፤ ያየኛል፤ አብሮኝም ይሰራል፡፡ የማልሞክረው ነገር የለም፡፡ ኦፕራሲዮን አድርጌ በክራንች ነበር የምሄደው፡፡ ስለዚህ ለምን ተዘቅዝቄ በክራንች በእጄ አልሄድም ብዬ ተነሳሁ፡፡ በኢንተርኔት ላይ እንደዚህ ዓይነት ሪከርድ ያስመዘገበ የለም፡፡ በዚህ መንገድ ለምን ራሴን አላወጣም ብዬ ጀመርኩ። ወደቅሁ፣ ተነሳሁ፣ ተጋጋጥኩ፡፡ አሁን ከመቶ ሜትር በላይ እሄዳለሁ፡፡ የሚፈለገው በአንድ ደቂቃ ውስጥ ምን ያህል ሜትር ይኬዳል የሚለው ነገር ነው።›› ብሎም ነበር፡፡  በዓለም ላይ እንደዚህ ዓይነት ጅምናስቲክ የሚሰራ እንዳለም ተጠይቆ ነበር፡፡ ‹‹የለም፡፡ ተዘቅዝቆ በክራንች ላይ በእጅ በመሄድ እኔ ብቻ ነኝ፡፡ ቆየሁና ለምን በክራንች ላይ ሆኜ ደረጃ አልወርድም አልኩና ልምምድ ጀመርኩ፡፡ በተደጋጋሚ ወደቅሁ፤ ተጋጋጥኩ ግን አደረግሁት።›› የሚል ምላሽ ሰጥቶ የነበረው ታምሩ ፀጋዬ በዚያው ቃለምልልስ ለማስመዝገብ ስላሰበው ሪኮርዱ ስኬታማነት ማብራርያ እንዲሰጥ ተደርጎም ነበር፡፡ ‹‹በአንድ ደቂቃ ከ76 ሜትር በላይ ተዘቅዝቆ በክራንች ላይ በእጅ በመሄድ ሶስት ድርጅቶች እውቅና ሰጥተውኛል፡፡ “ወርልድ ሪኮርድ አካዳሚ”፣ “ወርልድ ሪኮርድ ሴንተር”፣ እና “ወርልድ ኦቶራይዝ›› ናቸው፡፡ የእነዚህ ሪከርዶች ባለቤት ነኝ፡፡ ሁለቱ ሪከርዶች ያገኘሁት በክራንች በመሄድ ነው፡፡ የራሴን ስም አስጠርቼ አገሬን ማስጠራት ነበር የምፈልገው፡፡ ይሄው ተሳካልኝ፡፡ ጊነስ ወርልድ ሪከርድ በዚህ ወር እውቅና ይሰጠኛል፡፡›› ብሎ ነበር፡፡  

Read 1736 times