Monday, 07 April 2014 15:21

የሃይማኖት አክራሪነትና ሽብር፤ የጎሰኝነትና የብሄረተኝነት አባዜ

Written by  ዮሐንስ ሰ.
Rate this item
(7 votes)

ለመፍትሄ ያስቸገሩ ሦስት ቀውሶችና በእንጥልጥል የቀሩ ሦስት ምኞቶች
         ሰሞኑን ሲሰራጩ ከነበሩት ዜናዎች መካከል ኬንያንና ሶማሊያን፣ ሱዳንና ኢትዮጵያን የሚመለከቱ አራት የዜና ርዕሶችን ልጥቀስላችሁ። ሰላም ርቋት ከ20 አመታት በላይ በእግሯ መቆም የተሳናት ሶማሊያ ውስጥ፣ ከተለያዩ የአፍሪካ አገራት የተውጣጡ ከ20ሺ በላይ “ሰላም አስከባሪ” ወታደሮች ምን እየሰሩ ነው? ሰላም እያስከበሩ አይደሉም። ሰላም የለማ። ይልቅስ፣ በሃይማኖት አክራሪነቱ ከሚታወቀው አልሸባብ ጋር እየተዋጉ ነው። በርካታ የገጠር ከተሞችን ከአልሸባብ እያስለቀቁ መሆናቸውም ከሰሞኑ ተነግሯል።
በሌላ በኩል በዚሁ ሳምንት ሰኞ እለት፣ ኬንያ ናይሮቢ ውስጥ አሸባሪዎች በፈፀሙት ሁለት የፍንዳታ ጥቃት፣ ስድስት ሰዎች ሞተው ከሃያ በላይ ቆስለዋል። ጥቃቱ የአልሸባብ ሴራ መሆኑን የተናገሩት የኬንያ ባለስልጣናት፣ የሃይማኖት አክራሪነትን የሚያስፋፉ የአልሸባብ ደጋፊዎችን እያደኑ ለመያዝ ዘመቻ መጀመራቸውን ገልፀዋል። ቤት ለቤትና በየጎዳናው አሰሳ እንዲያካሂዱ የታዘዙ ፖሊሶች በአንድ ቀን ውስጥ ከ650 የሚበልጡ ሰዎችን ይዘው አስረዋል። በእርግጥ የአክራሪነትና የሽብር ወሬ የምንሰማው ከኬንያና ከሶማሊያ ብቻ አይደለም። እዚሁ አዲስ አበባ በሽብር የተከሰሱ ሰዎች የፍርድ ሂደት ሲዘገብ ሰንብቶ የለ?
እስከ ፍንዳታና ግድያ ድረስ ባይሄድም፤ አሜሪካ ውስጥ የክርስትና አክራሪዎች እንደ “ኤቮሊሽን” የመሳሰሉ የሳይንስ ትምህርቶችን ለመበረዝ የሚያካሂዱት ዘመቻ ቀላል አይደለም። ግን የባሰ ሞልቷል። ዘመናዊውን ትምህርት በመቃወም “ቦኮ ሃራም” በሚል ስያሜ በናይጄሪያ የግድያ ዘመቻ ሲያካሂድ የከረመውን ድርጅት ማየት ትችላላችሁ። በአንደኛው ሳምንት፣ አዳሪ ትምህርት ቤት ውስጥ ገብቶ 60 ታዳጊ ተማሪዎችን ይፈጃል፤ በሌላ ሳምንት የመኖሪያ ሰፈሮችን በመውረር መንደርተኛውን ይረሽናል። መረጋጋት ያቃታቸው ሊቢያና ቱኒዚያን የመሳሰሉ አገራት ውስጥም፤ አንዱ የሰላም ችግር የሃይማኖት አክራሪነትና ሽብር ነው። የከተማ ሰፈሮችንና የገጠር መንደሮችን ሸንሽነው የተከፋፈሉ አብዛኞቹ የሊቢያ ታጣቂ ቡድኖች፣ አንድም በጎሳ የተቧደኑ አልያም በሃይማኖት አክራሪነት የተደራጁ ናቸው።  የግብፁ ቀውስማ፣ የእለት ተእለት ዜና ነው። ከሰሞኑ በአሸባሪዎች በተፈፀሙት የፍንዳታ ጥቃቶች ከሞቱት ግብፃውያን መካከል አንዱ፣ የጦር ጄነራል ናቸው። የማሊ ጉዳይም ስንዝር አልተሻሻለም። በአንድ ወገን በጎሳ የተቧደኑ ታጣቂዎች፣ በሌላ በኩል ደግሞ አልቃይዳን በአርአያነት የሚከተሉ አክራሪ አሸባሪዎች አሰፍስፈውባታል። ያ አልበቃ ብሎ፤ የሴንትራል አፍሪካ ግጭትና እልቂት ተጨምሮበታል። በሃይማኖት ተቧድነው ለመጨፋጨፍ የተፋጠጡ አክራሪዎች አገሪቱን ደም ለማልበስ የቆረጡ ይመስላሉ።
ለነገሩ፤ በአፍሪካ ብቻ ሳይሆን በሌላውም አለም፤ የሃይማኖት አክራሪነትና ሽብር ያልነካካው አገር ፈልጎ ማግኘት ይከብዳል። የሶሪያና የኢራቅ፣ የፓኪስታንና የአፍጋኒስታንን ብቻ ማለቴ አይደለም። በሃይማኖት አክራሪነት ላይ የተመሰረተው የሳውዲ አረቢያና የኢራን አምባገነንነት ብቻም አይደለም። የሃይማኖት አክራሪነት ከእነዚህም አልፎ፣ ቱርክንና ኢንዶኔዢያን ጭምር ማበላሸት ጀምሯል። ምዕራብ አውሮፓም አልዳነም። ሌላው ቀርቶ፤ የሁስኒ ሙባረክን አምባገነንነት ሸሽተው በእንግሊዝ የተጠለሉ የሙስሊም ብራዘርሁድ አባላት፤ ያስጠለለቻቸውን አገር በአክራሪነት ለማሸበር ከማሴር አልተመለሱም። ለዚህም ነው፤ የእንግሊዙ ጠቅላይ ሚኒስትር ዴቪድ ካሜሩን፤ የሙስሊም ብራዘርሁድ አባላት ጉዳይ እንደገና እንዲመረመር በቅርቡ ትዕዛዝ ያስተላለፉት። በግልፅ አውጥተን ባንናገረውም፤ በአገራችንም የሃይማኖት ነገር ውስጥ ውስጡን እየተንተከተከ መሆኑን በስሜት ደረጃ ሳናውቀው የምንቀር አይመስለኝም። በአጭሩ፤ ለመፍትሄ ካስቸገሩት የዘመናችን ሦስት ቀውሶች መካከል አንዱ፤ የሃይማኖት አክራሪነት ነው።
በሶማሊያና በኬንያ ዜናዎች የጀመርነውን ርእስ እዚህ ላይ በመግታት ነው ወደ ሱዳን ዜና የምናልፈው። በመጀመሪያም የደቡብ ሱዳንን እንይ። በስልጣን የሚሻኮቱ የደቡብ ሱዳን ገዢ ፓርቲ መሪዎች ባለፈው ታህሳስ ወር፣ የፈጠሩት ግጭት፤ ውሎ ሳያድር በጎሳ ወደ መቧደን እንዳመራ ታስታውሱ ይሆናል። ለጊዜው በአካባቢው አገራት፣ በአሜሪካና በአውሮፓ እንዲሁም በአፍሪካ አንድነትና በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ተደራራቢ ጫና የተነሳ ግጭቱ ቢረግብም፤ በዚያው አልከሰመም። ድርድሩ እየተጓተተ፤ ግጭቱ ቀጥሏል።
በግጭቱ እስካሁን 10ሺ ሰዎች መሞታቸውን በመጥቀስ የተባበሩት መንግስታት ማክሰኞ እለት ባወጣው መግለጫ፤ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሰዎች ከመኖሪያቸው ተፈናቅለው ሩብ ሚሊዮን ያህሉ አገራቸውን ጥለው ለመሰደድ እንደተገደዱ አስታውቋል። ብዙዎቹ የተሰደዱት ወደ ኢትዮጵያ ነው። ሌሎች አራት ሚሊዮን ሰዎች ደግሞ፤ ኑሯቸው በግጭት ሳቢያ ተናግቶ ለረሃብ እንደተጋለጡ ዩኤን ገልጿል። እንግዲህ አስቡት። ከጎሳና ከብሄር ተወላጅነት በተጨማሪ ሃይማኖታዊ ገፅታ የነበረው የበርካታ አመታት ጦርነት የተቋጨው ደቡብ ሱዳን ከሰሜን ሱዳን ስትገነጠል ነው። ግን፤ ሰላም አልተገኘም፤ ሃይማኖታዊ ገፅታው ቢደበዝዝም፤ በጎሳ ወይም በብሄር የመቧደን ግጭት አገሪቱን ያመሳቅላት ይዟል።
ምን ያደርጋል? የደቡብ ሱዳን ብቻ አይደለም ችግሩ። ከሃይማኖት አክራሪነት ጋር አያይዤ የጠቃቀስኳቸው ግጭቶች፤ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ፤ በጎሳ ወይም በብሄር የተቧደኑ ግጭቶችንም አዳብለው የያዙ ናቸው። አንድ ቋንቋ የሚነገርባት ሶማሊያ እንኳ፤ ከዚህ ችግር አላመለጠችም። የሃይማኖት አክራሪዎች በሚፈፅሙት ሽብር ብቻ ሳይሆን፣ በጎሳ የተቧደኑ ሰዎች በሚፈጥሩት ግጭትም ነው ሶማሊያ ለ20 አመታት የተበጠበጠችው። ኬንያም እንዲሁ፤ ከጎሰኝነትና ከብሄረተኝነት ጣጣ የራቀች አይደለችም። ፕሬዚዳንቱ ኡሁሩ ኬንያታ፣ ከአገራቸው ውጭ ብዙም ዝር ለማለት ያልቻሉት ወደው አይደለም። ከ7 አመት በፊት ከምርጫ ግርግር ጋር ተያይዞ በተከሰተው ግጭት ላይ፤ ሰዎችን በጎሳ አቧድነው ግድያና ጥቃት እንዲፈፀም አድርገዋል በሚል ክስ፣ ዘሄግ የሚገኘው አለማቀፍ የወንጀል ፍርድ ቤት የመያዣ ትዕዛዝ ቆርጦባቸዋል።
እንዲያው የጎረቤቶቻችንን ጠቀስኩ እንጂ፤ ከብሩንዲ እስከ ናይጄሪያ፣ ከደቡብ አፍሪካ እስከ ኮንጎ፣ ከኢትዮጵያ እስከ ማዳጋስካር፤ የመጠን ልዩነት ይኖራል እንጂ በጎሰኝነት አደጋ ያልተከበበ የአፍሪካ አገር ከወዴት ይገኛል? ግን የአፍሪካ ብቻ ችግር አይደለም። መጤ እና ተወላጅ የሚል መቧደኛ ሰበብ በያዙ ሰዎች አማካኝነት የሚበጠበጡ የደቡብ አሜሪካ አገራት በርካታ ናቸው።
ከጦርነትና ከቀውስ የማይላቀቀው የመካከለኛው ምስራቅንማ ብንተወው ይሻላል። ኢራን እና ሳውዲ አረቢያ፤ ከማንም በላይ እርስ በርስ እንደ ደመኛ ጠላት የሚተያዩት፤ “የሱኒ ሙስሊም” እና “የሺአ ሙስሊም” በሚለው የሃይማኖት አክራሪነት ምክንያት ብቻ አይደለም። “አረብ” እና “ፐርሺያ” በሚል የተወላጅነት ሰበብም ጭምር ነው። እንደ አንድ አገር የቆመች የምትመስለው ኢራቅ፤ በአንድ በኩል “የሱኒ ሙስሊም” እና “የሺአ ሙስሊም” በሚሉ እውቅና ያልተሰጣቸው ድንበሮች ለሁለት እየተሰነጠቀች ነው። በሌላ በኩል ደግሞ፤ “የኩርድ ተወላጆች ግዛት” የሚል ስሜት፣ ያለ አዋጅ ለብቻ የተነጠለ ሶስተኛ ክፍል አለ። ሶሪያም በተመሳሳይ ሁኔታ፤ ለሶስት እየተከፈለች ነው።
ብቻ ምን አለፋችሁ? ዩጎዝላቪያ፣ በሃይማኖትና በጎሰኝነት ብትንትኗ እንደወጣው ሁሉ፤ በርካታ የአለማችን አገራትም በተመሳሳይ ችግሮች ሳቢያ እየተቃወሱ ናቸው። የዩክሬንም ተመሳሳይ ነው። “የራሺያ ተወላጅ”ና “የዩክሬን ተወላጅ” ከሚለው መቧደኛ በተጨማሪ፤ “የኦርቶዶክስ ተከታይ”ና “ወደ ካቶሊክ ያዘነበለ” በሚል የጥላቻ ሰበብ ጭምር ነው፤ ያ ሁሉ የዩራሬይን ችግር እየተፈጠረ የሚገኘው። ቻይና ውስጥ የቲቤት፣ የኡድገር፣ የሃን ተወላጆች በሚል ግጭቶች እየተፈጠሩ ነው። በህንድ ደግሞ፤ ሃይማኖታዊና ብሄረተኛ ግጭቶችን ያነሳሳል ተብሎ ሲወገዝ የነበረ ፓርቲ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየገነነ ዘንድሮ በምርጫ የበላይነት ይይዛል ተብሎ ይጠበቃል።
የጐሰኝነት ወይም የብሄረተኝነት ቀውስ ማለቂያ ያለው አይመስልም። በስልጣኔ ደህና ተራምደዋል የሚባሉ የምዕራብ አውሮፓ አገራትም፤ ከዘመኑ የጎሰኝነት ችግር ማምለጥ የቻሉ አይመስሉም። ስኮትላንድን ከብሪታኒያ ለመገንጠል፣ በሚቀጥለው መስከረም ወር የውሳኔ ሕዝብ ምርጫ ይካሄዳል ተብሏል። በስፔን ደግሞ ካታሎኒያን ለመነጠል  ተመሳሳይ ምርጫ በህዳር ወር ለማካሄድ ታቅዷል። ስኮትላንድ ከብሪታኒያ የምትገነጠልበት፣ ካታሎኒያ ከስፔን የምትነጠልበት አንዳች አሳማኝ ምክንያት ሊኖር ይችላል ብላችሁ ትገምቱ ይሆናል። ግን በብሄር ወይም በጎሳ ከመቧደን የዘለለ ብዙም ምክንያት አይታይም።
ቢሆንም፣ የእንግሊዝ መንግስት በስኮትላንድ የታቀደው ምርጫ እንዲካሄድ ተስማምቷል። የስፔን መንግስት ግን፣ በካቶሎኒያ የታሰበው ምርጫ ህገወጥ እንደሆነ በመግለፅ ምርጫውን እንደሚያግድ አሳውቋል። መገንጠልን የሚደግፉ ፖለቲከኞች ግን፤ ከአላማቸው ፍንክች እንደማይሉና እቅዳቸው እንደማይለወጥ ተናግረዋል። ለበርካታ አመታት የያዙትን አቋም፤ “አሁኑኑ ተግባራዊ ካላደረግን ሞተን እንገኛለን” ማለታቸው ለምን ይሆን? ምላሽ አላቸው። “አንደኛ፤ ስኮትላንድ በአርአያነት እንድንነሳሳ አድርጋለች፡፡ ሁለተኛ ደግሞ ዛሬ እንደ ድሮ አንፈራም። ስፔን የአውሮፓ ህብረት አባል ከሆነች ወዲህ፣ ዲሞክራሲ ተጠናክሮ ነፃነትና መብት የሚከበርባት አገር ሆናለች።  እንታሰር ይሆናል፤ እንገደል ይሆናል የሚል ስጋት ስለሌለን፤ የመገንጠል አቋማችንን ለማሳካት ምርጫውን እናካሂዳለን” ብለዋል- ካታሎኒያን ለማስገንጠል ዘመቻ የሚያካሂዱ ፖለቲከኞች። በአንድ በኩል፣ የፖለቲከኞቹ አባባል ቀጥተኛ ምላሽ ይመስላል። በሌላ በኩል ግን የሚያስገርም ነገር አለው።
አገሪቱ የእያንዳንዱ ሰው መብትና ነፃነት የሚከበርባት ከሆነች፤ መገንጠል ለምን አስፈለገ? የአስተሳሰብ ጉዳይ ነው። ከ17ኛው ክፍለዘመን ጀምሮ፤ ስልጡን የፖለቲካ አስተሳሰብ እየተስፋፋ በነበረበት በ18ኛውና በ19ኛው ክፍለ ዘመን ላይ፤ ማንኛውም የፖለቲካ ውሳኔም ሆነ አቋም፤ ከሁሉም በፊት የእያንዳንዱን ሰው መብትና ነፃነት ለማስከበር ያለመ መሆን አለበት የሚል መርህ ይከበር ነበር። አሜሪካ ከእንግሊዝ እንድትገነጠል ዘመቻ ያካሄዱ እንደ ጀፈርሰንና ማደሶን የመሳሰሉ መስራች ፖለቲከኞችም በዚህ ይስማሙ ነበር። ይህንን መርህ ነው የነፃነት መግለጫ በሚል ስያሜ ባዘጋጁት ሰነድ ውስጥ በጉልህ ያሰፈሩት።
የመገንጠልም ሆነ የመዋሃድ ውሳኔ፤ ለአመፅ የመነሳትም ሆነ የመስማማት ውሳኔ ምክንያታዊ ተቀባይነት የሚኖረው መቼ ነው? የእያንዳንዱ ሰው መብትና ነፃነት እንዲከበር አወንታዊና ጉልህ ውጤት የሚያበረክት ከሆነ ብቻ ነው። በአንዳች ውሳኔ የሚገኘው ውጤት ወይም ለውጥ፣ አወንታዊ መሆኑ ብቻ በቂ አይደለም። ጉልህ ለውጥ ወይም ጉልህ ውጤት የሚያስገኝ መሆን አለበት። ለጥቃቅን ለውጥ ተብሎ፣ ነባሩን ስርዓት ማናጋት ተገቢ እንዳልሆነ የአሜሪካ የነፃነት መግለጫ በአፅንኦት ያሳስባል።
ዛሬ ግን፣ ያ ስልጡን የፖለቲካ አስተሳሰብ ብዙም ትኩረት ሲሰጠው አይታይም። ጭራሽ፤ የመገንጠል አቋማችንን የምናፋጥነው፤ አገሪቱ መብትና ነፃነትን ማክበር በመጀመሯ ነው የሚሉ ፖለቲከኞችን እየሰማን ነው።
የራሺያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን፤ ክሬሚያን በውሳኔ ሕዝብ ከዩክሬን አስገንጥለው የጠቀለሉበት ድራማም ተመሳሳይ ነው። ብዙ ራሺያውያን (ወደ 70 በመቶ ያህሉ) የፑቲንን ድርጊት መደገፋቸው አይደለም አስገራሚው ነገር። የፑቲን ቀንደኛ ተቃዋሚ የሆኑና በዚህም ታስረው የተንገላቱ ፖለቲከኞች ጭምር፤ ክሬሚያ ከዩክሬን ተገንጥላ በራሺያ ስር መግባቷን እንደሚደግፉ ለታይም መፅሔት ገልፀዋል። ለምን? በቃ፤ በክሬሚያ የሚኖሩ አብዛኞቹ ሰዎች የራሺያ ተወላጅ ናቸው። ከዚህ በመቀጠል የተናገሩትን ደግሞ ተመልከቱ።
“በእርግጥ” አሉ አንዷ ቀንደኛ የፑቲን ተቃዋሚ፤ “በእርግጥ፤ የክሬሚያ ነዋሪዎች በውሳኔ ሕዝብ ወደ ራሺያ በመጠቃለላቸው የሚያተርፉት ነገር የለም። እንዲያውም፤ መብትና ነፃነታቸው እንዲከበር የሚፈልጉ ከሆነ ከዩክሬን ጋር መቀጠል ይሻላቸው ነበር። በራሺያ ስር ለመሆን የወሰኑ ጊዜ፣ ከመብትና ከነፃነት ጋር ተለያይተዋል። እንዲያውም ከእንግዲህ በኋላ፤ ውሳኔ ሕዝብና ምርጫ የሚባል ነገር እንደገና የማየት እድል አይኖራቸውም” ብለዋል። በሌላ አነጋገር፤ ክሬሚያ ከዩክሬን የተገነጠለችበትና ወደ ራሺያ የተጠቃለለችበት ውሳኔ፤ የሰዎች መብትና ነፃነት እንዲከበር አንዳችም አወንታዊ አስተዋፅኦ አይኖረውም። እንዲያውም መብትና ነፃነትን የሚያሳጣ ውሳኔ ነው። ይህንን የተናገሩት፤ የፑቲን ቀንደኛ ተቃዋሚ የሆኑት ፖለቲከኛ ናቸው። ግን ደግሞ ውሳኔውን ይደግፋሉ። ዋና መመዘኛቸው፤ “የመብትና የነፃነት” ጉዳይ ሳይሆን፤ የዘር እና የብሔር ተወላጅነት ነው።
በአጠቃላይ፤ ከአፍሪካ እስከ ኤስያ፣ ከደቡብ አሜሪካ እስከ አውሮፓ... አለምን እያመሳቀሉ ከሚገኙት ሶስት ቀውሶች መካከል ሁለተኛው፣ ይሄው የጎሰኝነት ወይም የብሄረተኝነት አባዜ ነው። አንደኛ የሃይማኖት አክራሪነትና ሽብር፤ ሁለተኛ የጎሰኝነትና የብሄረተኝነት አባዜ።
ታይም መፅሔት ባለፈው ሰኞ በሽፋን ገፁ ላይ አጉልቶ ያወጣው ዋና ርዕሰ ጉዳይም፤ በእነዚህ ነጥቦች ላይ ይስማማል። በመፅሔቱ ቅድሚያ ስፍራ ተሰጥቶት የታተመው ፅሁፍ በጥቅሉ፤ “የኋላቀርነት ትርምስና ግጭት - በ21ኛው ክፍለዘመን” የሚል ጭብጥ የያዘ ሲሆን፤  አለማችን ብዙዎች ባልጠበቁት ቀውስ ከዳር ዳር እየተናጋች መሆኗን ይገልፃል። ከብሔረተኝነትና ከሃይማኖት ጋር በተያያዙ ኋላቀር ስሜቶች አማካኝነት በየአገሩና በየአቅጣጫው የሚፈጠሩ ትናንሽና ትላልቅ ግጭቶች፣ ምድሪቱን እያናወጧት ነው። ኋላቀር ግጭትና ማብቂያ በሌለው ትርምስ መበራከቱ መንግስታትንና ባለስልጣናትን፣ ምሁራንና ፖለቲከኞችን ግራ እንዳጋባ የሚተነትነው የመፅሔቱ ሰፊ ፅሁፍ፤ “21ኛው ክፍለዘመን እንዲህ ይሆናል ተብሎ አይጠበቅም ነበር” በማለት ነው የሚጀምረው። ... This isn’t what the 21st century was supposed to look like የሚለው አባባል በተጨባጭ ለማሳየት፣ በዩክሬን፣ በአረብና በአፍሪካ አገራት የተከሰቱ ቀውሶችን እያጣቀሰ ወደ ትንታኔው ይቀጥላል።
ለመፍትሄ ያስቸገረው ሦስተኛ ቀውስ፤ እንዲሁም በእንጥልጥል እየቀሩ ያስቸገሩ ሶስት ምኞቶችን ለሳምንት ላቆያቸው። እስከዚያው፤ ከሁለቱ የቀውስ ምንጮች ለመዳን እየተጋን እንሰንብት።

Read 4796 times