Monday, 31 March 2014 10:52

“ጅቡን የወጋኸው ምኑን ነው?” ቢሉት፤ “አፉን” አለ፡፡

Written by 
Rate this item
(6 votes)

“አፉን ከወጋኸውማ አሰፋኸው!”
(የጐንቸ ኤትወኸተታ ወካዀንም ቢውሪ አንቃታ ባረም፣
አንቃሸታ ቦካዀ አቤተትዀንም) - የጉራጊኛ ተረት

በዩናይትድ ስቴትስ እንደቀልድ የሚወራ ዛሬ ተረት የሆነ አንድ ትርክት አለ፡፡
ከዕለታት አንድ ቀን የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዝቅ ብሎ የህዝቡን የኑሮ ደረጃ ማየት ወሳኝ ነው በሚል እሳቤ፣ በመጀመሪያ የሴተኛ አዳሪዎችን ህይወት  ሊያዩ ሄዱ፡፡ ሦስት ዓይነት ደረጃ ያላቸው ሴቶችን አገኙ ይባላል፡፡
አንደኛ ደረጃ የምትባለዋ ባለ ወርቃማ ፀጉት ናት፡፡
ሁለተኛ ደረጃ የምትባለው ባለቀይ ፀጉር ናት፡፡
ሦስተኛ ደረጃ የምትባለው ባለጥቁር ፀጉር ናት፡፡ ይቺኛዋ የኑሮ ደረጃዋ የመጨረሻ ዝቅ ያለ ሴት ናት ማለት ነው። በመጀመሪያ አንደኛ ደረጃዋ ዘንድ ይሄዱና፤
“እኔ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ነኝ፡፡ ከአንቺ ጋር አንድ ምሽት ማሳለፍ እፈልጋለሁ፡፡ ምን ያህል ገንዘብ ትጠይቂኛለሽ?” አሏት፡፡
ባለ ወርቃማ ፀጉሯ ሴትም፤
“ሰላሳ ሺ ዶላር ይበቃኛል” አለቻቸው፡፡
“ጥሩ፤ እንግዲህ ዘወር ዘወር ብዬ ሌሎችን አጠያይቄ እመለሳለሁ” ብለው ወደ ሁለተኛ ደረጃዋ ባለ ቀይ ፀጉር ሴተኛ አዳሪ ይሄዳሉ፡፡
ለእሷም፤
“እኔ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ነኝ፡፡ ከአንቺ ጋር አንድ ማታ ማሳለፍና ተዝናንቼ ለማደር ምን ያህል ገንዘብ ይፈጅብኝ ይሆን?” ሲሉ ይጠይቃሉ፡፡
ባለ ቀይ ፀጉራ ሴትም፤
“ሃያ ሺህ ዶላር በቂ ነው ለእኔ” ትላቸዋለች፡፡
ፕሬዚዳንቱም፤
“እስቲ ዘወር ዘወር ብዬ የተሻለ ክፍያ አገኝ እንደሆነ አጠያይቄ እመለሳለሁ፡፡ ይሄ የመጨረሻ ዋጋ መሆኑ ነው አይደለም?”
“አዎን” አለቻቸው ሳታመነታ፡፡ በመጨረሻ ወደ ዝቅተኛዋ ባለጥቁር ፀጉር ሴት ዘንድ ይሄዱና፤
“እኔ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ነኝ፡፡ ከአንቺ ጋር አንድ ቆንጆ ምሽት ለማሳለፍ እፈልጋለሁ፡፡ ምን ያህል ገንዘብ እንደሚያስፈልገኝ ንገሪኝ፡፡ ታዲያ፤ ምንም ሳትፈሪ የሚያዋጣሽን ሀቀኛ የገንዘብ መጠን ነው የምትነግሪኝ እሺ?” አሏት፡፡
ባለ ጥቁር ፀጉርዋ ሴተኛ አዳሪም አውጥታ፣ አውርዳ የሚከተለውን መልስ ሰጠቻቸው፡፡
ስድስት ቅድመ - ሁኔታዎችን ካሟሉ ከእኔ ጋር በነፃ ለማደር ይችላሉ፡፡ ብላ ጀመረች፡፡
ፕሬዚዳንቱም በችኮላ፣
“ምን ምንድናቸው?” ብለው ጠየቋት፡፡ ባለ ጥቁር ፀጉሩዋ ሴትም፤
“አይቸኩሉ፤ ልነግርዎት ነው፡፡ ደግሞም እርሶ ጋዜጣዊ መግለጫ ሲሰጡ እንደሚያስረዝሙት አላንዛዛውም፡፡”
1ኛ/ ቀሚሴን በጣም ከፍ የሚያደርጉት የሚያስከፍሉኝን ቀረጥ ያህል ለመሆን ከቻለ፤
2ኛ/ የውስጥ ሱሪዬን ዝቅ የሚያደርጉት የሰራተኛው ህዝብ ዝቅተኛ ደሞዝ ድረስ ከሆነ፤
3ኛ/ የሰውነትዎ ጥንካሬ እንደ ኑሮ የከበደ ከሆነ፣
4ኛ/ በዚሁ ከባድና ጠንካራ ሁኔታ እኔ ለዳቦ ስሰለፍ የምቆመውን ያህል ጊዜ፤ ጠንክረው የሚቆዩ ከሆነ፤
5ኛ/ እቅፍዎ ውስጥ ሲያስገቡኝ፤ ከምኖርበት በክረምት ብርድ የተሞላ ቤት የተሻለ የሚሞቀኝ ከሆነ
6ኛ/ የፍቅር ጨዋታዎ ህዝቡን የሚጫወቱበትን ዓይነት ከሆነ፤ ነው፡፡ ዕውነቴን ነው የምልዎት አምስት ሳንቲም ሳይከፍሉ ከእኔ ጋር በነፃ ማደር ይችላሉ” አለቻቸው፡፡
*     *      *
የህዝብን የኑሮ ደረጃ ዝቅ ብሎ ወርዶ የሚያይ መሪ፣ አለቃ፣ ኃላፊ ማግኘት መታደል ነው፡፡ ያስቀናል፡፡ የዋጋ መናርና የታክስ ማሻቀብ አንድን ማህበረሰብ የጦርነትን ያህል ያጠፋዋል፡፡ ለዚህ ነው መሪዎች ሁሉ የህዝባቸውን ኑሮ በቅርብ ያስተውሉ የሚባለው፡፡ ህዝብ የሀገር ሙቀት መለኪያ ነው፡፡ ህዝብ የሚከፍለው ግብር ከሚያገኘው አገልግሎት ጋር ካልተመጣጠነ የቀዘቀዘች አገር ውስጥ ነው የሚኖረው፡፡ ህዝብ ደሞዙ ከሚኖረው ኑሮ ጋር ካልተመጣጠነለት ኖረ አይባልም፡፡ ህዝብ ከዕለት ዕለት ህይወት እየከበደው ከሄደ ከሳቁ ምሬቱ፣ ከደስታው ሐዘኑ እየበረታ ሥርዓቱን፣ አገዛዙን፣ ገዢዎቹን፣ አስተዳዳሪዎቹን ይጠላል፡፡ ሀገሩም የእሱ አትመስለውም፡፡ ህዝብ መሰረታዊ የፍጆታ ዕቃዎችን ለማግኘት ነግ-ሠርክ የሚሰለፍ ከሆነ፤ አልፎ ተርፎም ከናካቴው ዕጥረት የሚከሰትበት ሁኔታ ከመጣ፣ ብሶቱ ወሰን አይኖረውም፡፡ ህዝብ በመኖሪያ ቤት ችግር የሚሰቃይ ከሆነ መሰረታዊ የኑሮ አስፈላጊ ነገር ጎሎበታል ማለት ነው፡፡ ከዚህ ሁሉ የሚከፋው ደግሞ ይህንን የሚገልፅበት መንገድ ካጣና በፍርሃት ተሸማቆ ከተቀመጠ ነው፡፡ “አዲስ ያይጥ - ወጥመድ በሰራህ ቁጥር” አዲስ አይጥ የምትወለድ ከሆነ፣ ወይ ወጥመዷ ላይ ወይ አጥማጁ ላይ ችግር አለ ማለት ነው” ይባላል፡፡ በሙስና የተሞላ ልማት ዘርዛራ ወንፊት ነው፡፡ ዕብቁንም፤ እንክርዳዱንም፤ እያሳለፈ፤ እያዩ እህል አለን እንደሚሉት አይነት የዋህነት ይሆናል፡፡ የዚህ ሁሉ መጨረሻው ድህነት ነው፡፡ ድህነት ሲመጣ ቃላት ይበዛል። ስብሰባ፣ ንግግር፣ የማይተገበር ቃል - መግባት እንደህይወት ይወሰዳል፡፡ እንደኑሮ ይለመዳል፡፡ “አንድ መንግሥት ከሌላ መንግሥት የሚማረው ጥበብ ከህዝብ ኪስ ገንዘብ አሟጥጦ መውሰድ ነው” ይለናል፤ አዳም ስሚዝ የጥንቱ የጠዋቱ የኢኮኖሚ ሊቅ፡፡  
አንድ የአሜሪካኖች አባባል አለ:- “በአንድ አገር ከዋናው ይልቅ ምክትሉ ነው ምርጥ ሥራ አለው የሚባለው፡፡ ምክንያቱም ትልቁ ሥራው ጠዋት ሲነሳ ‘ዋናው አለቃ ደህና አደሩ?’ ማለት ብቻ ነው!” ከዚህ ይሰውረን፡፡
ኑሮ እጅግ በከፋ ሁኔታ ላይ ሲገኝ፤ እንግሊዞች “ሶስት ትውልድ ሙሉ ሸሚዛችንን እንደጠቀለልን አለን” ይላሉ፡፡ ጣሊያኖች ደግሞ፤ “ከከዋክብት እስከ ጋጣ/በረት እየኖርን ነው” ይላሉ፡፡ ስፔይኖችም፤ “ሀብትን፤ የሌለው ይሠራዋል። ያለው ያላግባብ ይጫወትበታል” ይላሉ፡፡ ኢትዮጵያውያን፤ “ኑ እስኪለን መከራችንን እናያለን” ይላሉ፡፡ አምላክ አንደኛውን እስከሚጠራን ቀን ድረስ አበሳ ፍዳችንን እየቆጠርን ነው እንደማለት ነው!! ሁሉ የምሬት ቋንቋ አለው! ጊዜውና ደረጃው ይለያይ እንጂ ምሬቱ የሚፈታበትም መንገድ እንደዚያው ይለያያል፡፡ ማናቸውም ዕቅድና ስትራቴጂ ህዝብ ኑሮ ላይ ያነጣጠረ መሆን አለበት፡፡ ይሄ ማለት የእርስ በርስ ሙግትና የአዕምሮ አክሮባት ከመሥራት ይልቅ፤ የህዝቡስ ሁኔታ እንዴት ነው? ማለት ዋና ጉዳይ ነው፣ ማለት ነው፡፡ ለህዝብ ተብሎ፣ በህዝብ ስም የተቀረፀውንም አጀንዳ ለግል ጥቅም እንዳይውል ጠንክሮ መጠበቅ ይገባል፡፡
በሀገራችን “ሲሾም ያልበላ ሲሻር ይቆጨዋል” የተባለው ተረት ዕድሜው እጅግ ረጅም ነው፡፡ የሥርዓቶቻችንን ያህል አርጅቷል፡፡ በተግባር ሲተረጐም ግን ገና ዛሬ የተወለደ ነው የሚመስለው፡፡ በየቢሮው፣ በየማህበሩ፣ በየፓርቲው የምናየው ሀቅ ነው፡፡ “አዲስ እረኛ ከብት አያስተኛ”፣ “እከክልኝ ልከክልህም” አብሮ ሲተረት የኖረ ነው፡፡ እዚህ ላይ፤ ሁለት የአሜሪካ ፕሬዚዳንቶች ሲቀያየሩ ሂያጁ ለመጪው ያለውን መጥቀስ መልካም አርአያነት ያለው ነው:-
“እኔ ይሄን ሥልጣን (ቢሮ) ለቅቄ ስወጣና ወደቤቴ ስሄድ፤ የተደሰትኩትን ያህል አንተ ወደዚህ ሥልጣን በመምጣትህ የምትደሰት ከሆነ፤ በዚች አገር የመጨረሻው ከፍተኛ ደስተኛ ሰው አንተ ነህ ማለት ነው!” (ይህን የተባሉት አብርሃም ሊንከን ናቸው) ይሄ መታደል ነው፡፡ በማናቸውም መንገድ ሥልጣን ላይ የሚወጣ ሰው፤ “ሥልጣን በሸተተው ማግስት አካሄዱ ሁሉ ይለዋወጣል፤ እንደድመት ኮርማ ይሆናል” ይባላል፡፡ ከዚህም ይሰውረን። አክብሮታችን ለመንበሩ እንጂ ለሰውዬው አይደለም፡፡ ዞሮ ዞሮ ህዝብን ማገልገያ መንበር መሆን አለበት፡፡ አንዱ ባለሥልጣን ሌላውን ባለሥልጣን የጐዳ መስሎት በሚሠነዝረው ጥቃት የዝቅተኛው ክፍል ህዝብ መጠቃቱ ትልቅ ጉዳት ነው፡፡ አፍ በሰፋ ቁጥር ተሳዳቢው ህዝብ ነው፡፡ የሚላክበት ህዝብ ነው፡፡ ጎረቤትም ቢቆስል ጦሱ ላገር ነው፡፡ የቆሰለ አውሬ ለያዥ ለገራዥ አስቸጋሪ ነው፡፡ ጣጣው ግን የህዝብ ነው፡፡   
ለዚህ ነው “ጅቡን የወጋኸው ምኑን ነው?” ቢሉት፤
“አፉን” አለ፡፡ “አፉን ከወጋኸውማ አሰፋኸው” የሚለው የጉራጊኛ ተረት ለማንም የማስጠንቀቂያ ደውል የሚሆነው!! \\\

Read 4116 times