Saturday, 15 March 2014 12:32

አንድነት ለቀጣዩ ምርጫ ቅድመ ሁኔታዎች አስቀመጠ

Written by 
Rate this item
(34 votes)

ነገ የሦስት ወር ንቅናቄውን በአዲስ አበባ ይጀምራል

      ከመድረክ ጋር ያለውን ጥምረት አቋርጦ ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር የውህደት ድርድር የጀመረው አንድነት ለፍትህና ለዲሞክራሲ ፓርቲ፤በመጪው ዓመት ምርጫ የሚሳተፈው የምርጫው አስፈፃሚ አካላት ነፃና ገለልተኛ መሆናቸው ከተረጋገጠ ብቻ እንደሆነ  ሊቀመንበሩ ኢ/ር ግዛቸው ሽፈራው ገለፁ፡፡
በ97 ምርጫ ቅንጅት የነበረውን ጥንካሬ ፓርቲያቸው መድገም እንደሚፈልግ የገለፁት ኢ/ር ግዛቸው፤ ህዝቡ ብሶት ላይ ስለሆነ በምርጫው ተቃዋሚዎች በቀላሉ ሊያሸንፉ እንደሚችሉ ተናግረዋል፡፡ ፓርቲያቸው ወደ ምርጫው የሚገባው ግን ለምርጫው ነፃና ፍትሃዊ መሆን አስፈላጊ የሚባሉት ገለልተኛ የምርጫ ቦርድ፣ ሚዲያ እና የፍትህ ተቋማት መኖራቸውን ካረጋገጠ በኋላ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ “ይህ ጥያቄያችን ከተመለሰ በምርጫው በእርግጠኝነት እናሸንፋለን” ብለዋል የፓርቲው መሪ፡፡
ፓርቲያቸው ከመድረክ ጋር ስላለው ግንኙነት የተጠየቁት ኢ/ር ግዛቸው፤ አንድነት ከቢሮ እና ከመግለጫ ፖለቲካ ተላቆ ትግሉን ወደ ህዝብ ለማውረድ  ያደረገው እንቅስቃሴ የመድረክ አመራሮችን እንዳስኮረፈና እገዳው እንደተላለፈ ጠቅሰው “እገዳው ትክክል አይደለም፤ አንሱትና ባቀረብነው የውህደት ጥያቄ መሰረት አብረን እንስራ ብለናቸዋል” ብለዋል፡፡
“መድረክ ከአንድነት የተሻለ ጥንካሬ እንደሌለው ገምግመናል” ያሉት ሊቀመንበሩ፤ ውህደቱን አንፈልግም ቢሉም እንኳን በሚያግባቡን ጉዳዮች ላይ በቅንነት አብረን ልንሰራ እንደምንችል ነግረናቸዋል ብለዋል፡፡
ከእዚህ በኋላ አንድነት በቀጥታ ውህደት ከመፈፀም ውጪ ከየትኛውም ፓርቲ ጋር ግንባርና ቅንጅት የመፍጠር ፍላጎት እንደሌለውም ኢ/ር ግዛቸው ጨምረው ገልፀዋል፡፡
ፓርቲው በነገው እለት “የሚሊዮኖች ድምፅ ለነፃነት” ሁለተኛ ዙር ንቅናቄ በአዲስ አበባ የሚጀምር ሲሆን  አጀንዳውም መሬት የግል እንዲሆን የሚጠይቅ ነው ተብሏል፡፡ ለ3 ወር ይዘልቃል የተባለውን ይሄን ንቅናቄ በተመለከተ የተጠየቁት ኢ/ር ግዛቸው፤“በአንድነት ፕሮግራም ውስጥ ከመንግሥት ይዞታና ከአንዳንድ ተቋማት ይዞታ በስተቀር መሬት የግል መሆን አለበት በሚል በግልፅ አስቀምጠናል፡፡ ይህን መነሻ አድርገን በመሬት ጉዳይ ላይ ህዝብ ተወያይቶ የራሱን አቋም የሚይዝበት ትልቅ ንቅናቄ አዘጋጅተናል” ሲሉ አስረድተዋል፡፡
 አሁን ያለው የመሬት ፖሊሲ ለኑሮ ውድነቱ መባባስ አስተዋፅኦ አበርክቷል ያሉት ኢ/ር ግዛቸው፤ “የኑሮ ውድነቱ ካለን የመሬት ሃብት ተጠቃሚ ያለመሆናችን ውጤት ስለሆነ፣ ጥያቄያችን የኑሮ ውድነት አጀንዳንም በበቂ ሁኔታ የያዘ ነው” ብለዋል፡፡ መንግስት በበኩሉ፤ መሬት የህዝብና የመንግስት ነው የሚል ፖሊሲ እንደሚያራምድ ይታወቃል፡፡
(ከአንድነት ፓርቲ ሊቀመንበሩ ኢ/ር ግዛቸው ሽፈራው ጋር የተደረገው ቃለምልልስ ሙሉ ቃል በገፅ 5 ላይ ያገኙታል፡፡)


Read 4451 times