Saturday, 15 March 2014 12:31

በህግ ታራሚዎች ይቅርታ አሰጣጥ ላይ የሚወስን ረቂቅ አዋጅ ወጣ

Written by  መታሰቢያ ካሣዬ
Rate this item
(2 votes)

         በተለያዩ ወንጀሎች ፍርድ ተሰጥቶባቸው በማረሚያ ቤት ለሚገኙ የህግ ታራሚዎች የሚደረግ ይቅርታ አሰጣጥን የሚወስንና በቀድሞ አዋጅ ላይ ማሻሻያዎች የሚያደርግ ረቂቅ አዋጅ ወጣ፡፡ ረቂቅ አዋጁ በይቅርታ አሰጣጡ ላይ በሚኖረው የፕሬዚዳንቱ ሚና ላይ ማሻሻያዎችን አድርጓል፡፡ ሰሞኑን ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው ይኸው ረቂቅ አዋጅ፤ በ1996 ዓ.ም የወጣውን የይቅርታ ስነ-ስርዓት ለማሻሻልና አዋጁ ያሉበትን ክፍተቶች ለማስተካከል ታስቦ እንደተዘጋጀ ተገልጿል፡፡
በቀድሞው አዋጅ፤የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ለታራሚዎች ይቅርታ የመስጠት ሥልጣን እንዳላቸው የተደነገገ ሲሆን አንቀፁ መሻሻያ ተደርጎበት የይቅርታ ጥያቄዎችን በመመርመር፣ ለፕሬዚዳንቱ የውሳኔ ሃሳቡን በማቅረብ የሚያጸድቀው የይቅርታ ቦርዱ እንደሆነ ተጠቁሟል፡፡ ለፕሬዚዳንቱ የሚቀርቡላቸው ይቅርታ ሊደረግላቸው የሚገቡ ሰዎች ዝርዝር ብቻ እንደሆነም ረቂቅ አዋጁ አመልክቷል፡፡
የፕሬዚዳንቱ ይቅርታን የመሰረዝ ስልጣን፣ በአዲሱ ረቂቅ አዋጅ ለይቅርታ ቦርድ የተሰጠ ሲሆን የይቅርታ ቦርዱ የመጨረሻ ውሳኔ በመስጠት፣ይቅርታን የመሰረዝ ስልጣንና ተግባር እንዳለው ረቂቅ አዋጁ አመላክቷል፡፡
በቀድሞው አዋጅ፤አንድ ታራሚ የይቅርታ ጥያቄ አቅርቦ ይቅርታ ከተደረገለት ግብረ አበር ወይም አባሪ የሆነው ታራሚ፣ይቅርታ እንደሚያገኝ የተደነገገ ቢሆንም ይህ አሰራር በአዲሱ ረቂቅ አዋጅ ተቀባይነት የለውም፡፡
ረቂቅ አዋጁ ይቅርታን ሊያስከለክሉ የሚችሉ ወይንም የይቅርታ ጥያቄ ሊቀርብባቸው የማይችሉ ብሎ በዝርዝር ከጠቀሳቸው ወንጀሎች መካከል ሙስና፣ ሽብርተኝነት፣ ህገወጥ የጦር መሳሪያና የሰዎች ዝውውር፣ በመሰረተ ልማት አውታር ላይ የሚፈፀም ወንጀል፣ የሃሰት ገንዘብ መስራት፣ ማዘዋወር፣ የአደገኛ እፅ ዝውውር፣ የጠለፋና አስገድዶ መድፈር ወንጀል፣ ግብረ ሰዶማዊነትና ህገወጥ የቅርሶች ዝውውር ይገኙባቸዋል፡፡
የይቅርታ ጥያቄዎችን የሚመረምርና የውሳኔ ሃሳቦችን ለፕሬዚዳንቱ በማቅረብ የሚያሰወስነው ከፍትህ፣ ከጤና ጥበቃ፣ ከሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ፣ ከፌዴራል ጉዳዮች፣ የሴቶች ህፃናትና ወጣቶች፣ ከመከላከያ ሚኒስቴር መ/ቤቶች፣ ከፌደራል ፖሊስ ኮሚሽንና ከፌደራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር የሚዋቀር የይቅርታ ቦርድ እንደሆነም በረቂቅ አዋጁ ላይ ተገልጿል፡፡

Read 2210 times