Saturday, 08 March 2014 13:16

ጠ/ሚኒስትር ኃይለማርያም እየመሩን መሆናቸውን ለምን ተጠራጠርን?

Written by  ኤልያስ
Rate this item
(28 votes)

ማነው ሲምካርድ? ማነው ቀፎው? (ሁለቱም ከሌሉ አንደውልም!)

    አንዳንድ የአፍሪካ አምባገነን የስልጣን ሱሰኞች ትዝ ሲሉኝ ማንን እያስታወስኩ እንደምፅናና ታውቃላችሁ? የአውራውን ፓርቲ ሹማምንት! ቧልት እንዳይመስላችሁ---ከልቤ ነው፡፡ እርግጥ ነው ፓርቲው ኢትዮጵያን መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገራት ከማሰለፉ በፊት ከስልጣን የመልቀቅ ሃሳብ እንደሌለው በግልፅ አስታውቋል፡፡ ነገርዬው እውነት ይሁንም ሃሰት ፓርቲው እንጂ አባላቱ ስልጣን ላይ የመክረም ሃሳብ እንደሌላቸው በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል፡፡ በተለይ ደግሞ የቀድሞዎቹ አንጋፋ ታጋዮች፡፡ ፓርቲው ስልጣን ላይ እስካለ ድረስ መሪዎቹ ማንም ቢሆኑ አንድ ናቸው ልትሉኝ ትችላላችሁ (“ድስት ቢለዋወጥ ወጥ አያጣፍጥም”እንደማለት) እውነት ብላችኋል፡፡ እኔ ደግሞ ከቅኝ ግዛት ነጻነት ማግስት ጀምሮ ዚምባቡዌን እንደ ግል ንብረታቸው እየተቆጣጠሩ በቅርቡ 80 ምናምነኛ ዓመት የልደት በዓላቸውን ያከበሩትን ሮበርት ሙጋቤን ለንፅፅር አመጣላችኋለሁ፡፡ በነገራችሁ ላይ ሙጋቤ ልደታቸውን ሲያከብሩ   ስልጣን የመልቀቅ ሃሳብ እንዳላቸው ተጠይቀው “ፓርቲዬን ለማን ትቼ!” ሲሉ ከስልጣን የሚገላግላቸው ሞት ብቻ እንደሆነ በተዘዋዋሪ ተናግረዋል፡፡
ከጥቂት ዓመታት በፊትም አንድ የውጭ ጋዜጠኛ “ሚስተር ፕሬዚዳንት የዚምቧቡዌን ህዝብ መቼ ነው የሚሰናበቱት?” ሲል ይጠይቃቸዋል (መቼ ነው ከስልጣን የሚለቁት ለማለት ፈልጎ ነው) አጅሬው ሙጋቤ ምን ቢሉ ጥሩ ነው? “ህዝቡ ወዴት ሊሄድ ነው?” ብለው አረፉት፡፡ ህዝቡ እስካለ ድረስ መሰነባበት የለም ማለታቸው እኮ ነው፡፡ አንዴ የድሮ ቅኝ ገዢአቸውን የእንግሊዙን ጠ/ሚኒስትር ቶኒ ብሌይርን ለማብሸቅ ብለው ምን እንዳሉ ታውቃላችሁ? “ሚስተር ብሌር፤ ዚምባቡዌ ኢዝ ማይን!” ብለዋል አሉ፡፡ (“አትልፋ! ዚምባቡዌ የእኔ ብቻ ናት” ማለታቸው ነው)  እስቲ አስቡት--- የኢህአዴግን የመተካካት ስትራቴጂ ሙጋቤ ቢሰሙ እንዴት እንደሚቀልዱ! “ማን አባቱ ነው ማንን የሚተካው!” ብለው ቱግ ነበር የሚሉት።  እሳቸው ብቻ ግን አይደሉም በአፍሪካ ስልጣንን የሙጥኝ ብለው በአምባገንነት ሕዝባቸውን የሚገዙት፡፡ የጥንቱ የኢህአዴግ ወዳጅ የአሁኑ ቀንደኛ ጠላት የኤርትራው መሪ ኢሳያስ አፈወርቂ እንኳንስ እንደኛ አገር 70 ምናምን ተቃዋሚ ፓርቲዎች እንዲቋቋሙ ሊፈቅዱ ቀርቶ፣ስለተቃዋሚ ፓርቲ ሲወራ ቢሰሙ እንኳ ኤሌክትሪክ ነው የሚጨብጡት፡፡ (ተቃዋሚ በእኔ መቃብር ላይ እንጂ እስትንፋሴ እያለች አይሞከርም ባይ ናቸው!) የኡጋንዳው ሙሴቪኒስ ቢሆኑ? እንዴት ነው ይሄን ሁሉ ዓመት ተቃዋሚን እያሸነፉ በስልጣን የዘለቁት? አያችሁ ---- በአገሬ ባለስልጣናት የምፅናናው ወድጄ አይደለም፡፡ ለምሳሌ በቅርቡ ጠ/ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ በቀጣዩ ምርጫ በጠቅላይ ሚኒስትርነት የመቀጠል ፍላጎት እንዳላቸው ሲጠየቁ ምን አሉ? “ይሄ የሚወሰነው በፓርቲዬ እንጂ በእኔ ፍላጎት አይደለም፤ ኢህአዴግ ታች ወርደህ የቀበሌ ሊቀመንበር ሁን ካለኝ እሆናለሁ፤ በጠ/ሚኒስትርነት የበለጠ አስተዋፅኦ ታበረክታለህ ካለኝም---” ብለዋል፡፡ ሙጋቤ ተመሳሳይ ጥያቄ ቢቀርብላቸው ምን እንደሚሉ አልታያችሁም፡፡ “እኔ ካልቀጠልኩ ታዲያ ሕዝቤን ማን ይመራዋል!? ይሉ ነበር፡፡ ለዚህ እኮ ነው በኢህአዴግ የምፅናናው፡፡ እንዲያም ሆኖ በአንድ ወቅት አቦይ ስብሃት “ከአፍሪካ ፓርቲዎች ኢህአዴግን የሚስተካከለው የለም” ባሉት ነገር አልስማማም፡፡ (በግምት ነዋ የተናገሩት!)
እርግጥ ነው ኢህአዴግም ቢሆን የስልጣን ኮርቻው ላይ ከተፈናጠጠ ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ አስቆጥሯል፡፡ ግን ቢያንስ አንድ መሪ (ጠ/ሚኒስትር) እስከ 80 ምናምን ዓመቱ በድዱ አይገዛንም፡፡ (የፓርቲው ባህል አይፈቅድማ!) ስለዚህ በዚህ እፅናናለሁ፡፡ ለምሳሌ ከ20 ዓመት በላይ ኢህአዴግንና ጦቢያን የመሩት ጠ/ሚኒስትር መለስ ድንገት በሞት ሲለዩ የስልጣን ፉክቻ አላየንም (ቢያንስ በአደባባይ!) እነሙጋቤ አገር ቢሆን ኖሮ ምን እንደሚፈጠር አስቡት፡፡ እናም ኢህአዴግ የጠ/ሚኒስትሩን ህልፈት ተከትሎ በትጥቅ ትግሉ ያልነበሩትን አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ በፓርቲው ሊቀመንበርነትና በጠ/ሚኒስትርነት መምረጡ የጦቢያን ልጆች ማስገረሙ አልቀረም፡፡ ዛሬም ድረስ እኮ ጠ/ሚኒስትሩ እየመሩ መሆናቸውን የምንጠራጠር ቀላል አይደለንም፡፡
ለዚህ እኮ ነው ብዙዎች በግልም በቡድንም፣ በአማርኛም በእንግሊዝኛም ደጋግመው “ጦቢያን በትክክል እየመራት ያለው  ማነው?” ወይም “Who is in Charge?” እያሉ የሚጠይቁት፡፡ እዚህች ጥያቄ ውስጥ ግን ብዙ የተጠቀጠቁ ጥርጣሬዎችና መላምቶች አሉ፡፡ ለምሳሌ አንድ የኒዮሊበራሊዝም አቀንቃኝ የሆነ ወዳጄ ያለኝን ላጋራችሁ፡፡ (ኒዮሊበራሊዝም የሚለውን ቃል “አክራሪ ነፍጠኛ” በሚል ወደ አገር-በቀል ፍቺ ለውጬዋለሁ!) እናላችሁ … ይሄ ወዳጄ፤ አሁንም ድረስ የአገሪቱ ጠ/ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ናቸው ብሎ አያምንም፤ እሳቸው ለስሙ ወንበሩ ላይ ተቀመጡ እንጂ ከጀርባ ሆነው መሪነቱን የሚዘውሩት አንጋፋ የኢህአዴግ ታጋዮች ናቸው ባይ ነው፡፡ (ህወሓቶች ማለቱ መሰለኝ!)
እውነቱን ልንገራችሁ አይደል----እኔ በበኩሌ “የጠ/ሚኒስትርነቱን ቦታ በትክክል ማነው የያዘው?” የሚለው ብዙም አያስጨንቀኝም፡፡ የደቡብ ህዝቦች ግንባር ይሁን ህወሓት ወይም ኦህዴድ አሊያም ብአዴን  ለእኔ ለውጥ የለውም (ያው ኢህአዴግ ነዋ!) ለእኔ ቁምነገሩ ምን መሰላችሁ? “እንዴት ነው የሚገዛኝ?” የሚለው ነው። “ራዕዩ የማን ነው” በሚለውም አልጨነቅም፡፡ “ራዕዩ ምንድነው?” በሚለው እንጂ፡፡
በአሁኑ ሰዓት ጦቢያን የሚመራት ማነው “Who is in Charge?” የሚለው ጥያቄ ያሳሰባቸው ቧልተኞች  የፈጠሩትን ቀልድ ላልሰማችሁ ላሰማችሁ፡፡ (ኮፒራይቱ የሰፊው ህዝብ እንደሆነ ይታወቅልኝ!)
 አንዱ ኤፍኤም ሬዲዮ ይደውላል - ዘፈን ለመምረጥ።
ደዋይ - ዘፈን ለመምረጥ ነበረ፤ የእገሌን …
ኤፍ ኤም- ማን እንበል? ከየት ነው?
ደዋይ-    የገዢው መደብ አባል ነኝ---- ከደቡብ!
ኤፍ ኤም- (ደንገጥ ብሎ) ከደቡብ … እሺ ዘፈኑ ይቀጥላል …
(የኤፍኤሙ ጋዜጠኛ ከድብልቅልቅ ስሜት ሳይወጣ ሌላ ዘፈን መራጭ ይደውላል)
ኤፍ ኤም- ሄሎ … ማን እንበል? ከየት ነው?
ደዋይ -    ዘፈን ለመምረጥ ነበር
ኤፍኤም- ራስህን አስተዋውቀን?
ደዋይ -    የገዢው መደብ አባል ነኝ - ከትግራይ!
ኤፍኤም - እንዴትነው ነገሩ? አሁን ከደቡብ ደውሎ የገዢው መደብ አባል ነኝ ብሎኛል እኮ?    
ደዋይ- ዝም ብሎ ነው ባክህ … እነሱ ቀፎ፤ እኛ ሲም ካርድ ነን!
እውነቱ ግን ምን መሰላችሁ? ቀፎውም ሲምካርዱም ያስፈልገናል፡፡ አንዱ ያለሌላው ጥቅም አይሰጥም፡፡   ሲም ካርድ ብቻውን አይደውልም ፤ ቀፎ ብቻውንም እንደዚያው፡፡
ስለዚህ ቀፎውም ሲምካርዱም እኩል ያስፈልጉናል እያልኩ ነው፡፡ በእርግጥ በቴሌ አሰራር ነገሩ የተለየ ሆኗል፡፡ ቀፎም ሲም ካርድም አንድ ላይ ሆነው መደወል አልተቻለም - ኔትዎርክ በሚሉት ችግር!! ገዢዎቻችንን ከኔትዎርክ መቆራረጥ ይሰውርልን! በተረፈ ያንዱ ቀፎ መሆንና የሌላው ሲም ካርድነት ጣጣ የለውም፡፡ ሁለቱም እኩል ያስፈልጉናል!!

Read 7907 times