Tuesday, 04 March 2014 11:26

ማረሚያ ቤት ለአቶ አሥራት ጣሴ የሰጠው ምላሽ

Written by 
Rate this item
(2 votes)

ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ የካቲት 15 ቀን 2006 ዓ.ም በወጣው አዲስ አድማስ ዕትም ላይ የቀድሞው የአንድነት ለፍትህና ለዲሞክራሲ ፓርቲ ዋና ፀሐፊ የነበሩትና በአዲሱ ካቢኔ ውስጥ ሳይካተቱ የማዕከላዊ ምክር ቤት አባል የሆኑት አቶ አስራት ጣሴ፤ “የሙስና አዋጁ እንደገና ሊፈተሽና ሊታይ ይገባል” በሚል ርዕስ “በእስር በቆየሁባቸው 10 ቀናት ውስጥ ስለ ቂሊንጦ ማረሚያ ቤት የታዘብኳቸው” በማለት ከከፍተኛ ሪፖርተር አለማየሁ አንበሴ ጋር ያደረጉትን ቃለ ምልልስ ተመልክተነዋል፡፡ ይሁን እንጅ አቶ አስራት ጣሴ ስለማረሚያ ቤቱ የተናገሩት ወደ አንድ ፅንፍ ያዘመመና የተቋሙን ገፅታ ሙሉ በሙሉ በሚያበላሽ መልኩ የቀረበ ሲሆን ማረሚያ ቤቱን በተመለከተ ትክክለኛው መረጃ ለህብረተሰቡ ይደርስ ዘንድ ምላሻችንን እንደሚከተለው አቅርበናል፡፡
1ኛ/ በእስር ቤት ቆይተዎ ምን ታዘቡ? ተብለው ለተየጠቁት ጥያቄ
“በእውነት በቂሊንጦ ማረሚያ ቤት በቆየሁባቸው ስምንት ቀናት በዚች ሀገር የፍትህ ስርዓት እንዴት ፈታኝ እንደሆነ ተረድቻለሁ” ሲሉ መልስ ሰጥተዋል፡፡ (ገፅ 14)
በአሁን ሰዓት መንግስት ዜጎች የፍትህ ተደራሽነት ይኖራቸው ዘንድ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ ተግቶ እየሰራ ይገኛል፡፡ በዚህም መሰረት ከቅርብ ዓመታት በፊትም የፍትህ አካላትን በማዋቀር “ፍትህ ለሁሉም ይዳረስ” በሚል መሪ ቃል፣ የፍትህ አካላት በከፍተኛ ሁኔታ እየሰሩ ይገኛሉ፡፡ ከፍትህ አካላትም መካከል የፌደራል ማረሚያ ቤቶች አንዱ ሲሆን መንግስት በሰጠው ተልዕኮ በፍርድ ቤት ውሳኔ ያገኙ የህግ ታራሚዎችንና የቀጠሮ እስረኞችን ተቀብሎ በመጠበቅ፣የታረመና የታነፀ ዜጋ ለማድረግ ፍትህ በማስጠበቅ የህግ ታራሚዎችም አውቀውም ሆነ ሳያውቁ በፈፀሙት ወንጀል ተፀፅተው ከእርምት በኋላ ወደ ማህበረሰቡ ሲቀላቀሉ አምራች ዜጋ ለመፍጠር እየሰራ የሚገኝ ተቋም ነው፡፡ አቶ አስራት ጣሴ ግን በቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ውስጥ ተአማኒነት ያለው አስተያየት ለመስጠት በቂ የእስር ጊዜያትን ሳያሳልፉና ሁኔታዎችን ሳያጤኑ በአጠቃላይ የማረሚያ ቤቱን ስም በሚያጎድፍ መልኩ “ፍትህ የለም” ብለው መናገራቸው አግባብነት የሌለውና ከእውነት የራቀ ነው፡፡ በመሰረቱ ማንኛውም ሰው ነፃ አስተያየት የመስጠት መብት ቢኖረውም እነዚህ አስተያየቶች ግን በማስረጃና በደጋፊ እውነታዎች መመስረት ሲገባቸው፣ ተጠያቂው ግን “በዚች አገር ፍትህ እንዴት ፈታኝ እንደሆነ ተረድቻለሁ” በሚል ያለምንም መገለጫ ከእውነት በራቀ መልኩ የተናገሩት ንግግር ሆኖ አግኝተነዋል፡፡ ስለዚህ አስተያየቱ ከአሉባልታ የማይሻገርና መንግስት ግልፅ የሆነ አሰራር እየተከተለ ባለበት ጊዜ የማረሚያ ቤቱን ፍትህ የማረጋገጥ ጉዞ በሚያሰናክል መልኩ የቀረበ   በመሆኑ የሚስተካከል ቢሆን፡፡
2ኛ/ “የማረሚያ ቤት አያያዝ ባልተፃፈ ህግ የሚመራበት ሁኔታ እንዳለም ተረድቻለሁ” በማለት ትዝብታቸውን አስቀምጠዋል፡፡ (ገፅ 14)
ነገር ግን የፌደራል ማረሚያ ቤቶች መቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 365/95 በተሰጠው ስልጣን እንዲሁም ደንብ ቁጥር 138/99 የታራሚዎች አያያዝ በሚኒስትሮች ምክር ቤት በወጣው ደንብ መሰረት፣ በፍርድ ቤት ውሳኔ ያገኙ የህግ ታራሚዎችና የቀጠሮ እስረኞችን ተቀብሎ ከውስጥና ከውጭ ሊደርስ ከሚችል ጥቃት በመጠበቅ፣ መሰረታዊ ፍላጎታቸውን በማሟላትና አርሞና አንፆ አምራች ዜጋ የማድረግ ኃላፊነት አለበት ሲል የሚደነግግ ነው፡፡
ከዚህም በመነሳት ታራሚዎች የፍርድ ግዜያቸውን ጨርሰው እስከሚወጡ ድረስ ማረሚያ ቤት የራሱ የሆነ ህግና ደንብ አውጥቶ የህግ ታራሚዎችንም ሆነ የተቋሙ ሰራተኞችን ያስተዳድራል፡፡
ነገር ግን አቶ አስራት ጣሴ፣ በማረሚያ ቤት ውስጥ ምንም አይነት የተፃፈ ህግ እንደሌለና በመተዳደሪያ ደንብ ሳይመራ በዘፈቀደ ማረሚያ ቤቱ ደስ ባለው ህግ እንደሚተዳደር አድርገው መናገራቸው አግባብነት የሌለውና በእርግጥም ስለሚሰጡት አስተያየት ግልፅ እውቀት የሌላቸው መሆኑን ያሳያል፡፡ የህግ ታራሚዎችን ለማስተዳደር በወጣው ደንብ አንቀጽ 27 ላይ በግልፅ እንደሚደነግገው፣ አሁንም ያለው አሰራር እንደሚያሳየው፣ ማንኛውም የህግ ታራሚ ወደ ማረሚያ ቤት በሚገባበት ጊዜ የማረሚያ ቤቱ የስነስርአት ደንቦች በቃልና ግልፅ በሆነ ቦታ ሁሉም ታራሚ በሚመለከተው ሁኔታ የማስቀመጥና በዝርዝር የሚገለፅበት አሰራር አለ፡፡ አቶ አሥራት ግን በማረሚያ ቤቱ ጥበቃ የተደረገላቸውን መረጃ የማግኘት መብት በማጥላላት፣ምንም ዓይነት የተፃፈ ህግ የለም በሚል ያቀረቡት አስተያየት በማረሚያ ቤቱ ውስጥ ያለውን አሰራር የማያመለክት ከመሆኑም በላይ የህግ ታራሚዎችም መመሪያው በሚፈቅደው የዝውውር፣ የአመክሮ፣ የቅበላና የድልደላ መመሪያዎች እየተዳደሩ የሚገኙ ሲሆን ይህም ጉዳይ በአፋጣኝ ታርሞ የሚቀርብ ቢሆን፣
3ኛ/ ህገ-መንግስቱ ላይ ሰው በሰውነቱ ሊያገኛቸው የሚገባ ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች ተብለው በዝርዝር ተቀምጠዋል፡፡
ሰብአዊ መብት ተብለው ከተቀመጡትም የመናገር፣ የመፃፍ፣ የማንበብና የመማር ወ.ዘ.ተ ይገኙበታል፡፡ ይሁን እንጂ አቶ አስራት ጣሴ የካቲት 15 ቀን 2006 ዓ.ም በወጣው አዲስ አድማስ እትም ላይ ለህግ ታራሚዎች የግል ጋዜጦችና መፅሔቶች ያለመግባታቸውን ሰብዓዊ መብትን እንደመጣስ ይቆጠራል ብለዋል፡፡ (ገፅ 14)
እርግጥም የማንበብን መብት መንፈግ ሰብዓዊ መብት እንደመጣስ የሚቆጠር ቢሆንም ማረሚያ ቤቶች ባለው ደንብና መመሪያ መሰረት ታራሚዎችን ሲያስተዳድሩ ስነ-ፅሁፎች፣ ጋዜጦችና መፅሄቶች እንዳይገቡ የሚከለክል ሳይሆን የእርምት ሂደቱ ላይ አሉታዊ ጫና የሚያሳድርና በታራሚዎች መካከል ጤናማ ግንኙነት የሚያበላሽ መሆን ስለማይገባው፣ ወሲብ ቀስቃሽ የሆኑና ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን የሚፃረሩ ይዘት ያላቸው መፅሄቶች፣ መፅሀፎችና ጋዜጦች እንዳይገቡ ይደረጋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ወንጀል ሰርታችኋል ተብለው በፍርድ ቤት የተወሰነባቸው በእርምት ላይ የሚገኙ የህግ ታራሚዎች፣ ለእርምታቸው መሰናክልን ሊፈጥሩ ይችላሉ ተብለው የታመነባቸው ጋዜጦችና መፅሔቶች እንደየአስፈላጊነቱ የማይገቡ ቢሆንም በአጠቃላይ መፅሀፎች እንዳይገቡ አልተከለከለም፡፡
ይህ ደግሞ ሰብዓዊ መብትን መጣስ ሳይሆን ወንጀለኛ ተብሎ የተፈረደበት የህግ ታራሚን ተመልሶ ወደ ጥፋት እንዳይገባ ለማድረግ እንደሆነና የማንበብ መብቱን ለመንፈግ እንዳልሆነ አንባቢያን እንዲረዱ እንፈልጋለን፡፡ ምክንያቱም የማንበብ መብታቸው ቢነፈግ ኖሮ፣ የተለያዩ መፃህፍቶችና መማሪያ ፅሁፎች እንዲሁም ለማረም ማነፅ የሚያግዙ በራሪ ፅሁፎች ወደ ማረሚያ ቤት ባልገቡ ነበር፡፡ ከዚህም አልፎ ተርፎ በማረሚያ ቤት ውስጥ ቤተ-መፃህፍት ማቋቋም ባላስፈለገ ነበር፡፡
በአጠቃላይ አስተያየት ሰጭው ተራ የፖለቲካ ተወዳጅነትን ለማትረፍና ህግ ታራሚዎች ላይ የፖለቲካ ቅስቀሳ ለማድረግ የተጠቀሙት መንገድ እንጂ በቂ መረጃና ደጋፊ መገለጫ ችግሮችን አንስተው ህብረተሰቡን ወይም ማረሚያ ቤቱንም ለለውጥ ትግሉ አጋዥ የሚሆን አስተያየት እንዳልሰጡ ተገንዝበናል፡፡ ግለሰቡ በእውቀት ላይ የተመሰረተ አስተያየት ባለመስጠታቸውና ዘለፋና አሉባልታ ላይ በማተኮራቸው ሊታረሙና ለሰጡትም አስተያየት አንባብያንን ይቅርታ ሊጠይቁ ይገባቸዋል፡፡  
የፌደራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር

Read 2100 times