Tuesday, 04 March 2014 11:24

አንድ ሌሊት በማንዴላ እልፍኝ

Written by 
Rate this item
(2 votes)

ወጪት ሰባሪው ኮለምበስና…

ግዞተኛው ኔግሮ የባቢሎን ሰማይ ጨለማ የዋጠው፤
አንድ የካቲት ማለዳ የያማካን ጦማር ሻጭ ወሬ ቢጠይቀው፤
በLe petit ፊት ገጽ ጠሀይቱ ወጥታለች
ከአድዋ ድሏ ጋር ከሚያንፀባርቀው፤
ከአለም ጥቁር ህዝቦች የግፍን እግር ብረት ላንዴው ካወለቀው፡፡
                /ውዳሴ አድዋ - ያልታተመ/
ታህሳስ 6 2006 ዓ.ም - ራስ ሆቴል፡፡
ሁለተኛ ፎቅ ላይ በሚገኘውና በኔልሰን ማንዴላ ስም በተሰየመው ኮሪደር  (Nelson Mandela Floor) የማስታወሻ ፎቶ እየተነሳን ነው፡፡  እርጋታ የሚስተዋልበት የአፍሪቃዊው የነፃነት ታጋይ  ፎቶ፤ በእስራት ዘመናቸው የቁፋሮ የጉልበት ስራ ወቅት  በተሰገሰጉ የአቧራ ብናኞች  በሞጨሞጩ አይኖቻቸው በትዝብት የሚያስተውሉ ይመስላል፡፡ የምስሉ ትልቅነት ደግሞ ራሳቸው ግዘፍ ነስተው መሀላችን የተገኙ ያህል ይሰማል፡፡ ወደ ዋናው ሳሎን ገብተን ዋንጫችንን ስናነሳ፤ታናሽ ወንድማችን የምሽቱ ዲጄ ደረጄ የሚያጫውተው የሮበርት ኔስታ ማርሌይ ሬጌ ዜማ Africa Unite ይላል፤ If you know your history from where you came…
ከግማሽ ምዕተ አመት በፊት፤እኛ ዛሬ የወይን ብርጭቆ በምናጋጭበትና ታሪካዊ አሻራው በቋሚ ቅርስነት በክብር በተጠበቀው በዚህ ክፍል ውስጥ፤እርሳቸው፤ በሰፊው ልባቸው ውስጥ የታላቁ ራዕያቸውን ወይን እየጠመቁ፤ በያንዳንዱ ሌሊት ስለ አፍሪቃ መፃኢ ዕድል ምን ምን እያውጠነጠኑ አድረው ይሆን? ግድ ሆኖባቸው፤ ከሰላማዊው ትግል ወደ ትጥቁ ትግል ለማምራት፤ጭቆና ያንገፈገፈው የደቡብ አፍሪቃ ህዝብ በየታዛው ስር ከሚያወድስላቸው የሽምቅ ውጊያ መሪነታቸው የተሻለ የውትድርና ስልጠናቸውን አጠናቅቀው፤የእፎይታ አየር እየተነፈሱ ከሰነበቱበት ከዚህ ባለአራት ክፍል የእንግዳ ማረፊያቸው፤ምስራቃዊ የገነት ነፋስ ከሚነፍስባት የአቢሲኒያ ምድር ተሰናብተው በሄዱ ማግስት ነበር፤ 27 አመታትን  በማቀቁባት የሮቢን ደሴት ጠባቧ እስር ቤት ውስጥ የተከረቸመባቸው፡፡ እርግጥ ነው፤ የወህኒውን የደንጊያ መቃብር በትዕግስትና ፅናት ፈንቅለው የነፃነትን ትንሳኤ እንደዋጁት ሁሉ፤ኖረው፤የአፍሪቃዊያን ህብረት እውን ሆኖ አይተው ማለፈቸው ሀዘናቸውን ይከላል፡፡
ማዲባ ወደ ኢትዮጵያ ባይመጡ ኖሮ፤የቀብር ስርአታቸው በተፈፀመባት እለት በዚህች ሌሊት፤ መንፈሳቸው ባረበበበት እልፍኛቸው ውስጥ ታድመን በትውስታ ባልዘከርናቸውም ነበር፡፡ ከመሳሳት የተወለደ ‹‹ምነው ተመልሰው ባልሄዱ ኖሮ ?›› የሚል ሞኝ ምኞት ሽው ማለቱ አይቀርም፡፡ መስቀሉን ይሸከሙ፡ ይቸነከሩ ዘንድ ግድ ነበራ፡፡ ተመልሰው እንደ መሄዳቸውም መምጣታቸውም ግድ ነበር፡፡ይህቺ ምድር፤ በዘመናት መሀል እረፍትን የሚሹ፣ መፍትኄን የናፈቁ፣ ነፃነትን የተጠሙ፣ ፍትህን የቃተቱ ሁሉ የክፉ ጊዜ መሸሸጊ ናትና፡፡ አምላከ አማልዕክቱ ዜዩስ በመብረቅ አክናፉ ከኦሊምፐስ ተራራ ከንፎ እፎይ የሚልባት፤ነቢዩ ሙሴ (ወደ አዜብ ምድር) የተመላለሰባት፤እየሱስ በድንግል እናቱ በእምዬ ማሪያም እቅፍ ሆኖ ከንጉሥ ሄሮድስ የሸሸባት፤የነቢዩ መሀመድ ሰሎላ ወአለ ወሰለም ተከታዮች አርሂቡ ተብለው በሰላም ያረፉባት…
ቦብ ማርሌይ If you know your history from where you came…‹‹የታሪክህን ዳና ተከትለህ የእትብት ቀዬህን ብታውቅ›› ሲል ያቀነቀነው፤ በመግቢያችን ላይ ባነበብነው ዘለግ ካለ ግጥም የተቀነጨቡ ስንኞች መሀል፤በጨለማው የባቢሎን ሰማይ ስር ሲንከላወሱ ለኖሩት አፍሪቃዊያን ወንድሞቻችን ነበር፡፡ እኒያ በግፍ እግር ብረት የተጠፈነጉ መከረኞች፤ለዚያ አይነት የዘቀጠ ህይወት የዳረጋቸውን፣ ስብዕናቸውን ያዋረደውን የቅኝ ግዛትና የዘር መድልዎ ካቴና ለመበጣጠስ፤ የኔልሰን ማንዴላንና መስል ጸረ ዘረኝነትን አቋም የሚያራምዱ አብዮተኞችን መፈጠር ግድ ያለበትን የታሪክ ድርሳን እየመዘዝኩ ስቆዝም፤ ከአምስት መቶ አመታት በፊት የተከሰተችውን፤ ለረጅሙ የጥቁር ህዝቦች ጭቆናና የጨለማ ዘመን መነሾዋን፤ ያቺን ክፉ ምሽት አውጠነጥን ነበር፡፡ እነሆ…
1494  እ.ኤ.አ - ያማካ ደሴት፡፡
በሰው ዘር ታሪክ ውስጥ ውድቀት መሰስ ያለው፤በኤደን ገነት አፀድ በየዋህነት ይኖሩ የነበሩትን አዳምና ሄዋንን፤ በእባብ የተመሰለው ሌባው፣ አታላዩ፣ ውሸታሙ ሰይጣን ዲያቢሎስ፤ በሀሰት አቀራረብ ወዳጅ መስሎ በረቀቀ ሴራ ሲያጭበረብራቸውና እነርሱም በምስኪንነት ተታልለው አጥፊ ሀሳቡን በማመናቸው ነበር፡፡
ያማካ Xyamaca የአሜሪካ ኢንዲያን ጎሳዎቹ አራዋክስ በሰላም የሚኖሩባት ደሴት ነበረች፤ኮለምበስና ተከታዮቹ ድንበራቸውን ጥሰው እስከመጡባቸው እስከዚያች ምሽት ድረስ፡፡ ምናልባትም ያ ጊዜ በአውሮጳዊያኑና አራዋክሱ መካከል የተደረገ በታሪክ የመጀመሪያው ግንኙነት ነው፡፡ አሳሹ ኮለምበስ በመርከቡ የሰነቀው የጉዞ ማዕድ ተሟጥጦ፤ የሚቀምሱት ምናምኒት አልነበራቸውም፡፡  ተከታዮቹ ጠኔ ሆድ ባባሰው አመፅ ውስጥ እንደ አውሬ በተፋጠጡበት መአልት፤ዕድል እየመራ ከዚያች የተዋበች ለምለም ደሴት አደረሳቸው፡፡ ሀራዋኮቹ፤  ከተፈጠሩ አይተውት በማያውቁት ጋጠወጥ አቀራረባቸው ኮለምበስና ተከታዮቹን ተጠይፈዋቸው፤ እፍኝ ታህልም ላይሰፍሩላቸው ወስነው ፊት ነሷቸው፡፡ ያኔ ነው እንግዲህ ክርስቶፈር ኮለምበስ፤ የረቀቀ የሴራ መረቡን በላያቸው የጣለውና ኢንዲያኖቹ ተገድደው የሚፈልገውን እንዲያደርጉ ያጠመዳቸው፡፡
ኮለምበስ፤ በዚያ ምሽት የጨረቃ ግርዶሽ እንደሚኖር አስታወሰ፡፡ ለምስኪን ሀራዋኮቹም፤ አሁኑኑ ምግብና መጠጥ ካላቀረቡለት፤ አምላኩ ተቆጥቶ የጨረቃዋን ብርሃን አንደሚያጠፋባቸው አስጠነቀቃቸው፡፡ ሀራዋኮቹ፤ እንኳን የእንግዳው ሰው ነጭነት ተጨምሮበት ለአጉል አምልኮ የሚብረከረኩ ቢሆኑም በእምቢተኝነታቸው ፀኑ፡፡ ምሽቱ እየገፋ ሲመጣ ግን እውነትም ሰማዩ ደበዘዘ፡፡ ጨለመ፡፡ በሀራዋኮቹ ዘንድ ጥልቅ ፍርሀት ነገሰ፡፡ ወዲያውም በጭንቀት እየተደነባበሩ፤ በትልልቅ የሸክላ ሰታቴ ድስቶችና ዋዲያቶች ሙሉ ምግብና መጠጦችን በደሴቲቱ ዙሪያ ከሚበቅሉ አትክልቶች፣ ፍራፍሬዎች እና የተጠበሱ የአሳማ ስጋና አሶች ጋ ጢም አድርገው አስታቀፏቸው፡፡ የሰማይ ላይ ግርዶሹ እንዳመጣጡ ጨረቃዋን አልፎ ሲሄድ፤መርከቡን በምግብና መጠጥ የጠቀጠቀው ኮለምበስም፤ በስጋት ተወጥረው ኋላ ኋላው ሱክ ሱክ እያሉ የሚሸኙትን በድንጋጤ የተንጰረጰሩ ምስኪን ሀራዋኮች በሰይጣናዊ ፈገግታው እያማተረ ወደፊቱ ቀዘፈ፡፡
ኮለምበስ ከመጣ ጥቂት አመታት በኋላ ታዲያ፤ ስፔንያርዶቹ፤ በሁለት ጎኑ የተሞረደ ስለታም ገጀራቸውን እያፋጩና እያፏጩ መጡአ! ወደ ድንግሏ ያማካ፡፡
ሀራዋኮቹ፤ደሴታቸውን ያማካ Xyamaca ብለው የጠሯት፤ለውሃማና የልምላሜ ምድርነቷ ውዳሴ ነበር፡፡  Xyamaca – the land of wood and water. አመቱን ሙሉ ውሃ ያጋቱ ፏፏቴዎች፣ ምንጮችና የማይደርቁ ወንዞች፤ የጥጥ ጫካዎች፣ በማሆጋኒ፣ አዋንጎ፣ ማሮኢና ካስያ ዛፎች የተቸመቸሙ ጥቅጥቅ ደኖች፡፡
ስፔንያርዶች፤ ጃማይካን Xyamaca ወርረው በቅኝ ግዛት ስር ካዋሉ በኋላ ቀስስስስ እያሉ የሀራዋኮቹን ዝርያ አርደው ጨረሷቸው፡፡ ከዚያስ? ከዚያማ በግዙፍ መርከቦች እያጨቁ በሚዘረግፏቸው ጥቁሮች ደሴቲቱን አጥለቀለቋታ፡፡ ሰዎቹ ተማርከው የሚወሰዱት ከእኛዋ አኅጉር ከምዕራብ አፍሪካ ሲሆን፤ እዚያ ከደረሱ በኋላም በሸንኮራ አገዳ ማሳ  ስራ ተጠምደው በባርነት የሚያገለግሉ የዕድሜ ልክ ግዞተኞች ይሆናሉ፡፡ ባሮቹ የማያከናውኑት ተግባር አልነበረም፡፡ ሴቶቹ ለጌቶቻቸውና ለባሪያ አለቆቹ የወሲብ ጥማት መርኪያነትም ይውላሉ፡፡ ቢሆንም ግን፤ የሴቷ ሆነ የወንዱ፣ የህፃናቱም፣ የወጣቱም፣ ሰየሽማግሌውም የአሮጊቱም፣ ብቻ የመላው አፍሪቃዊያን ባሮች የሰውነት ክብራቸው መጠን መገለጫው ከእንስሳነት መሳ  የሆነ፤ በሚተነፍሱ ግዑዛን ፤በሚናገሩ እቃዎች ወይም በተንቀሳቃሽ ፍጡራንነት ደረጃ የተቀነበበ ሆኖ ቀረ፡፡
ስፔንያርዶች እስከ 1665 ድረስ ገዟት፡፡ እንግሊዛዊያን በተራቸው መጡ፡፡ ስፔንያርዶቹንና ከእነርሱ ጋር ሆነው ለመዋጋት የሞከሩትን ባሮች፤ አፍንጫው ድረስ በታጠቀው የጦር ኃይላቸው ብርቱ ክንድ እየደቆሱ አሽመደመዷቸው፡፡ ወደ ኩባም አስፈረጠጧቸው፡፡ ደሴቷ በእንግሊዛዊያኑ መዳፍ ውስጥ ገባች፡፡ የታላቋ ብሪታኒያ ንግስት ኤልሳቤጥ ቀዳማዊት፤‹‹ዌስት ኢንዲያ የባሪያ ንግድ ኩባንያ››ዋን በይፋ አቋቋመች፡፡ ከዚያማ ምኑ ይነገራል? ከአፍሪቃ ምድር ተግበስብሰው ታድነው በትልልቅ መርከቦች እየተጠቀጠቁ ወደ ብሪትሽ ዌስት ኢንዲስ የሚጋዙ ብዛታቸው ለቁጥር የሚታክት ባሮች እንደማይነጥፍ ዥረት እየተግተለተሉ በመንጋ ሲነዱ ‹‹ይብቃ!›› የሚል ጠፍቶ፤ እልፍ አዕላፍ እስኪደርሱ አራት መቶ አመታት ነጎዱ፡፡
አፍሪቃዊያን ወንድሞቻችን ለባርነት በገፍ ሲጋዙ፤ በገዛ ምድራቸው ላይ በቁጥጥር ስር ከሚውሉበት መንገድ አንዱን፣ የቀንደኛውንና ምስጉን የባሪያ አዳኝ ‹‹ዠግናውን›› ስልት እንይ…ሀውኪን!
የሀውኪን የባሪያ አደን ከሌሎች የተለየና ላቅ ያለ ነው ተብሎ የሚደነቅለት፤ቆፍጣና፣ ኮስታራ፣ ጭካኔ የተሞላበትና ‹‹በባሪያ ምርቱ›› የተትረፈረፈ ውጤት ማስገኘቱ ነበር፡፡ በድንገት ባንድ ሰላማዊ የአፍሪካ መንደር ላይ ታጣቂዎቹን አሰማርቶ ጥቁሮቹን ያስከብባቸዋል፡፡ በዚህ ከበባ ቀለበት ውስጥ የገቡ ሁሉ በሰልፍ እርስ በእርስ ተያይዘው ወደ መርከቡ እንዲደርሱ በተዘጋጀላቸው በእጅ፣ እግር ወይም ባንገት የሚጠልቅ ብረት ሰንሰለት ተቆላልፎ መነዳት ብቻ ነው፡፡ ወደ መርከብ ከመግባትም ሆነ በመርከቡ ውስጥ የምድር ቤትና ተደራራቢ ፎቆች ወለል ላይ ተፋፍገው ከሚጫኑበት ውልፍት ለማለት የሞከረ ደመ ከልብ ይሆናል፡፡ በቃ! በዚሁም አሰቃቂ የጭካኔ ተግባሩ ሀውኪን በከፍተኛ ክብርና ሙገሳ ሲምነሸነሽ ኖሯል፡፡ የሰርነትን ማዕረግ ጨምሮ፡፡ Sir John Hawkins.
በሚሊዮን የሚቆጠሩ አፍሪቃዊያን ወንድሞቻችንን እትብታቸው ከተቀበረበት ምድራቸው ወደ ጃማይካ ሲያጓጉዙ ከኖሩት መርከቦች ሁለቱ እጅግ ግዙፎቹ ኤስ ኤስ ዞንግ እና ኤስ ኤስ ይባላሉ፡፡ በተለይ ሀገር የሚያህል ስፋት ባለው ሆዱ አፍሪቃዊያኑን የቂጣቸው ጫፍ ብቻ ወለል እንዲስም ተደርጎ፣ በአየር ላይ የማንጠላጠል ያህል እንደ ጡብ ሰካክቶ አጭቆ በመውሰድ ጉልህ ድርሻ የነበረው ኤስ ኤስ በጎኑ ላይ በትልቁ የተፃፈ ጽሁፍ ነበረው Jesus of Lubeck የሚል፡፡ የላቲን ቋንቋው ትርጉም ‹‹እየሱስ እስኪመጣ›› ማለት ነው፡፡ ታዲያ፤ለዘመናት ቢጠብቁ… ቢጠብቁ… እየሱስ ከየት ይምጣ? ወንጌሉ ደሞ ‹‹በነጻነት ልንኖር ክርስቶስ ነጻ አወጣን›› ይላል-ገላትያ 5-1፡፡ ስለዬህ ነበር ባሮች ወንድሞቻችን የራሳቸውን ነጻ አውጪ መሲህ ከወደ ምስራቅ ፀሀይ መውጫ ያስተውሉ ዘንድ ግድ የሆነባቸው፡፡ ራስ ተፈሪ መኮንን፤ በጥቅምት ወር 1923 ዓ.ም፡፡
የእንግሊዙን የዌልስ ልዑል ጨምሮ የአውሮጳ ንጉሣዊያን ቤተሰቦች በተገኙበት፤በአዲስ አበባ በሞአ አንበሳ ዘ እምነገደ ይሁዳ ስያሜ የንጉሰ ነገስትነት ዘውድ ደፉ፡፡ His Imperial Majesty Emperor Haile Sellassie I King of Kings, Lords of Lords, Conquering Lion of the Tribe of Judah, Lebna Denghel, Keeper of the Faith of the Dynasty of Judah, Keeper of the Faith of the Dynasty of David, and The Elect of God. ይህን ለንግስናቸው የተሰጠ ስያሜ ከመጽሐፍ ቅዱስ የትንቢት ድርሳናት ሀረጋት ጋር እያመሳከሩና እያስተነተኑ በንጉሱ መሲህነት አምነው ተጠመቁ፡፡ በእግዚአብሄር የተቀባ፤የዳዊት ዙፋን ወራሽ፤የይሁዳ አንበሳ…
ከዚህ ክስተት መቶ አመታት አስቀድሞ፤ በነሀሴ 1 1826 ዓ.ም፤የእንግሊዝ ንግስት ቪክቶሪያ በመላው የእንግሊዝ ግዛት ያሉ ባሮችን የይስሙላ የነፃነት አዋጅ አናፍሳ፤ለካሪቢያን ደሴቶች ጥቁር አፍሪቃዊያን ካሳ የሚሆን 20 ሚሊዮን ፓውንድ ብትበጅትም፤አንድም ባሪያ ሽራፊ ድምቡሎ ሳይደርሰው የባሮቹ አለቆች ገንዘቡን ተቀራመቱት፡፡
ከዚያ በኋላ 60 አመታት አልፈው ነው፤በሞአ አንበሳ ዘ እምነገደ ይሁዳ ንጉሰ ነገስት ዘ ኢትዮጵያ ዳግማዊ አጤ ምኒልክ መሪነት፤ ክርስቲያኑም እስላሙም፤ አራሹም ተኳሹም፤ ወንዱም ሴቱም፤ወጣቱ አዛውንቱ፤ ሀገር ከዳር ዳር ነቅሎ በዘመተበት ጦርነት ኢትዮጵያ የተቀዳጀችው የጥቁር በነጭ ላይ የድል ብስራት ዜና ከአፅናፍ አፅናፍ ያስተጋባው፡፡ በፈረንሳይኛ ቋንቋ የሚታተመው Le petit ጋዜጣ  የአድዋን ድል ከእቴጌ ጣይቱ ደርባባ ምስል ጋ በፊት ገጹ ይዞ ሲወጣ፤ በባርነት ቀንበር ስር በነበሩ በመላው አለም ጥቁር ህዝቦች ልብ ውስጥ ተስፋ ናኘ፡፡ የአርነት ጎህ ቀደደ፡፡ ጨለማው በራ፡፡ ጥቁር ህዝብ ሁሉ ‹‹ለካ ይቻላል!›› አለ፡፡የጨካኝ ነጭ ጌቶቹን ጉሮሮ ማነቅ ጀመረ፡፡ እነሆ ከኢትዮጵያ አብራክ ፍትህ ፈለቀ፡፡
ከአድዋ ድል 40 አመታት ቆይቶ፤ቀዳማዊ ኃይለ ስላሴ፤ በብፁዕነታቸው አቡነ ባሲሊዮስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ፓትርያርክ ቅዱስ ቡራኬ እንደነገሱት ሁሉ፤ ከ5 አመታት በኋላ ደግሞ፤ ጣሊያንን ከመልቀቃቸው በፊት ለጥፋት ዘመቻቸው ስኬት በሮማ ካቶሊክ የእምነት አባቶች እኩይ ቡራኬ የተሸኙት፤በአምባገነኑ ቤኒቶ ሙሶሎኒ ትዕዛዝ፤ በማርሻል ባዶሊዮ የሚመሩት የጣሊያን ወታደሮች ኢትዮጵያን ወረሩ፡፡ ይህም በምድር ዙሪያ ያሉ ጥቁሮችን ቁጣ ቀሰቀሰ፡፡ ‹‹የተስፋ ምድራችንን አትንኩ!››…ንጉሠ ነገስቱ ለመንግስታቱ ጉባኤ ያደረጉትን ‹‹በዛሬው ጊዜ ታላላቅ ሀገሮች አንኳን የራሳቸውን እድል ለመወሰን አይችሉም፡፡ የሁላችንም እድል ያው አንድ ነው፤ወይ መጥፋት ወይ መዳን፡፡ እድል ስናገኝ ጊዜ ሳያልፍ የሚቻለንን ሁሉ እናድርግ። ደስ የማይል እርምጃ ከመውሰድ እንዳን። …የመጀመሪያውን እሳት የሚለኩሰው ማን እንደሆን ይታወቃልን?...››  ንግግራቸውን ተከትሎ፤ በተለይ አውሮጳዊያኑን እርስ በርስ ያስተላለቀው ሁለተኛው የአለም  ጦርነት መጣና አረፈዋ፡፡ ያን ጊዜ፤ A Nation without the knowledge of its past history is like a tree without its root. ‹‹ያለፈ ታሪኩን የማያውቅ ህዝብ፤ ሥር እንደሌለው ዛፍ ነው›› በሚል መርሁ የሚታወቀው የህዝቦች ንቅናቄ መሪው ማርከስ ጋርቬይ ተከታዮች Garveyites ‹‹ይኸዋ!ትንቢቱ ደረሰ! መሲሁን አልሰማ ብለው ጉድ ሆኑ!›› እያሉ፤ የኢትዮጵያዊውን ንጉስ ወንጌል አስፋፉ፡፡That H.I.M Emperor Haile Sellassie I of Ethiopia is the returned Messiah, the God Head, the Ancient of Days. የንጉሱ የጃማይካ ጉብኝትና ድንገቴ ግጥምጥሞሾች ሁሉ ደግሞ ጉዳዩን ሰማይ አስነካው፡፡ በራሳቸው በንጉሰ ነገስቱ ‹‹እኛ አምላክ አይደለንም!›› ብለው እንዲሰብኩ የተላኩ ሀበሻ ካህን በራስ ተፈሪያኑ ተሰብከው፣ አምነው፣ ተጠምቀው እስኪቀሩ፡፡ እንደእምነታችሁ ይሁንላችሁ ተብለው መጥተው ለኢትዮጵያ (ሻሸመኔ) ምድር እንደበቁትም፤ ጋርቬይ ይዞት የተነሳው  One God,One aim  and One Destiny  መሪ ቃል፤  መላው ጥቁር ህዝብ ነገውንና ዘላለሙንም በተስፋይቱ ምድር በኢትዮጵያ ላይ እንዲያንተርስ አደረገው፡፡ ዝማሬዎች ሁሉ የኢትዮጵያን ምድር መቀኘት ጀመሩ፡፡ የኖህን ቃል ኪዳን  አርማ የቀስተ ደመና ቀለማት ሰንደቅ የሚያውለበልቡ ስንኞች ተዥጎደጎዱ…
Ethiopia, the land of our fathers;
The land where all Gods love to be,
As swift bees to hive suddenly gathers;
So thy children come rushing to thee.
With red, yellow , and green floating ‘oer us,
And our emperor to shield us from wrong.
With our God and our future before us;
We hail thee with shouts and with songs!
ዶሮ ሊጮህ ገደማ - ማዲባ እልፍኝ፤ አዲስ አበባ።
በስማቸው በተሰየመው የእንግዳ ማረፊያ ክፍል በር ላይ ከቁጥር 206 ስር Nelson Mandela Room የሚል ጽሁፍና የጎልማሳነታቸው ፎቶ ተለጥፏል። በፎቶው ላይ የነፃነት ታጋዩን የሰውነት አቋም ያየ ሰው፤ ለቦክስ ስፖርት የነበራቸውን ፍቅር ማስታወሱ አይቀርም፡፡ በሙሉ ሱፍ ሽክ ብለዋል፡፡ በዚህ እድሜያቸው ነበር ወደ ኢትዮጵያ የመጡት። እርሳቸውም እንደአብዛኛው የአለም ጥቁር ህዝቦች ሁሉ ስለ ኢትዮጵያ የነበራቸው ላቅ ያለ ክብር በመለኮታዊ እምነት የታሸ እንደነበር በእድሜያቸው አመሻሽ ላይ በከተቡት Long Walk To Freedom መጽሀፋቸው ገጾች  ውስጥ ሰፍሮ ይገኛል፡፡
ማዲባ፤በነጮች ጫማ ስር ከመረገጥ ነፃ የመውጣትን አላማ አንግበው ወደ ሀገራችን በመጡ ጊዜ የነበራቸውን ትዝታ የተረኩት፤‹‹ጥቁር ሰው ክብር ያገኘባትን ምድር ለመጀመሪያ ጊዜ ማየታቸውን›› በመጥቀስ ነበር፡፡ ተሳፍረው የመጡበት የኢትዮጵያ አየር መንገድ አይሮፕላን አብራሪ ካፒቴን ጥቁር በመሆኑ በእጅጉ ስለመገረማቸውና መልሰው ‹‹ግን ለምንድር ነው የሚገርመኝ?›› ስለማለታቸው፡፡ ለዚህ መሰል ደካማ አስተሳሰብ ምርኮኛ ያደረጋቸውን አፓርታይድን በውስጣቸው መኮነናቸውን፡፡ ውለው ሲያድሩ ደግሞ ጥቁር ጄኔራሎችን አዩና አፋቸውን ያዙ፡፡ ‹‹እኛም አንድ ቀን እንዲህ እንሆናለን›› ሲሉም ተመኙ፡፡ ኢትዮጵያን በቀደምት መጠሪያዋ ‹‹አቢሲኒያ›› ብለው እየጠሩ፤ከንግስት ሳባና ጠቢቡ ሰለሞን በልጃቸው ቀዳማዊ ምኒልክ በኩል የሚመዘዘውን ሰለሞናዊ ስርወ መንግስት ወራሽ ንጉሰ ነገስት ቀዳማዊ ኃይለ ስላሴን ሲገናኙ፤ ‹‹እነሆ ከይሁዳው አንበሳ ጋር ተገናኘሁ!›› ሲሉ ተአምራትነቱን ይመሰክራሉ። በዕድሜ ዘመናቸው በየትኛውም አለም ካደረጉት ጉብኝት ሁሉ የኢትዮጵያን ምድር መርገጣቸውን እጅግ ላቅ ያለ ስፍራ ይሰጡታል፡፡ ‹‹ምድሪቱ፤ ያለማቋረጥ ወረራ የተፈፀመባትና ግን ለአንዲትም ጊዜ እንኳ በቅኝ ግዛት ስር ያልተንበረከከች፤የነፃነት ቀንዲል፣ የአፍሪቃዊያን እምብርት፣ ሉዐላዊት ሀገር ናት፡፡››ይላሉ፡፡ ምስክርነታቸው በአዛውንትነት ዕድሜ የተሰጠ መሆኑ የሚያመለክተውም ፤ንፅፅሩ፤ኃያላን ሀገራቱን ጨምሮ በአለም ዙሪያ በመቶ የሚቆጠሩ ዶክትሬት ዲግሪዎችንና ሽልማት መአት ያንበሻበሿሰቸውንም ሁሉ ሚዛን ደፍቶባቸው መሆኑን ነው፡፡ ጉዳዩ የነፃነት ጥያቄ ነዋ!
ያኔ ጥቁር አፍሪቃዊያን እንደ ከብት ሲነዱ ለ400 አመታት አላየንም አልሰማንም ብለው፤እንደ መለኮታዊ ቁጣ እነርሱው በጫሩት እሳት ውርጅብኝ ሀምሳ ሚሊዮን ዜጎቻቸውን ባረገፈው የሁለተኛው አለም (የእርስ በርስ) ጦርነታቸው ብድራታቸውን ዋጥ ያደረጓትን ሀገራትንም ያጠይቃል የማንዴላ ሩህ፡፡ ከ500 አመታት በፊት የአሳሽነት እቅዱ እንዲሳካ ምርኩዝ (ስፖንሰር) ለሆኑት ለስፔኑ ንጉስና ለሚስቱ ለንግስት ሳቤላ ሀራዋኮችን በገፀ በረከትነት አሳልፎ ከሰጠው፤ ከበላበትን ወጪት ሰባሪው ኮለምበስ የክህደት ተግባሩና መዘዙ ተምረው ተፀፅተው ይሆን እውነት? እላለሁ፤ ተሲያት ላይ እርሳቸው በተወለዱባት በትንሷ ኩኑ መንደራቸው፣ አስከሬናቸው በሰላም በሚያርፍ ጊዜ፤ ለቴአትር ትወና ቆሜበት በነበረው የቀዳማዊ ኃይለ ስላሴ (የኢትዮጵያ ብሔራዊ) ቴአትር ቤት መድረክ ላይ ካከናወንነው የቀለበት ስነ ስርአት መልስ፤የጫጉላ ምሽታችንን ለማሳለፍ በተከራየነው፤ማንዴላ ልክ ከ55 አመታት በፊት በዚሁ በታህሳስ ወር 1961 ዓ.ም በእንግድነት መጥተው ባረፉበት በአፍሪቃ መዲና፤በሉአላዊቷ፤የነጻነት አርማዋ፤የእምዬ ኢትዮጵያ ምድር ዋና ከተማ፤መሀል አዲስ አበባ ፤ራስ ሆቴል፤ ሁለተኛ (ማንዴላ) ፎቅ፤  መኝታ ክፍል ቁጥር 206 የማንዴላ እልፍኝ ውስጥ፡፡ ወዳጆቼና ቤተሰቦቼ ዘና ባለ ስሜት ውስጥ ናቸው፡፡  የምሽቱ የዜማ ዘዋሪያችን፤ ዶሮ ሳይጮህ፤ ድምፃዊው ስቲቪ ወንደር ለታታ ማንዴላ ያበረከተላቸውን I just called to say I love you ዜማ እንዲጋብዘን ልጠይቀው አሰብኩ፡፡ ላሁኑ ግን የእልፍኙን ድባብ ሬጌ ሙዚቃ ሞልቶታል…Babylon is falling , Ethiopia she is calling ይላል፡፡ ሙሽራዬና የበኩር ልጃችን በግራና ቀኝ ጎኔ በኩል ተደግፈውኛል፡፡ በዛሬው እለት በአ.አ ስብሰባ ማዕከል በተመረቀውና ሶስታችንም በትረካ በተካፈልንበት የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ትርጉም ፊልም ውስጥ ስለ ኃጢዐት ምግባር እንዲህ የሚል ዐረፍተ ነገር አለ…‹‹ሽብር ሲነዛ ክፋት ሲያውጅ ጊዜ የሰጠው ሹመኛ፤ሰለባ ይሆናል ቀሪው የፍርሀቱ ምርኮኛ!››… ወደ ባቢሎናዊያኑ ሙግት ላንዴ መለስ አልኩ…
አዎን! በፈጠረችው የባቢሎን ምድር የባሪያ ንግድን ያለ እረፍት ስታጧጡፍ የኖረችው እንግሊዝ፤ ዛሬ በከተማዋ አደባባይ ለኔልሰን ማንዴላ ሀውልት ያቆመችው እውን የነፃነት ታጋዩን ህልምና ራዕይ የምትጋራ ሆና ነውን? በነፃነት ታጋዩ ህልፈት ሰሞን ማዲባን በክብር ተሰናብቶ ለመሸኘት ከአለም ዙሪያ የተሰባሰቡት የየሀገራቱ ክቡራን መሪዎች ሁሉስ? እንቅልፍ አጥተው ውብ ቃላቶችን አርቅቀው ሆድ የሚያባቡ ንግግሮችን የቀሸሩት፤ የየሀገራቸውን ሰንደቅ ዝቅ አድርገው ያውለበለቡት፤ ብሔራዊ የሀዘን መግለጫዎችን ያወጁ፤ለሰውየው ራዕይ ከሆነ እንዲያ የባጁ፤ መልካም…ገብቶናል ካሉ…ዛዲያ ዛሬም ድረስ  እየታደኑ ወደ ማጎሪያ ጣቢያ የሚዶሉትን ጂፕሲዎች ለምን ነፃ አያደርጓቸውም? በመላው አለም በተለይም በአውሮጳ ምድር የተንሰራፋው በጥቁር ህዝቦች ላይ ያነጣጠረ የአድልዎና ማግለል Xenophobia ምግባራቸውስ? በምድሪቱ ዙሪያ ዳግም እየተቆሰቆሰ ያለው የፀረ - ጽዮናዊነት ጉዳይስ?....ወዘተ፤ ሌሎችም…!?አባባ ጃንሆይም፤በሊግ ኦፍ ኔሽን መድረክ ቆመው ለመንግስታቱ ጉባኤ መሪዎችና ታዳሚዎች ይህንኑ ነበር ያሉት...
‹‹...በአንድ ሀገር ውስጥ አንደኛና ሁለተኛ ዜጋ የሚባለው ነገር  እስካልተወገደ፤ሁላችንም የምንደክምለት የአለም ሰላም ጉዳይ ዋጋ ቢስና ከንቱ ሆኖ እንዳይቀር ያሰጋናል . . .፡፡››
ኔልስን ማንዴላ የታገሉት ለጥቁር ወይም ለነጭ የበላይነት አይደለም፡፡ በፍፁም! ለመላው የሰው ዘር እኩልነት እንጂ!ይኼ የዘር ነቀርሳ ሰንኮፉ የሚነቀልበት ዘላቂ መፍትኄ እስካልተገኘ ድረስ ፤ በማንኛውም ጊዜ፤ በየትኛውም ስፍራ ፤ የሰው ልጆች ሁሉ እኩልነትና ሰብአዊ መብት እንዲከበር ትግሉ ይቀጥላል! ሀኩና ማታታ!

Read 3303 times