Tuesday, 04 March 2014 11:21

የገንዘብ ቀለማት!

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

“ገንዘብ ንጉሥም ሎሌም ያደርግሃል”

ሲጀመር
የልጆች የአስተሳሰብ  ነፃነት መቼም ያስቀናል። እኛ ትልልቆቹ በማህበራዊ፣ ሀይማኖታዊ፣ ዘልማዳዊ ፣ መንግስታዊ ፣ ምናምናዊ--- ወጥመዶች አስተሳሰባችንን ከማሰራችን በፊት ያለውን ንፅህና ማለቴ ነው፡፡ ይህንኑ ባርነታችንን እንደሚረባ ውርስ፣ ሲለን በሽንገላ ሳይለን በቁጣ፣ አሳልፈን ነፃነታቸውን እስክንነጥቃቸው ያለውን፡፡ የነፃነታቸው መገለጫ ደሞ ያልተገደበው ንግግራቸው ይመስለኛል፡፡ ድንገት ሲያወርዱት፣ ለእኛ ለትልልቆቹ፣ በባርነት ላለነው የአይምሮ ፈተናም የሃሳብ ፍንዳታም ነው፡፡
 አንድ ማታ እቤት እራት እየበላን ነበር።  ናታን፣ እድሜ 9፣ በትንንሽ እጆቹ የእንጀራ ቁርጥራጮች እያንገላታ “ሀብታም ብንሆን ደስ ይለኝ ነበር” አለ። ለተወሰኑ ደቂቃዎች ፀጥታ ሆነ፡፡ ሃሳብ ፈነዳ። በቀላሉ “እኔም ደስ ይለኝ ነበር” ብሎ ለመዝጋት የወላጅነት ህሊና ይፈቅድ እንደሆን እንጃ፡፡ በተቃራኒው “ገንዘብ አጋንንታዊ ነው፡፡ ባለህ መደሰት አለብህ ምናምን” ብሎም ለማለፍ፣ ለወላጅ ግልግል  ቢመስልም ፣ ህፃኑ ይቀበለዋል ወይ ብሎ ማሰብ የአባት ነው፡፡ ከእኛው ጀምሮ፣ በትምህርት ቤትም በመዝናኛም በመፅሃፍትም፣ ሁሉ ቦታ  ሰበካው ሁሉ  ገንዘብና ሀብት ነው፡፡ ለወላጅ “ገንዘብ የለኝም” ፣ “ገንዘብ ሳገኝ---” እና የመሳሰሉት ለሕፃናት የሚሰጡ የዘወትር  መልሶች ናቸው፡፡ እናማ “ባለፈው ሎተሪ ከደረሰን ዱባይ እንሄዳለን ተብያለሁ” ብሎ ቀን ሲቆጥር የነበረ ህፃን፣ ሀብታም መሆንን ቢመኝ ምኑ ይገርማል? እኔ ግን  መጠየቄ አልቀረም -
“ምን ማለት ነው ሀብታም መሆን?”
“ብዙ ብር ማግኘት”
“ምን ለማድረግ?”
“ቲቪ ለመግዛት! እነ እንትና እኮ ሀብታም ናቸው። እሱ ክፍል  ቲቪ አለው፡፡ እኔም ቲቪ እፈልጋለሁ” አለኝ ናታን፣ የአንዱን ጓደኛውን ስም እየጠራ፡፡
የተንተባተበ ነገር መልሼለት ፣ ነው ሰብኬው፣ ባለህ ብትደሰትስ ምናምን  ብዬው አለፍኩት። “ሴክስ” ምንድነው ብሎ እንዳፋጠጠኝ ቀን፣ የራሴው ቃላት ከጉሮሮዬ ተቀርቅረውብኝ፣ የፈለኩትን ሳይሆን የተባልኩትን አሳልፌ ሰጥቼው፣ የወሬውን ቻናል አስቀይሬ አረሳሳሁት፡፡
ይቆጠቁጠኝ ገባና ፣ ማሰቤን ቀጠልኩ፡፡ እንዲህ ብለውስ ኖሮ አልኩኝ…..
….የገንዘብ ሀይል ምትሃታዊ  እንጂ ጋኔላዊ አይደለም። ገንዘብ በራሱ ያሰክራል እንጂ ነፍስ አያረክስም፡፡  ገንዘብ ነፃነትንም ባርነትም አጣምሮ የያዘ ይመስለኛል፡፡ ይህን ሀይል በቅጡ መረዳት ከፈለግህ  መልሱ ያለው እውስጥህ እንጂ ከውጭ አይደለም፡፡ ገንዘብን ቀርበህም እርቀህም ማየት፣ ያየኸውንም ከውስጥህ ማስታረቅ ግድ ይልህ ይሆናል፡፡ እኔ ግን የገባኝን ልንገርህና መነሻ ከሆነህ ጥሩ፣ ከረከሰብህና የተሻለ የመሰለህን ካፈለቅህም እሰየው። ልጅ ከወላጆቹ የተሻለ ካላሰበ ፣ ወላጆች የተፈጥሮን ግዴታ ከማሟላት ያለፈ ስራ አልሰሩም ማለት አይደል?
ይኸውልህ እንግዲህ….ገንዘብ  ቁሳዊ፣  ማህበራዊና ስነልቦናዊ  ገፅታዎችን ያዘለ ነው፤  እየረቀቁ የሚሄዱ የተሳሰሩ ትርጉሞችን ያቀፈ አስገራሚ የሰው ልጅ ፈጠራ። አዎ እንደምትመገብበት ሳህን ሰው ሰራሽ ቢሆንም፣ የሰው ልጅ ሊገለገልባቸው ሰርቶ ተገልብጠው ጌታው ከሆኑበት ውልዶቹ ገንዘብ ምናልባትም ቀዳሚው ነው፡፡
ቁሳዊው ሀይሉ የሚመነጨው ገንዘብ ባንተና በምትፈልጋቸው ወይም ያስፈልጉኛል ብለህ በምታስባቸው ነገሮች መሃል ርቀትን መፍጠር በመቻሉ ነው፡፡ ገንዘብ ባልነበረበት ዘመን እንዴት ነበር ብለህ እስኪ አስብ፡፡ የሚያስፈልግህን አድነህ፣ ካልሆነ ቆፍረህ ሲልም ሁለት ሶስቱን አንድ ላይ አስረህ ትገለገላለህ። ተፈጥሮ ታቀርብልሃለች፣ አንተ ታመሰግናታለህ። ጅል ካልሆንክ በስተቀር ለማያስፈልግህ ጉልበትህን አታባክንም፡፡ የሚያስፈልግህን ውስጥህ ይነግርሃልና ሌሎች እንዲወስኑልህ አትጠብቅም፣ ምናልባትም አትፈቅድም፡፡
አሁን ነገሮች እንደዛን ዘመን ቀላል አይደሉም። ሲጀምር የሚያስፈልጉህ ነገሮች ምግብና ከወገብ በታች የምታገለድመው ብጣሽ ቅጠል አይደለም።  በቃኝ ማለት ብትችል እንኳ፣ እራስህን ከዋሻ ቆልፈህ ካልዘጋህ በስተቀር የምትኖርበት ህብረተሰብ፣ እኔንም ጨምሮ፣ አበድክ ብለን ሰው ሰራሽ ዋሻ ውስጥ እንቆልፍሃለን፡፡
ስለዚህ  በእኛ መለኪያ፣ እንደ ጤነኛ ሰው የሚያስፈልግህን ካበዛኸው ገንዘብ ማግኘት ግድ ይልሃል፡፡ በምትፈልጋቸው ነገሮችና በማግኘትህ መሃል ገንዘብ መሰናክል ሆኖ ቆሟል ማለት ነው። ምን ያህል ገንዘብ የሚለው ትርጉም አልባ ነው፡፡ ሁሌም የፍላጎትህ ደንቃራ ገንዘብ ሆኖ ታገኘዋለህ። ምንም ያህል ወደምትፈልገው ብትጠጋ፣ ምንም ያህል የገንዘብ እጦት የዘጋብህን በሮች ብትከፍት፣ የጎደለህን እስክትሞላ የምትፈልገው ከፍላጎትነት ሳያልፍ ይቆይሃል፡፡ አገኘሁት ስትል የሚርቅህም ብዙ ነው፡፡      
ሁሉንም ባትችልም ታዲያ ፣ የምትፈልጋቸውን ነገሮች በሂደት ማግኘትህ አይቀርም፡፡ አንዳንዱን በቀላል፣ ሌላውን ለፍተህ የግልህ ታደርጋለህ። ደሞ ያኛው ዋጋ የማይወጣለትን ያሰዋሃል፡፡ ካገኘሃቸውም በኋላ ፣ አንዳንዱ የምትጠቀምበት፣ ሌላው ቢቀር ምንም የማያጎድልብህ ሆኖ ሊሰማህ ይችላል፡፡ ያኛው ደሞ በጊዜያዊ ሞኝነት ተታለህ  እንጂ እድሉ ቢሰጥህ ደግመህ የማትሰራው ስህተት መስሎ ይታይህ ይሆናል፡፡
ግን ሁለት ነገሮች አይቀሬ ናቸው፡፡ አንድም ያ እንደዛ የለፋህለት፣ ተሟላ ብለህ የተደሰትክበት ፍላጎትህ ክብሩን ያጣብሃል፡፡ ያንተ ያልነበረው ያንተ ሲሆን፣ በሌሎች እጅ ያማረህ ተራ ይሆንብሃል፡፡ ዋጋ ከፍለህ ገንዘብ ሰርተህ፣ ቁሳቁስ ገዝተህ ያገኘህ የመሰለህ ልባዊ እርካታ፣ እንደ በልግ ዳመና ድንገት ብን ብሎ ይሰወርብሃል፡፡ ገንዘብ ጊዜያዊ ደስታ ሰጥቶህ መልሶ ይነጥቅሃል፡፡
ያን ጊዜ፣ በሁለተኛ ደረጃ፣ ካለህ የተሻለ ፍለጋ ታንጋጥጣለህ፡፡ የሚገርምህ ታዲያ ካንተ የተሻለ ያላቸው ብዙሃን እንደሆኑ ትረዳና፣ አዲስ ፍላጎት ፈጥረህ፣ ያለህን ንቀህ በምትፈልገውና በአንተ መሃል እንደገና ገንዘብን ደንቃራ ትገትራለህ፡፡ እንዳንተው፣ አንተ ባለህ ማልለው፣ እነሱ ሽቅብ አንተ ቁልቁል የምታያቸውም ብዙሃን እንደሆኑም አትገነዘብም፡፡ ወደ ላይ አንገትህን ሰብረህ እንዴት ወደ ታች ልታይ ትችላለህ? የገንዘብ የመጀመሪያው ምትሃታዊ ሀይሉ እዚህ ላይ ነው፡፡
እንዳትሳሳት አደራህን! 1 ሺህ ወይም 1 ቢሊዮን አልያም ከዛም በላይ ይኑርህ፣ አይኑርህ እያልኩህ አይደለም፡፡ ግን ምንም ያህል ገንዘብ እንደ ፈንዲሻ በድስትህ ሲንከተከት ቢውል፣ ምትሃታዊ ሀይሉ ካወረህ ቅምም አይልህም  ማለቴ ነው፡፡
ይህንን አልፈህ ማየት ስትችል - ከፍ ስትል ማለት አይደል? - የገንዘብ  ማህበራዊ ትርጉም ሌላ ፈተና አዝሎ ያፈጥብሃል፡፡

ሲቀጥል----
ባጭሩ ሁለት ነገር ላስጨብጥህ ሞክሬያለሁ። ገንዘብ በራሱ ጥፋተኛ እንዳልሆነ፣ ሆኖም የፍላጎታችን ጣሪያ አድማሳዊ ብቻ ስለሆነ፣ የሚበቃንን ያህል መቼም ማግኘት እንደማንችል ነገርኩህ፡፡ ይህም ለገንዘብ ያልታቀደለትን ሀይል እንዳጎናፀፈውም አወራን፡፡
ይህንን ተከትሎ ሁለተኛው የገንዘብ ምትሃት ያለው ከማህበራዊ ገፅታው ላይ ይመስለኛል፡፡ ያለህ የገንዘብ መጠን በምትኖርበት ማህበረሰብም ሆነ ከዛ በዘለለ ከባለፀጎች ተርታ  ያስመድብሃል፡፡ ከመናጢ ድሃ ይጀምርና፣ መካከለኛ ደሃ፣ ከድህነት ሊወጣ የደረሰ፣ መሃል ሰፋሪ፣ ጀማሪ ሀብታም፣ የናጠጠ ሀብታም ሌላም ሌላም እየተባለ ማህበረሰቡ ይከፋፈላል፡፡  እያንዳንዱ ክፍል ከታቹ ካለው የበለጠ፣ ከላይ ካለው ያነሰ “ሀይል/ጉልበት” አለው፡፡ ይህ ጉልበት የገንዘብ ማህበራዊ ምትሃት መቀመጫ ነው፡፡
ጉልበቱ ምንድ ነው አትልም?
ነገሮችን ከመግዛት አቅም ተከትሎ የሚመጣው ሰዎች ባለህ ሀብት መጠን የሚሰጡህ ቦታና ክብር ነው። በዚያው ምልከታ የምትገዛቸው ነገሮች መጠቀሚያ ብቻ ሳይሆኑ ያለህበትን የማህበረሰብ ክፍል መግለጫም ናቸው፡፡ ይህን ያህል ገንዘብ አለኝ፣ ሀብቴ ይህን ያህል ነው፣ እንደዚህ ብላችሁ ልታዩኝ ይገባል፣ በናንተ መሃል ያለኝ ደረጃ ይኸውላችሁ ---- ብለህ የምታውጀው በምትገዛቸው ቀሳቁሶች ዋጋ ሸፍነህ ይሆናል፡፡ ያኔ ከአንተ በታች ያሉትን ቁልቁል የማየትን ሀይል ገንዘብ ይሰጥሃል፡፡ እነሱም ባለህ ሀብት ያከብሩሃል፡፡ ድሮ ቢሆን  የሀገር ንጉስም ሊያደርግህ ይችል ነበር፡፡ አሁንም ትንንሽ ንግስናዎች ያንተ ይሆናሉ፡፡ ከዚህም የአሸናፊነትን፣ የስኬትን መንፈስ ታጭዳለህ፡፡ ያሰክርሃል ቢባል ያስኬዳል፡፡
የሀብት ደረጃዎችን  ስትቀበል፣ የስኬትህ  መለኪያነታቸውንም ያንተ ማድረግህ ግድ ነው፡፡  መቶ ብር ካረረበት ጀምሮ፣ ቢሊየነር እስከምትለው፣ ሁሉም ያለውን ምድራዊ ስኬት ባለበት የሀብት ክፍል ለመለካት ሲገደድ፣ ገንዘብ የቁሳዊ ፍላጎት ማሟያ መሆኑን አልፎ መጠሪያ ይሆናል፡፡ ለዚህም ነው በየጊዜው የአገራችን 100 ሁብታሞች፣ የአለም አንደኛ ሀብታም፣ የአፍሪካ ደሃዋ አገር እየተባለ ደረጃ የሚወጣው፡፡ በግልባጩ ከተመደብክበት የሀብት ደረጃ  በላይ ያሉትን መመልከትህ አይቀርም፡፡ “የት ጋ ነው ያለሁት?” ብለህ ትጠይቃለህ፣ ከበላይህ ብዙ ደረጃዎች  ይታዩሃል።  ከፍ ወዳለው ክፍል መግባትን ትሻለህ፤ የንግስና ርስትህን ለማስፋት መሆኑ ነው፡፡
ገንዘብ መጠሪያህ ከሆነ በኋላ ማብቂያ የለውም። ሁሌም ብዙ ገንዘብ ስምህን ተከትሎ እንዲጠራልህ ትፈልጋለህ፡፡ የቱንም ያህል ብታባክነው የማያልቅ ገንዘብ ብትይዝ፣ በሀብት ምድብ ቁንጮ ላይ  ብትቀመጥ፣ በስምህ የተመዘገበልህን ለመጨመር ስትል ብቻ ገንዘብን ትሻለህ፡፡ ይህን ጊዜ ገንዘብ ሁለተኛውን ምትሃቱን ጣለብህ ማለት ነው፡፡ ከሰዎች በልጦ መታየትን አቅምሶህ፣ የዘላለም ሱሰኛው አደረገህ፡፡
ገንዘብ ንጉስም ሎሌም አደረገህ ማለት አይደል፡፡

መጨረሻው
ገንዘብን ለጥቅሙ ሳይሆን ለስሙ ስትል ማሳደድ ከጀመርክ፣ ያንተው የስነልቦናህ አካል ይሆንልሃል፡፡ ይህንን ሲያደርግ ጫማ ቆንጥጦ ሽቅብ እንደሚያዘግም ጉንዳን፣ ሳታየው በዝግታ ነውና የማንነትህ አካል፣ የስሪትህ ምሰሶ ሲሆን ላታውቀው ትችላለህ፡፡ ያለህ ገንዘብ የስራህን ስኬት መግለፅ ብቻ እጣው ሊሆን ሲገባ፣ የልብህ ማማ እንዲሆን ስትፈቅድለት ፣ እሱ ጌታ አንተን ሎሌ የማድረግ ስልጣንን ይቀዳጃል፡፡ ሶስተኛው ምትሃትም እዚህ ላይ ነው ያለው፤ ገንዘብ ከላይ ያወጋናቸውን ውጫዊ ገፅታዎቹን ዘሎ ነፍስህ ላይ ሲጠመጠም የማይነካ ኃያል ይሆንብሃል፡፡  
ምትሃቱን የሚያገኘውም በሁለት ምክንያት ይመስለኛል፡፡
መጀመሪያ ገንዘብን በዚህ መልኩ ስታሳድደው፣ ለክብሩ ብለህ የምትፈፅማቸው ድርጊቶች በአብዛኛው ንፁህም  ህጋዊም አይሆኑም፡፡ ሱሰኛ ነህና እሱን ለማርካት ስትል አስተካክለህ ከተከልከው ከማጨድ ይልቅ ካልዘራህበት መሻትህ ግድ ነው። በስራ ብቻ ካለህበት ፈቀቅ ማለት ሲከብድህ፣ የምታልመውን የተሸነቆረ የገንዘብ ጎተራ በስራህ ልትሞላው እንደማትችል ስትረዳ፣ ሌሎች ሰርቀው ሲከብሩ፣ ከታችኛው ምድብ በድንገት ተፈትልከው ከላይኛው ሲሰኩ፣ የምትኖርበት ህብረተሰብ ተሸናፊ ነህ ብሎ ሲሳለቅብህ ፣ አንተም ሽንፈት ይውጥሃል፡፡ ስለዚህ ላለመሸነፍ ስትል አንተም ትገባበታለህ፡፡ ሲሰርቁ ትሰርቃለህ፡፡ ተራ ሌባም ባትሆን፣ ያንተ ባልሆነው መክበርን መሻትህ  ግን ከተራዎቹ ተርታ ያስመድብሃል፡፡
ሰርቀው ላልተያዙ ሲጨበጨብ አብረህ ታጨበጭባለህ፡፡ መስረቅን ሸሽተው ከድሃው ተርታ በተመደቡ ሲሳለቁ፣ በስንፍናቸው ሲገረሙ ትታደማቸዋለህ፡፡ ‹‹ሲሾም ያልበላ ሲሻር ይቆጨዋል›› የእለት ፀሎትህ አካል ይሆናል። ለገንዘብ ብለህ ዋጋ የማይወጣላቸውን ነገሮች ስታጣ ብዙም አይሰማህም። ከጓደኛህ ነጥቀህ ስትከብር ትደሰታለህ፣ ብዙዎችም በተራህ ያጨበጭቡልሃል፡፡ የቤተሰብህን ፍቅር በገንዘብ ስትለካ ምንም አይመስልህም፡፡
ታሪክ መሰረት ከሆነን ደሞ፣ እያንዳንዱ ስርቆት ቅጣትን ሳይሆን ሽልማትን ሲያድል ታያለህ። መጀመሪያ ግራ ይገባህ ይሆናል፣ ከዛ መቀበልን ትመርጣለህ፣ በመጨረሻም መብትህ እንደሆነ ትቆጥረዋለህ፡፡ ከሽልማቱም አልፎ የስርቆትን ድብብቆሽ ትወደውም ይሆናል፡፡  መጀመሪያ በፍራቻ ታጥረህ የፈፀምከው ስርቆት ልምድህ ሲዳብር እንደ ጥሩ ጨዋታ ማየትም ትጀምራለህ፡፡ በደም ስሮችህ የሚለቅብህን እፅ አጣጥመህ ትወደዋለህ ቢባል ማጋነን አይሆነም፡፡  
በሁለተኛ ደረጃ በእጅህ ያለህን የማጣት ፍርሃት ይጠናወትሃል፡፡ ልብ በል! ምንም የሚያስፈራህ ነገር እንኳን ባይኖር ፣ ቀናቶች የሚሰግዱልህ ቢመስልህ፣ የማጣት ፍርሃት ግን የቀን ተሌት ህልምህ አካል ይሆናል፡፡ የገንዘብ ማግኘት ሱስህን ከፍ ወዳለው ደረጃ የማሻገር አቅም ያላቸው ነገሮች መሪ ሆኖ እንዲቀመጥ ትፈቅድለታለህ፡፡ ከማጣት ፍርሃት ለመገላገል  መልሱ የበለጠ፣ የማያልቅ ገንዘብ ነው ብለህ ስለምታምን ለዚሁ ትንከራተታለህ፡፡ የማያስፈልግህን ላታገኘው!  
ይሄን ጊዜ ሶስተኛውና የመጨረሻውን ምትሃቱን ገንዘብ አሰፈረብህ ማለት አይደል? ስራውን ጨረሰ! እስከመጨረሻው ጌታህ ሊሆን ዙፋኑን ተቆናጠጠ፡፡
እናማ ምን ይሻላል ካልከኝ ፣ ጥቂት ልጨምር፡-
ቤንጃሚን ፍራንክሊን እንዳለው “ገንዘብ ደስተኛ እድርጎን አያውቅም፣ ሊያደርገንም አይችልም። ገንዘብ በራሱ ደስታን ማምረት የሚያስችለውን ስጦታ አልታደለም፤ ባገኘነው መጠን ጭማሪ እንሻለን እንጂ።” ደስታና እርካታም ይለያያሉ፡፡ ገንዘብ ሁለቱንም ሊሰጥህ የሚችለው አጠቃቀምህን ተከትሎ ነው። በገንዘብ ከምትገዛቸው ነገሮች እርካታን እንጂ ደስታን አትሻ፡፡ እርካታ አንፃራዊ ስለሆነ፣ የተሻለ ቁስ የበለጠ እርካታ ይሰጥሃል፡፡ እርካታ እንዲሁ ጊዜያዊ ነው፡፡ ሁሌም እድሳት ይፈልጋል፡፡
በተመሳሳይ ደስታንም አንፃራዊና ጊዜያዊ አድርገህ መመልከት ግን ስህተት ይሆናል፡፡ ከገንዘብ ደስታን የምትሻ ከሆነ፣ ካለህ ላይ ለሌላቸው ወይም ላነሳቸው ያለቅድመ ሁኔታ አሳልፈህ ስጥ። በማትጠቀምበት ቁሳቁስ መከበብን አትምረጥ። የህይወት ስኬትህን በገንዘብ ሳይሆን ባሉህ ዋጋ የማይወጣላቸው በረከቶች መዝነው፡፡ ይህ ከተሳካልህ ገንዘብ ከመገልገያ መሳሪያነቱ እንደማይዘልብህ እርግጠኛ መሆን ትችላለህ። የገንዘብን መጥፎ ገፅታ እስከገባኝ ነገርኩህ፣ ጥሩውንማ እራሱ ያስተምርህ የለ? …..ብዬ ናታንን ብመክረው ምን ያህል ትርጉም ያገኝበት እንደሆነ አንጃ፡፡ ከዛ አልፎ “ደስታ ግን ምንድነው?” ካለኝ ሌላ አርእስት አገኘን ማለት አይሆንም?

Read 2670 times