Tuesday, 04 March 2014 11:11

“ትክክለኛ ጋዜጠኛውንና ነውጠኛውን መለየት ያስፈልጋል”

Written by 
Rate this item
(4 votes)
  • የት አገር ነው የፓርቲ ልሳን አባላት ጋዜጠኞች የሚባሉት?
  • እጃችሁን ሰብስቡ ስንል ከሰበሰቡ እሰየው! ካልሰበሰቡ እናጋልጣቸዋለን
  • ‹‹የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች መድረክ›› ስለሚባሉት ምንም  መረጃ የለኝም

ባለፈው ማክሰኞ ኢብጋህ፣ ኢነጋማ እና ኢገማ የጋራ መግለጫ መስጠታችሁ ይታወሳል፤ ዓላማው ምንድን ነው?
የተለያዩ ፅንፈኛ አክራሪ ወገኖች፣ የጋዜጠኝነት ሞያን ለእኩይ ተግባራቸውና ለዓላማቸው ማስፈፀምያ ለማዋል ጠይቀውን ነበር፡፡ ይሄንንም ተግባር ለመቀበልና ተባባሪ ሆነን ለመቅረብ ፈቃደኛ አልሆንም፡፡ ይሄንንም ባለመሆናችን ምክንያት ወደ ሚዲያ ሃውሶቹ በመሄድ የተለያዩ ስራዎችን ለመስራት አቅደው አንዳንድ ስራዎችን ጀምረዋል፡፡ ይሄ ደግሞ የጥፋት ስራ ነው፡፡ ጋዜጠኛውን ይዞ ወደ ጥፋት ስራ ለመግባት እየተደረገ ያለ ዝግጅት ነው፡፡ ስለዚህ ይሄንን ጋዜጠኛው እንዲያውቅ፣ እንዲነቃ፣ እንዲጠነቀቅ፣ እንዳይተባበር ለመጠየቅ ነው፡፡ ጋዜጠኞች በሽብር ተጠርጥረው ቢታሰሩ፣ በእኛ በኩል ለመሟገት ስለሚያስቸግረን ነው፡፡ ሀገር ውስጥ በህጋዊ መንገድ ተደራጅተን የምንንቀሳቀስ ስለሆንን ለመከላከልም፣ ጥብቅና ለመቆምም በኋላ ስለምንቸገር ከወዲሁ በቅድሚያ ማሳወቅ ስላለብን ነው፡፡ የእኛ አባሎቻችን አሉ፡፡ ጋዜጠኞችና የሚዲያ ሰራተኞች አሉ፡፡ እነሱ ማወቅ ስለሚገባቸው ነው፡፡ ከሽብርተኞች እና ከአሸባሪ ቡድኖች ጋር የሚደረግ ማንኛውም ዓይነት ህገወጥ ግንኙነት ዋጋ የሚያስከፍል እንደሆነ ማንም ያውቀዋል፡፡ እኛ ስለምናውቅ ህገወጡን ግንኙነት ጋዜጠኛው እንዲጠነቀቅ ብቻ ነው ያሳሰብነው፡፡ የ2007 ዓ.ም ምርጫን መምጣት ተከትሎና ከዛው ጋር በተያያዘ ስማቸውን የማንጠራቸው አገሮች አሉ፤ ወደ አገራቸው ጭምር ጋብዘውን ነበር። ያንን እኛ አልተቀበልንም፤ ነገር ግን ያንን ተቀብለው በግልፅ የሚንቀሳቀሱ አሉ፡፡ ይሄንን ጋዜጠኛው ተገንዝቦ እንዲተባበረንና ማን እንደሆነ በግልፅ ስለሚታወቅ አደጋ እንዳይመጣበት እንዲጠነቀቅ ለማሳሰብ ነው፡፡ ይሄው ነው የመግለጫው መንፈስ፡፡
የአገራቱን ስም ለመጥቀስ ያልፈለጋችሁበት ምክንያት ምንድነው?
በጥቅሉ ማድረግ የፈለግንበት ምክንያት አለ። በጥቅል ሲደረግ እና ስማቸው ሳይጠቀስ ሲቀር እጃቸውን ይሰበስባሉ፡፡ እጃቸውን ካልሰበሰቡ በቀጣይ ይፋ እናደርጋለን፡፡ እጃችሁን ሰብስቡ ይሄ የሀገር ጉዳይ ነው፤ ከሀገር (ከብሄራዊ ጥቅም) የሚበልጥ ስለሌለ ተጠንቀቁ፣ ለማለትም ጭምር ነው፡፡ ከተወሰነ ጊዜ ወዲህ ሶስቱ ማህበራት በጋራ በመሆን በየጊዜው እየተገናኘን እየተወያየንበት ነው ያለነው፡፡ በሞያው ላይ እያንዣበበ ያለ አደጋ በጋራ ለመከላከል በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ውይይት አድርገን መስማማት ላይ ስለደረስን፣ ያንን እግረ መንገዳችንን ለመግለፅ ነው፡፡ በቀጣይ እነዚህ ችግሮች ገፍተው እንዳይሄዱ ቋሚ የሬድዮ እና ቴሌቪዥን የአየር ሰዓት ይዘን፣ እንደ ማህበር እንደ ባለሞያ ሞያውን ለማሳደግ የምንወያይበትና የምንሰራበት ሁኔታ እንዲኖር ከሚመለከታቸው ጋር ተወያይተናል፡፡ መግባባት ላይም ደርሰናል፡፡ በቅርብ ጊዜ ውስጥ ወደ ተግባር እንገባለን። ትክክለኛውን ጋዜጠኛና ነውጠኛውን መለየት ያስፈልጋል።
ታቅዶና ታስቦ እየተሰራ ያለ ነገር ነው፡፡ በማን ታቅዶ፣ በማን ተሳታፊነት እየተሰራ እንደሆነና የገንዘብ ምንጩ ማን እንደሆነ በግልፅ የምናውቀው ጉዳይ ነው፡፡ እኛ ዋናው ነገር “ለምን ቀድማችሁ አልነገራችሁንም” የሚል ነገር እንዳይመጣ ማሳሰብ ስላለብን ነው፡፡ ለሀገርና ለወገን የሚያስብ ጋዜጠኛ ይሄን ማሳሰቢያ ሰምቶ ራሱንና ወገኑን ከጥቃት የሚያድን፣ የሚጠባበቅና የሚከላከል እንዲሆን ነው፡፡ እየተደረገ ያለው ጋዜጠኞችን መከፋፈል ነው፡፡  ማህበራቸው ውስጥ ሰላም እንዳይኖራቸው መበታተን፣ ጋዜጠኞችን እርስ በርስ እያጋጩ በሚዲያ ውስጥ ያለውን ሰላምና መረጋጋት፣ በመናድና በማፈራረስ የስርጭት አድማሱን ማናጋት ነው፡፡ ከተለያዩ የሚዲያ ባለቤቶችም ጋር በዚሁ ጉዳይ ላይ ተወያይተናል በግል፡፡ ከስርጭት ጋር በተያያዘ ሰፊ አፈና አለ፡፡ እነሱ የማይፈልጉዋቸው ሰዎች በጋዜጣ እንዳይስተናገዱ፣  እንዳይወጡ፣ እንዳይፃፉ-- የስም ዝርዝር ሁሉ አዘጋጅተው እስከመስጠት የደረሱበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡
“የሽብርና የሽብርተኛ ወገኖች፣የኢትዮጵያን ጥቅም ለመጉዳት የተሰለፉ የውጪ ሃይሎች” የተባሉት እንዲሁም ጋዜጠኛውን መጠቀሚያ ለማድረግ የሚንቀሳቀሱት እነማን ናቸው? እንዳላችሁት ጋዜጠኛውን ለማንቃት በግልፅ መናገሩ  አይሻልም ?
አሁን እጃችሁን ሰብስቡ ነው ያልናቸው፡፡ እነሱና እኛ እንተዋወቃለን፡፡ እጃችሁን ሰብስቡ ስንል ከሰበሰቡ እሰየው! ካልሰበሰቡ ደግሞ እናጋልጣቸዋለን እያልን ነው። እኛን እኮ መጥተው አነጋግረውናል፡፡ የገንዘብ ምንጩም ሁሉም ነገር ተሰጥቶናል እኮ! ያንን የቀረበልንን አማራጭ አንቀበልም ብለናል፡፡ ግን ጊዜ ይፈልጋል፡፡ ለህዝብም ለመንግስትም ይፋ እናደርጋለን፡፡ የኢትዮጵያ ጠላቶች ዙሪያችንን እያንዣበቡ ነው ያሉት፡፡ በተለያየ መንገድ ያኮረፈን፣ የተጎዳን፣ በጥቅም በመደለል ወደሚፈልጉት መስመር ለማስገባት ይሻሉ፡፡ ስለዚህ የተመቻቸ ሁኔታ እንዳይኖራቸው ጥንቃቄ ማድረግ አለብን በሚል ነው፡፡ ሰለባ እንዳንሆን ነው፡፡
የሽብርና የሽብርተኞች  ጉዳይ ከሆነ መንግስት እንዴት ዝም አለ?  
መንግስት ጋ መረጃው አልደረሰ ይሆናል፡፡ ለመንግስትም ዝርዝር መረጃ እኛ አልሰጠናቸውም፡፡ ምን አልባት እኛ ስንሰጣቸው ያዩት ይሆናላ፡፡ እጃቸውን ካልሰበሰቡ መረጃውን ለመንግስት አሳልፈን እንሰጣለን፡፡
‹‹የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች መድረክ›› ከተባለው አዲሱ የጋዜጠኞች ማህበር ጋር በስያሜ ውዝግብ ውስጥ እንደገባችሁ ሰምቼአለሁ፡፡ እስቲ ስለእሱ ንገሩኝ----
‹‹የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች መድረክ›› በሚል ስያሜ ወር በማይሞላ ጊዜ ውስጥ የሬድዮና የቴሌቪዥን ፕሮግራማችንን እንቀጥላለን፣ ከሁለት ዓመት በፊት የተቋረጠ ነው፡፡ ‹‹የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች መድረክ›› በሚል ሁለት ማህበር ሊጠራ አይችልም፣ በሃገሪቱም ህግም በአሰራርም የሌለ ነገር ነው፡፡ አንቺ አዲስ አድማስ ብለሽ ጋዜጣ እየሰራሽ ከጎንሽ ሌላ ሰው መጥቶ አዲስ አድማስ ብሎ ሊሰራ አይችልም፡፡ ለማንም አሳልፈን የምንሰጠው አይደለም፡፡ ለአንድ ዓመት ኮንትራት ነበረን፣ ከኢቴቪ ጋር፡፡  ለተወሰነ ጊዜ ተላልፎ ነበር፡፡ አሁን መግባባት ላይ ተደረሰ፣ ያለው ዕውነት ይሄው ነው፡፡
በቅርቡ ‹‹የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች መድረክ›› በሚል ስያሜ  የጋዜጠኞች ማህበር ለማቋቋም እየተንቀሳቀሱ ስላሉት ቡድኖች የምታውቁት ነገር የለም ?
ስምንት የጋዜጠኛ ማህበራት አሉ፤ በኢትዮጵያ ውስጥ፡፡ የሴት ጋዜጠኞች ማህበር፣ የአካባቢ ጥበቃ ጋዜጠኞች ማህበር፣ የጤና ጋዜጠኞች ማህበር፣ የሳይንስ ጋዜጠኞች ማህበር፣ የስፖርት ጋዜጠኞች ማህበር፣ ቀድመው የተመዘገቡና የኢትዮጵያ የሚለውን ስም የሚጠቀሙ አገራዊ ይዘት ያላቸው ግን ሶስት ናቸው። ‹‹የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች መድረክ›› ስለሚባሉት ምንም  መረጃ የለኝም፡፡
መግለጫ ስትሰጡ ለምንድነው የግል ሚዲያውን የማትጠሩት? ለምሳሌ ባለፈው ሳምንት የመንግስት የመገናኛ ብዙሃንን ብቻ መርጣችሁ ነው መግለጫ የሰጣችሁት---
ከዚህ በኋላ በየሳምንቱ መግለጫ ስለምንሰጥ ሁሉም እንዲያውቅ እናደርጋለን፡፡ እስከ ዛሬ ክፍተት ፈጥረን ነው የቆየነው፡፡ እስከዛሬ የተለያዩ አሉባልታዎች ሲፃፉም ሲወሩም ዝም ብለን ስናይ ነበር፡፡ እንዳላየ ሆነን ችላ ብለን እናልፍ ነበር፡፡ ነገር ግን አሁን በውጪ አገር የሚሰበሰበውን ገንዘብ፤ በተለይ የሽብር ቡድኑ  ግንቦት 7 የሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎች መበራከትና አጠቃላይ ዙሪያ ገባ  እንቀስቃሴው ሲታይ ግን---
አሁን የሚታየው ግርግር ምርጫ ስለተቃረበ የተወሰነ የገንዘብ ድጋፍ (ፈንድ) ለማግኘት ሲባል ነው የሚሉ ወገኖች አሉ---
እኛ የፈንድ ችግር የለብንም፤ ስራ ለመስራትም፣ ስልጠና ለመስጠትም ማን እምቢ ይለናል፡፡ ጋዜጠኞችን አሰልጥኑልን ብለን እምቢ ተብለን አናውቅም፡፡
ከሃገር ውስጥ ነው ከውጪ?
ከሀገር ውስጥ ማንም እምቢ አይለንም፡፡ የውጪም ቢሆን እኛ የአለም ጋዜጠኞች ፌዴሬሽን አባላት ነን፤ ስለዚህ ጠይቀን መቀበል እንችላለን፡፡ እኛ ፈልገን ገንዘብ ያጣንበት ወቅት የለም፡፡
የጋዜጠኛ ማህበራት ብታቋቁሙም በጋዜጠኝነት ሙያ እየሰራችሁ አይደለም በሚል ትችቶች ይሰነዘርባችኋል፡፡ የት ጋዜጣ ወይም ሚዲያ ላይ ነው የምትሰሩት?
ዌብሳይት ላይ እጽፋለሁ፣ ጋዜጠኛ ነኝ እኔ፣ ወግ ብሎግ ላይ እፅፋለሁ ጋዜጠኛ ነኝ እኔ፣ ብሎገር ነኝና ጋዜጠኛ ነኝ፡፡ የት አገር ነው የፓርቲ ልሳን አባላት ጋዜጠኞች የሚባሉት። የፓርቲ አባል ሲሆኑ ያኔ  ጋዜጠኝነታቸው ያበቃል፡፡ እኛ የማንም ፓርቲ አባል አይደለንም፡፡ የሰማያዊ፣ የአንድነት ፓርቲ አባላት ተሰብስበው የጋዜጠኛ ማህበር እናቋቁም ሲሉ ይገርማል፡፡ ያቋቁሙ---- መንግስት ከፈቀደላቸው፡፡  እኛ ከልካይም ፈቃጅም አይደለንም፡፡ እኛ የራሳችንን ስራ ነው የምንሰራው፡፡
በሀገራችን ጉዳይ ላይ በጋራ ነው የምንሰራው፣ ተለያይተን አናውቅም፣ የጋራ አቋም ነው የምንይዘው፡፡ የአገር ጥቅም፣ ሰላም፣ ብሄራዊ ፀጥታ--- የሁላችንም ጉዳይ ነው፣ ስለዚህ መቼም ቢሆን ተለያይተን አናውቅም፡፡

Read 3798 times