Tuesday, 04 March 2014 11:05

“ለጋዜጠኞች ተቆርቋሪ የሆነ ማህበር ያስፈልጋል”

Written by 
Rate this item
(2 votes)
  • ስም የማጥፋት እንቅስቃሴ መደረጉ ተገቢ አይደለም
  • ከሲፒጄ ጋራ በመሞዳሞድ የሚመጣ ለውጥም ይኖራል ብለን አናምንም
  • መግለጫ ካወጡት ማህበራትም ጋር ቢሆን ለመነጋገር በራችን ክፍት ነው

“የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች መድረክ” በሚል ስያሜ የምስረታ ሂደቱን የጀመረው አዲሱ የጋዜጠኞች ማህበር፤ ገና ህጋዊ ፈቃዱን ባያገኝም አመራሮቹን  መርጦ በእንቅስቃሴ ላይ ይገኛል፡፡ ወደ ስምንት የሚደርሱ በጋዜጠኞች ስም የተቋቋሙ የተለያዩ ማህበራት ቢኖሩም አሁንም ድረስ የጋዜጠኞች መብትም ሆነ የፕሬስ ነፃነት አለመከበሩን የአዲሱ ማህበር አመራሮች ይናገራሉ፡፡ የተቋቋሙት ማህበራትም ጋዜጠኞች ሲታሰሩ ድምፃቸውን አሰምተው አያውቁም የሚሉት አመራሮቹ፤ ለጋዜጠኞች ተቆርቋሪ የሆነ፣ ለመብታቸው የሚታገልላቸው ማህበር ያስፈልጋል በሚል ተሰባስበው፣ አዲሱን ማህበር የመመሥረት እንቅስቃሴ መጀመራቸውን ገልፀዋል፡፡  የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አበባየሁ ገበያው የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች መድረክ ፕሬዚዳንት አቶ በትረ ያቆብንና የህዝብ ግንኙነት ሃላፊውን አቶ ዘሪሁን ሙሉጌታን በማህበሩ ዓላማ፣ ሦስቱ የጋዜጠኞች ማህበር ሰሞኑን ባወጡት አነጋጋሪ መግለጫ ዙርያና ሌሎች ጉዳዮች ላይ አነጋግራቸዋለች፡፡  

“የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች መድረክ” በሚል ስያሜ አዲስ የጋዜጠኛ ማህበር ለማቋቋም በእንቅስቃሴ ላይ ናችሁ፡፡ በአገሪቱ ውስጥ ስምንት የጋዜጠኞች ማህበራት እያሉ አዲስ ማህበር የማቋቋም ፋይዳው ምንድነው?
በትረ ያዕቆብ- አሁን ባለው ሁኔታ፣ የጋዜጠኞች መብት አልተከበረም፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ፣ የፕሬስ ነፃነት እየተከበረ አይደለም፡፡ ጋዜጠኛው ሀሳቡን በነፃ የመግለፅ መብቱ አልተከበረለትም፡፡ የጋዜጠኛ ማህበራቱ ተቋቋሙ እንጂ እነዚህን ችግሮች በቅጡ መፍታትም ሆነ ለጋዜጠኞች ሊታገሉላቸው አልቻሉም፡፡ ይሄ ሁሉ ጋዜጠኛ ሲታሰር ሲፈታ፣ ድምፃቸውን አሰምተው አያውቁም፡፡ ጋዜጠኞች ሲታሰሩም ለምን ሲሉ አንሰማም፡፡ ስለዚህ የሆነ፣ ክፍተት አለ ማለት ነው፡፡  እኛ የመጣነው ያንን ክፍት ለመሙላት ነው፡፡ ለጋዜጠኞች ተቆርቋሪ የሆነ፣ ለጋዜጠኞች የቆመ ማህበር ያስፈልጋል፡፡ ለጋዜጠኞች ታማኝ የሆነ ነፃ፣ ገለልተኛና ለማንም ያልወገነ ማህበር ያስፈልጋል ብለን ነው ማህበሩን ለማቋቋም የተሰባሰብነው፡፡
በፊትም የጋዜጠኛ ማህበር የማቋቋም ፍላጎቱ ነበረን። በተለይም በቅርቡ በ “ኢትዮ ምህዳር” ጋዜጠኞች ላይ የደረሰውን አደጋ ተከትሎ በተለይም የመኪና አደጋ በደረሰበት ኤፍሬም ምክንያት ነው መነቃቃቱ የተፈጠረው። “ለምን አሁን አይሆንም?” በሚል ተሰባሰብን፡፡
ዘሪሁን ሙሉጌታ - የጋዜጠኞች ማህበር የማቋቋም ፍላጎቱ በየኮሪደሩ ነበር፡፡ ነገር ግን ኤፍሬም አደጋ በደረሰበት ወቅት ምንም ያህል ብንሮጥ የሚታከምበት ገንዘብ ማግኘት አልተቻለም፡፡ ጋዜጠኞች በወቅቱ “ለካ የሚደርስልን የለም፣ ለእኛ የሚቆም የለም” በማለት ተደናገጡ፡፡ ማህበር ቢኖረን እኮ ይሄ ሁሉ ችግር አይኖርብንም፤ ጠንካራ ማህበር ያስፈልገናል፤ የሚል ሀሳብ መጣ፡፡ የተወሰኑ ልጆች ይሄንን የተቀሰቀሰ ሀሳብ በአጀንዳነት ይዘው መምከር ያዙ፡፡ በመቀጠል ጊዜያዊ ኮሚቴ ተቋቋመ፡፡ ጥናቶች ተደረጉ፤ በኋላም ማህበራችን እንደዚህ አይነት ቅርጽ ሊኖረው ይገባል ብለን እንቅስቃሴውን ሊመሩ ይችላሉ ያልናቸውን ስምንት ሰዎችን መረጥን፡፡
ከምስረታችሁ ጋር በተያያዘ ከበስተጀርባችሁ ግፊት የሚያደርጉ ወገኖች እንዳሉ ይነገራል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ምን ትላላችሁ?
በትረ - በስተጀርባችን ምንም አካል የለም፡፡ የተሰባሰብነው ጋዜጠኞች ነን፣ በሞያችን የሚገጥሙንን ችግሮች ለመጋፈጥ በሚል ነው ማህበር ለማቋቋም የተነሳነው፡፡ በጋዜጠኛው ላይ ተፅዕኖ የሚያሳርፈው መንግስት ብቻ አይደለም፤ የእምነት ተቋማት ተፅዕኖ ያሳድሩበታል፤ ሌሎችም አሉ፣ ጋዜጠኛውን ከእነሱ ለመጠበቅ  ነው ዓላማችን፡፡  
ዓለም አቀፉ የጋዜጠኞች ማህበር ሲፒጄ ከየሚዲያው ጋዜጠኞችን በማሰባሰብ አሁን ያሉትን ሶስት ማህበራት ማለትም ኢብጋህ፣ ኢገማ፣ ኢነገማን ስለማላምናቸው አዲስ ማህበር አቋቁሙ ብሏችሁ ነው የተሰበሰባችሁት የሚባል ወሬ ይናፈሳል..
በትረ- መሠረት የሌለው ነገር ነው፡፡ የተቋቋምነው ራሳችን ተሰብስበን ነው፡፡ ሲፒጄን ማን እንዳመጣው አናውቅም፡፡ አላስፈላጊ ነገር እየተወረወረብን ነው፡፡ ገና ሊቋቋም ያለ ማህበር ማጠልሸት ለምን እንዳስፈለገ አናውቅም፡፡ የተሰባሰብነው ከሚደርስብን ጥቃት ራሳችንን ለመጠበቅ ነው፡፡ ለጋዜጠኞች ድምፅ ለመሆን ነው፡፡ ከበስተጀርባችን ድብቅ አላማ ያለው፤ የደገፈንም አካል የለም፡፡ ነገ ከነገ ወዲያ አብረውን ሊሰሩ የሚፈልጉ አካላት ሊኖሩ ይችላሉ፤ መንግስትም አንዱ አካል ነው፡፡ በተረፈ ሌላውን እንደ አሉባልታ ነው የማየው፡፡
ዘሪሁን- ሲፒጄ ማንዴትም የለውም፤ ጋዜጠኞችን ኢትዮጵያ ውስጥ የማደራጀት፣ የመምራት፣ የማስተባበር ማንዴትም የለውም፡፡ እኛ ጋዜጠኞች ነን፣ ብዙ ነገር እናውቃለን፡፡ የሀገሪቱን ህግ ጠንቅቀን የምናውቅ ነን፡፡ ከሲፒጄ ጋራ በመሞዳሞድ የሚመጣ ለውጥም ይኖራል ብለን አናምንም፡፡ ዝም ብሎ አሉባልታ ነው፡፡ ይሄን ማህበር ለየት የሚያደርገው በራሳቸው በጋዜጠኞች ተነሳሽነት፣ ችግሩንም ተጋፋጭ እንደሆኑ አምነው የፈጠሩት ስብስብ መሆኑ ነው፡፡ በዚህ ደረጃ መፈረጁ በጣም የሚያሳዝን ነው፡፡ እንዲህ መፈራረጁም ነው ጋዜጠኞችን ትክክለኛ ማህበር እንዳይኖረን የሚያደርገን። አሁንም ዳር ሆኖ አቃቂር ማውጣቱ ስለማይጠቅም እንደውም ጋዜጠኞች መጥተው በግልፅ እንዲሳተፉና የራሳቸውን አስተዋፅኦ እንዲያበረክቱ እንጠይቃለን፡፡
ምርጫ ካደረጋችሁ በኋላ በአመራርነት ላይ የተቀመጡት የፓርቲ ልሣናት ላይ የሚሰሩ፣ የፖለቲካ ፓርቲ  አባል የሆኑ ናቸው የሚባለውስ ?
በትረ- አዎ የፓርቲ ልሣን ላይ የሚሰሩ ሰዎች በመሃላችን አሉ፡፡ የፓርቲ ልሣን ላይ ስለሚሰራ የጋዜጠኝነት ሞያ አይተገብርም ማለት የሚቻል ግን  አይመስለኝም፡፡ የመንግስት ልሣን ላይ የሚሰራ ጋዜጠኛ ነገ በአባልነት ቢመጣ እየተገበረ ባለው ሞያ ከለላ የሚያስፈልገው ከሆነ፣ የእኛ ማህበር እጁን ስሞ ነው የሚቀበለው፡፡ እኛ የምንፈልገው የማህበራችን መርሀግብሮች እና ዓላማ ላይ ያላቸውን እምነት ብቻ ነው። በተረፈ ማንንም ጋዜጠኛ እንቀበላለን፡፡ ልሣንም ላይ ይስሩ …ምንም ይስሩ፣ በሚሠሩት ስራ ከሞያቸው አንፃር ከለላ ያስፈልጋቸዋል፤ እነሱን መጠበቅ የማህበራችን ዓላማ ነው፡፡
ዘሪሁን- ሀሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት ይከበር እያልን፣ አንድ ሰው በያዘው የፖለቲካ አመለካከት የተነሳ በጋዜጠኞች ማህበር ውስጥ አትገባም በሚል መከልከል አንችልም፡፡ ዋናው ነገር የያዘውን የፖለቲካ አስተሳሰብ ማህበሩ ላይ እንዳይጭን መከላከል ነው፡፡ ከዚህ ቀደም የነበሩ ማህበራት ስህተት ከባህሪያቸው፣ የአንድ የፖለቲካ ፓርቲ ባህሪ ያላቸው መሆናቸው ነው፡፡ የአንድ የፖለቲካ ፓርቲ ባህሪ፣ ስልጣን ለመያዝ የሚታገል ነው፡፡ ማህበር ግን የአባላቱን ጥምቅ ማስከበር እንጂ ስልጣን መያዝ አይደለም ግቡ፤ እኛ እየመሰረትን ያለው የጋዜጠኞች ማህበር መድረክ የቆመው ስልጣን ለመያዝ ሳይሆን፤ በአገሪቱ ያሉ የጋዜጠኞችን መብት ለማስከበር፣ የሀሳብ ነፃነትን እንዲረጋገጥ ለመታገል ነው፡፡ የአብዮታዊ ዲሞክራሲ ልሣን፣ የኢህአዴግ ልሣን ነው፡፡ በዛ ውስጥ ተቀጥረው የሚሰሩ በእኛ ማህበር ሀሳብ የሚስማሙ ከሆነ እነሱም በአባልነት እንይዛለን፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ሀሳብን በነፃ የመግለፅ ነፃነትና የጋዜጠኞች መብት አልተከበረም የሚል አቋም አለን፡፡ ይህን የሚያምን የአብዮታዊ ዲሞክራሲ፣ የኢቴቪ ጋዜጠኛ ካለ በአባልነት እንቀበላለን፡፡ ይኼው አመለካከታችን ተቃዋሚ ፓርቲ ላይ ቢሰራ ለምንድን ነው ልዩ የሚሆነው? የተቃዋሚዎችን አላማ በማህበራችን ላይ እንዳይጭን ግን  እንጠብቃለን፡፡ በጉባዔው ላይ አንድም ያከራከረን ይሄው ነበር:: የመንግስትና የግል ጋዜጠኛ የሚል ሀሳብ ተነስቶ በስፋት ተወያይተንበታል፡፡ ይሄ ማህበር በጋዜጠኝነት ሞያ አማራጭ ዘርፎች ማለትም በብሎገርነትም፣ በኤሌክትሮኒክስ ሚዲያ፣ በጋዜጣም ያሉ ሀሳብን በመግለፅ እንቅስቃሴ ውስጥ ተሳታፊ የሆኑትን በሙሉ ያቅፋል፡፡
ማህበራችሁ የግልንም የመንግስትንም ጋዜጠኞች ያቀፈ ነው ማለት ነው?
እስካሁን የመንግስት ሚዲያ ላይ ከሚሰሩት መካከል በድፍረት መጥቶ ማህበሩን የተቀላቀለ የለም፡፡ ወደፊት አላማውን ሲረዱ ሊመጡ ይችላሉ፡፡
በኢትዮጵያ ስምንት የጋዜጠኞች ማህበራት አሉ። እናንተ ከእነዚህ ማህበራት ጋር ያላችሁ ግንኙነትና መስተጋብር ምን ይመስላል? በተለይ ሶስቱ ማህበራት ኢብጋህ፣ ኢነጋማና ኢገማ የተባሉት ሰሞኑን መግለጫ አውጥተዋል፡፡ የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች ከሽብርና ከሽብርተኞች ተጠንቀቁ የሚል፡፡ መግለጫውን እንዴት አገኛችሁት?
በትረ- እኛ እነሱን የምንላቸው እህት ማህበራት ነው፡፡ ፅንፍ መያዝ የትም አያደርስም፡፡ እኛ የፖለቲካ ጥያቄ አይደለም የምናነሳው፡፡ እየመሰረትን ያለነው የሞያ ማህበር ነው፡፡ ስልጣንም አይደለም ጥያቄያችን፡፡ ጥያቄያችን፤ ሀሳብን በነፃ የመግለፅ መብት መከበር አለበት የሚል ነው፡፡ ጋዜጠኛ በጋዜጠኝነቱ ሊታሰር፣ ሊደበደብ፣ ሊሰደብ ወይንም ዛቻ ሊቀርብበት አይገባውም ነው የምንለው፡፡ ይሄን ለማስተካከል ፅንፍ መያዝ አይገባም። ከሁሉም አካል ጋር በመስራት ነው የሚፈታው፡፡ ሁሉም አካል ስንል መንግስትንም ይጨምራል፡፡ ፅንፍ መያያዙ የትም አያደርሰንም ነው የምለው፡፡ ፅንፍ መያዝ ለቆምንለት አላማ ግብ መምታት ፋይዳ የለውም፡፡ የሚያዋጣን፤ ባሉት ችግሮች ላይ መወያያት፣ መፍትሄ ማቅረብ ነው፡፡ ከእነሱ ጋርም ቢሆን ለመነጋገር በራችን ክፍት ነው፡፡
የጋዜጠኞች ማህበራቱ በመግለጫቸው፤ በሽብርተኝነት የተፈረጁ አካላት ጋዜጠኞችን ለመጠቀም ጥረት እያደረጉ ነው ብለዋል ---
በትረ- ማህበራችን ነፃና ገለልተኛ ነው ስንል ራሳችንን የምንጠብቀውና ነፃነታችንን የምናስጠብቀው ከመንግስት የሚደርስብንን ተፅዕኖ በመቋቋም ነው፡፡ ነገር ግን ተፅዕኖው ከፖለቲካ ፓርቲዎችም ሊመጣ ይችላል፡፡ ተፅዕኖውን ለመፍጠር ፍላጎቱ ያላቸው ቡድኖች አሉ፡፡ እኛ ግን ከዚህ ገለልተኛ ሆነን የምናራምደው የጋዜጠኞችን መብት ነው፡፡ ሌላው ነገር አሉባልታ ነው፤ እኛ ጋዜጠኞች ነን፡፡ የዚህ አገር ዜጎች ነን፡፡
ዘሪሁን- ይሄ ውንጀላ በጣም የሚያሳዝን ነው፡፡ እኛን ያውቁናል፡፡ እኛ የምንፅፈውን ነገር የሚያነቡ ሰዎች ናቸው፡፡ አሉባልታ ነው፡፡ መብት ለማስከበር ፍላጎት ያላቸው ጋዜጠኞች ተነስተው ማህበር ለመመስረት እንቅስቃሴ ሲጀምሩ መወንጀላቸው ተገቢ አይደለም፡፡ በመቋቋም ላይ ያለን ሰዎች ነን፡፡ ጣቢያውም በእንደዚህ አይነት ነገር ተባባሪ በመሆኑ እና ስም የማጥፋት እንቅስቃሴ መደረጉ ተገቢ አይደለም፡፡ ይህ ስለተባለ ደግሞ የሚያስበረግግ፣ የሚያስደነግጥ ነገር አይሆንም፡፡ ጋዜጠኛውም ይህንን በደንብ ያውቀዋል፡
በትረ- አዲስ ማህበር ሲመጣ ቢቻል ማበረታታት፣ ድክመቶች ሲታይ ገንቢ በሆነ መንገድ አስተያየት መስጠት ይገባል፡፡ ከዛ አልፎ ግን ሰዎችን ጽንፍ ማስያዝ፣ ያልሆነ ስም መለጠፍ ጤናማ አይደለም፡፡
ዘሪሁን- ማህበር ያቋቋማችሁት ለመሰደድ ነው ተብለናል፡፡ ማህበሩ ከተቋቋመ በኋላ ብዙ ነገሮች እንሰማለን፡፡ እርግጥ ነው፤ ማህበር የሚባል ነገር ሲመሰረት እንደዚህ ዓይነት ነገሮች ይመጣሉ ተብሎ ይገመታል፡፡ አሁን ግን ባልገመትነው መጠንና ሁኔታ ነው እየተናፈሰ ያለው፡፡ ለመሰደድ ከተባለ ኢትዮጵያ ውስጥ..እኛ እንደውም ሳንሰደድ በስማችን ብዙ ጋዜጠኛ ነው የሚሰደደው፡፡ በጣም የተበላሸ አሰራር እንዳለ እናውቃለን፡፡ በጣም ጠንካራና እንደዚህ ዓይነት ማህበር መኖሩ በእኛ ስም የሚነገደውን መላ ለማስያዝ አንድ መስመር ነው የሚሆነው፡፡ ለመሰደድ ለመሰደድማ እንኳን ጋዜጠኛ፣ እህቶቻችን የቤት ሠራተኛ ለመሆን ይሰደዱ የለ፡፡
በአመራር ምርጫ ወቅት አንዳንድ ችግሮች ተስተውለዋል የሚባል ነገር ሰምቻለሁ …
ምርጫው ፍፁም ዲሞክራሲያዊ ነበር፡፡ በታዛቢዎች፣ ገለልተኛ የነበሩ ሰዎች ባሉበት የተካሄደ ምርጫ ነው፡፡ እኔ ካልመራሁት ብሎ በማህበሩ ላይ ቅር በመሰኘት የሚወጣ ሰው ሊኖር ይችላል፡፡ ሂደቱ ውጣ ውረድ የነበረው ቢሆንም አሁን  እንደ ማህበር ቆሟል፡፡
ምርጫውን የታዘቡ ገለልተኛ አካላት የተባሉት እነማን ናቸው?
ዘሪሁን- ኤምባሲዎች መታዘብ ፈልገው መጥተው ታዝበዋል፡፡ የእንግሊዝና አሜሪካ ኤምባሲዎች መጥተው ነበር፡፡
ስንት አባላት አሉዋችሁ?
በትረ- ወደ 30 የሚሆኑ አባላት አሉን፡፡ በተባባሪ፣ በክብር አባልነት የምንይዛቸው ይኖራሉ፡፡
የአጭር ጊዜና የረጅም ጊዜ እቅዳችሁ ምንድን ነው?  
የሶስት ወርና የስድስት ወር እቅድ አለን፡፡ ማህበሩ እውቅና እንዲያገኝ እንሰራለን፡፡ ልናቋቁመው የፈለግነው ተቋም ነው፡፡ የሚያስፈልጉትን መረጃዎች እያዘጋጀን ነው። የፕሬስ ነፃነትን ፕሮሞት በማድረግ ረገድ ያዘጋጀናቸው ነገሮች አሉ፡፡
ሜይ 3 ‹‹የአለም የፕሬስ ነፃነት›› ቀንን ልናከብር የስድስት ወር እቅድ ይዘናል፡፡ ቀኑን በተለያዩ ዝግጅቶች ለማክበር ተሰናድተናል፡፡ የእግር ጉዞ፣ የሻማ ማብራት፣ ኮንፍረንስ አድርገን እለቱን እንዘክረዋለን፡፡
የገንዘብ ምንጫችሁ ምንድነው?
የገንዘብ ምንጭ ብለን የያዝነው አባላቱን ነው፡፡ አዲስ ማህበር እንደመሆኑ በዓመት የሚከፈል የአባላቱ ክፍያ፣ የመመስረቻ ክፍያ፣ የገቢ ማሰባሰቢያ የራት ምሽት …  ለጊዜው እኒህ ናቸው፡፡

Read 2846 times