Print this page
Tuesday, 04 March 2014 11:03

በህገ-ወጥ መንገድ ስልክ በማስደወል መንግስትን ከ16 ሚ. ብር በላይ አሳጥተዋል የተባሉ ተቀጡ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(15 votes)

እስከ 12 ዓመት እስርና 3ሚ 898ሺ ብር የገንዘብ ቅጣት ተበይኖባቸዋል

የተራቀቁ የቴሌኮም ሶፍትዌሮችን ተጠቅመው በህገወጥ መንገድ ስልክ በማስደወል፣በመንግስት ላይ ከ16 ሚሊዮን ብር በላይ ጉዳት አድርሰዋል የተባሉ 15 ነጋዴዎችን ጉዳይ ላለፉት ሶስት አመታት ሲመለከት የቆየው የፌደራሉ አራተኛ ፍ/ቤት 15ኛ ወንጀል ችሎት፣ ከትላንት በስቲያ ከ2 ዓመት ከ9 ወር እስከ 12 ዓመት እስርና ከ25ሺ ብር እስከ 3 ሚሊዮን 898ሺ ብር የገንዘብ ቅጣት በይኖባቸዋል፡፡
“ፒሲቶከር እና ራስ አዲስ” የተባሉ ህገወጥ ሶፍትዌሮችንና በሶፍትዌሮቹ ላይ የሚሞሉ የካርድ ቁሮችን ወደ ሃገር ውስጥ በማስገባት ሲሰሩ ተደርሶባቸው እንዲዘጋ ሲደረግ፤ በዚሁ የክስ መዝገብ አንደኛ ተጠሪ ሆነው ከተከሰሱ በኋላ የቀረበባቸውን የአቃቤ ህግ ማስረጃ በሚገባ ተከላክለዋል ተብለው በነፃ ከተሰናበቱት የኢትዮ-ቴሌኮም ሁለት ኢንጂነሮች አንዱ ከሆኑት አቶ ነቢያት መላኩ ጋር በመገናኘት አስከፍተው፣ሶፍትዌሮቹን ሌሎች ህገወጥ ስልክ አስደዋዮች እንዲጠቀሙበት በማድረግ በመንግስት ጥቅም ላይ ጉዳት አድርሰዋል በሚል በአቃቤ ህግ ክስ የቀረበባቸው አቶ መላኩ ሃይሉ በ12 አመት ፅኑ እስራት እና በ315 ሺ ብር የገንዘብ መቀጫ እንዲቀጡ ተወስኗል፡፡
ቴክኖሎጂውን ተጠቅመው ከ16 ሚሊዮን ብር በላይ መንግስትን አሳጥተዋል በተባሉት ቀሪ ተከሳሾች ላይ ጽ/ቤቱ የአቃቤ ህግን የቅጣት ማክበጃ እና የተከሳሾችን የቅጣት ማቅለያ ከመረመረ በኋላ በእያንዳንዳቸው ላይ ከ2 ዓመት ከ9 ወር እስከ 6 ዓመት ከ6 ወር ፅኑ እስራት የወሰነ ሲሆን የገንዘብ መቀጮውም መንግስትን አሳጥተዋል የተባለውን ሁለት እጥፍ እየታሰበ ከብር 25 ሺህ እስከ 3 ሚሊዮን 898 ሺህ ብር እንዲቀጡ ሲል የቅጣት ውሳኔ አስተላልፏል፡፡
የእስራት ፍርዱ ተከሳሾች በማረሚያ ቤት የቆዩበትን ጊዜ ታሳቢ ያደረገ መሆኑን ያመለከተው ፍ/ቤቱ፣ ከ3 አመት ከ8 ወር በታች የተፈረደባቸው አራት ተከሳሾች፣ የመፈቻ ትዕዛዝ እንዲፃፍላቸው አዝዟል፡፡ የገንዘብ መቀጮውን በተመለከተም የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር ተከታትሎ ያስፈፅም ሲል ፍ/ቤቱ ትዕዛዝ አስተላልፏል፡፡  

Read 3912 times