Tuesday, 04 March 2014 10:54

“መላጣ አናት ላይ ጠብ ያለች ውሃ እስካፍንጫ ለመውረድ ምን ያግዳታል?!”

Written by 
Rate this item
(10 votes)

              ዓለም በሁለት ተከፍላ በነበረ ዘመን ማለትም በካፒታሊስትና በሶሻሊስት ጐራ፤ ይወራ የነበረ አንድ ውጋውግ (witticism) አለ፡፡
ድሮ አንድ ጊዜ በፖላንድ አገር ከፍተኛ የሥጋ ዕጥረት ተፈጠረ፡፡ ህዝቡ አማረረ፡፡ ጋዜጦች፣ ሬዲዮ፣ ቴሌቪዥን፣ ወሬው የሥጋ ዕጥረት ነገር ሆነ (ያው እንደኛው አገር)፡፡ ልዩ ልዩ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች እንደልማዳቸው ሰፋፊ ዘገባ ይሰጡበት ጀመር፡፡ (ያው በእኛ ላይ እንደሚያደርጉት)
ይህን የተገነዘበ አንድ ኩባንያ “ዓለም-አቀፍ የጥያቄና መልስ ውድድር” አዘጋጅቶ “በጣም ከባድ ከባድ ሽልማት ስለምሰጥ የቻለ ይወዳደር”፤ ብሎ አዋጅ አወጣ፡፡
በአዕምሮአችን እንተማመናለን ያሉ አዋቂዎች በሺዎች ተመዘገቡ፡፡ የማጣሪያ ውድድሮች ተካሄዱ፡፡ ጉዳዩ ስለ ፖላንድ የኢኮኖሚ ችግር ነው፡፡ ለመጨረሻ ፍልሚያ የደረሱት ፋይናሊስቶች ሶስት ናቸው፡፡ የአሜሪካ፣ የህንድና የሩሲያ ተፎካካሪዎች፡፡
ለመጀመሪያው ተረኛ የቀረበለት ጥያቄ
“Why is there a shortage of meat in Poland?” የሚል ነው፡፡ “በፖላንድ የሥጋ ዕጥረት ለምን መጣ?” ነው፡፡
በመጀመሪያ የአሜሪካዊው ተራ ነበረ፡፡ እሱም፤ አሰበ አሰበና፣ “What is Shortage?” አለ፡፡ ዕጥረት ማለት ምን ማለት ነው? (እንግዲህ “ዕጥረት” ማለት ቃሉም እራሱ በእኔ አገር አይታወቅም ማለቱ ነው፡፡)
ሁለተኛው የህንዱ ተራ ሆነ፡፡ ሌላ ጥያቄ ይጠይቁኛል ብሎ ሲጠብቅ ያው ጥያቄ ቀረበለት
“why is there a shortage of meat in poland” “በፖላንድ የሥጋ ዕጥረት ለምን መጣ? ህዳንዊውም፤ ትንሽ አሰበና፤ “what is meat?”
“ሥጋ ማለት ምን ማለት ነው?” አለ፡፡ (በህንድ አገር ሥጋ ከማይበሉት ወገን ነው ማለት ነው ህንዱ)
በመጨረሻ፤ ተራው የሩሲያዊው ሆነ፡፡ እሱም ሌላ ጥያቄ ይጠይቁኛል ብሎ ሲጠብቅ፤
“why is there a shortage of meat in Poland?” ሆነ ጥያቄው፡፡ “በፖላንድ ለምን የሥጋ ዕጥረት መጣ?”
ሩሲያዊውም አስቦ አስቦ፤ አስራሚ ጥያቄ አመጣ፡-
What is “why?” ሲል ጠየቀ፡፡
“ለምን?” ብሎ ጥያቄ ራሱ፤ ምን ማለት ነው ማለቱ ነው! (ያኔ በሩሲያ “ለምን?” ብሎ መጠየቅ የማይሞከር ነገር ነው፡፡)
*             *                    *
“ለምን?” ብሎ የማይጠይቅ ህብረተሰብ ተስፋ የለውም፡፡ “ለምን?” ተብሎ መጠየቅን የማይፈልግ መንግስትም ተስፋ የለውም፡፡ ሌሎች ብዙ ተጨማሪ ነገሮች ቢኖሩበትም የሩሲያ መንግስት መንኮታኮት ዕጣ-ፈንታው የሆነበት ምክንያት “ለምን?” መባል አለመፈለጉ፤ ኢ-ዲሞክራሲያዊነቱ፣ ሀሳባችሁን አትግለፁ ማለቱ፣ ህዝቡ ቃሉ እስኪጠፋው ድረስ “ለምን?” በማለት መገደቡ ነው፡፡ ለምን ብለን እንጠይቅ፡፡
ነዳጅ ይጠፋል! ለምን? መብራት ይጠፋል! ለምን?፤ ስልክ ይሰወራል! ለምን?፤ ውሃ ይደርቃል! ለምን … የባንክ ሲስተም የለም ይባላል-ለምን? ብዙ ለምኖች አሉ፡፡ ግን ጠያቂ የለም ተጠያቂም የለምም፡፡ ለምን? ለምን ብዙ? ነው፡፡... የሚታሸጉ ቤቶች አሉ፡፡ አንዳንድ ቤቶችን እየዘለሉ ይታሸጋሉ፡፡ ዝላዩ ለምን መጣ?... ዛሬ ለምን ብሎ መጠየቅ ያልቻለው ህዝብ ለምኖቹን ማጠራቀሙ አይቀርም፡፡ ከለምን ወደ ለምንም አልመለስም እንዳይሸጋር ማሰብ ያስፈልጋል፡፡ እኛ ትልቅ ነገር እየሰራን ሊሆን ይችላል፡፡ ወደ ትላልቆቹ ተግባሮች የሚመጡትን ቀጫጭን ቧንቧዎች ቆሻሻ ከዘጋቸው ትልቁ ቧንቧ የት ይደርሳል?
በሀገራችን እንደሰንሰለታሙ ተራራ፤ ሰንሰለታማ ሙስና መኖሩን እየሰማን ነው (network of corruption መሆኑ ነው) እንደዋዛ የሚዘረጋ አይደለም-በአገራዊ መስክ ስናስበው፡፡ ይህ አይነኬ (insulated) ሰዎች መኖራቸውን ነው የሚናገረው:: ወይም ብረት-ለበስ ናቸው ማለት ነው:: ጥይት-ከላ (Bullet-proof) አካል የታደሉ፡፡ አንድ የፖለቲካ አቋሙን የቀየረ ፖለቲከኛን አንድ አድናቂው፤ “ብርሃኑን በማየትህ ተደስቻለሁ” አለው “አዬ ወዳጄ እኔ ብርሃኑን አላየሁም ይልቅስ ቃጠሎው፣ ቃጠሎው ነው የባሰብኝ!” አለ ይባላል፡፡ በሙስና ረገድ ቃጠሎው ገና የመጣ አይመስልም፡፡ በፓርቲ ቃጠሎ ገና ይፋ ያልሆነ ተቃጣይ ብዙ አለ፡፡ ሙስና የማያደርሰን ቦታ የለም! የናይጄሪያን ሙስና ጉድ ጉድ ስንል እኛው ሃዲድ እየሰራን ነው! “ጮሃ የማታውቅ ወፍ እለፉ እለፉ ትላለች!” ሆኗል! ኧረ ለምን እንበል!
ኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ የዓለም-አቀፍ ቀኖች ማክበር ወደ ፋሽንነት እየተቀየረ ይመስላል፡፡ የግሎባላይዜሽኑ በዓላዊ ገፅታ ካልሆነ በስተቀር ነው እንግዲህ፡፡ ቢቀናን “የጉዳይ-አስፈፃሚዎች ቀን” ብናከብር ለእኛ አግባብነት ሳይኖረው አይቀርም፡፡ ጉደኛ አገር ሆነናል እኮ፡፡ “ምን ትሰራለህ?” ሲባል ጉዳይ አስፈጽማለሁ ይላል አንድ ባለሙያ፡፡ የተማርከውስ አካውንቲንግ፣ ምህንድስና፣ ታሪክ፣ ማኔጅመንት ወዘተ ሲባል፤ “እሱን እንኳ በትርፍ ጊዜዬ እሰራዋለሁ” ይላል፡፡ ኢትዮጵያ ግን ይሄን ያህል የተማረ ዜጋ አለኝ ብላ ለዓለም ባንክ አስመዝግባለች፡፡ እሷም በትርፍ ጊዜዋ ካልሆነ!! ሰሞኑን “የአፍ መፍቻ ቀን” ተከብሯል፡፡ ለብዙ ዓመት የኢንፎርሜሽን ቀንም አክብረናል፡፡ ብዙ የነፃነት ቀኖችንም አክብረናል፡፡ የጀግንነት ቀናት ብዙ አሉን፡፡ የአድዋ ዋዜማ፣ የህውሃት ምስረታ ቀን አለ (የካቲት 11 እና የካቲት 23፤ የከተማ ልጆች ከአድዋ ወደ አድዋ እንዲሉ) ብዙ የፆም ቀኖችንም እናከብራለን፡፡  ዓለም-አቀፍ የጾም መያዣ ቀን ቢኖር ይገላግለን ይሆን? የኤች አይ ቪ ዓለም-አቀፍ ቀን አለ፡፡ የፍትህ ቀን አለ፡፡  የ ---- ቀን፣ የ ---- ቀን፣ የ----ቀን ብዙ ቀን አለን፡፡ (ተስፋዬ ካሳ የተባለው ኮሜዲያን .. “ኧረ ማታውን እንኳን ልቀቁልን” ብሎ ቀልዶ ነበር) እንደቀኖቹ ምክንያትና ብዛት .. ምነው ብዙ ደስታ በኖረን፣ ምነው ብዙ ተግባር በኖረን … ምነው ብዙ ፍቅር በኖረን! ግን የለንም፡፡ አንዳንዴ እንደኛ በኢኮኖሚ የደቀቁ አገሮች ቀኖቹን በውል ለማጣጣም ይችሉ ይሆን ያሰኛል? በባዶ ሆድ የእገሌ ቀን፣ የእንትን በዓል .. ምን ስሜት ይሰጣል? የሚል ብርቱ ጥያቄ ያስነሳል፡፡ ይሄንንም ለምን? ብለን እንጠይቅ፡፡ ትላንትም ዛሬም ምንም ዓይነት ስም እንስጣቸው፤
ሁኔታዎች በከፉ ቁጥር ትኩረት ሳንሰጣቸው ይገዝፉና አልነቃነቅ የሚሉ ይሆናሉ፡፡ ግምገማም፤ አዋጅም፣ ማስፈራራትም፣ ማፈራራትም፣ ካገር ማስወጣትም የማይበግራቸው ደረጃ፤ አይቀሬው ነገር ወደድንም ጠላንም ፈጦ ይመጣል - “መገነዣው ክር ከተራሰ፣ መቃብሩ ከተማሰ “እንደሚለው ነው አበሻ! ከወዲሁ አመጣጡን፣ ከወዲሁ አወጣጡን፣ ከወዲሁ ክፋቱን፣ ከወዲሁ ዐይነ-ውሃውን ስናየው ውጤቱ፤ አንድ የምናውቀው ፊልም እየመሰለን መጥቷል - አጨራረሱ የሚታወቅ!
“አለ አንዳንድ ነገር፣
አለ አንዳንድ ነገር
በዚህ ቢሉት በዚያ፣ ከመሆን የማይቀር”… ብለው ነበር ከበደ ሚካኤል፡፡
“መላጣ አናት ላይ ጠብ ያለች ውሃ እስካፍንጫ ለመውረድ ምን ያግዳታል?!” የሚለው የወላይታ ተረት መንፈሱ ይሄው ነው! ከዚህ ይሰውረን ጎበዝ!         

Read 4433 times