Saturday, 22 February 2014 13:08

“...አለም ከተማ እናት ሆስፒታል...”

Written by 
Rate this item
(0 votes)

“...ሀገራችን ፀሐይ ወጥቶ! አሁንማ ፀሐይ ወጥቶልናል። ሆስፒታላችን ከተሰራልን ወዲህ ምን ችግር አለ... ሞትማ እንዲህ በቀላሉም አይደፍረን፡፡ መቼም ነብስ የእግዚሀር ናትና ሲያበቃላት መትረፊያ የላትም እንጂ... እንዲህ በምኑም በምኑም አልጋ መያዝማ ቀርቶአል፡፡ ይኼው አሁን እኔን ከበሽታ ነጻ አውጥቶኛል፡፡ እዚህ ጉያዬ ስር አንድ ሕመም ነበረብኝ... ፍልፍል አድርጎ አውጥቶ ወርውሮልኝ... ይኼው አሁን ነጻ አውጥቶኛል፡፡ ሐኪሙም አየለ የሚባለው ዶ/ር ነው...”
ከላይ ያነበባችሁት በመርሐቤቴ አለም ከተማ እናት ሆስፒታል ያገኘናቸው አባወራ እማኝነት ነው፡፡ መርሐቤቴ በአማራው ክልል የምትገኝ ስትሆን ከአዲስ አበባ በጎጃም መንገድ መካጡሪ ከተማ ሲደረስ ወደ ቀኝ በመታጠፍ ወደ /111/ አንድ መቶ አስራ አንድ ኪሎ ሜትር ጥርጊያ መንገድ ተገብቶ የምትገኝ ነች፡፡ መርሐቤቴ ተራራማ ስትሆን ዠማ የሚባል ወንዝ መሐል ለመሐል የሚጉዋዝባት እጅግ አስደናቂ ተፈጥሮአዊ ውበት ያላት ናት፡፡ በእርግጥ ከስድስት አመት በፊት መንገዱ እንዲህ በዋዛ የማይደፈር ሲሆን አሁን ግን ዳገት ቁልቁለቱ እንዳለ ቢሆንም ጥርጊያው በማማሩ በጥንቃቄ መንዳት እንጂ እንደቀድሞው ሰውን ማሰቃየቱ አብቅቶአል፡፡ እንደሀገሬው ተስፋም ብዙም ሳይቆይ ወደ አስፋልትነት ይቀየራል፡፡ ግራና ቀኙን እያዩ የተራራውን አቀማመጥ፣ ተፈጥሮአዊ ሀብቱን እያደነቁ ከአንዱ ተራራ ወደአንዱ እየተ ዙዋዙዋሩ ሲጉዋዙ ድካሙን ሳያስቡ ከመርሐቤቴ አለም ከተማ ይደርሳሉ፡፡ አለም ከተማ መሐል አደባባይ ላይ አንድ ልጅ የታቀፈ ሰው ሐውልት ያያሉ፡፡ ቀረብ ብለው ሲያጣሩ ምስሉ የሜንሽን ፎር ሜንሽን መስራች የዶ/ር ካርል ሄንዝ ቦም  ነው፡፡ ሜንሽን ፎር ሜንሽን በመርሐቤቴ ከሰራቸው የልማት ስራዎች መካከል እናት ሆስፒታል አንዱ ሲሆን በመሀል ከተማው አደባባይ ላይ የሚገኘው ሐውልት ለአስተዋጽኦው ማስታወሻ ሐገሬው ለመስራቹ ዶ/ር ካርል ያቆመለት ሐውልት ነው፡፡ እኛም ፈልገን የተጉዋዝነው እናት ሆስፒታልን ነውና በመጀመሪያ የሆስፒታሉ ስራ አስኪያጅ የሰጡትን ማብራሪያ ለንባብ እንላለን፡፡
“...እኔ አቶ ደነቀ አየለ እባላለሁ፡፡ በዚህ ሆስፒታል ቀደም ሲል የጤና መኮንን ሆኜ የሰራሁ ስሆን አሁን ደግሞ ስራ አስኪያጅ ነኝ፡፡ በአለም ከተማ እናት ሆስፒታል የተሰራው በሜንሽን ፎር ሜንሽን አማካኝት ሲሆን የመሰረት ድንጋዩ እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር በ1991 ዓ/ም ተጥሎ በ1996 ዓ/ም በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ እና በሆስፒታሉ መስራች ዶ/ር ካርል ሄንዝ ቦብ ተመርቆ ህብረተሰቡን በማገልገል ላይ ይገኛል፡፡
ጥ/ ሆስፒታሉ እናት ሆስፒታል የተባለበት ምክንያት ምንድነው?
መ/    የሆስፒታሉ መጠሪያ እናት እንዲሆን የተወሰነው በመስራቹ በዶ/ር ካርል ነው፡፡ ይኼውም የመሰረት ድንጋይ በሚጣልበት ወቅት ለሚሰራው ሆስፒታልም ስም እንዲወጣ ህብረተሰቡ ተነጋግሮ ሁሉም ለምርጫ የሚሆነውን ስም በልቡ ይዞ ነበር ወደስፍራው የተሰበሰበው፡፡ ከወጣው ህብረተሰብ መካከልም ህጻናትም ይገኙ ነበር፡፡ ከህጻናቱ መካከል አንዲት በዝቅተኛ ደረጃ ከሚኖሩ ቤተሰቦች የተወለደች ልጅ በጣም ቆሽሻ፣ በዝንብ ተወርራ በሚያሳዝን ሁኔታ ቆማ ነበር፡፡ ዶ/ር ካርልም ከልጆቹ መካከል ብድግ አድርገው አቅፈው እያዘኑ ከተመለከቱዋት በሁዋላ ስሙዋ ማን እንደሆነ ጠየቁ፡፡ ስሙዋ እናት መሆኑ ሲነገራቸው  ...በቃ ሆስፒታሉ እናት ተብሎአል ብለው ወሰኑ፡፡ በጊዜው ህብረተሰቡ በተለያዩ  ስሞች ላይ ውይይት አድርጎ የነበረ ስለሆነ ለምን በሚል ቅር ቢለውም ውሳኔው በመወሰኑ ሆስፒታሉ እናት ሆስፒታል ተብሎ ተሰይሞአል፡፡ ልጅቱም በሰዎች ለሰዎች ድርጅት ከነቤተሰቦችዋ እየተረዳች ትምህርቷን እንድትቀጥል ተደርጎአል፡፡
ጥ/    ሆስፒታሉ ደረጃው ምንድነው?
መ/    አለም ከተማ እናት ሆስፒታል ደረጃው በመጀመሪያ ደረጃ ወይንም በወረዳ ደረጃ ዲስትሪክት ሆስፒታል ሆኖ የሚሰራ ነው፡፡ ከአካባቢው አቀማመጥ ጋር ተያይዞ ሌላም ተመሳሳይ የጤና ተቋም ባለመኖሩ በአካባቢው የሚኖሩ ወደ 250‚000 /ሁለት መቶ ሀምሳ ሺህ/ የሚሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን በማገልገል ላይ ነው፡፡ ከሌሎች አጎራባች ክልሎች ወይንም ዞኖች ...ለምሳሌ ከኦሮሞ የሚመጡትንም ተገልጋዮች አካቶ በርካታ ሰዎችን እያገለገለ ይገኛል፡፡ በአሁኑ ወቅት ወደ /158/ አንድ መቶ ሀምሳ ስምንት ሰራተኞችን የያዘ ሲሆን በተለይም ባለሙያዎችን በሚመለከት ከአምስት በላይ ዶክተሮች እና አንድ የጽንስና ማህጸን ሕክምና እስፔሻሊስት ስለሚገኝ ከደረጃው በላይ እየሰራ ነው ማለት ይቻላል፡፡
ዶ/ር አየለ ተሸመ በአለም ከተማ እናት ሆስፒታል የማህጸንና ጽንስ ሐኪምና የሆስ ፒታሉ  ሜዲካል ዳይሬክተር ናቸው፡፡
ጥ/ ዶ/ር አየለ መርሐቤቴን ለስራ ከመመደብ ውጭ አስቀድሞ ያውቁዋታል?
መ/ እኔ ተወላጅነቴም እድገቴም በዚሁ በመርሐቤቴ ነው። አሁን የምኖርበት ቤት ቀደም ሲል ጤና ጣቢያ የነበረና እኔም የተወለድኩበት ማዋለጃ የነበረ ቤት ውስጥ ነው፡፡ ከህክምና ትምህርት ቤት ተመርቄ እንደወጣሁ በጠቅላላ ሐኪምነትም የሰራሁት በዚሁ ሆስፒታል ነው፡፡ ከዚያም ለአራት አመት ያህል ከ2000-2004 እንደገና ስፔሻላይዜሽን ተምሬ በመመለስ የጽንስና ማህጸን ሕክምና እስፔሻሊስት በመሆን በማገልገል ላይ እገኛለሁ፡፡
ጥ/  ምደባው በአጋጣሚ ነው ወይንስ በምርጫ?
መ/ እኔ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሕክምና ትምህርት ቤት በጥቁር አንበሳ የመጀመሪያ ዲግሪዬን ስማር የማህጸን መፈንዳት ሪፖርት ሲደረግ ብዙዎች ከመርሐቤቴ የሚመጡ መሆናቸው የሚነገር ነበር፡፡ በጊዜው መንገዱ እጅግ አሳዛኝ እና አስቸጋሪ ስለነበር እንዲሁም የሚፈለገው ሕክምና በጊዜው በአካባቢው ካለው የጤና ጣቢያ አቅም በላይ የሆነ ችግር ስለሆነ ወላዶች በጣም ይሰቃዩ ነበር፡፡ በእርግጥ የሰዎች ለሰዎች ድርጅት አምቡላንስ ይሰጥ ስለነበር ወደአዲስ አበባ እንዲደርሱ የሚደረግ ቢሆንም ከመዘግየት የተነሳ ረጅም ጊዜ በምጥ በመቆየት ሴቶቹ ይጎዱ ነበር፡፡ እናም አንዳንድ ጊዜ የጠዋት ሪፖርት ላይ የማህጸን መፈንዳት ደርሶአል ሲባል ከየት ከመርሐቤቴ ናት? እስከማለት ድረስ መነጋገሪያ መሆኑ በጣም ያሳዝነኝ ነበር፡፡ በእርግጥ ካለው ዘርፈ ብዙ የጤና ችግር ምክንያት አንባቢው በጤና ጣቢያ ደረጃ ባለበት ጊዜም ሶስት እና አራት ሐኪሞች ይመደቡ የነበረ ቢሆንም ሐኪሞቹም በዚህ የመቆየት ፍላጎት ስለሌላቸው እና ከጤና ጣብያው አቅምም ጋር በተያያዘ በተለይም ለወላዶች በቀላሉ የማይፈቱ የጤና ጠንቆች ይገጥሙዋቸው ነበር፡፡ ስለዚህ እኔም ትምህርቴን ልጨርስ እንጂ በዚያ ገጠራማ ቦታ ገብቼ ህብረተሰቡን ማገልገል አለብኝ ብዬ ወሰንኩ፡፡ መጀመሪያ ላይ ምንም እንኩዋን ጠቅላላ ሐኪም ብሆንም የእናቶችን ችግር ስለማውቅ ከሰዎች ለሰዎች ድርጅት ጋር ተነጋግሬ ለሶስት ወር ለወላዶች የድንገተኛ ቀዶ ሕክምና ስልጠና አግኝቼ በማዋለድ ተግባር ላይ እንድሰማራ እራሴን አዘጋጀሁ፡፡ ከዚያም ከኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር በተገኘው እድል እንደገና ለስድስት ወር ባለሙያዎችን አሰልጥኜ እኔም ስራዬን እዚሁ ቀጠልኩ፡፡
ጥ/ በገጠር ሆስፒታል ውስጥ እስፔሻሊስት ይመደባልን?
መ/ በጀት ስለሌለ የገጠር ሆስፒታል ውስጥ እስፔሻሊስት አይመደብም፡፡ እናም የጤና ቢሮው እምቢ ቢልም ከዚህ የስራ አመራር ቦርድና ሽማግሌዎች ሄደው በማስፈቀዳቸው እና የእኔም ፍላጎት ስለነበረበት እንድመደብ ተደርጎ በመስራት ላይ ነኝ፡፡
ዶ/ር አየለ ተሸመ በስራቸው ያጋጠማቸውን እንዲህ ሲሉ አውግተዋል፡፡
“...አንዲት ሴት በምጥ ተይዛ በቤቷ ትቆይና ልጇን ትገላገላለች፡፡ ነገር ግን እንግዴ ልጁ እምቢ ስላለ ወደሆስፒታል ያመጡአታል፡፡ ሴትየዋ በሞት እና በህይወት መካከል ነበረች። ስለዚህም እንግዴልጁን ለማውጣት መጀመሪያ የደም ልገሳ እንደሚያስፈልግ ስንነግራቸው እንዴት ተደርጎ የሚል ነገር ተነሳ፡፡ እኛም ምንም ችግር የለውም አልንና... ባለቤቷን...
አንተ ባለቤቷ አይደለህም? አልነው... ነኝ የእርሱ መልስ ነበር፡፡ ታድያ ሚስትህ ከምትሞት አንተ ደም ስጥ... ስንለው  ...አረግ …እኔማ ገበሬ ነኝ ከየት አምጥቼ ነው ለእሷ ደም የምስጥ? መልሱ ነበር፡፡
በመቀጠልም እናትየውን አነጋገርን፡፡
አረግ ...እኔማ ልጄ ብትሞት አልሻም፡፡ ነገር ግን ...እኔ አሮጊት ነኝ ደም ከወዴት አመጣለሁ? ለእኔም አልበቃኝ... መልሳቸው ነበር፡፡ አብረው የነበሩትም ይልቁንም ሳትሞት ይስጡን እና እንውሰድ፡፡ ከሞተች መውሰጃውም አይገኝ ወደሚል ውይይት ገቡ፡፡ እኛም አይናችን እያየ እንዳትሞት ተነጋገርንና ሰዎቹን አስወጥተን ...አንድ ሰራተኛና አንድ አስታማሚ ደም ሰጥተው ህይወቷን አተረፍናት፡፡
ከዚያም ያ ደም የለገሰ ሰውየ ተናደደና ወደሰዎቹ በመሄድ ...ሴትየይቱ  እኮ ሞታለች ...ለምን አስከሬኑን አትወስዱም ሲላቸው... ከተማይቱ እስክትናወጥ ድረስ ኡኡታቸውን አቀለጡት፡፡ በሁዋላም በሉ ዝም በሉ ...እሱዋ ድናለች ሲባል ተደሰቱ፡፡  ከዚያም ወደህብረተሰቡ ሄደው ምስክርነታቸውን ሲሰጡ ለካንስ ይኼም አለ በሚል አሁን ደም የሚለግሱ ሰዎች ማህበር ተቋቁሞአል፡፡ ወደ ሁለት መቶ የሚደርሱ ሰዎች የደም ልገሳ ማህበርተኞች ሆነው ተመዝግበዋል፡፡ ስለዚህም ሰዎቹ የደም አይነታቸው፣ የሚኖሩበት አካባቢ፣ የስልክ ቁጥራቸው ተመዝግቦ የሚገኝ ስለሆነ አስፈላጊ በሆነ ጊዜ ካሉበት ድረስ አምቡላንስ እየላክን እንጠራቸዋለን፡፡ ከሰራተኞቹም እኔን ጨምሮ ፈቃደኞች የሆንን በየሶስት ወሩ ደም እንሰጣለን። እናት ሆስፒታል የደም ባንክ ባይኖረውም አስፈላጊው የላቦራቶሪ ስራ እየተሰራ ለተጠቃሚዎች ደም ይሰጣል፡፡ በእርግጥ ከአዲስ አበባም ደም ባንክ የተቻለውን ያህል ደም ቢሰጠንም በቂ ስለማይሆን ከህብረተሰቡ የሚደረግልን እገዛ ችግሩን አስቀርቶልናል፡፡ ይህም ጥሩ ተሞክሮ ስለሆነ ለሌሎች እንደምሳሌ የሚነሳ ሆኖአል፡፡
ይቀጥላል፡፡

Read 3694 times