Saturday, 22 February 2014 12:53

መንግስት ሆይ፤ የኩረጃ “ኤጀንሲ” ይቋቋምልን?

Written by  ኦርዮን ወ/ዳዊት
Rate this item
(2 votes)

ፈጠራ ብቻ ሳይሆን ኩረጃም የማይችል ትውልድ!

ጽሑፌን የሚያነብቡ ሰዎች “የተሳሳተ ማጠቃለያ ሰጥተሃል፤ በርካታ የፈጠራ ባለሙያዎች በአገራችን የሉም ወይ?” የሚል ጠንካራ ጥያቄ ሊያነሱልኝ ይችላሉ፤ ጥያቄያቸው ደግሞ ተገቢ ነው፡፡ ግን “ትውልድ” ስል ራሴን ጨምሬ እየወቀስሁ መሆኑም ግምት ውስጥ ሊገባልኝ ይገባል፡፡ እንዲያውም ኃይሉ ገብረ ዮሐንስ (ገሞራው) በ1966 “በረከተ መርገም” በሚል ርዕስ ካሳተመው ረጅም ግጥሙ ውስጥ የሚከተሉትን ስንኞች ብቻ ብጠቅስ አቋሜን ይገልጹልኛል ብዬ አምናለሁ፡፡
“… በእሱነቱ ግምት፣ በተዛባ መንፈስ መሰሌን መርገሜ ኃጥእ ነው ቢያሰኘኝ፣
ራሴው በራሴ የእኔው ገሃነም ነኝ”
ስለሆነም በትውልዴ ውስጥ ፈጠራና ጥሩ ነገር ካለ የእኔ ድርሻ ጥቂትም ቢሆን ቦታ ይኖረዋል፤ ትውልዴ ከሰነፈና አገሬ ከጠቅላላ ችጋር ካልወጣች ከተወቃሾች ታሪክ ውስጥ ተገቢው ድርሻ ይኖረኛል ብዬ አምናለሁ፡፡ ለዚህም ነው ተገቢ በሆነ ድፍረት ትውልዴን በጅምላ ልወቅሰው የተነሳሁት፤ በነገራችን ላይ “ትውልድ” ስል መንግሥትንም ይጨምራል፡፡ በኩረጃ በተደነቁ የዘመናችን ፖለቲከኞች የሚመራ የትውልዱ ዋናው ቁንጮስ እሱ አይደለም?
የወቀሳዬ ዋና ፍሬ ነገር ኩረጃ ነው፡፡ መንግሥት በ“አንድ ለእናቱ” ቴሌቪዥኑና ሬዲዮ ጣቢያው የ10ኛ እና የ12ኛ ክፍል ፈተና ጊዜ በቀረበ ቁጥር “ኩረጃ ወንጀል ነው፤ ሲኮርጅ የተገኘ ተማሪ ፈተናው ዋጋ ቢስ ይሆናል፤ አስኮራጁም ተመሳሳይ ዕጣ ይደርሰዋል” እያለ እስኪሰለቸን ድረስ ይነግረናል፡፡ ለትምህርት ጥራት ጠንክሮ እንደሚሰራም በየጊዜው ይምል ይገዘታል፡፡
በመገናኛ ብዙኃኑ አማካይነት የኩረጃን አደገኛነት እየሰበከ፣ራሱ ግን ያውም ከፍተኛ ዶላር እየመነዘረ ቱባ ባለሥልጣናቱን በየሀገሩ ለኩረጃ ይልካል፡፡ ባለሥልጣናቱ የተላኩበትን የኩረጃ ተልዕኮ በአግባቡ ስለማይወጡም ድካማቸው ሁሉ ከንቱ ይሆናል፤ ዶላሩም አለት ላይ የተዘራ ዘር ሆኖ ይቀራል፡፡ ማስረጃ ልጥቀስ፡-
ለዘመናት ሥር ሰድዶ የኖረውን የሲቪል ሰርቪስ አደረጃጀትና አገልግሎት አሰጣጥ ዘመናዊ ለማድረግ አስቦ በ1993/94 አካባቢ ባለስልጣናቱን ወደተለያዩ አገሮች ልኮ ነበር፡፡ በየሀገሩ ተጉዞው የነበሩት ባለሥልጣናትና አጃቢዎቻቸው (ጥቃቅን ባለሥልጣናት) በተሰጣቸው ዶላር የሆኑትን ሆነው ከተመለሱ በኋላ “በሲቪል ሰርቪሱ ውስጥ የነበረው ችግር ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ዕልባት ሊያገኝ ነው” ተብሎ ሌት ከቀን ተሰበከ፤ ቁጥሩ የማይገመት መዋዕለ ንዋይ እየወጣም በአውደ ጥናት፣ ሲምፖዚየምና ሴሚናር ስም በየሆቴሉ ተበተነ፡፡ በፕሮፓጋንዳ የማለለው ህዝብ “ተአምር ሊፈጠር ነው” ብሎ ሲጠብቅ በወቅቱ የአቅም ግንባታ ሚኒስትር የነበሩትና ጥሩም ይሁን መጥፎ እንደልባቸው በመናገር የሚታወቁት አቶ ተፈራ ዋልዋ ድንገት በቴሌቪዥን መስኮት ብቅ አሉና “የሲቪል ሰርቪስ ማሻሻያ ፕሮግራሙ ጨንግፏል” አሉ፡፡
እርግጥም ያ ብዙ የተደከመበት፤ በወረቀት፣ በቀለም፣ በውሎ አበል፣ በጽሑፍ አቅራቢነት፣ በአዳራሽ ኪራይ እና በመሳሰሉት የትየለሌ ገንዘብ የባከነበት መርሐ ግብር፣ ጠብ የሚል ቁም ነገር ሳይታይበት የውሃ ሽታ ሆኖ ቀረ፡፡ መንግሥት ከዚህ ቢማር መልካም ነበር፤ ግን ሌላ ስም አወጣና ሌላ ጉዞ ወደ አሜሪካ፣ አውሮፓና ኤሽያ ጀመረ። ዘመቻውንም “ዘመቻ ቢፒአር” ብሎ ጠራው፡፡ አሜሪካዊው የምጣኔ ሃብትና የመዋቅራዊ ችግሮች ዘዴ ቀያሽ እንደሆኑ የሚነገርላቸው ሐመርና ሌሎች የሰሯቸው መጻሕፍት እየተባዙም በየመንግሥት ተቋማቱ ተበተኑ፤ እንደ ማርክሲስት ሌኒኒስት ካድሬዎች በርካታ ጮሌዎች በየመድረኩ ብዙ ለፈለፉ፡፡
በዚህም “አሁን ገና ለውጥ መጣች” ተባለ፤ ግን ለውጡ የመጀመሪያው (በአቶ ተፈራ አባባል የጨነገፈው) “የሲቪል ሰርቪስ ማሻሻያ ፕሮግራም” ሲባል ሁለተኛው “ቢፒአር (መሠረታዊ የአሠራር ሂደት ለውጥ)” መባሉ ብቻ ነው፡፡ እርግጥ ነው ቢፒአር ነባሩን የተቋማትና መምሪያዎችን እንዲሁም ዋና ክፍሎችን ስም አጥፍቶ በሥራ ሂደት መሪ፣ዳይሬክቶሬት፣ ዳይሬክተር፣ ወሳኝ የሥራ ሂደት ባለቤት፤ ኤጀንሲ፣ ኮሚሽን፣ ወዘተ--- አይነት ግራ አጋቢ ስሞችን አትርፏል፡፡ “መልከ ጥፉን በስም ይደግፉ” እንደማለት ነው፡፡ ወይም የሀገራችን ፖሊስ ባለ ማዕረጐች ኢትዮጵያዊ በሆነውና ህዝቡ በለመደው የማዕረግ ሥም መጠራታቸው ቀርቶ “ሳጅን፣ ዋና ሳጅን፣ ኢንስፔክተር፣ ወዘተ” የሚል የተውሶ የማዕረግ ስም ከእንግሊዝ እንደመጣላቸው  ማለት ነው፡፡ እውነት ለመናገር ሲጠሩት ደስ የሚለው “ሻለቃ፣ መቶ አለቃ፣ ሃምሳ አለቃ፣ አስር አለቃ፣ ወዘተ ሲባል ነው ወይስ ግራ በሚያጋባው “ኮንስታብል” አይነት መጠራት? ኮንስታብል መታወቂያ ላይ ሲጻፍ “ኮ/ል” ተብሎ ስለሆነ ብዙ ሰው “ኮሎኔል” እያለ ለመጥራት መገደዱን ከፖሊስ አካባቢ የሚወጡ ወጐች ያስረዱናል፤ “ኮንስታብል” ማለት’ኮ “ተራ ወታደር” ማለት ነው፡፡ ታዲያ ለምን ስም እንኮርጃለን? በኩረጃስ ለምን እንደናገራለን?
የመንግሥት ኩረጃ በቢፒአር አላቆመም፤ በለውጡ የተገኙ ውጤቶችን ሲነግረን “የሰነዶች ማረጋገጫና የውልና ማስረጃ ጽ/ቤት” እንዲሁም “የኢምግሬሽንና የዜግነት ጉዳይ ዋና መምሪያ ቀልጣፋ አገልግሎት በመስጠት አርአያ ለመሆን በቁ” ተብሎ ተጨበጨበላቸው፤ ግን እውነታው በግልባጩ ሆነና አረፈው፡፡ በተለይ የኢምግሬሽንና የዜግነት ጉዳይ ዋና መምሪያ ወደ ተለያዩ አገሮች ለመሰደድ ገና ከንጋቱ 11 ሰዓት ጀምሮ በሚኮለኮሉ ዜጐቻችን ተከብቦ መዋልና አገልግሎቱን ለማግኘት እስከ አምስት ወራት የሚደርስ ቀጠሮ ለመስጠት ተገደደ፡፡ ግን ይህንን ችግር የሰው ኃይልና ተጨማሪ ቢሮዎችን በጊዜያዊነትም ቢሆን በመክፈት ማቃለል ይቻል ነበር፡፡
መንግስት ህግ ሲያወጣም እየኮረጀ ነው፣ “የመረጃ ነፃነት ህጉ እና የፀረ-ሽብር ህጉ አያሰሩም አፋኝ ናቸው” ሲባል፣ብዙዎቹ አንቀፆች እገሌ ከተባለው ሥልጡን አገር ቃል በቃል የተቀዳ ነው ይላል - ደረቱን ነፍቶ፡፡   ጥያቄው ግን “ለምን ኩረጃውን ትተህ በኢትዮጵያዊ ህግ አትመራም?” የሚል ነው፡፡ አሁን ደግሞ መንግሥት ፊቱን ወደ ጃፓን አዞረና “የችግሮች ሁሉ መፍቻ ጠንካራው ዘዴ የአንድ ለአምስት አደረጃጀት ብቻ ነው” ብሎ ለተግባራዊነቱ ደፋ ቀና እያለ ነው፡፡ “ቢኤስሲ” የሚባል የአሰራር ዘዴ ሥራ ላይ ማዋል ከጀመረም ቆየ፤ ግን ውጤቱ ሁሉ ጉቦኛነት እና በሙስና የተዘፈቁ በርካታ ደቀመዛሙርትን ከመፈልፈል በቀር ጠብ ያለ ነገር የለም፡፡ ምክንያቱም ዘዴዎቹ ሁሉ በኩረጃ የተገኙ ናቸዋ! የሃገራችንን ዘርፈ ብዙ ችግሮች ለመፍታት መፍትሔው ኩረጃ ሳይሆን ኢትዮጵያዊውን የአስተዳደር ዘይቤ በአግባቡ አጥንቶ መተግበር ነው፡፡ እንዲያ አድርገው ሲያበቁ የጐደለ ሲኖር ከውጭ መበደር የአባት ነው፡፡ አለዚያ ግን ከንቱ መዋተት ነው፡፡
ኩረጃን ከመንግሥት የኮረጁት ኮራጆች በየቦታው ሞልተዋል፡፡ ማንነታቸው አሳፍሯቸው ወይም የሰለጠኑ እየመሰላቸው የልጆቻቸውን ስም፣ የንግድ እና የቤት እንስሶቻቸውን ስም ሳይቀር በባዕዳን ስሞች እየተኩ ናቸው፡፡ ከሁሉም በላይ አደገኛው ኩረጃ የሚስተዋለው በኪነ-ጥበቡ መስክ ነው፡፡ አንዱ ድምፃዊ የሌላውን ይኮርጃል እንጂ አይፈጥርም፤ የፈጠራ ስራ ባለመኖሩም ጆሮአችን ውስጥ የሚገባ ዘፈን መስማት እየናፈቀን ነው፡፡
በእነ ጥላሁን ገሠሠ፣ አለማየሁ ቦረቦር፣ መሐሙድ አህመድ፣ ዓለማየሁ እሸቴ፣ ሂሩት በቀለ፣ አበበ ተሰማ፣ ብዙነሽ በቀለ፣ ሙሉቀን መለሰ፣ ወዘተ--- ዘመን የነበሩ ዘፈኖች ሁሉ በጊዜያቸው ብቻ ሳይሆን ዛሬም በፍቅር ይደመጣሉ፡፡ ምክንያቱም ጥርት ያሉ፣ ኢትዮጵያዊ የፈጠራ ሥራዎች ናቸዋ! የሚገርመው ደግሞ የዚያ ሁሉ ፈጠራ ባለሙያዎች የነበሩት በትምህርት እምብዛም ያልገፉ፣ ወይም ስማቸውን እንኳን መጻፍ የማይችሉ ነበሩ፡፡ ለምሳሌ አለማየሁ ቦረቦር ሲፈርም እንኳ በጣቱ ዱካ እንጂ የፊደሉን እጅና እግር መለየት እንደማይችል ከታሪኩ አንብቤያለሁ፤ ግን ዘፋኝ ብቻ ሳይሆን ድንቅ የዜማና የግጥም ደራሲም ነበር “በላይ በላይ፣ ዓባይ ማዶን፣ ያችውና መጣች፣ መስታወቴን፣ አንችና አንችዋ፣ ተው እረስ ገበሬ …” በራሱ ዜማና ግጥም የተጫወታቸው ናቸው፡፡ አበበ ተሰማም በዚያ በማይሰለች ድምፁ ካቀነቀናቸው በርካታ ዘፈኖቹ ውስጥ አብዛኛው ግጥምና ዜማ የራሱ ነበር፡፡
ዛሬ እንደ አበበ ተሰማ፣ እንደ ዓለማየሁ ቦረቦርና እንደ ጥላሁን ተንሰፍስፈን የምናዳምጠው ዘፈን ያጣነው ኩረጃ ላይ በማተኮራችን ነው፡፡ መንግሥት የራሱ ኮራጅነት አንሶ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የኩረጃ “ጥበብ” የሚስተናገድበት መድረክ ከፍቷል። መድረኩ “የባላገሩ አይዶል” የሚባለው ነው፡፡ ቀደም ሲልም “ኢትዮጵያን አይዶል” የሚባል የኩረጃ መርሃግብር ነበር፡፡ ልብ አድርጉ! ስሙ ራሱ የኩረጃ ነው “አሜሪካን አይዶል” ከሚባለውና ከሌሎች አገሮች የተኮረጀ፡፡
“የባላገር አይዶል” ገንዘብ እየተከፈለው የሚያወዳድረው ግልገል ኮራጆችን ነው፤ ነገ የተዋጣላቸው ኮራጆች ሆነው አገርን እንዲያስጠሩ በማሰብ የሚካሄድ መርሃ ግብር፡፡ ምን አለ ይህንን ሃሳብ በፈጠራ ስራዎች ላይ ቢያደርጉትና ከዚያ ሁሉ መንጋ ኮራጅ መሃል በጣት የሚቆጠሩ ወጣቶች በራሳቸው የፈጠራ ስራ ሲወደሱ ብናይ? ዳሩ የውድድሩ ዓላማና ግብ ፈጠራን ማበረታታት ሳይሆን ገንዘብና ሌላ ነው፡፡
ይህን እውን ለማድረግ ከፈረንጅ መኮረጅ አያስፈልግም፤ አገራችን ውስጥ ያሉ ነባር የጥበብ ተቋማትን ለምሳሌ ቅኔ ቤትን መጎብኘት ብቻ በቂ ነው፡፡ አንድ የቅኔ ተማሪ ወይም ዘራፊ አንድ ቦታ የተቀኘውን የራሱን ቅኔ ሌላ ቦታ መልስ መቀኘት አይችልም፡፡ ከእነ ምሳሌው “የቅኔ ቋንጣ የለውም” ነው የሚባል፡፡ ይህ የሚያገለግለው ታዲያ በየቀኑ ቅኔ እንዲቆጥር፣ በየጊዜው እንዲመራመር ነው። ይህ ዘዴም የቅኔ ጥበብ በአገራችን እንዲያብብ አድርጎታል፡፡ ታዲያ ጥበብን እንጂ ኩረጃን ለምን እናበረታታለን?
በአገራችን ዜማው ብቻ ሳይሆን ትክክልም ይሁን አይሁን አለባበስም ይኮረጃል፤ የማንም የባህል ልብስ ያልሆነ ጥብቆ አንድ ዘፋኝ ለብሶ ከታየ ምድረ ኮራጅ “ለምን?” ብሎ ሳይጠይቅ በነጋታው ለብሶት ብቅ ይላል፡፡ ልብስ ብቻ ሳይሆን አነጋገርም ይኮረጃል፤ የፖለቲካ መሪዎች “… ያለበት ሁኔታ ነው ያለው” ሲሉ የሰሙ ጋዜጠኞች ሁሉ ይህንኑ እየደጋገሙ ያሰለቹናል፡፡ መንግሥት ሆይ! ካልሆነ ኩረጃን በሥርዓት የሚመራ የኩረጃ “ኤጀንሲ” አቋቁምልን!


Read 2206 times