Saturday, 22 February 2014 12:37

የጥብቅና ሞያ ሥነምግባር ጉድለቶችን ለማረም ምን ይደረግ?

Written by 
Rate this item
(4 votes)

የጥብቅና ሞያን በፈቃደኝነት ላይ በተመሰረተ የሲቪክ ማኅበር ማስተዳደር አይቻልም
የሌሎች አገራት የሕግ ባለሞያዎች ወይም የጠበቃ ማኅበራት የሚሰሩት እንዴት ነው?
የህግ ባለሙያ ድርጅቶች (ፈርሞች)  ስላላቸው ፋይዳ ያብራራሉ
በቅርቡ የአገር አቀፍ የፍትህ ዘርፍ የፍትህና መልካም አስተዳደር መድረክ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በተገኙበት ተካሂዶ ነበር፡፡
በመድረኩ ላይ በተለይ ከጠበቆች የሥነምግባር ችግሮች ጋር በተገናኘ በተነሱ ጉዳዮች ዙርያ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ኤልሳቤት እቁባይ ከጠበቆች ማህበር ፕሬዚደንት አቶ ወንድምአገኘሁ ገብረስላሴ ጋር ሰፊ ቃለምልልስ አድርጋለች፡፡


የአገር አቀፍ የፍትሕ ዘርፍ የፍትሕና መልካም አስተዳደር መድረክ ጉባዔ እንዴት ነበር?
 ጥሩ ነበር፡፡ በፍትሕ ሥርአቱ ላይ የሚታዩ በርካታ ችግሮች ተነስተዋል፡፡ መፍትሔም ሊሆኑ ይችላሉ የተባሉ ኃሳቦች ቀርበዋል፡፡ ችግሮቹንም ለማቃለል እቅድም ተዘጋጅቷል፡፡ የታሰቡት ነገሮች በሙሉ እንኳን ባይሆኑ በአብዛኛው ሥራ ላይ ከዋሉ መልካም መሻሻሎች ሊታዩ ይችላሉ ብዬ እገምታለሁ፡፡
 ከተነሱት ችግሮች አንዱ የሕግ ባለሞያዎች ወይም ጠበቆች በፍትሕ አሰጣጥ ረገድ መደገፍና መርዳት ሲገባቸው ፍትሕ እንዲጨናገፍ ያደርጋሉ፣ ጉቦ ያቀባብላሉ፣ ከጥብቅና ሥነምግባር ውጭ ይሰራሉ የሚል ነው፡፡ በዚህ ወቀሳ ላይ የእርስዎ አስተያየት ምንድነው?
 በስብሰባው ላይ ከፍተኛ ትኩረት ተሰቶት ከነበረው መሰረተ ሃሳብ አንዱ ሁልጊዜ ውጫዊ ምክንያቶች ላይ ብቻ ከምናተኩር የራሳችንን የውስጣችንን ሁኔታ እንመርምርና ለችግሮቻችን መፍትሔ እንስጥ የሚል ነው፡፡ በዚህም ላይ ተመስርቶ በዳኝነት ሥርዓቱ ላይ የሚታዩ ችግሮች፣ በአቃቤ ሕግ መሥሪያ ቤት ላይ የሚታዩ ችግሮች፣ በፖሊስ እና በሌሎችም ተዛማጅነት ባላቸው ተቋማት ላይ የሚታዩ በጣም በርካታ ችግሮች ተነስተዋል። እንደውም ለጉባኤው የቀረበው ሪፖርት በዋናነት ያተኮረው ችግሮች ላይ ብቻ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ይህ እንግዲህ ቀደም ሲል ከሚታዩት ሪፖርቶች ጋር ሲነፃፀር በጣም የተለየ ነው፡፡ በአብዛኛው በየቤታችን የምናነሳቸው ችግሮች በሪፖርቱ ውስጥ ተካተዋል። ችግሮቹ በዚህ አይነት መልክ ተነቅሰው ከወጡ ደግሞ ፈቃደኝነትና ቅንነት ታክሎበት መፍትሔ ሊያገኙ ይችላሉ የሚል ተስፋ ይሰጣል። ከዚህ አኳያ ሲታይ የሕግ ባለሞያዎች በተለይም ደግሞ ጠበቆችን በተመለከተ የቀረበው ሪፖርት፣ በሌሎቹ የፍትሕ ሥርዓት አካላት ላይ ከሚታየው ችግር የተለየ እንዳልሆነ ማየት ይቻላል፡፡ ጉቦ ሰጭ አለጉቦ ተቀባይ አይኖርም፡፡ ፈረንጆቹ እንደሚሉት ታንጎ ለመደነስ ሁለት ደናሾች ያስፈልጋሉ፡፡ ስለዚህ ችግሩ በሁሉም ቤት ያለ ነው ማለት ነው፡፡ እኛም ብንሆን የምንሰማቸው ስሞታዎች አሉ፡፡ እንዲያውም ብዙ ጥሩ ችሎታና ሥነምግባር ያላቸው ጠበቆች፣ ከሚያዩትና ከሚሰሙት ችግር ለመሸሽ ከሥራው የመራቅ ሁኔታ ሁሉ ይታያል፡፡ ከዚህ በፊት ቅር ያሰኘን የነበረው ወቀሳ “ጠበቆች ሲባሉ በአብዛኛው ችግር አለባቸው” የሚል አንድምታ ያለው አገላለፅ ይቀርብ ስለነበር ነው፡፡ የችግሩም ምክንያቶች ጠበቆች ብቻ እንደሆኑ በሚመስል ሁኔታ ነበረ የሚገለጸው፡፡ በዚህኛው ጉባኤ ላይ ግን አጥፊዎች ቢኖሩም ብዙዎቹ ጠበቆች  የሞያ ስነምግባራቸውን አክብረው እንደሚሰሩ፣ እንደውም ከእነዚህ ጠበቆች ጋር በመሆን ችግሩን ተጋፍጠን እናስተካክለዋለን የሚል መንፈስ የተንፀባረቀበት በመሆኑ ከቀደሙት ጊዜያት በጣም የተሻለና የተለየ ነው፡፡ እኔም ከጠበቅሁት በላይ አስደስቶኛል፡፡
 ጥብቅና ሞያ እንደመሆኑ መጠን የሞያውን ስነምግባር ሳያከብሩ መገኘትን እንዴት ያዩታል?
 እውነት ነው፤ ጥብቅና በጣም ረጅም ዕድሜ ያለው ሞያ ነው፡፡ እንደውም እስከቅርብ ዘመን ድረስ እንደ ሞያ ይቆጠር የነበረው የሕግ ሞያና ሕክምና ነበር፡፡ እነዚህ ሞያዎች የእድሜያቸውን ርዝመት ያህል በጣም በርካታ የሞያ ደንብ፣ ስነምግባርና ዲሲፕሊን ያላቸው ናቸው፡፡ ሞያ እንዲባሉ ካበቃቸውም ነገር አንዱ የሞያ ሥነምግባርና ዲሲፕሊን ያላቸው መሆናቸውም ጭምር ነው፡፡ ከዚህ አኳያ ሲታይ አንዳንድ የሞያው አባላት ጉድለት ሲታይባቸው ማሳዘኑ አይቀርም፡፡ የስነምግባርና ዲስፕሊን ጉድለቶች በሞያው ክብርና ግርማ ሞገስ ላይ የራሳቸውን ጥላ ማጥላታቸው አይቀርም፡፡ ታዲያ በዚህ ሁኔታ ጉዳቱ አመዝኖ የሚታየው ችግሩን በፈጠሩት ሰዎች ላይ ሳይሆን በአጠቃላይ በሞያው እና ስርአት ጠብቀውና አክብረው በሚሰሩ ባለሞያዎች ላይ ነው፡፡ የዚህ አይነት ችግር እየተስፋፋ ሲሄድ፣ የሚጎዳው ችግር ፈጣሪውን ሳይሆን መልካም ስነምግባር ያለውን ባለሞያ፣ የፍትሕ ሥርዓቱንና አገርን በአጠቃላይ በመሆኑ አሳሳቢ ችግር መሆኑ አይካድም፡፡ እንደግለስብ እንዲሁም እንደ የሕግ ባለሞያዎች ማኅበር መሪነቴ በጣም ያሳስበኛል፡፡ ያሳዝነኛልም። ሆኖም ግን ሁላችንም ሰዎች በመሆናችን የተለያየ አስተሳሰብ፣ እምነትና አመለካከት ሊኖረን ይችላል። በዚህም የተነሳ ምንም ጊዜ ቢሆን ከመስመር ወጣ የሚሉ ሰዎች መኖራቸው አይቀርም፡፡ የሕግ ሞያ ከዚህ ሙሉ በሙሉ ንጹህ ይሆናል ብሎ መጠበቅም አይቻልም፡፡ አልፎ አልፎ ደግሞ ሆን ተብለው ሳይሆን በአጋጣሚ የሚፈጠሩ የሥነምግባር ጉድለቶችም ይኖራሉ፡፡ ዋናው ነገር ችግሮች ለምን ይፈጠራሉ ወይም መፈጠር አልነበረባቸውም ብሎ ማማረር ብቻ ሳይሆን ችግሮች እንዳይፈጠሩ የሚረዳ፣ ችግሮች በተለያየ ሁኔታ ከተፈጠሩም በኋላ አግባብ ባለው ሁኔታ የእርምት እርምጃ የሚወስድ ተቋማዊ ስርአት ማደራጀትና በአግባቡ እንዲሰራ ማድረግ ነው፡፡ ይህ የሆነ እንደሆነ የስነምግባርም ሆነ ሌሎች ችግሮች እንደሁኔታው አፋጣኝ፣ አግባብ ያለውና ፍትሐዊ የሆነ መፍትሄ ያገኛሉ፡፡ ይሄን እውን ለማድረግ መሥራት አለብን ብዬ አምናለሁ፡፡  
እስካሁን  ይህን ችግር ለማቃለል ወይም ለማስወገድ ምን የሠራችሁት ሥራ አለ?
 ጥሩ ጥያቄ ነው፡፡ ይህንን ጥያቄ ለመመለስ ግን ትንሽ የማኅበራችንን ባሕርይ ማየት የሚያስፈልግ ይመስለኛል፡፡ ምናልባት እንደምታውቀው፣ ማኅበራችን የተቋቋመው በ1957 ዓ.ም ሲሆን ሲቋቋም የነበረው ዓላማ የመረዳጃ ዕድር መልክ የያዘ ነበር፡፡ ቀስ በቀስ እና ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ  ዓላማውን በማሻሻል የጠበቆች ማኅበር ሲባል ቆይቶ አሁን ደግሞ የሕግ ባለሞያዎች ማኅበር ለመሆን በቅቷል፡፡ በ2002 ዓ.ም ተሻሽሎ የፀደቀው የማኅበሩ ዓላማዎች፣ የፍትሕ አስተዳደር በተቀላጠፈ ሁኔታ እንዲካሄድ መርዳት፣ የፍትሕ ስርአቱ እንዲሻሻል ማገዝ፣ የሕግ የበላይነት እንዲሰፍን መርዳት፣ የሕግ ሳይንስ (jurisprudence) እንዲዳብር መርዳት፣ የሙያ ሥነምግባር ደረጃውን የጠበቀ እንዲሆን መጣር፣ አቅም ለሌላቸው ሰዎች ነፃ የሕግ አገልግሎት መስጠት፣የሕብረተሰቡ የሕግ ንቃተ ህሊና እንዲድግ መስራት፣ በአባላት መካከል መቀራረብና መተባበር እንዲዳብር ማድረግ የሚሉት ወዘተ.. ሲሆኑ፣ ማንኛውም የሕግ ባለሞያ የሆነ ሰው አባል መሆን ይችላል፡፡ ማለትም ማኅበሩ የፈቃደኝነት ማኅበር ነው፡፡ ጠበቃም፣ ዓቃቤ ሕግም፣ የሕግ ት/ቤት መምሕራን፣ በመንግሥት መሥሪያ ቤት ውስጥ የሚሰሩ የሕግ ባለሙያዎችም ወዘተ. አባላት ሊሆኑ ይችላሉ። የፈቃደኝነት ማኅበር በመሆኑም ሊሰራ የሚችለው አባላቱን በማስተባበርና መልካም ሥነምግባርን መከተል እንዳለባቸው፣ የሞያው ክብርና ሞገስ እንዲያድግ የድርሻቸውን እንዲወጡ በመምከርና በማሳሰብ ነው፡፡ ይህ ደግሞ የውይይትና የሥልጠና ፕሮግራሞችን በማዘጋጀት፣ማሳሰቢያዎችን ከመስጠት ያለፈ አይደለም፡፡ የስነምግባር ጉድለት የሚፈጽሙ የሕግ ባለሞያዎችን ወይም አባላቱን የሚያርምምበት ወይም የዲሲፕሊን ቅጣት የሚጥልበት ኃይልና ስልጣን የለውም፡፡ በርግጥ አባላት በውሳኔያቸው ማኅበሩ ዲሲፕሊን እንዲቆጣጠርና ጥሰት በሚፈጽሙ አባላት ላይ የቅጣት ውሳኔ እንዲያሳልፉ መስማማት ይችላሉ። ይህ ግን ሊሆን የሚችለው በአባላቱ ላይ ብቻ ሲሆን አባላቱም ቢሆኑ በዚህ ውሳኔ እስካልተስማሙ ድረስ ማኅበሩን ለቀው መውጣት ይችላሉ፡፡ ስለዚህ ማኅበሩ የራሱ የሆነ ምንም አይነት አስገዳጅ ሥልጣንና ኃይል የለውም። ይህ ባልሆነበት ሁኔታ ሊያደርግ የሚችለው አባላቱ በበጎ ፈቃዳቸው የሞያው ሥነምግባር ተገዢዎች እንዲሆኑ ማበረታትና መምከር ነው። ይህንን ደግሞ አቅም በፈቀደ መጠን በማድረግ ላይ እንገኛለን፡፡ ሲጠቃለል፣ የኛ ማኅበር በአባላት የተቋቋመ የሲቪክ ማኅበር ነው፡፡ ከዚህ የተለየ ሥራ መስራት አይቸልም፡፡  የሌሎች አገር የሕግ ባለሞያ ወይም የጠበቃ ማኅበራት ግን ሰፋ ያለ ኃይልና ሥልጣን አላቸው፡፡
 እንዴት ነው የሌሎች አገራት የሕግ ባለሞያዎች ወይም የጠበቃ ማኅበራት የሚሰሩት?
የሌሎች አገራትን በተመለከተ የተለያዩ ልምዶች መጥቀስ ይቻላል፡፡ መሰረታዊው ነጥብ ግን የጠበቆች ማኅበራት ሦስት ዋና ዋና ተግባራትን ያከናውናሉ፡፡ 1. ሞያውን የማስተዳደር፣ ማለትም ፈቃድ መስጠት፣ የዲሲፕሊን ደንቦችን የማስከበርና የማስፈጸም፣ የሕግ ትምሕርት የሚሰጥበትን ደረጃ መወሰን፣ ለጠበቆች ተከታታይ የሕግ ሞያ ስልጠና መስጠት፣ ከዳኝነት አካሉና ከሕግ አስፈፃሚው አካል ጋር የጥብቅና ሞያንና ሥራን በተመለከተ ተፈፃሚ በሚሆኑ ደንቦች፣ ሥነሥርአቶች፣ የሥነምግባር ደንቦች እና በመሳሰሉት ጉዳዮች ላይ በጋራ መሥራት እና የመሳሰሉትን ሥራዎች ማከናወን፤ 2. የሕዝብ አገልግሎት ሥራዎችን መስራት፣ ማለትም፣ ከፓርላማ ጋር በመተባበር የሚሰሩ ተግባራትን ለምሳሌ በሕግ ረቂቆች ላይ በሚደረግ ዝግጅት፣ ውይይት መሳተፍ፣ አስተያየቶችን አዘጋጅቶ ማቅረብ፣ ነፃ የሕግ አገልግሎት መስጠት፣ ለሕግ የበላይነትና የፍትሕ ሥርዓቱ እንዲጠናከር መስራት፣ 3. ሞያውን መወከል፣ ይህ የሞያ ማኅበር ወይም የዩኒየን ተግባራትን የሚመለከት ሲሆን፣ ሞያውን በመንግሥትና በተለያዩ ወገኖች ዘንድ መወከል፣ ከሌሎች የሞያና ሲቪክ ማኅበራት ጋር መስራት፣ ሕግን፣ የሞያ ስነምግባርን በጠበቀ መልኩ ለአባላት መብትና ጥቅም መቆምን ይጨምራል። በብዙ ሀገራት የሞያ ማኅበራቱ መጀመሪያ በፈቃደኝነት ላይ ተመስርተው ከተቋቋሙ በኋላ ቀስ በቀስ በሕግ የተቋቋሙበት ሁኔታ ነው ያለው፣ ለምሳሌ በአሜሪካ ማኅበራቱ ሦስቱንም ተግባራት ያከናውናሉ፡፡ እንደ እንግሊዝ ባሉ ሀገራት ደግሞ የሞያ ማኅበራቱ በረጅም ጊዜ እየዳበረ የመጣ በኮመን ሎው ላይ የተመሰረተ ሦስቱንም ሥራዎች የመሥራት ሥልጣን አላቸው፡፡ የእንግሊዞቹ እንደውም ከአራት መቶና እና አምስት መቶ አመት በላይ እድሜ ያላቸው ናቸው፡፡ በፈረንሳይ ደግሞ አደረጃጀታቸው ከፍርድ ቤቶች ጋር የተያያዘ ሲሆን ሞያውን የማስተዳደር፣ ፈቃድ የመስጠት፣ የዲሲፕሊን አርምጃ የመውሰድና የሕዝብ አገልግሎት ሥራዎችን የመሥራት ስልጣን አላቸው፡፡ በህንድም የዚሁ አይነት አሰራር ነው ያለው፡፡ የብራዚል የጠበቆች ማኅበር ከ750,000 በላይ አባላት ያሉት ሲሆን የጥብቅና ሞያውን የማስተዳደር፣ ሞያውን የመወክል እና የሕዝብ አገልግሎት ተግባራትን ያከናውናል። እዚሁ አቅራቢያችን የሚገኙት የኬንያ፣ የኡጋንዳ፣ የታንዛንያ የጠበቆች ማኅበራትም በሕግ እንዲቋቋሙ ተደርገው ሞያውን በተለያየ ደረጃ የማስተዳደር፣ የመወከል እና የሕዝብ አገልግሎት ተግባራትን ያከናውናሉ፡፡ በነዚህ ማኅበራት ውስጥ አባል መሆን ግዴታ ነው፡፡ በአንዳንዶቹ ሀገራት ቀድሞ ነገር በማኅበራቱ መመዘኛ መሰረት ትምሕርት ወስዶ፣ ፈተናውን አልፎ ጠበቃ መሆን ይችላል ያልተባለ ባለሞያ፣ በማናቸውም ፍርድ ቤት ቆሞ ሊከራከር አይችልም። ስለዚህ ፈቃዱን ካገኘ በኋላም የስነምግባር ጉድለት ፈጽሞ ቢገኝ የሚቀጣው በማኅበሩ ነው፡፡ ቅጣቱም የጥብቅና ፈቃድ እስከመሰረዝ ሊደርስ ይችላል፡፡ ስለዚህ የጠበቆች ማኅበራቱ በቂ አቅምና ኃይል አላቸው፡፡ አባላቶቻቸውን ያስተምራሉ፣ ይመክራሉ፣ ይገስፃሉ፣ ይቀጣሉ፡፡  በነዚህ ደረጃዎች የማይታረም አባል ከማኅበሩ ይባረራል፤ የጥብቅና ሥራ እንዳይሰራ ይደረጋል፡፡  
ወደኛ አገር ስንመለስ ታዲያ ማኅበሮቻችን በጣም የተወሰነ ተግባር ያላቸው ሲሆኑ ሞያውን የማስተዳደር ምንም አይነት ሥልጣን ስለሌላቸው፣ የስነምግባር ጥሰቶችን የመከታተልና የማረም ሥራዎችን አይሰሩም፡፡ የዚህ አይነት አቅም የሌላቸው ማኅበራት ከኛ ሌላ በሌሎች ሀገሮች ለመኖራቸው ብዙም መረጃ የለኝም፡፡ ቢኖሩም ደግሞ መኮረጅም ካለብን የተሻለ አሰራርና ጥቅም የሚሰጡትን ልምዶች ከሀገራችን ሁኔታና ፍላጎት ጋር አጣጥመን መሆን ይኖርበታል የሚል እምነት አለኝ፡፡ ስለዚህ ለሀገራችን የጥብቅና ሞያ አስተዳደር በርካታ መሻሻሎች ያስፈልጉታል፡፡
የአባላት የስነምግባር ጉዳይ አይመለከተንም እያሉ ነው?
አይመለከተንም ሳይሆን፣ ሥልጣን በሕግ የተሰጠው የጠበቆች ማኅበር ስለሌለ፣ የማኅበሮቻችን አባልነት በፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ ስለሆነ፣ በዚህም ምክንያት ብዙ አባላት በማናቸውም ማኅበር ውስጥ አባል ስላልሆኑ፣ አባል የሆኑትም በማናቸውም ጊዜ ለቀው መውጣት ስለሚችሉና ይህ ከማኅበር የመውጣት እርምጃቸውም የጥብቅና ፈቃዳቸውን ስለማይነካ፣ ማለትም ከማኅበሩ ወጥተውም የጥብቅና ሥራቸውን መቀጠል ስለሚችሉ አስገዳጅ የሆነ ስነምግባር የማስከበር ሥራ መሥራት እንችልም ለማለት ነው እንጂ አያገባንም ለማለት አይደለም። ስለሚያገባንማ የሲቪክ ማኅበር ብንሆንም በየጊዜው በስነምግባር ሕጉና በተያያዙ መልካም የስነምግባር ደንቦች ስልጠና እንሰጣለን፣ ውይይቶች እናዘጋጃለን፡፡ ባለፈው አመት ለምሳሌ ከጠበቆች ሥነምግባር ጋር በተያያዘ ሁለትፕሮግራሞች አዘጋጅተን የነበረ ሲሆን በዚህ አመት በእቅዳችን ውስጥ የተያዙ ሁለት ስልጠናዎች አሉ፡፡ ዋናው ለማለት የፈለግሁት ምንድነው፣ የጥብቅና ሞያን በፈቃደኝነት ላይ በተመሰረተ የሲቪክ ማኅበር ማስተዳደር አይቻልም፡፡ ቋሚ የሆነ ዘለቄታ ያለው አደረጃጀት ወይም ተቋም ያስፈልገዋል፡፡  
 የጠበቆች ማኅበር አለ አይደለ?
 የጠበቆች ማኅበር አለ፡፡ ሆኖም ግን በጠበቆች ማኅበርም ዘንድ ያለው ችግር እላይ ከገለጽኩት የተለየ አይደለም፡፡ የጠበቆች ማኅበርም ቢሆን የፈቃደኝነት ማኅበር ነው፡፡ በርግጥ የጠበቆች ማኅበር በፍትሕ ሚኒስቴር ውስጥ ባለው የጠበቆች የዲሲፕሊን ኮሚቴ አባል ቢሆንም በአጠቃላይ የጠበቆችን ስነምግባር በተመለከተ እንደ አባል ኮሚቴው ውስጥ ከመሳተፍ በቀር የማስፈጸም ኃይሉ የሕግ ባለሞያዎች ማኅበር ካለበት ችግር የተለየ አይመስለኝም፡፡  
በዚህ ችግር ዙርያ መፍትሔ ለማምጣት ለምን በትብብር አትሰሩም?
 በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ ሃሳብ እየተለዋወጥን ነው፡፡ በሁለቱም ማኅበራት አመራር በኩል በጋራ ተረዳድቶ መሥራት ጥቅም እንዳለው መተማመን ላይ ተደርሷል፡፡ አብረን እንዳንሰራም የሚያግደን ነገርም የለም፡፡ ለወደፊቱ በጋራ የምንሰራቸው በርካታ ነገሮች ስላሉ እየተመካከርን ውጤት ያለው ሥራ ልንሰራ እንደምችል አምናለሁኝ፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ በሰፊው መነጋገር እንችላለን፡፡  
ዘላቂ መፍትሔው ምንድነው ይላሉ?
 እንደኔ እንደኔ፣ መፍትሔው በሕግ የተቋቋመ ሞያውን ማስተዳደር የሚችል፣ ሁሉም ጠበቃ በየደረጃው የግዴታ አባል የሚሆንበት የጠበቆች ማኅበር ማቋቋም ቢቻል አብዛኛው ችግር የሚቀረፍ ይመስለኛል፡፡ ምናልባት እንዳደጉት ሀገሮች ሁሉንም ሥልጣን ማኅበሩ እንዲኖረው ማድረግ አይቻል ይሆናል ግን በተወሰነ ደረጃ ሞያውን የማስተዳደር ሥልጣን የግድ ማኅበራት ያስፈልጋቸዋል፡፡ ማኅበራት ያልኩበት ምክንያት በፌደራል፣ በክልል እና በአዲስ አበባ እንዲሁም በሌሎች ፌደራል ከተሞች ደረጃ ሞያውን በተወሰነም ደረጃ ቢሆን ማስተዳደር የሚችሉ፣ በየደረጃው ሞያውን የሚወክሉ፣የሕዝብ አገልግሎት የሚያከናውኑ ማኅበራት ስለሚያስፈልጉ ነው፡፡ በየደረጃው ካልሆነ አሁንም በአባላትና በማኅበሩ መካከል መራራቅ፣ ማለትም የቦታም፣ በፌደራል ስትራክቸሩ መሰረት  የአሰራርም፣ የግንኙነትም ወይም የእንቅስቃሴና የተሳትፎ ወዘተ…ይጨምራል፣ ዞሮ ዞሮ ውጤታማ የሆነ ክትትልና አርምት ማድረግ አይቻልም፡፡ በአጠቃላይ ግን ቅርጹን የማጥናትና የአሰራር ደረጃውን በጥሩ ጥናት ላይ ተመስርቶ መምረጡ እንደተጠበቀ ሆኖ ይህ መንገድ ይሰራል ብዬ የማምንበት ምክንያት በሌሎች ሀገሮች ተሞክሮ ውጤት ያመጣ እንዲያውም በአብዛኛው ሀገራት የሚሰራበት በመሆኑ ሲሆን ሌላው ደግሞ ጠበቃው በሥራ አጋጣሚ ስለሚገናኝ፣ ስለሚተዋወቅ፣ በቅርብ አብሮ ስለሚኖር ሞያውንና ሥነምግባሩን በቅርብ መነጋገር መወያየት፣ ማረም አስፈላጊም ሲሆን በማኅበሩ በኩል እርምጃ መውሰድ ስለሚችል፣ በሌላ በኩል ደግሞ የሞያው ስነምግባር መሻሻልና ተፈፃሚ ሲሆን ክብርና ሞገስ የሚሰጠው ለሞያውና ለባለሞያው ስለሆነና ይህ ደግሞ በቀጥታ የባለሞያው ዋና ጥቅም በመሆኑ ለውጥ ያመጣል ብዬ አምናለሁ፡፡ ማኅበራቱን ከበላይ ሆኖ የሚያስተባብር ደግሞ ባር ካውንስል ማቋቋም ይቻላል፡፡ ይህ በብዙ አገራት የሚሰራበት ነው። ይህ ከሆነ በኋላ አሁን ያሉት ማኅበራት አባላቱ እስከፈለጉ ድረስ ሲቪክ ማኅበራት ሆነው መቀጠል የማይችሉበት ምክንያት አይኖርም፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የጠበቆች ድርጅት ወይም የጠበቆች ፈርም ቢቋቋም፣ በጥብቅና ሞያው ጥራትና ደረጃ እንዲሁም በሥንምግባር ጥበቃ በኩል ከፍተኛ ጠቀሜታ ይኖረዋል ብዬ አምናለሁ፡፡
የጠበቆች ድርጅት ሲሉ ምን ማለትዎ ነው? ያሏቸውን ጥቅሞችስ ሊያመጣ የሚችለው እንዴት ነው? ትንሽ ቢያብራሩልን?
 በኛ አገር ጠበቆች የጥብቅና አገልግሎታቸውን የሚሰጡት በተናጠል ወይም በግል ነው፡፡ ጠበቆች እንደ ሥራ አንድ ላይ ተሰባስበው ሞያዊ አገልግሎት የሚሰጡበት ሁኔታ የለም፡፡ እንደሚታወቀው ሕግ ደግሞ በጣም ሰፊ ዘርፎች አሉት፡፡ ሕግ የማይነካው ምንም አይነት ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት የለም፡፡ ያለማጋነን ማናቸውም እንቅስቃሴ በሕግ የሚገዛ ነው፡፡ ስለዚህም የንግድ ሕግ፣ የኮንስትራክሽን፣ የትራንስፖርት፣ የተፈጥሮ ሀብት፣ የአካባቢ ጥበቃ፣ የቤተሰብ፣ የአሰሪና ሰራተኛ፣ የወንጀል፣ የባሕር፣ የውጭ ንግድ፣የመሬት፣የባንክ፣የኢንሹራንስ፣የታክስ፣የኢንቨስትመንት ወዘተ… እያለ ማናቸውንም እንቅስቃሴ የሚመሩ ሕጎች አሉ፡፡ በዚህ ሁሉ የሕግ ዘርፍ ደግሞ አንድ የሕግ ባለሞያ በቂ አውቀትና ልምድ ኖሮት የተሟላ አገልግሎት ለመስጠት ይቸገራል፡፡ በአንፃሩ ደግሞ በተለያየ የሕግ ዘርፍ ከፍ ያለ አውቀትና ልምድ ያላቸው ሰዎች ተሰባሰበው መሥራት ቢችሉ፣ በተሰባሰቡት ባለሞያዎች መካከል የሥራ ክፍፍል ይደረጋል፡፡ እያንዳንዱ ባለሞያ የተሻለ አውቀትና ልምድ ባለው መስክ የሚመጡ ሥራዎችን ይሰራል፣ በየዲፓርትመንት ይደራጃል፤ሥራውን ያከናውናል። ባለሞያዎቹ ባጋጠሙዋቸው የሕግ ጥያቄዎች ላይ ይመካከራሉ፤ ኃሳብ ይለዋወጣሉ፣ የተነሳውን የሕግ ጥያቄ እንዴት አድርገው መፍታት እንዳለባቸው መክረው ዘክረው ይወስናሉ፡፡ ይህ እንግዲህ ጥራት ያለው ሥራ እንዲሰሩ ይረዳቸዋል፡፡ ባለሞያዎቹም በሙሉ ልብ ሥራቸውን ያከናውናሉ፤ ተገልጋዩም ከፍተኛ ደረጃና ጥራት ያለው ምክር ያገኛል፣ ፍርድ ቤትም ሲወከል በደንብ በተዘጋጀ አቤቱታና ክርክር ይወከላል፡፡ ይህ በራሱ አንድ ትልቅ ችግር ይቀርፋል፡፡ ባለሞያዎች በስራ ብዛትና መደራረብ ብዙም በማያውቁት የሕግ መስክ እንዳይዳክሩ በማድረጉ ቅልጥፍናና ጥራት ያመጣላቸዋል። ከዚህ ጋር ተያይዞ ከሚፈጠር የሥነምግባር ጉድለትም ይጠብቃቸዋል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ባለሞያዎቹ በቡድን  መልክ ስለሚሰሩ የእውቀትና የልምድ ጉድለትን እያሟሉ እንደሚሄዱ ሁሉ፣ የሚታዩ የሥነምግባር ጉድለት አዝማሚያዎችንም እያረሟቸው ይጓዛሉ፡፡ በሦስተኛ ደረጃ ደግሞ ፈርሙ ወይም የባለሞያዎቹ ድርጅት የተሻለ ሥራ ማግኘት የሚችለው በሥራው ደረጃና ጥራት እንዲሁም በሥነምግባር ጥንካሬው ስለሚሆን ለራሱ ለድርጅቱ ወይም ለፈርሙ ሕልውና ሲል የሥነምግባር ጉድለቶችን እንዲያርም ይገደዳል። በዚህም ጠበቆች የተሻለ አገልግሎት የሚሰጡ፣ ከፍተኛ የሥነምግባር ብቃት ያላቸው እንዲሆኑ ይረዳል፡፡
ስለዚህ በአገራችን የጠበቆች ድርጅቶች ወይም ፈርሞች እንዲቋቋሙ የሚያስችል ሕግ ቢወጣ ቀደም ብዬ እንደጠቀሱት በርካታ ችግሮችን በመፍታት ለፍትሕ ሥርአቱ መጠናከር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል የሚል እምነት አለኝ፡፡
 እስከዛሬ በዚህ ረገድ ምንም ሥራ አልተሰራም ማለት ነው?
ምንም አልተሰራም ማለት አይቻልም። ከጥቂት አመታት በፊት ፍትሕ ሚኒስቴር በጠበቆች ድርጅት ላይ ረቂቅ አዘጋጅቶ በሰፊው እንድንወያይበት አድርጎ ነበር፡፡ እኛም ይጠቅማሉ ያልናቸውን አስተያየቶች ሰጥተናል፡፡ ይህ ከሆነ አንድ ሁለት አመት የሆነው መሰለኝ፡፡ ከዚያ ወዲህ ረቂቁ ምን ላይ እንደደረሰ አልፎ አልፎ ስንጠይቅ ማስተካከያዎች እየተደረጉበት እንደሆነ ተነግሮናል። በቀደም በተካሄደው የሀገር አቀፍ የፍትሕ ዘርፍ የፍትሕና መልካም አስተዳደር መድረክ ላይም በጉዳዩ ላይ አስተያየት የሰጡ ከፍተኛ የፍትሕ ሚኒስቴር ኃላፊ፣ ሥራው እየተጠናቀቀ መሆኑን እና ብዙዎቹ ያነሳናቸው ነጥቦች በተሻሻለው ረቂቅ ውስጥ የተካተቱ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ እኛም በተሰጠው አስተያየት ከፍተኛ ተስፋ አድሮብናል፡፡  
እዚህ ላይ አንድ መጨመር የምፈልገው ነገር የጠበቆች ጅርጅት ወይም ፈርም መቋቋም ቀደም ሲል ከገለጽኩት በተጨማሪ በቀጥታ ከውጭ በሚመጣው ኢንቨስትመንት ወይም direct foreign  investment ላይም ከፍተኛ ተጽእኖ አለው፡፡ ወደ ሀገራችን የሚመጡት ኢንቨስተሮች በብዙ መልኩ የሕግ ባለሞያዎች በሚሰጡዋቸው ምክር ላይ እምነት በመጣል ውሳኔዎችን ይሰጣሉ። በአብዛኛው የዓለም ሀገራትም ለሕግ አማካሪህ፣ ለሀኪምህና ለንስሃ አባትህ የሚደበቅ ነገር የለም የሚባለው መርህ በከፍተኛ ደረጃ የሰረፀ በመሆኑ የኢንቨስትመንት ውሳኔያቸው በሚያገኙት የሕግ ምክር ላይ በከፍተኛ ደረጃ የተመሰረተ ነው። ጉዳያቸው ወደ ፍርድ ቤት ሲሄድም በሙሉ እምነት ጉዳያቸው ተገቢውን ትኩረት ተሰጥቶት ክርክሩ እንዲቀርብ እና ክትትልም እንዲደረግበት ለሚያምኑት ባለሞያ መስጠት ይፈልጋሉ፡፡ በማናቸውም ሁኔታ የሰጡት እምነት እንዳይፋለስ እንዳይደናቀፍ ይፈልጋሉ፡፡ ያ ባለሞያ ግን አንድ ብቻ ሆኖ የሚሰራ በመሆኑ ደስተኞች አይደሉም። የሕግ አማካሪያቸው ወይም ጠበቃቸው አንድና  ብቻውን የሚሰራ መሆኑ ስጋታቸውን በጣም ከፍ ያደርገዋል፡፡ የሕግ ባለሞያው ወይም ጠበቃው አንድ ችግር አጋጥሞት ፍርድ ቤት መቅረብ ባይችልስ? ቢታመምሰ? ቢሞትስ? ወዘተ. ማነው ጉዳዩን የሚከታተለው? ፋይሎቹ የት ይገኛሉ? ማነው ጉዳዩን በቀላሉ ተክቶት መሥራት የሚችለው? በነዚህና በበርካታ ጥያቄዎች ምክንያት ጉዳያቸው እንዳይበላሽ በጣም ይፈራሉ፡፡ ለዚህም ወደኛ ሀገር ኢንቨስት ለማድረግ ሲመጡ ሀገራችን ለኢንቨስትመንት ምቹ ነች ወይ? ብለው ከግምት ከሚያስገቧቸው መመዘኛዎች አንዱ ብቃት ያላቸው የሕግ ባለሞያዎች አሉ ወይ? የሕግ ድርጅቶች ወይም ፈርሞች አሉዋቸው ወይ? የሚለው ነው፡፡ ብዙውን ጊዜ ከውጭ የሚመጡት ባለሀብቶች በዚህ ረገድ ደስተኞች አይደሉም፡፡ በተለይ ከፍተኛ ሥራ ሊሰሩ የሚችሉት ትላልቅ ድርጅቶች ብዙውን ጊዜ የሕግ ባለሞያ ድርጅቶች ወይም ፈርሞች ባለመኖራቸው ወደ ሀገራችን መጥተው በተለያዩ የሥራ መሥኮች መሰማራት ቢፈልጉም ይህ ጉድለት ያሳስባቸዋል፡፡
ሌላው ከዚህ ጋር መታየት ያለበት ሀገራችን ወደ ዓለም የንግድ ድርጅት ወይም WTO ለመግባት ድርድር ላይ መሆኗ ይታወቃል፡፡ የሕግ ሞያ በዚህ ረገድ ብዙ ዝግጅትና ሥራ የሚጠብቀው ይመስለኛል፡፡ ተወዳዳሪ ለመሆን ጠንካራ የጠበቆች ማኅበር ወይም ማኅበራት ያስፈልጉናል እንዲሁም የሕግ ባለሞያዎች ድርጅቶች ወይም የጠበቃ ፈርሞች ያስፈልጉናል፡፡ የነዚህ ተቋማት ያለመኖር ተወዳዳሪነታችንን መፈታተኑ አይቀርም። የሀገራችንን እና የሀገር ውስጥ ሥራዎችን እና ድርጅቶችን ጥቅምም በአግባቡ ለማስጠበቅ እንዲሁም ከውጭ የሚመጡ ድርጅቶች በተገቢው መንገድ ለመርዳትና ሀገራችንን ጠቅመው እነሱም እንዲጠቀሙ ለማስቻል የነዚህ ተቋማት በአግባቡ መደራጀት እጅግ በጣም አስፈላጊ ነው፡፡
 ለመሆኑ ሞያውን የማስተዳደር ሥልጣን በሕግ ቢሰጥ ወይም ማኅበሩ በሕግ ቢቋቋም፣ሥራውን ለመስራት አቅሙ አለን ብላችሁ ታስባላችሁ?
 ሃ!ሃ! ይህ ብዙ ጊዜ የሚነሳ ጥያቄ ነው፡፡ እና በዚህ ጉዳይ ላይ ሳንነጋገር ብናልፈው ኖሮ ይቆጨኝ ነበር፡፡ በእኔ እምነት ችግር አይፈጠርም ባይ ነኝ። ቀድሞ ነገር አቅሙን የሚሰጠን እኮ ሕግ ነው። ሕጉ ሞያውን በማስተዳደር በኩል ማኅበራቱ ሊኖራቸው የሚገባውን ደረጃ ይወስናል፣ ሕጉ ማናቸውም ጠበቃ የጠበቆች ማኅበር አባል የመሆን ግዴታ አለበት የሚል ከሆነ፣ የጠበቆች ማኅበር የአባላቱን ሥነምግባርና የተከታታይ ሥልጠና እንዲወስዱ ፕሮግራም አዘጋጅቶ ያስፈጽማል የሚል ከሆነ፣ ጠበቆች በሕዝብ አገልግሎት ተግባር እንዲሳተፉ ፕሮግራም አውጥቶ ያስፈጽማል የሚል ከሆነና ሌሎችም ዝርዝር ጉዳዮችን የያዘ ሕግ ከወጣ  ማኅበሩ ወይም ማኅበራቱ ያንን ማስፈጸም የማይችሉበት ምንም ምክንያት አይኖርም፡፡ ማኅበሩ ወይም ማኅበራቱ እኮ ራሳቸውን የቻሉ ጽ/ቤቶችና ሰራተኞች ይኖሯቸዋል፡፡ ከባለሞያዎቹ ውስጥ ደግሞ ጥሩ ጥሩ ችሎታ ያሉዋቸው አባላት ለማኅበራቱ መሪነት ይመረጣሉ፡፡ የተለያዩ ኮሚቴዎች ይኖራሉ፣ አባላትም የአባልነት መዋጮዋቸውን በአግባቡ እንዲያዋጡ ስለሚደረግ የአባልነት መዋጮን መክፈል ግዴታም ስለሚሆን ሥራዎቹን ለማከናወን አስቸጋሪ አይመስለኝም፡፡ በዚያ ላይ ደግሞ መታወቅ ያለበት የሕግ ባለሞያዎች እኮ በተለይ በጥብቅና የተሰማሩት ከፍተኛ ትምሕርት ያላቸው፣ በተለያያ ደረጃ አገራቸውን በመንግሥት ሥራ ያገለገሉ፣ በግል ድርጅቶች የሰሩ፣ ከፍተኛ የአስተዳደርና የሥራ መሪነት ልምድ ጭምር ያካበቱ ናቸው፡፡ ስለዚህ እድሉ ከተፈጠረ ሞያቸውን ማገልገልና ወደ ተሻለ ደረጃ ማሸጋገር ያቅታቸዋል ብዬ አላምንም፡፡   
  ሌላ የሚያክሉት ነገር አለ?
 የተጠናከረ ተደራሽ፣ ብቁ፣ ነፃና ፍትሕን ማስፈን የሚችል የዳኝነት ሥርአት ለአንድ ሀገር ሰላምም ሆነ እድገት አጅግ አስፈላጊ ነው። ዳኝነት በአጠቃላይ የአንድ አገር ሕዝብ መብት፣ ሀብት፣ ሕይወት የሚጠበቅበት ሥርአት በመሆኑ አስፈላጊነቱን አበክሮ ለመግለጽ በቂ ቃል አይኖርም፡፡ እጅግ በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ ስለዚህ ዳኝነት እንዲጠናከርና በብቃት የሚሰራበት ሁኔታ እየተሻሻለ መሄዱ አስፈላጊ ነው፡፡  የዳኝነት ሥርዓቱ መጠናከር ሥንል፣ የዚህ ሥርዓት አንዱ አካል የሆነው የጠበቆች አገልግሎት፣ ነፃ የሆነና ብቃት ያለው፣ ሥነምግባር የጠበቀ የተሟላ አገልግሎት መስጠት መቻል አብሮ የሚታሰብ ነው፡፡ ምክንያቱም የፍትሕ ሥራ የሚሰራው በፍትሐብሄር ጉዳይ ሲሆን በዳኞችና በጠበቆች ነው፡፡ በወንጀል ፍትሕ ደግሞ በዳኞች፣ በተከላካይ ጠበቆች እና በአቃቤ ሕጎች ነው፡፡ ከነዚህ ውስጥ የአንዱ ወገን መጉደል ወይም መዳከም የፍትሕ ሥርአቱን በእጅጉ ይጎዳዋል፡፡ በተጨማሪም የሕግ ባለሞያዎች ከፍርድ ቤት ውጭም በበርካታ መስኮች ኢንቨስትመንትን ጨምሮ ሰፊ የሥራ ድርሻ አላቸው፡፡ ስለዚህ እነዚህ መሰረታዊ የፍትሕ ሥርአቱ አካላት እየተሻሻሉና እየተጠናከሩ መሄዳቸው ለሀገራችን ሰላም፣ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ፣ እድገትም ሆነ ልማት መሰረታዊ ሚና ያላቸው በመሆኑ፣ አሁን በተያዘው መልኩ ትኩረት ተሰጥቶት መቀጠሉና የሚጠበቅበትን አስተዋጽኦ እንዲያበረክት ማድረግ ቀጠሮ የሚሰጠው ጉዳይ አይደለም የሚል እምነት አለኝ፡፡

Read 4429 times