Saturday, 22 February 2014 12:34

ዐይን አውጣ ሌባ ሰርቆ ያፋልጋል (የኦሮምኛ ተረት)

Written by 
Rate this item
(14 votes)

ከዕለታት አንድ ቀን ሁለት የድርጅት አሰሪዎች ስለሰራተኞቻቸው ዳተኝነት ይወያያሉ፡፡
አንደኛው፡-
“እኔ መቼም እንደሚገባኝ፤ እኔ ድርጅት ውስጥ እንዳለው እንደ አቶ እገሌ ደደብ፣ ደንቆሮ ሰራተኛ በዓለም ቢዞሩ አይገኝም ባይ ነኝ፡፡”
ሁለተኛው፤
“ለምን እንዲህ አልክ? ምን አጥፍቶ አግኝተኸው ነው?” አለው፡፡
“ይህን ዳተኛው ቆይ ልጥራውና ምን ዓይነት ደደብ እንደሆነ ላሳይህ”
የተባለው ሰውዬ ተጠርቶ መጣ፡፡
“ይሄኔ አሰሪው ይህን አምስት ብር ይዘህ ሂድና ማርቼዲስ መኪና ገዝተህልኝ ና”፤ አለው፡፡ ሰራተኛው ዝም ብሎ ገንዘቡን ተቀበለና ሄደ፡፡”
ሁለተኛው፤
“አይ ወዳጄ የዛሬ ሰራተኛ ሰራተኛ መስሎሃል? የእኔን ሰራተኛ ጉድ ብትሰማ ምን ልትል ነው?”
አንደኛው፤
“እንዴት?! አሁን ከነገርኩህ የበለጠ ደደብ ሰራተኛ ይኖራል እንዴ?”
ሁለተኛው፤
“ቆይ ላስጠራውና ምን ዓይነት ጉደኛ እንደሆነ አሳይሃለሁ” አለና፤ የተባለውን ሰራተኛ አስጠርቶ፤
ወደ ሰራተኞች ክበብ ሂድና እኔ እዛ መኖር አለመኖሬን አይተህ ና” አለው፡፡ ሰራተኛው እሺ ብሎ ምንም ሳይል፣ ጥያቄም ሳይጠይቅ፣ ወጥቶ ወደ ክበቡ ሄደ፡፡
እደጅ ሁለቱ ሰራተኞች ይገናኛሉ፡፡ ጉዱ እዚህ ላይ ነው፡፡ ሁለተኛ የተላከው ሰራተኛ ለመጀመሪያው እንዲህ አለው፣
“አለቆቻችን ደደቦች መሆናቸውን አየህልኝ?”
“ምን ትጠራጠራለህ? አገር ያወቃቸው ደደቦችኮ ናቸው፡፡ የእኔ አሰሪ ምን እንዳለኝ ታውቃለህ?”
“ምን አለህ?”
“5 ብር ሰጥቶኝ ማርቼዲስ መኪና ገዝተህ ና አለ፡፡ የደደብነቱ ደደብነት ግን ምን እንደሆነ ታውቃለህ? ምን ዓይነት ቀለም ያለው መኪና እንደሚፈልግ ሳይነግረኝ!”
“ኧረ ያንተ አለቃ በምን ጣሙ? የእኔው አለቃ ምን እንዳለኝ ታውቃለህ?”
“ምን አለህ?”
“ሂድና ክበብ ውስጥ እኔ መኖር አለመኖሬን አይተህ ና አለኝ፡፡ የደደብነቱ፤ ደደብነት እኔን ማንከራተት መፈለጉ ነው እንጂ፤ እስቲ ምናለበት ስልኩን ብድግ አድርጎ፣ ክበብ ደውሎ አለሁ የለሁም ብሎ ቢያረጋግጥ!!” አለ፡፡     
*      *      *
ዕውነተኛ ሰራተኛ የሌለው አገር ለውጥ አያመጣም፡፡ ልቡ ዳተኛ የሆነ ትውልድ ለውጥ አያመጣም፡፡ መሰረቱ የተናደ ህብረተሰብ ልመልስህ ቢሉት አይንድም፡፡ “መንገድ ሲበላሽ ትራፊክ ይበዛል፤ አገር ሲበላሽ ጃርት ያፈራል፤” ይላሉ ህንዶች፡፡ ሥነ-ልቦናችን በአሉታዊነት ነቅዟል። ያለሸር፣ ያለጥፋት፣ ያለሌብነት፣ ያለ ቢሮክራሲ ጥልፍልፍ … የሚታይ ደግ ነገር ጠፍቷል፡፡ አንድ ፋይል ካንድ ክፍል ሌላ ክፍል እንዲሄድ ገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ በስልክ ቀና መልስ ለማግነት እንኳን ገንዘብ አስፈልጓል፡፡ ምናልባት ፈገግ ለማለትም ገንዘብ የሚያስፈልግበት ዘመን ሳይመጣ አይቀርም፡፡ ስለመልካም አስተዳደር ማውራት የሚቻለው የፀዳ አዕምሮ ሲኖር ነው፡፡ የጌታ-ሎሌ አስተሳሰብ እያለ የስራ ሂደት ባለቤትነት ዘበት መሆኑን አንርሳ፡፡
የጀርመን ግንብ በአደባባይ እንዲፈርስ ተደረገ እንጂ ግንቡ ጭንቅላታችን ውስጥ አለ”፤ ይላሉ ጀርመኖች፡፡
ፍጥነት አስፈላጊ ቢሆንም፣ ምን ተይዞ ጉዞ ማለትን አንዘንጋ፡፡ ከአሁኑ፤ ከውሃ ልኩ ያላስተዋልነው ነገር ነገ ጠልፎ ሊጥለን ይችላል፡፡ ያለውን ችግር የለም፣ የሌለውን ችግር አለ ማለት ፈረንጆቹ Denial የሚሉት በሽታ ነው፡፡ እያወቁ መካድ! ይሄ ለማይቀለበስ (irreversible) ችግር ከዳረገን አለቀልን ማለት ነው፡፡
አንዴ የተቀጠፈች አበባ ለዘለዓለም ትሞታለች፤ ይለናል ኦማር ካህያም፡፡ (A flower once pluck’d forever dies)፡፡ የምንፈልገውን ማወቅ ዋና ጉዳይ ነው፡፡ ካፒታሊዝም ከፈለግን የካፒታሊዝምን ትክክለኛ አውታሮች እንጨብጥ፡፡ የራሳችን ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት የምንገነባ ከሆነ፤ በወጉ ቀርፀነው፣ በወጉ መሬት ላይ አስፍረነው፣ በወጉ ተግብረነው መንገዱ ይሄ ነው እንበል፡፡ አንዱ አንድ አዞ ሌላው ሌላ እያዘዘ፤ ከተምታታ፤ ስራም አይሰራ፣ ለውጥም አይመጣ። ይሆናል ሲሉን አህያ አረድን፡፡
አይሆንም ሲሉን አውጥተን ጣልን፡፡
ለምን ጣላችሁት፣ ይሆን ነበርኮ ቢሉን
ወጥተን ብንፈልግ አጣን!
እንደተባለው የኦሮምኛ አገላለፅ፤ ሌሎች ያሉንን እየሰማንና ዕውነት ነው እያልን፣ አደጋችሁ ሲሉ እሺ፣ አላደጋችሁም ሲሉን እሺ እያልን፤ መሸነጋገል አይገባንም፡፡ ሁሉም ለየራሱ ጥቅም እንደሚሮጥና ግሎባላይዜሽን የራሱ መዘዝ፤ የራሱ አባዜ እንዳለው ላንዲትም ደቂቃ መዘንጋት አይገባም፡፡
“መንግሥት ዝሆን ነው፡፡ ሁሉን ነገር ዞሮ አያይም፤ ማሳየት ያስፈልጋል” ያለው የድሬደዋ ገበሬ አባባል አይረሴ ነው፡፡ ዐይን ያለው የሰው ያስፈልጋል፡፡ የሰው ጎዶሎ የሰው ድርጭት፣ መፃጉእ ነው እንዲያፈራ፤ የሰው ተራራ የሰው ዋርካ፣ ጀግና ነው እያፈራ ይላልና ልባም ዜጋ ለማፍራት መጣር አለብን፡፡ ሰራተኛ ትውልድ፣ ጠያቂ ትውልድ፣ ተፋላሚ ትውልድ፣ ማፍራት አለብን፡፡ መንገድ የሚመራ ሰውና ድርጅት የሚመራ፣ ህዝብ የሚመራ፤ ባትሪው እጁ ላይ ነው። ባትሪውን አብርቶ ዐይኑን ከጨፈነም፣ ዐይኑን ገልጦ ባትሪውን ካጠፋም፤ መንገዱ አይሳካም፡፡ ሁሉ ነገር ከጨላለመ በኋላ እገሌ ነው እገሌ ነው እያሉ መወነጃጀል፤ “ዐይን-አውጣ ሌባ ሰርቆ ያፋልጋል” ከመባል አያመልጥም! ልብና ልቡና ይስጠን!!

Read 6782 times