Saturday, 22 February 2014 12:20

የህክምና ተቋማትን አሠራር የሚወስን አዲስ መመሪያ ወጣ

Written by 
Rate this item
(8 votes)
  • መሥፈርቱን የማያሟሉ ከሐምሌ 1 ጀምሮ እርምጃ ይወሰድባቸዋል  
  • በሥራ ላይ ካሉት ክሊኒኮች መስፈርቱን የሚያሟላ  አይኖርም ተብሏል
  • የግል ክሊኒኮች ማህበር በቂ የዝግጅት ጊዜ ሊሰጠን ይገባል አለ  


የመንግሥትና የግል የጤና ተቋማት አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችላቸውን መስፈርቶችና ደረጃዎች የሚወስን አዲስ መመሪያ ወጣ፡፡ የጤና ተቋማቱ በአዲሱ መስፈርት መሰረት ራሳቸውን እንዲያደራጁ እስከ ሰኔ 30 ቀን 2006 ዓ.ም ጊዜ የተሰጣቸው ሲሆን ከሐምሌ 1 ጀምሮ መሥፈርቱን ባላሟሉት ላይ እርምጃ ይወሰዳል ተብሏል፡፡
የኢትዮጵያ የምግብ የመድኃኒትና የህክምና መሳሪያዎች ቁጥጥር ባለስልጣን ያወጣውና በአገሪቱ የሚገኙ ሁሉንም የመንግስትና የግል የጤና ተቋማት ይመለከታል የተባለው አዲስ መመሪያ፤ ተቋማቱ ማሟላት የሚገባቸውን ዝርዝር ጉዳዮች ይፋ አድርጓል፡፡ በዚሁ መመሪያ ላይ እንደተገለፀው፤ ሆስፒታሎች የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል፣ አጠቃላይ ሆስፒታልና ስፔሻላይዝይድ ሆስፒታል ተብለው በ3 መደቦች የሚከፈሉ ሲሆን የጤና ማዕከላት፣ የጤና ጣቢያዎችና ልዩ ማዕከላትም በዘርፉ እንደሚጠቃለሉ ተጠቅሷል፡፡
መመሪያው ሆስፒታሎች እንደየደረጃቸው የተለያዩ አገልግሎቶችን መስጠት እንደሚገባቸው በዝርዘር የገለፀ ሲሆን የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታሎች ቢያንስ 35 አልጋዎች፣ አጠቃላይ ሆስፒታሎች 50 አልጋዎች እንዲሁም ስፔሻላይዝድ ሆስፒታሎች ከ300 የማያንሱ አልጋዎች እንዲኖራቸው ያስገድዳል። ሁሉም የጤና ተቋማት የማዋለድ አገልግሎት መስጠት እንደሚገባቸው የገለፀው መመሪያው፤ በክሊኒኮች ውስጥ አልጋ በማዘጋጀት ህሙማንን በመደበኛነት አስተኝቶ ማከም እንደማይቻልና መካከለኛ ክሊኒኮች ለድንገተኛ ህመምና ለማዋለድ አገልግሎት የሚሆኑ 10 አልጋዎች ብቻ ሊኖራቸው እንደሚገባ ይደነግጋል፡፡ ክሊኒኮችን በስም መሰየም እንደማይፈቀድም በዚሁ መመሪያ ላይ ተገልጿል፡፡
የኢትዮጵያ የምግብ የመድኃኒትና የህክምና መሣሪያዎች ቁጥጥር ባለስልጣን፣ የቁጥጥር አስተባባሪ ሲስተር የሺአለም በቀለ መመሪያውን ማውጣት ያስፈለገበትን ምክንያት ሲናገሩ፤ በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ በጤናው ዘርፍ ተሰማርተው ለህዝብ አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኙ የጤና ተቋማትን ለመቆጣጠርና ተቋማቱ በምን ደረጃ ላይ እንዳሉ ለማወቅ ባለመቻሉ፣ ይህንን ችግር በማስወገድ ተቋማቱ የሚሰጧቸው አገልግሎቶች ጥራታቸውን የጠበቁ እንዲሆኑ ለማድረግና ህብረተሰቡን ለአደጋ የሚያጋልጡ አሰራሮችን ለማስወገድ ነው ብለዋል። በጤናው ዘርፍ የሚታዩ ህገወጥ ተግባራትን በመቆጣጠር ለህብረተሰቡ ብቃት ያለው አገልግሎት እንዲሰጥ ለማድረግ እንደሆነም አክለው ገልፀዋል፡፡
ባለስልጣን መ/ቤቱ የጤና ተቋማቱ የሚተዳደሩበትን መመሪያና መስፈርት ህግ አድርጎ ከማፅደቁ በፊት ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ሰፋ ያለ ውይይት ማድረጉን የጠቆሙት ሲስተር የሺዓለም፤ በመመሪያው ላይ የተካተቱና ለአሰራር እንቅፋት ይሆናሉ የሚባሉ ጉዳዮች ካሉ ማሻሻያዎችን ለማድረግ እንደሚቻል በተደጋጋሚ መገለፁን አስታውሰዋል፡፡ ይሁን እንጂ መመሪያው ሊያሰራን አይችልም የሚል ሃሳብ ከየትኛውም ወገን ባለመነሳቱ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ህግ ሆኖ እንዲፀድቅ መደረጉንም ገልፀዋል፡፡ በዘርፉ የተሰማሩ አካላት ድርጅቶቻቸውን በመመሪያው መሰረት እንዲያደራጁ እስከ ሰኔ 30 ቀን 2006 ዓ.ም ድረስ ጊዜ እንደተሰጣቸውና የጊዜ ገደቡ ሲጠናቀቅ ባለስልጣን መ/ቤቱ የራሱን እርምጃ እንደሚወስድ ተናግረዋል፡፡
የአዲስ አበባ የግል ክሊኒኮች ባለቤቶችና አሰሪዎች ማህበር ምክትል ሊቀመንበር አቶ አበበ ያለው በበኩላቸው፤ መመሪያው የአገሪቱን ወቅታዊ ሁኔታ ያላገናዘበና በዘርፉ የተሰማሩ በርካታ ባለሙያዎችን ከስራ ውጪ የሚያደርግ በመሆኑ ሊታሰብበት ይገባል ብለዋል፡፡ ህብረተሰቡ ጥራት ያለው የህክምና አገልገሎት እንዲያገኝና ዘርፉም ወደተሻለ ደረጃ ከፍ እንዲል ታስቦ የወጣውን መመሪያ እንደማይቃወሙ ምክትል ሊቀመንበሩ ገልፀው፤ሆኖም በአገሪቱ የተሰማሩ የጤና ተቋማትን ወቅታዊ ሁኔታ ያላገናዘበና ምንም የመፍትሔ ሃሳብ ያላቀረበ በመሆኑ ብዙዎችን ከስራ የሚያፈናቅል ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ከ500 በላይ አባላት ያሉት ማህበሩ፤ አዲሱን ህግና መመሪያ ተከትሎ በመስፈርቱ መሰረት በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ አገልግሎት መስጠት ይቻላል ብለው እንደማያስቡ ገልፀው መንግስት በቂ የዝግጅት ጊዜና የጤና ተቋም መገንቢያ ቦታ ሊሰጠንና የብድር አገልግሎት ሊያመቻችልን ይገባልም ብለዋል፡፡ “እንደዚያ ካልሆነ የምንሰራው ከግለሰቦች በተከራየናቸው ክሊኒኮች በመሆኑ መስፈርቱ የሚጠይቀውን ለማሟላት ስንል ማፍረስም ሆነ መቀየር አንችልም” ሲሉ ችግራቸውን ጠቁመዋል፡፡ መስፈርቱን ካላሟላችሁ መስራት አትችሉም ከተባለ ግን በርካታ ባለሙያዎች ከስራ እንደሚፈናቀሉና ህብረተሰቡም በቂ አገልግሎት ለማግኘት እንደሚቸገር መታወቅ ይገባዋል ብለዋል።
ሲስተር የሺዓለም በቀለ በበኩላቸው፤“በአገሪቱ ውስጥ በህጋዊ መንገድ ተመዝግበው አገልግሎት ከሚሰጡ የጤና ተቋማት መካከል አዲሱን መስፈርት በበቂ ሁኔታ የሚያሟሉ ተቋማት ስለመኖራቸው አፍን ሞልቶ መናገር አይቻልም” ይላሉ፡፡

Read 3404 times