Saturday, 22 February 2014 12:18

የጉራጊኛ ዘፋኙ በንግድ ሱቅ ውዝግብ በአጎቱ ተገደለ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(9 votes)

የጉራጊኛ ዘፋኙ ፍታ ወልዴ በንግድ ሱቅ ምክንያት በተፈጠረ አለመግባባት የእናቱ ወንድም በሆነው አጎቱ ባለፈው ሰኞ በጥይት ተደብድቦ ተገደለ፡፡ ተጠርጣሪው በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውሎ ምርመራ እየተደረገበት ሲሆን የሟች አስከሬን ወደ ትውልድ ሃገሩ ተወስዶ የቀብር ስነ ስርአቱ ተፈፅሟል፡፡
ሟች እና ገዳይ ከስጋ ዝምድናቸው ባሻገር ከአመታት በፊት በፈጠሩት የልብ ወዳጅነት ነበር መርካቶ በሚገኘው አትክልት ተራ አካባቢ የንግድ ሱቅ የተከራዩት፡፡ ገዳይ የቤቱን ግማሽ አከራይቶ የተቀረውን የአሣ ንግድ ሲያካሂድበት፣ ሟች በበኩሉ ከሙዚቃ ስራው ጎን ለጎን የተለያዩ ተባራሪ ስራዎችን እየሰራ ኑሮውን ይገፋ እንደነበር ምንጮቻችን ይገልፃሉ፡፡
ከጊዜ በኋላ ነው ሟች የሱቁ ባለድርሻነት ጥያቄውን ያነሳው፡፡ ጉዳዩ እስከ ፍርድ ቤት ደርሶም የንግድ ቤቱን ሟች እንዲያስተዳድረው ወደሚል ውሳኔ ይቃረባል፡፡ ይሄኔ ገዳይ “ሁሉም ይቅርና በጋር እንስራ” የሚል ሃሳብ ማቅረቡን የሚናገሩት ምንጮች፤  ሟች ግን በዚህ አልተስማማም ይላሉ “እስከዛሬ በጋራ ፍቃድ እናውጣ ስልህ አሻፈረኝ ብለህ ለኔ ሊወሰን ሲል ነው እንዲህ የምትለው” በማለት ሃሳቡን ሳይቀበለው ቀረ፡፡ ሁለቱን ለማስማማት ጣልቃ የገቡ ሽማግሌዎችም የሱቁ ጉዳይ የመጨረሻ እልባት እስኪያገኝ ገዳይ በኢኮኖሚ እንዳይጎዳ ሟች በወር 4ሺህ ብር እንዲከፍለው አስማሟቸው ይላሉ - ምንጮች፡፡
ከስምምነቱ በኋላ ሟች እና ገዳይ ሰላማዊ ግንኙነት መቀጠላቸውን ያስታወሱት ምንጮች፤ በመሃል ገዳይ “4ሺህ ብሩ አይበቃኝም” የሚል ጥያቄ ማንሳቱን ይናገራሉ፡፡ ባለፈው ሰኞ ገዳይ ሟችን ልጋብዝህ በማለት መርካቶ ሰባተኛ አካባቢ በሚገኝ መጠጥ ቤት ውስጥ ከተገናኙ በኋላ በሽጉጥ ሶስት ጊዜ ተኩሶ እንደገደለው ምንጮቻችን ገልፀዋል፡፡ ነዋሪነቱ መርካቶ 7ኛ አካባቢ የነበረው ሟች፤ ባለትዳር እና የልጆች አባት ሲሆን አስከሬኑ ረቡዕ እለት ቤተሰቦቹ ወደሚገኙበት ሰባት ቤት ጉራጌ መሸኘቱንና የቀብር ስነ-ስርአቱም እዚያው መፈፀሙን ለማወቅ ተችሏል፡፡ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የወንጀል ምርመራ፤ ገዳይን በቁጥጥር ስር አውሎ ምርመራውን እያጣራ መሆኑን ለአዲስ አድማስ ገልጿል፡፡  
ሟች ፍታ ወልዴ ቀደም ሲል ከተለያዩ አርቲስቶች ጋር የጉራጊኛ ዘፈን አልበም ያወጣ ሲሆን በቅርቡም የራሱን አልበም እንዳወጣ ታውቋል፡፡

Read 6089 times