Saturday, 15 February 2014 13:29

በግብረስጋ ግንኙነት ምክንያት የሚከሰቱ አካላዊ ጠንቆች...

Written by 
Rate this item
(31 votes)

የማህጸን በር ካንሰር፣
በማህጸን አካባቢ የሚፈጠር የቅማል ዘር በግብረስጋ ግንኙነት ምክንያት ከሚተላለፉ  መካከል ናቸው፡፡
ዶ/ር ሰሎሞን ኩምቢ (ተባባሪ ፕሮፌሰር) በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጽንስና ማህጸን ሕክምና ትምህርት አስተማሪ እና እስፔሻሊስት ናቸው፡፡ ዶ/ር ሶሎሞን በግብረስጋ ግንኙነት ምክንያት የሚተላለፉ በሽታዎችን ምንነት እና መፍትሔያቸውን ለዚህ እትም ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
ጥ/    የግብረስጋ ግንኙነት ሲባል ምን ማለት ነው?
መ/    የግብረስጋ ግንኙነት ማለት በተለምዶ የወንድ ብልት በሴቷ ብልት ውስጥ ሲገባ ማለት ነው፡፡ ነገር ግን እንደሰዎቹ ስምምነት የሚፈጸሙ ሌሎችም የግብረስጋ ግንኙነቶች አሉ?
ጥ/    በሰዎች ስምምነት የሚፈጸሙ ሲባል ምን አይነቶች ናቸው?
መ/    የግብረስጋ ግንኙነት እንደ ሰዎቹ ስምምነት ይፈጸማል ሲባል በእንግሊዝኛው (Oral & Anal) ማለትም አንዳንድ ጊዜ በአፍ እና በፊንጢጣም በኩል ይፈጸማል፡፡
ጥ/    በግብረስጋ ግንኙነት ምክንያት የሚተላለፉ በሽታዎች ሲባል ምን አይነት ናቸው?
መ/    የሚከሰቱትን ችግሮች በግብረስጋ ምክንያት የሚከሰቱ አካላዊ ጠንቆች ቢባሉ የሚሻል ይመስለኛል፡፡ ችግሮቹ የተለያዩ ሲሆኑ በብዛት የሚታወቁት ግን የአባላዘር በሽታዎች ተብለው የሚጠቀሱት ናቸው፡፡ ከዚህ በተለየ ግን ለምሳሌ...
የማህጸን በር ካንሰር፣
የማህጸን በር ካንሰርን የሚያመጡት ቫይረሶች በመሆናቸው ከወንድ ወደሴት በሚተላለፉበት ወቅት ለበሽታው መከሰት እንደ አንድ ምክንያት ይቆጠራል፡፡ አንዲት ሴት የማህጸን በር ካንሰር እንዳይከሰትባት ለመከላከል ሲባል የሚሰጠው ክትባት የግብረስጋ ግንኙነት መፈጸም ከመጀመሩዋ በፊት ቢሆን የሚመረጥ መሆኑን የህክምናው ዘርፍ ባለሙያዎች ያስረዳለሉ፡፡  
በአስገድዶ መደፈር ወይንም በሰምምነት በሚደረግ ግንኙነት ምክንያት የሴቷ ብልት የውስጥ ክፍል መቀደድ፣
በማስገደድም ይሁን በስምምነት በሚፈጸም ግንኙነት ሳቢያ የሚከሰት የሽንት መቋጠር ችግር፣
በግብረስጋ ግንኙነት ጊዜ ከሚፈጠር አግባብ ያልሆነ የኃይል መጠቀም ወይንም የሰውነት አለመመጣጠን ሳቢያ የሚፈጸም ከሆነ በሴቷ ብልት አካባቢ የሚገኙትን አካላት ጭምር የሚያጠቃ ይሆናል፡፡
ማህጸን አካባቢ የሚፈጠር የቅማል ዘር፡-
በማህጸን አካባቢ የሚፈጠር የቅማል አይነት ከወንድ ወደ ሴት ወይንም ከሴት ወደ ወንድ ሲተላለፍ በሚፈጠረው የመራባት ሁኔታ ቅጫም ሊኖረው ሲችል ከዚያም ወደብብት እና ወደ አይን ፀጉር ጭምር ሊተላለፍ ይችላል፡፡ ስሜቱም በብልት ወይንም በብልት ጸጉር ላይ የማሳከክእና የማቃጠል ሊሆን ስለሚችል ሴትየዋ ወይንም ሰውየው እንደዚህ ያሉ ስሜቶች ከታዩባቸው ቶሎ መፍትሔ መውሰድ ይጠበቅባቸዋል፡፡   
የተለያዩ የቆዳ በሽታዎች በግብረ ስጋ ግንኙነት ምክንያት ሊተላለፉ ይችላሉ፡፡
ጥ/    ሁሉንም በሽታዎች በግብረስጋ ግንኙነት ምክንያት የሚተላለፉ ማለት ይቻላል?
መ/    የሚተላለፉት …Sexually transmissible infectious… ተብለው የሚለዩት ናቸው፡፡ እነርሱም በአማርኛው ጨብጥ፣ ቂጥኝ፣ ውርዴ፣ አባኮዳ፣ ባምቡሌ፣ የሴቶችን ፈሳሽ የሚያመጣ ፕሮቶዝዋ፣ ካንዲዳ የሚባል የፈንገስ አይነት እና ሌሎችም በግብረስጋ ግንኙነት ምክንያት የሚተላለፉ ተብለው የሚፈረጁ ሕመሞች አሉ፡፡ ነገር ግን በብዛት በማህጸን አካባቢ የማህጸኑ፣ የቱቦው እና የእጢው መቆሸሽ (Pelvic inflammatory disease) በሚባል የሚጠራውን ሕመም የሚያመጡት ጎኖሪያ (ጨብጥ)፣ ክላይሚድያ፣ ማይኮ ፕላዝማ እና ዩሪያፕላዝማ የሚባሉ የህዋስ አይነቶች ናቸው፡፡ ስለዚህ ከግብረስጋ ግንኙት ጋር የሚያያዝ ችግር ነው ብሎ መውሰድ ይቻላል፡፡
ጥ/    በተላላፊ በሽታዎቹ ምክንያት የሚከሰተው ሕመም ምን ይመስላል?
መ/    ከተላላፊ በሽታዎቹ ጋር ያሉት ጠንቆች ከማህጸን በላይ እርግዝና፣ ማህጸን ወይንም ብልት አካባቢ የሚኖር ሕመም፣ መካንነት ወይንም ልጅ አለመውለድ፣ በውስጥ አካል (ጉበት)፣ የሆድ እቃ አካባቢ መሰራጨት፣ የአእምሮ፣ የቆዳ፣ የልብ ኢንፌክሽን የማምጣት ...ወዘተ የመሳሰሉትን ሕመሞች ሊያስከትል ይችላል፡፡ ከተጠቀሱት ሕመሞች በተጨማሪም በአለም አቀፍ ደረጃ በግብረስጋ ግንኙነት ምክንያት በመተላለፍ በሽታ ከሚባሉት ውስጥ ኤችአይቪ ቫይረስም አንዱ ነው፡፡
ጥ/    ከግብረስጋ ግንኙነት ጋር ተያይዘው የሚመጡ የሰውነት ጠንቆች ሲባል ምን ማለት ነው?
መ/    ከግብረስጋ ግንኙነት ጋር ተያይዘው የሚመጡ የሰውነት ጠንቆች ሲባል ከላይ እንደገለጽኩት ግንኙነት የሚደረግበት የሴቷ ብልት መቀደድ፣ ፊስቱላ የመሳሰሉት ነገሮች ባህሪያቸው መተላለፍ ሳይሆን በግንኙነት ምክንያት የሚከሰቱ ጠንቆች ሊባሉ የሚችሉ ናቸው፡፡ የማህጸን በር ካሰርንም በቀጥታ ተላላፊ በሚል ከባድ ድምዳሜ መስጠት ባይቻልም ቀደም ሲል ካንሰሩ የነበረባት ሴትጋር በወሲብ የተገናኘ ሰው ወደሌላ ሴት ሲሄድ ቫይረሱን ሊያስተላልፍ ይችላል የሚሉ አስተያየቶች አሉ፡፡
ጥ/    ተላላፊ የተባሉት በሽታዎች በዚህ ዘመንም አሉ? ወይንስ?
መ/    በእርግጥ በግሌ በቅርብ ያጠናሁት ጥናት የለም፡፡ ነገር ግን የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በግብረስጋ ግንኙነት ምክንያት የሚተላለፉ በሽታዎችን ወይንም የአባላዘር በሽታዎችን በጤና ጣቢያ ደረጃ በቀላል እንዴት ማከም እንደሚቻል ለማሳየት መመሪያ ሲያወጣ የተሰራ ጥናት እንደሚያሳየው ጎኖሪያ፣ ክላሚድያ፣ ትሪኮሞኒያሲስ፣ ካንዲድያሲስ የተባሉት ሕመሞች አሁንም ያሉ ሲሆን እንዲያውም በመሪነት ደረጃ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡  ባጠቃላይ ግን ሕመሞቹ በሙሉ አሁንም አሉ ማለት ይቻላል፡፡
ጥ/    በተላላፊ በሽታዎች ምክንያት የሚፈጠሩ የማሳከክ ስሜቶችን ጨው በመሳሰለው ነገር በመጠቀም መታጠብ ምን ይህል ይረዳል?
መ/    አንዳንድ ሴቶች ውሀ በማፍላት በጨው የመታጠብ ወይንም የመዘፍዘፍ እርምጃን ይወስዳሉ፡፡ ይህ በሰዎች ዘንድ ጥሩ ስሜትን ሊፈጥር ይችላል፡፡ ጨው ተፈጥሮአዊ ነገር ስለሆነ ምናልባት የማቃጠል ስሜት ይኖረው እንደሆነ እንጂ ጉዳቱ ብዙም አይታየኝም፡፡ ነገር ግን አንዳንድ ኬሚካሎችን እንደመታጠቢያ መውሰድ በቁስል ወይንም በተቆጣ ሰውነት ላይ ሌላ ችግር ሊያስከትል ስለሚችል አይመከርም፡፡ ጨው ግን ብዙም ጥቅሙ ባይታወቅም ጉዳት ግን የለውም፡፡
ጥ/    ሰዎች እንደመፍትሔ ሊወስዱት የሚገባ እርምጃ ምንድነው?
መ/    መፍትሔውን ስናስብ በቅድሚያ ትኩረት መደረግ ያለበት ጥንቃቄ የተሞላበት የግብረስጋ ግንኙነት ማድረግ ነው፡፡ ይህም ማለት መከላከል የሚቻልበትን ዘዴ መጠቀም ሲሆን ለዚህም አንዱ የሴቶችና የወንዶችን ኮንዶም መጠቀም ማለት ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በተለይም ወጣቶች ከትዳር በፊት የግብረስጋ ግንኙነት ማድረግ እንደማይገባቸው ይመከራል፡፡ ይህ ሀይማኖታዊ ብቻ ሳይሆን በሳይንሱም መንገድ የሚመከር ነው፡፡ ለወጣቶቹ እንደአማራጭ የሚመከረው ፍቅራቸውን በመላፋት ወይንም በመሳሳም ደረጃ ገድበው እንዲይዙት ነው፡፡ ከዚህ በተረፈ የሰውነትን እምቅ የሆነ ስሜት ለማውጣት Masturbation መጠቀም አንዱ ሳይንሳዊ ምክር ነው፡፡ ሁኔታዎች ከዚህ በላይ የሚገፉ ከሆነ ግን ሁለቱም ፍቅረኛሞች ምርመራ አድርገው የጤንነት ሁኔታቸውን በማረጋገጥ ግንኙነት ማድረግ ይችላሉ፡፡ ይህ ምክር የሚሰጠው ለኤችአይቪ ብቻ ሳይሆን ለአባላዘር በሽታዎችም ነጻ መሆን አለመሆን ማረጋገጫነት የሚመከሩ ናቸው፡፡ ከምር መራው በሁዋላም ከዚያ ከሚያውቁት ሰው ጋር ብቻ ግንኙነት ማድረግ ይገባቸዋል፡፡ የአባላዘር በሽታ በወንዶች ላይ ቶሎ ሲገለጽ በሴቶች ላይ ግን በተፈጥሮ ምክንያት ቶሎ ላይታወቅ ይችላል፡፡ ስለሆነም ሕመሙም በጊዜው ስለማይደረስበት በሴቶች ላይ ይበረታል፡፡ ነገር ግን የአባላዘር በሽታዎች ሊታከሙ ወይንም ሕመማቸውን ለመቀነስ የሚ ችሉ ናቸው፡፡ ስለዚህም ባጠቃላይ የሚሰጠው ምክር...
ችግሩ ከመከሰቱ በፊት አስፈላጊውን ጥንቃቄ ማድረግ
ችግሩ ከተከሰተ በግልጽ ከፍቅረኛ ወይንም ከትዳር ጉዋደኛ ጋር መመካከር
ችግሩ ከተከሰተ በአስቸኳይ ወደጤና ተቋም በመሄድ ማማከር ይገባል፡፡
    ሰዎች አስቀድመው አስፈላጊውን እርምጃ ከወሰዱ ቫይረሶቹ፣ ባክቴሪያዎቹ፣ ፈንገሶቹ እና የፕሮቶዞዋው እና ቅማሉን ጨምሮ የሚታከሙና ሊድኑ የሚችሉ ናቸው፡፡

Read 27211 times