Saturday, 15 February 2014 12:36

የራሷ ሲያርባት የሰው ታማስላለች

Written by 
Rate this item
(9 votes)

በዓለም ላይ “የመርፊ ህግ” በመባል የሚታወቅ ህግ አለ፡፡ የምንሠራው ሥራ ሁሉ ስህተት ይሆናል ብሎ የማመን አዝማሚያ ነው፡፡ ስለዚህ ጉዳይ የሚተረክ አንድ ተረት አለ፡፡
ከዕለታት አንድ ቀን አንድ ሰው፤ በአንድ በጣም በራበው ጠዋት፤ ቁርስ አስቀርቦ መብላት ጀመረ፡፡ ዳቦውን ሁለት ላይ ከፈለና አንዱን ግማሽ ቅቤ ቀባው፡፡ ጥሩ አድርጐ ግማሹን ክብ ዳር እስከዳር አሳምሮ ነው በቅቤው ያዳረሰው፡፡ ከዚያ ሻዩን ለማወራረጃ ስለሚፈልገው ስኳሩን አስቀድሞ ከቶ ሻዩን ብርጭቆው ውስጥ ቀድቶ እያዘጋጀ ሳለ፤ ሳያስበው ያን የተቀባ ግማሽ ዳቦ ከጠረጴዛው ገፋና ጣለው፡፡
ዳቦው ወለሉ ላይ ወደቀ፡፡
ደንግጦ ወደ ወለሉ ሲያይ በጣም አስገራሚ ነገር ገጠመው፡፡ የዳቦው ያልተቀባው ወገን ወደመሬት፤ የተቀባው ወገን ወደላይ መሆኑን አየ፡፡ አንዳች ተዓምር እንዳየ ሆኖ ተሰማው፡፡ ተደነቀ፡፡
ወደ ጓደኛዬ ሄደና፤
“ዛሬ ጉድ ነው ያየሁት!” አለ፡፡
“ምን አየህ?”
“ብታምኑም ባታምኑም - ተዓምር ነው ያየሁት!”
“እኮ ምን አየህ? ንገረና!?”
“ቁርስ ስበላ ድንገት ግማሹ ቅቤ የቀባሁት ዳቦ መሬት ወደቀ፡፡ የሚገርመው ያልተቀባው ወገን ወደታች የተቀባው ወደላይ ሆኖ ተገኘ!”
“እረ ባክህ? ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል? የተቀባ ዳቦ ሲወድቅኮ፤ ብዙ ጊዜ የተቀባው ወደ መሬት፣ ያልተቀባው ወደላይ ነው የሚሆነው፡፡ አንተ ያጋጠመህ ተዓምር ካልሆነ በስተቀር ወደላይ ሊሆን አይችልም። ምናልባት ለእኛ አልታወቀን ይሆናል እንጂ አንተ ቅዱስ ሳትሆን አትቀርም፡፡ አምላክ ምልክት ሲሰጥህ ነው” አለ
አንደኛው ጓደኛው፡፡
ከዚህ በኋላ በአንድ ጊዜ ወሬው በመንደሩ ተነዛ፡፡ ሁሉ ሰው ጆሮ ደረሰ፡፡
ሁሉ ሰው መጠያየቅ ጀመረ፡፡
“ይሄ እንዴት ሊሆን ቻለ? ማንም ሰው ያልተቀባው ወገን ወደታች ይሆናል ብሎ አይጠረጥርም፡፡ ዳቦው በተሳሳተ ወገንኮ ነው የወደቀው?” ተባለ፡፡
ማንም መልስ ሊሰጥበት ያልቻለ ትልቅ ጥያቄ ሆነ፡፡
በመጨረሻው “ለሰፈሩ ሊቅ ጥያቄውን እናቅርብለትና እሱ ይመልስልን” ተባለ፡፡
ወደመምህሩ ሊቅ ሄደው የሆነውን ተዓምር ነግረው እንዲያብራራላቸው ጠየቁት፡፡
አዋቂው፤ “በዚህ ጉዳይ ላይ፤ ለመፀለይ፣ ሃሳቡን ለማብላላትና መለኮታዊ ምጥቀት ለማግኘት፤ አንድ ማታ ያስፈልገኛል” አለ፡፡
ጊዜው ተሰጠው፡፡
በነጋታው በጉጉት ህዝቡ እየጠበቀው ሳለ መምህሩ መጥቶ፤
“ነገሩ እንኳን በጣም ቀላል ነው፡፡ ያ ዳቦ የወደቀው በትክክል መውደቅ ባለበት በኩል ነው፡፡ ቅቤው የተቀባው ግን በተሳሳተው ወገን ነው!!” አለ፡፡
                                                            *   *   *
እርግጥ በሀገራችን አንፃር ስናየው፤ ዳቦው ከሌለ ግማሹም ሆነ ሙሉው ተቀባ አልተቀባ ማለት አስቂኝ ይሆን ይሆናል፡፡ የተረቱ ምልኪ ግን፤ ስለወደቀውም ዳቦ አሉታዊ አስተሳሰብ ሊኖረን አይገባም ነው፡፡ ከዚያ ቀጥሎ ዳቦው የዳነው በተሳሳተ ወገን ስለተቀባ ነው የሚለው ሌላው አሉታዊ ምላሽ ነው፡፡ ከዚህ ይሰውረን። ህዝቡም መምህሩም አፍራሽ ይሆኑብናልና!
አንዳንዴ አንዳንድ ምናባዊ ፅንሰ-ሀሳብ ምድር ላይ ቢሆን ምናለበት ያሰኛል፡፡ የዳንቴ ፍልስፍና ለዚህ ይበጀናል፡፡
ሰይጣንን ከማግኘታችን በፊት የወንጀለኞች መቀጫ፤ አውቀው ኃጢአት የሰሩ የሚቃጠሉበት፤ ቦታ አንድ ህግ አለው ይባላል፡- የወሸሙና የከጀሉ፤ በዲያብሎስ ይገረፋሉ፡፡ ሸፋጮች አወናባጆች፣ አይነ ምድር ውስጥ ይደፈቃሉ አጨናባሪ አትራፊዎች እግር-ወደላይ-ራስ ወደ ታች ሆነው አዛባ ውስጥ ይዘፈቃሉ። ጠንቋዮች፣ ጠጠር ጣዮች፣ ዛጎል ወርዋሪዎች፤ አንገታቸው ወደ ጀርባ የሚዞርበት ምስል ይኖራቸዋል። አወናባጅ ፖለቲከኞች የአፈር-ውሃ ጥልቅ ጉድጓድ ውስጥ ይጣላሉ፡፡ አስመሳዮች መሸከም የማይችሉት ካፖርት ይጫንባቸዋል፡፡ ሌቦች በእባብ አለንጋ ይገረፋሉ፡፡ አጭበርባሪ የፖለቲካ አማካሪዎች በእሳት ይዋጣሉ የማይሆን ወሬ የሚነዙ ፍም ውስጥ ይቀበራሉ፣ ይለናል፡፡
ከዚህ ሁሉ ይሰውረን ዘንድ መንገዱን ያብጅልን! ይሄ የገባው እራሱን ይጠብቅ፡፡
የሃገራችን ውሃ፣ የመብራት፣ የስልክ… የባንክ፣፣ የቀረጥ ወዘተ የማይነጣጠሉ ችግሮች፤ የዘንድሮ ጉዴስ እኔም ገረመኝ፡፡
አንዱን ስለው አንዱ አንዱ ባሰብኝ!
የሚለውን የዱሮ የኦርኬስትራ ኢትዮጵያን ዘፈን ያስታውሰናል፡፡ በዚያው ዘመን ስለ ሎተሪ አዟሪ በሚዘፈን ዜማ፤
“እስኪ ተመልከቱት፣ ይሄንን ፈሊጥ
እሱ እድል የሌለው፣ ዕድልን ሲሸጥ!” የሚልም ነበር፡፡ ከሁሉም ይሰውረን፡፡
ዛሬ “የባሰ አታምጣ!” ብሎ መፅናናትም አስቸጋሪ ሆኗል፡፡ እንደዕውነቱ ከሆነ የዕውቀትና የሙያ ክህሎታችን ምን ዓይነት ለውጥ ያመጣል ማለት እንጂ “ፓርቲዬ ከመደበኝ የትም ቦታ እሰራለሁ” ብቻውን መፍትሄ አያመጣም፡፡ ችግሩ የተፈጠረው በፓርቲ ምደባ ምክንያት ከሆነስ? ብሎ መጠየቅም ያባት ነው፡፡ ህዝባችን ፓርቲን እንዲያልም ሳይሆን አገር እንዲያልም ብናስብ መልካም ሳይሆን አይቀርም፡፡
የሀገራችን አካሄድ ዕውን፣ በዳቦ የተሳሳተ ወገን መቀባት? ቅቤውን አፈር አይነካውም በማለት? ዓበው እንደሚሉት ከተምኔታዊ (utopian) ገጠመኝ ይልቅ ሌላውን ግማሽ ምን እናርገው? የትኛው ይበጃል? የሚለውን በቅጡ ማጤን ዛሬም ወሳኝ ነው! በወደቀው ላይ ከመፈላሰፍ እንዴት ቀጣዩን በወጉ እንያዘው? ማለት አንገብጋቢ ጉዳይ ነው፡፡
ከቶውንም በግሎባላይዜሽን (ትርጉሙ እኳኋን በእርግጥ ባልተረጋገጠው ፅንሰ ሀሳብ ተንተርሶ) አገርን ማሰብ የተሳሳተ ድምዳሜ ላይ እንዳያደርሰን ከልብ ማውጠንጠን ይኖርብናል፡፡ ምዕራባውያን አገሮች እስከዛሬ ያልታየ የፋይናንስ ድንገተኛ አደጋ (Financial Calamity) እየገጠማቸው መሆኑን በዋዛ አንየው! ታይቶ በማይታወቅ ደረጃ እየተንኮታኮተ ያለውን የኢኮኖሚ የበላይነት በተምታታ ብዥታ እንደሚመለከተው መታየት ፀሐይ የሞቀው ሀቅ ነው፡፡ ይሄን የውስጥ ድንግርግር በዓለም ዙሪያ በተለይም በአዳጊ አገሮች ላይ በመጫን የንግድ፣ የሽብርተኝነት፣ “የዲሞክራሲን አስፋፋለሁ” መርህ ምህዋር ለማስቀየር መጣጣራቸውን ከመፍራት ይልቅ ማወቅ፣ እጅ ከመስጠት ይልቅ ሉዓላዊነትን ጠንክሮ ማሰብ፤ ደግ መሆኑን የዘመኑ የፖለቲካ ጠበብት እንደሚመክሩ ልብ እንበል፡፡ ዘይት፣ ነዳጅ፣ ማዕድን… ያላቸው አገሮች የሚያስነሱትን ብጥብጥ ያስታውሷል፡፡ የራሳችንን ህዝብ ኢኮኖሚያዊ አሳር ቸል አንበል፡፡ የራሳችንን ህዝብ ፖለቲካዊ ምሬት የራሱ ጉዳይ አንበል፡፡ የራሳችንን ህዝብ አስተዳደራዊ በደል ለሌላ ለማንም ብለን ሳይሆን ለነገ የራሳችን ሰናይ ማንነት ስንል ከጉዳይ እንፃፈው፡፡ የራሳችንን ህዝብ የሞራልና የስነ-ምግባር ምንነት በትምህርት በንቃት፣ በአስተዳደጋዎ አስምህሮት ስራዬ ብለን እንደግፈው፡፡ እነዚህን ከላይ የጠቀስናቸውን ፍሬ - ጉዳዮች በቅጡ አስበንባቸው ችግሮቻችንን በየደረጃውና በወቅቱ ካልፈታን ለጎረቤት አገሮች እያሳየን ነው የምንለውን የመፍትሄ - አሽነት ሚና የለበለጠ ያስመስልብናል!  ትላንት ሩዋንዳ፣ ሱማሌ፣ ጅቡቲ ወዘተ… በሞፈር - ዘመትነት መሄዳችንን የአንገት - በላይ ያረግብናል፡፡ “የራሷ ሲያርባት የሰው ታማስላለች” እንዳይሆን እንጠንቀቅ፡፡  


Read 5032 times