Monday, 10 February 2014 07:06

“…ቁጭ ብለን የሰቀልነውን ቆመን…”

Written by 
Rate this item
(3 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ስሙኝማ…ተቀምጠን እየሰቀልን እኮ ቆመን ማውረድ አቃተንሳ! ልክ ነዋ…ይኸው በምኑም፣ በምናምኑም በአጋጣሚም ቢሆን ‘ወደ ላይ’ ያወጣናቸው “አይ፣ በቃችሁ…” ምናምን ስንል የሚሰማን አጣን፡፡
እኔ የምለው… መቼም ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ… “የተሸነፍነው ስፖርት ጋዜጠኞቹ ግራ አጋብተውን ነው…” ምናምን ተባለ የተባለው…በቃ እንደዚህ የ‘ቻርሊ ቻፕሊን ወራሾች’ ምናምን ሆነን እንቅር! ጭራሽ ታክቲክና ስትራቴጂ በጋዜጠኞች ሆነና አረፈው!
ችግሩ ምን መሰላችሁ…በዛ መያዣ መጨበጫ ባጣን ሰሞን ጋዜጠኞች የኳስ ሰዎቻችንን አወጣን አወጣንና እላይ ‘ጉብ’ ማድረግ! ነገሩ ሲረጋጋና ጎል እያቃሙንና ውራ እያደረጉን ሲልኩን “ለነገሩ እኮ ብዙ ይቀራችኋል…” ሲባል ማን ይስማ! እናላችሁ… እንዲሁ “ከዚህ ያክል ቡድኖች መካከል ምርጥ ተባልን…” “ዓለም በጉጉት የሚጠብቀው የናይጄሪያና የኢትዮጵያ ጨዋታ…” እያልን ነገር ስናሳምር ከረምንና ጭራሽ ቤተክርስትያን የገባች እንትን ጋዜጠኞች ሆነው አረፉት!
(ለነገሩ እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…አንዳንዶቻችን ጋዜጠኞችም እኮ አለ አይደል…ስናደንቅ ‘ቃላት አመራረጥ’ አልቻልንበትም ነበር፡፡ ቀስ ብለን በምትንቃቃ መሰላል በጥንቃቄ እየተረገጠ እንዲወጣ ከማድረግ ይልቅ መንኮራኩር ውስጥ ከተን እንተኩስና ከዛ ማውረዱ መከራ፡፡
እናማ… ቁጭ ብለን የሰቀልነውን ቆመን ማውረድ እያቃታን ነው፡፡   
ደግሞላችሁ…በስነ ጥበባችን አካባቢ መኮፈስ፣ ‘ማበጥ’፣ ምናምን በሽ እንደሆነ ነው የሚወራው። እናላችሁ…አንድ ፊልም ሲወጣ ለስፖንሰርሺፕ እንዲመችም፣ ለፈረንካውም “መቼም ግሩም የሆነ ፊልም” “ግሩም ትወና” ይባልና ሰዉ ሆዬ ያለክሬንና ያለክንፍ ላይ ወጥቶ ቁብ!
እናማ… ቁጭ ብለን የሰቀልነውን ቆመን ማውረድ እያቃታን ነው፡፡   
እናላችሁ… ያስቸገረን ነገር ኖር ከተሰቀሉበት ማማ ለመውረድ ፈቃደኛ አለመሆን ነው፡፡ አንድ ሰሞን እግር ኳሳችንን  ጄኔቭ ድረስ ሲያሯሩጥ የነበረው… ውረድ እንውረድ ብሎ ነገር የለም፡፡
ደግሞላችሁ…አንዳንድ ምሁራን ዘንድ ብትሄዱ…አለ አይደል… በቤተሰብ ጉባኤ፣ የቢራውን ሂሳብ እንዴት ‘እንደሚያዘጋ’ ዘዴው የገባው… የዓይን መነጽር የሚሰካና የኮቱን ኮሌታ ገደድ የሚያደርግ ሁሉ የአሪስቶትል ደቀ መዝሙር የሚያደርግ ምስኪን ተማሪ… ላይ አውጥተው ያስቀምጧቸውና እንዴት ይውረዱ! “ኧረ እንደ እሱ አይነት ችሎታ ያላቸው መአት አሉ፣ እነሱ እንኳን ላይ ሄደው ሊሰቀሉ አጠገባቸው መሰላልም አሳንሰርም የለም…” ሲባሉ ማን ሰምቶ! ነገርዬው… “እኔን ውረድ የምትሉኝ ማናችሁና ነው…” አይነት ነገር ነው፡፡
እናማ… ቁጭ ብለን የሰቀልነውን ቆመን ማውረድ እያቃታን ነው፡፡   
ሙዚቃ አካባቢ ብትሄዱ… አለ አይደል… አንዱ ዕድለኛ አንድ ሲንግል ይለቅና ምን አለፋችሁ፣ እዚህም እዛም የእሱ ዘፈን ከተማውን ሰቅዞ ይይዘዋል፡፡ ዕድሜ ለኤፍ ኤሞች ምን ችግር አለ! (እኔ እንደውም ከዕለታት አንድ ቀን “ኤፍ ኤም ላይ ‘እንዲህ ተደብቆ የከረመው ድምፀ መረዋ…’ ምናምን የሚሉኝ ከሆነ ሲንግል የማልለቅሳ!” ማለቴ አይቀርም፡፡
እናላችሁ…አንዳንድ ፕሮግራሞች ላይ ስለሆነ ሙዚቃ ወይም ስለ ፊልም ሲወራ ግርም ይላችሁና… “እንደው የሥራው ባለቤቶች የዚሀ አይነት ከመሬት እጅግ ከፍ ብሎ ከመንግሥተ ሰማያት ትንሽ መለስ የሚል አደናቆት ለራሳቸው ይሰጣሉ?” ያሰኛችኋል፡፡
እናማ… ቁጭ ብለን የሰቀልነውን ቆመን ማውረድ እያቃታን ነው፡፡   
አንድ የሆነ የማስቲካም ይሁን የመኪና ማስታወቂያ ላይ ሁለት ቀን ብልጭ ብላ የጠፋች እንትናዬ…በቃ ላይ ወጥታ ጉብ! “ኧረ ቀስ ብለሽ ተራመጅ፣ እንደ ሞዴል ‘ለመነስነስ’ ትደርሽበታለሽ…” ቢባል ማን ሰምቶ! በዚህ ላይ ደግሞ ዙሪያዋን ከበው “አንቺ እኮ የሀበሻ ክሌኦፓትራ ማለት ነሽ…” ምናምን የሚላት አሟሟቂ መአት ስለሆነ ኮከቦቹን ልትነካ ደርሳ ‘ማን፣ ኧረ ማን’ ነው ውረጂ የሚላት!”
እናማ… ቁጭ ብለን የሰቀልነውን ቆመን ማውረድ እያቃታን ነው፡፡   
እናላችሁ… የእልፍኝ አስከልካይ ረዳት እንኳን ሳንሆን እንደ ናፖሊዮንነት የሚቃጣን…አለ አይደል… ላይ አውጥተው ሲሰቅሉን ነው፡፡ ስሙኝማ…ምን ይገርመኛል መሰላችሁ…ሰዋችን ከደግነትም ይሁን፣ “ቲራቲር እንሥራበት …” ከማለት ሲያመሰግንና ሲክብ ምን አለፋችሁ…“አሞራ በሰማይ ሲያይሽ ዋለ…” አይነት ነገር ነው፡፡
እናማ… ቁጭ ብለን የሰቀልነውን ቆመን ማውረድ እያቃታን ነው፡፡   
እናላችሁ፣ ነገርዬው እኮ… አለ አይደል… ሰውን የማይሆን ቦታ አውጥቶ ጉብ ማደረግ፣ ልክ ለራሰ በራ ሰው ለልደቱ የማበጠሪያ ስጦታ እንደመስጠት ነው። አሃ፣ ምን ያደርግለታል… አንደኛውን ጭንቄውን ሊነቀስበት ካልሆነ፡፡ ቂ…ቂ…ቂ…
(“ኧረ የራስህ ጭንቄ! ሁለተኛ፣ አይደለም ክትፎና አሮስቶ ዲቢቴሎ ጮርናቄ እንኳን አታገኛትም። ማበጠሪያህን ብላ…” ምናምን የምትሉ ወዳጆቼ ብስጭታችሁ ስለገባኝ ደብዳቤ ሳታስገቡ፣ ኮሚቴ ሳይቋቋም ይቅርታ አድርጌላችኋለሁ፡፡ የቮድካው ተረኛ ማን ነበር!)
እናማ… ቁጭ ብለን የሰቀልነውን ቆመን ማውረድ እያቃታን ነው፡፡   
ስሙኝማ… እግረ መንገዴን… እንደ ድሮ ቢሆን ኖሮ “ጥር የልጃገረድ ጠር…” አበቃ ማለት ነበር! ለነገሩ ጥያቄ አለን… ለጥር ብቻ የተሰጠው ‘የልጃገረድ ጠርነት ለአሥራ ሦስቱም ወራት ይሰጥልንማ! እኔ የምለው…በዛ ሰሞን፣ ‘ያልተነካ’ ምናምን ነገሩ አሥር ሺህ ብር ያወጣል ነው የተባለው! እኔ የምለው…እሱም እንደ ‘ክትፎ’… አለ አይደል… ‘ኖርማልና ስፔሻል’ ነገር አለው እንዴ! አሀ..ማወቅ አለብና! ነገ ድንገት ዲታ ከሆንን ምድረ ሀብታም ሲያደርግ የነበረውን ነገር ሁሉ “ምን የተለየ ነገር  ቢኖረው ነው! ብለን መሞከራችን አይቀርማ!
እግረ መንገዴን…በቀደም አንድ ድረ ገጽ ላይ “ባልና ሚስት መናጠቅ ብሶበታል” ምናምን የሚል ነገር አንብበን ነበር፡፡ አንድ ተረት አለች…
“አገባሻለሁ ያለ ላያገባሽ ከባልሽ ሆድ አትባባሽ”
ይሄ እንግዲህ ያኔ መነጠቅ እንግዲህ የሚያስፎክር ባልነበረበት ጊዜ ይባል የነበረ ነው፡፡
ዘንድሮ ግን ነገርዬው ተሻሽሎ ምን ሊባል ይችላል መሰላችሁ…
“ባልሽ ነኝ ያለሽ መወሸሙ ላይቀር፣ የማንን ጎፈሬ ታበጥሪ ነበር”
ቂ…ቂ…ቂ… ‘ግጥም ተገጠመ’ ይሏችኋል እንዲህ ነው!
እኔ የምለው…እንገዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ… ማስታወቂያው ሁሉ ‘ግጥም፣ በግጥም’ የሆነው…የግጥም ምሽት ስለበዛ ነው እንዴ! ግራ ገባና…አንዳንዱ የማስታወቂያ ‘ግጥም ድርደራ’ እኮ…የድንጋይ ዘመን ትውስታ ነገር ይመስላል። ይሄኔ እኮ የእኔ ቢጤ አሟሟቂ “ፐ! የሠራኸውን ማስታወቂያ ስሰማ እኮ…ምን አልኩ መሰለህ…ይሄ ሰውዬ ኢትዮጵያ ውስጥ መወለድ አልነበረበትም ነው ያልኩት!” እያለ ‘እዛ ላይ’ ሰቅሏቸዋል!
እናማ… ቁጭ ብለን የሰቀልነውን ቆመን ማውረድ እያቃታን ነው፡፡   
ስሙኝማ…ቦተሊከኞችማ አንዴ ካወጧቸው… አለቀ በሉት! ማን ‘እናቱ የወለደችው’ ነው እነሱን ካሉበት ዙፋን ዝቅ ለማድረግ የሚሞክረውስ…አይደለም መሞከር ማንው የሚያስበውስ! ታዲያላችሁ… የአገራችንን መሽቶ ሲነጋ ‘ጠርቶ የማይጠራ’ ቦተሊካችንን ነገሬ ስትሉ የሚያባላን ስር የሰደደ እምነት ምናምን ሳይሆን ይቺ የ‘ውረድ እንውጣ’ ነገር አትመስላችሁም! “በሦስተኛው ዓለም ቦተሊካ ወጣህ ማለት በቃ ወጣህ ማለት ነው!” ብሎ እቅጩን የሚነግረን ሰው እየጠበቅን ነው፡፡ እናላችሁ…ዘላለም “ማን ባሞቀው ወንበር ማን ይቀመጣል፣ ሰማይ ከምድር ይደባለቃል! ” እየተባለ…የምንጨፍረው “ሠላሳ አንድ ዓመት…” ጠብቀን በምንገባባት የኳስ ውድድር ብቻ ሆኗል፡፡
እናማ… ቁጭ ብለን የሰቀልነውን ቆመን ማውረድ እያቃታን ነው፡፡   
ደህና ሰንብቱልኝማ!


Read 3579 times