Monday, 10 February 2014 06:51

የኢትዮጵያዊው የቴክኖሎጂ ፈጠራ በአሜሪካ ለሽልማት ታጨ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

የተሽከርካሪዎችን አቅምና ብቃት የሚለካ ቴክኖሎጂ ፈጥሯል

ኢትዮጵያዊው የምህንድስና ባለሙያ ናሆም በየነ ያቋቋመው ‘ኔቪቲ’ የተሰኘ የቴክኖሎጂ ኩባንያ፣ በየአመቱ በአሜሪካ በሚካሄደው ‘ኢቭሪዴይ ሄልዝ አዋርድስ ኦፍ ኢኖቬሽን’ የተባለ ሽልማት የመጨረሻው ዙር እጩ ተሸላሚ ሆነ፡፡
ኔቪቲ ኩባንያ ያመረተው ‘ናቪሴክሽን ሲስተም’ የተባለ የወጣቱ ኢትዮጵያዊ ፈጠራ፤ ‘ኢመርጂንግ ቴክኖሎጂ’ በተባለው ዘርፍ ለሽልማት ከተመረጡት የመጨረሻዎቹ እጩዎች አንዱ መሆኑ የተገለጸው፣ ላስቬጋስ ውስጥ በተካሄደው የዘንድሮው ዲጂታል ሄልዝ አመታዊ ጉባኤ ላይ እንደሆነ ታዲያስ መጽሄት ከኒዮርክ ዘግቧል፡፡
ኢትዮጵያዊው ናሆም ለሽልማቱ ያሳጨውን ፈጠራ የሰራው፣ በፒትስበርግ ዩኒቨርሲቲ ትምህርቱን በመከታተል ላይ በነበረበት ወቅት በ “ሪሃብሊቴሽን ሳይንስ” ዘርፍ ካከናወነው የዶክትሬት ድግሪ የመመረቂያ ጥናቱ በመነሳት እንደሆነ ተገልጿል፡፡የአሽከርካሪዎችን አቅምና ብቃት ለመለካት የሚያስችሉ መረጃዎችን በተደራጀ ሁኔታ ለመሰብሰብና በመንጃ ፈቃድ አሰጣጥና እድሳት ላይ ጉልህ አስተዋጽኦ ለማበርከት የሚችል የተቀናጀ ቴክኖሎጂ እንደሆነ የተነገረለት ‘ናቪሴክሽን ሲስተም’ በብዙዎች ዘንድ አድናቆትን ያገኘ ሲሆን፤ በአሽከርካሪዎች ደህንነት ላይ ለውጥ የሚፈጥር አዲስ ግኝት እንደሆነ እየተነገረለት ይገኛል፡፡
“የኩባንያዬ ግብ ቤተሰቦች መቼ ማሽከርከር መጀመርም ሆነ ማቆም እንደሚገባቸው የሚያሳይ መረጃ እንዲያገኙ ማድረግ ነው፡፡ አሁን አሁን ማሽከርከር የጤና ጉዳይ እየሆነ መጥቷል። ምክንያቱም በአለም ላይ ከሚከሰቱ የመኪና አደጋዎችና ግጭቶች 93 በመቶ የሚሆኑት ከአሽከርካሪዎች ስህተት ጋር በተያያዘ የሚፈጠሩ ናቸው፡፡” ብሏል፤ ናሆም፡፡
በአሜሪካ በአሽከርካሪዎች ደህንነት ላይ የሚታዩ ችግሮች፣ የመንጃ ፈቃድ አሰጣጥ ስርአቱን በቴክኖሎጂ ፈጠራ ማገዝ እንደሚገባ ማመላከታቸውን የጠቆመው ናሆም፤ ኩባንያው በቀጣይም በተለይ በእድሜያቸው ለጋ ለሆኑና ላረጁ ሰዎች የመንጃ ፈቃድ በሚሰጥበትና በሚታደስበት ጊዜ አግባብነቱን የሚያረጋግጡ መሰል የተሻሻሉ የመኪና ቴክኖሎጂዎችን የመፍጠር ስራውን በስፋት እንደሚቀጥል ተናግሯል፡፡
ናሆም የመጀመሪያ ዲግሪውን ከቴክሳስ ዩኒቨርሲቲ በሜካኒካል ኢንጂነሪንግ፣ሁለተኛ ዲግሪውን ደግሞ ከስታንፎርድ ዩኒቨርሲቲ በባዮ ሜካኒካል ኢንጂነሪንግ ተቀብሏል፡፡ ከፒትስበርግ ዩኒቨርሲቲም በ “ሪሃብሊቴሽን ሳይንስ” ዶክትሬቱን አግኝቷል፡፡ በ2012 “ኔቪቲ” የተባለ ኩባንያውን በማቋቋም ወደስራ ከመግባቱ በፊትም፣ በናሳ ጆንሰን የጠፈር ምርምር ማዕከል በኤሌክትሮኒክስና የኮምፒውተር መሳሪያዎች ዲዛይንና ፈጠራ መስክ ሲሰራ እንደቆየ ታውቋል።


Read 1904 times