Print this page
Sunday, 19 January 2014 00:00

የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ዳይሬክተር ተነስተው በሌላ ተተኩ

Written by 
Rate this item
(8 votes)

በስድስት ወር ጊዜ ውስጥ 28 ጋዜጠኞች ለቀዋል

የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅትን ለስምንት ዓመታት በዋና ዳይሬክተርነት ያገለገሉት አቶ ዘርዓይ አስገዶም ተነስተው፣ የኢህአዴግ የሚዲያ ተቋማትን ሲመሩ የነበሩት አቶ ብርሃነ ኪዳነማርያም እንደተተኩ ታወቀ፡፡ በኢህአዴግ ስር የተመዘገቡ የፓርቲው የሚዲያ ተቋማትን ብቻ ሳይሆን ኢህአዴግ ቀመስ የሆነውን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከልን በኃላፊነት በመምራት የሚታወቁት አቶ ብርሃነ፣ የመቀሌ ከንቲባ ሆነው መሥራታቸው ይታወሣል፡፡ በተጨማሪም ግዙፍ ኩባንያዎችን ባካተተው የኤፈርት ፋውንዴሽን የአመራር ቦታ ነበራቸው፡፡የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ዋና ዳይሬክተር የነበሩት አቶ ዘርዓይ አስገዶም፤ የኢትዮጵያ ብሮድካስት ኤጀንሲ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሆነው መሾማቸው ታውቋል፡፡

በሌላ በኩል፤ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጽ/ቤት ሚኒስትር አቶ ሬድዋን ሁሴን በሰብሳቢነት የሚመሩት የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ቦርድ ከትናንት በስቲያ ለፓርላማ ባቀረበው የግማሽ ዓመት ሪፖርት፣ ከተቃዋሚ ፓርቲ ተወካይ አቶ ግርማ ሰይፋ ትችት ተሰንዝሮበታል። የኢትዮጵያ ሬድዮና ቴሌቪዥን የኢህአዴግን የአብዮታዊ ዲሞክራሲ አስተሳሰብን ያራምዳል ያሉት አቶ ግርማ፤ ይህም ህገ መንግስቱን ይጥሳል ብለዋል፡፡ ድርጅቱ ልማትንና ዴሞክራሲን ለማዳበር እንደሚሰራ የተናገሩት አቶ ሬድዋን በበኩላቸው፤ የተለያዩ ድክመቶችና ችግሮች መኖራቸውን ጠቅሰው፣ ለልማትና ለዴሞክራሲ ግንባታ መስራት ግን ህገ መንግስትን የሚጥስ አይደለም ብለዋል፡፡ ባለፈው አመት በባህርዳር በተካሄደ የኢህአዴግ ጉባኤ፣ በመንግስት ሚዲያዎች ላይ የመንግስትን ብቻ እንጂ የህዝብን ሃሣቦችና ጥያቄዎችን አያስተናግዱም በማለት ፓርቲው ላይ ከፍተኛ አመራሮች ትችት መሰንዘራቸው ይታወሣል፡፡ የድርጅቱ ቦርድ ለፓርላማ ባቀረበው ሪፖርት፤ 118 ቅርንጫፎችና ከ470 በላይ ጋዜጠኞች እንዳሉት ቢገለጽም የአቅም እጥረት እንዳለበት ጠቅሷል፡፡ በግማሽ ዓመት ውስጥ ድርጅቱን ከለቀቁ 140 ገደማ ሠራተኞች መካከል 28ቱ ጋዜጠኞች ናቸው፡፡ በዝቅተኛ ደሞዝ እና ምቹ ያልሆነ የሥራ ሁኔታ ሳቢያ ሠራተኞች ድርጅቱን እንደሚለቅቁ ቦርዱ ገልጾ፤ የድርጅቱ መንታ መዋቅርም ችግር ፈጥሯል ብሏል፡፡

Read 4230 times
Administrator

Latest from Administrator