Saturday, 11 January 2014 12:28

“...እማዬ ጥሩ ሰርታለች...”

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ (ከኢሶግ)
Rate this item
(0 votes)

ከወሊድ በሁዋላ በቤተሰብ ወይንም በጉዋደኛ የሚደረገውን እንክብካቤ በሚመለከት ልጅ ወልደው የነበሩና እማኝነታቸውን የሚሰጡ እናቶችንና ባለሙያን ለዚህ እትም ማብራሪያ ጠይቀናል፡፡ የመጀመሪያዋ እናት የሚከተለውን አስተያየት ሰጥታለች፡፡ “...እኔ ልጅ ከወለድኩ አሁን አምስተኛ አመቴን ይዣለሁ፡፡ በወለድኩኝ ሰአት እናቴ በጣም ትንከባከበኝ ነበር፡፡ ለምሳሌም ...አጥሚት ቢጠጣም ባይጠጣም ጠዋትና ማታ በፔርሙስ እየተሞላ ከራስጌዬ ይቀመጥልኝ ነበር፡፡ እናቴ አጥሚቱ መጠጣት... አለመጠጣቱን ካረጋገጠች በሁዋላም በመጠጫው ትቀዳልኝና አጠገቤ ትቀመጣለች፡፡ ጨርሼ ካልጠጣሁኝ ከአጠገቤ አት ሄድም፡፡ ...በይ ጠጪ ...ጡት ይሆናል... ትለኛለች። ገንፎ በየጠዋቱ በጭራሽ በሌላ ነገር የማይተካ ቁርስ ነው፡፡ ...ይህ እንግዲህ ገና ወፍ ሲንጫጫ እንደሚባለው ከጠዋቱ ወደ 12፡30/ ገደማ ነው፡፡ ከዚያም ረፈድ ሲል ወደ ሶስት ሰአት ገደማ ...ፍርፍር ...ቅንጬ ወይንም ደግሞ ጥብስ... ብቻ የተቻለውን ነገር አዘጋጅታ ታቀርባለች። ...እማዬ ...ገንፎው እኮ ከአንገቴ አልወረደም... ስላት ...ችግር የለም... ይህን ስትበይበት ይወርዳል... የሚል ነው መልሱዋ፡፡ ከሶስት እስከ አራት ሰአት ቁርስ ከበላሁ በሁዋላ ወደ አምስት ሰአት ደግሞ አጥሚት ይቀዳልኛል፡፡ እኔ የፈለገ ነገር ብናገር እናቴ አትሰማኝም፡፡ ስለዚህ ቢያንስ ቢያንስ ቅባቱን ቀንሺው ስላት... አጥሚቱ የተሰራው በወተት ነው... ምንም ቅባት የለበትም ትለኛለች፡፡ ...እኔ ግን ስቀምሰው... ቅቤ እንደአለበት ሳረጋግጥላት... የእሱዋ መልስ... አይ... ትንሽ ላመል ነው ያስነካሁት የሚል ነው። ...እንዲያው ባጠቃላይ የእናቴን እንክብካቤ ምንም አልረሳውም፡፡ በጣም ተጨንቃ... አልፋ ተርፋ ሌሊት ቀስቅሳ አጥሚት የምትሰጠኝ ሳይነጋ የምታበላኝ... ምንም አይረሳኝም፡፡ ፍርፍሩ.. ጨጨብሳው... ጥብሱ... ክትፎው... አረ ምኑ ቅጡ... የማይረሳኝ ነገር የአራስ ጥሪ በግ ታርዶ ሌላ ሰው እንዳይበላው ከልክላ... ብቻዬን እንድበላ የወሰነችው ውሳኔ ነው፡፡ እኔም በዚህ ጊዜ ባለቤቴን ጠርቼ... በቃ እኔ ከመሞቴ በፊት ወደቤቴ መሄድ አለብኝ ብዬ ስወስን... በትንሹ ረገብ አለች፡፡ ለማንኛውም... እናቴ ... ክብደቴን በሶስት እጥፍ አሳድጋው ከአራስ ቤት ወጥቻለሁ፡፡ ይኸው እስከዛሬ ድረስ ሰውነቴ ወደነበረበት አልመለስ ወይንም አልስተካከል ብሎ እታገላለሁ፡፡ እማዬ ጥሩ ሰርታለች፡፡ ነገር ግን ...አጥፍታለችም፡፡” ከላይ ያነበባችሁት የወ/ሮ ትእግስት አለሙን አስተያየት ነው፡፡ ዶ/ር መብራቱ ጀምበር በብራስ የእናቶችና ሕጻናት ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተርና የጽንስና ማህጸን ሕክምና እስፔ ሻሊስት ማብራሪያ የሚከተለው ነው፡፡ ጥ/ ከወሊድ በሁዋላ ሊኖር የሚገባው እንክብካቤ ምን መምሰል አለበት? መ/ አንዲት ሴት በምትወልድበት ጊዜ ሊኖር ስለሚገባው ነገር ከመነጋገር በፊት ከመውለድዋ በፊት የነበረችበትን ማሰብ ይገባል፡፡ ከመውለድ በፊት የሚኖሩ የተለያዩ የጤና ሁኔታዎች በወሊድ ጊዜ ለሚኖረው ጤናማነት ወይንም የጤና መጉዋደል ምክንያት እንደሚሆን እሙን ነው፡፡ አንዲት ሴት አስቀድሞውኑም የተለያዩ የውስጥ ደዌዎች ...ለምሳሌ እንደ ስኩዋር... የደም ግፊት... የልብ ሕመም... የመሳሰሉት ችግሮች ቢኖሩባት ወልዳም ይሁን ከመውለድዋ በፊት ሊደረግላት የሚገባውን በተለይም ከምግብ ጋር በተያያዘ እንክብካቤውን በምን አቅጣጫ ማድረግ እንደሚገባ ያመላክታል፡፡ ከዚህ በተረፈ ግን ወላድዋ በምጥም ይሁን በኦፕራሲዮን ስትወልድ ሰውነትዋ ሊያገኝ የሚገባውን ንጥረ ነገር በተሟላ መልኩ ለመስጠት እንዲያስችል የተለያዩ ምግቦችን በመጠኑ ብትወስድ ይመከራል፡፡ ጥ/ ወላድዋ ወፍራም ወይንም ቀጭን ብትሆን በሚል የሚለይ አመጋገብ ይኖራል? መ/ የወለደችው ሴት ወፈረች ወይንም ቀጠነች ተብሎ የሚለይ ነገር የለም፡፡ በመሰረቱ የአመ ጋገብ ስርአት ለወላዶች ብቻ ሳይሆን... ለማንኛውም ሰው እንደጤናው እና ተፈጥሮአዊው ሁኔታው በምግብ ጥናት ባለሙያዎች በሚሰጠው ምክር በታገዘ መልኩ መመገብ ጥሩ ልምድ ይሆናል፡፡ አንድ ሰው ሰውነቱ የሚፈልገውን ስብ... ካርቦሀይድሬት... ኮለስትሮል... ቫይታሚን... አይረን... ወዘተ... በምን ደረጃ እንደሆነና ምን ምን አይነት ምግቦችን መመገብ እንደሚያስፈልገው የሚያማክሩ ባለሙያዎች በአገራችን በስፋት ቢገኙ ሁሉም ሰው ጤንነቱን በጠበቀ መልኩ መኖር ይችላል፡፡ ወደ ወላዶች ስንመለስ ቀደም ብሎም ይሁን በእርግዝናው ጊዜ የተከሰቱ ሕመሞች ካሉ በማገናዘብ ...ብዛትና ድግግሞሹን ከግምት ውስጥ በማስገባት ከሁሉም ነገሮች በመጠኑ ቢመገቡ ይመከራል፡፡ ቅባት ስኩዋር እና ጨው በምን ያህል ደረጃ ከምግብ ውስጥ መጨመር እንዳለበት አስቀድሞ መገመት ያስፈልጋል፡፡ ታሽገው የሚሸጡ ምግቦችን በሚመለከትም እንደ ቸኮሌት ወይንም ጂውስ የመሳሰሉት ላይ ከፍተኛ ጥንቃቅ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ምክንያቱም ሙሉ በሙሉ ስኩዋሮች ናቸውና መድፈር አያስፈልግም፡፡ ከዚህ ውጭ አልኮሆል ለወላዶች አይመከርም፡፡ የወለደችው ሴት ወፍራም ከሆነች ወይንም ቀጭን ከሆነች በሚል ልንከፋፍለው የምንችለው የአመጋገብ ስርአት ባይኖርም እንደአስፈላጊነቱ ከተለያዩ ምግቦች በመጠኑ እና በተጨማሪም አትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም ጥራጥሬ ዎችን የምግባቸው አካል ማድረግ ጠበቅባቸዋል፡፡” ሌላዋ አስተያየት ሰጪ ልጅ ከወለደች ገና አንድ አመቷ ነው፡፡ ወልዳ በተኛችበት ጊዜ የቤተሰብዋን እንክብካቤ በጥሩ ጎኑ በፍጹም አትረሳውም፡፡ ነገር ግን ጎጂ የነበሩ ሁኔታዎችንም ከዚህ በመቀጠል ለንባብ ብላዋለች፡፡ “...አመጋገብን በተመለከተ ብዙም ችግር አልነበረብኝም፡፡ ምክንያቱም እናቴ እራስዋ ወፍራም ስለሆነች እኔ እንድወፍር ስለማትፈልግ ነው፡፡ እናቴ ለሰውነትዋ ቅርጽ መበላሸት ዋነኛዋ ተዋናይ እናትዋ እንደሆነች በመግለጽ ሁሌ ስለምታማርራት እኔም እርስዋን እንዳማርራት አትፈልግም፡፡ ስለዚህ ምግብ ይቀርባል... ብበላው ባልበላው ብዙም ግልምጫ አይደርስብኝም ነበር፡፡ በዚህ በኩል የነበረው ነገር ብዙም ችግር አልነበረ ውም፡፡ እኔ ወልጄ በተኛሁበት ጊዜ የነበረብኝ ችግር ጠያቂዎችን የማስተናገድ ጉዳይ ነው፡፡ ሁሉም ሰው ሊጠይቀኝ ሲመጣ ታሪኩን ከመጀመሪያው እስከመጨረሻው መስማት ይፈልጋል፡፡ የወለድሽበት ሆስፒታል የት ነው? ሐኪምሽ ማን ነበር? ሆስፒታሉ በባለሙያዎች እንዲሁም በማዋለጃ መሳሪያው ምን ያህል የተደራጀ ነው? የወለድሽው በምጥ ነው ወይንስ በኦፕራሲዮን? ለምን በምጥ አልወለድሽም ? ጡት ታጠቢያለሽ? ...ወዘተ እያንዳንዱ ጠያቂ ከላይ የዘረዘርኩዋቸውን እና ሌሎችንም ጥያቄዎች ከወለድኩበት ቀን ጀምሮ ስለሚጠይቀኝ እጅግ አሰልቺው ነገር ነበር፡፡ በዚህ ላይ የመጣ ሰው ሁሉ የተወለደውን ልጅ ማየት ይፈልጋል። ማየት ሲባል ደግሞ የፊት ገጽታውን ብቻ ሳይሆን የተሸፋፈነውን አካሉን ጭምር ቢሆን የሚመርጡ በርካቶች ናቸው፡፡ በዚህ ላይ ማንን እንደሚመስልም መልስ መስጠት ይጠበቅብኛል፡፡ ሌላው ጥንቃቄ የሚያስፈልገው ነገር ጠያቂ ሲባል ጥንቃቄ በጎደለው መልኩ ሳሎንን አቋርጠው መኝታ ቤት በቀጥታ የሚገቡ ብዙዎች ናቸው፡፡ እንደ ጉንፋን... የተለያዩ የአካል ጠረኖች... የመሳሰሉ ልጁን ሊመርዙ የሚችሉ ነገሮችን በሚመለከት ጥንቃቄ የሚያደርጉ እጅግ ጥቂት ናቸው፡፡ ጠያቂዎች በቀጥታ ልጄ ጋ እንዳይደርሱ ለማድረግ እኔ ወደሳሎን እየሄድኩ ማነጋገር ጀምሬም ነበር። ነገር ግን ወገቤን እያመመኝ ተቸገርኩ፡፡ አንዳንድ ጊዜ ያንን የድሮውን የእናቶች መጋረጃ እመኝ እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡ ከዚህም በመነሳት ለእራሴ ያሰብኩት ነገር ምንድነው... ማንኛዋም ሴት ስት ወልድ ...ቢያንስ እስከ አንድ ሳምንት ድረስ ለሰው መናገር አያስፈልግም ከሚል ደረጃ ደርሻለሁ፡፡ በእነዚህ አስቸጋሪ ጊዜያቶች እናቴን በፍጹም አልረሳትም፡፡ ሳልተኛ ተኝታለች... ሳልታጠብ ሻወር ቤት ነች... ወዘተ... መልስ እየሰጠች ብዙ እረፍት እንዳ ኤልሳቤጥ ያሬድ - ከሰሚት ጥ/ ከሙያ አኩዋያ ጠያቂዎች እንዴት ይገለጻሉ? መ/ እኔ ብዙ ጊዜ የምናገረው ነገር አለ፡፡ ...ወላድዋን የምትወድዋት ከሆነ በስልክ ወይንም በፖስት ካርድ መጠየቅ ይበቃል... አትክበብዋት... የሚል ነው፡፡ ሰዎች ብዙ ጊዜ የማያስቡት ነገር አለ፡፡ የተወለደው ልጅ ወደዚህች አለም የመጣ አዲስ ፍጥረት ነው፡፡ ምንም ነገር የማያውቅ ...በሽታን መቋቋም የማይችል በመሆኑ ጥንቃቄ ልናደርግለት ይገባል፡፡ ነገር ግን ጠያቂዎች በተለይም በሆስፒታል ውስጥ ወላዶቹ ወደቤታቸው ሳይሄዱ እና ሳያመልጡዋቸው ለራሳቸው ጫናን የመቀነስ እርምጃ የሚወስዱ ይመስላሉ፡፡ ሰው ይቀነስ ...ግማሾቻችሁ ውጡ... ሲባሉ ይቆጣሉ... ከሰራተኞች ጋር ይጣላሉ... ወላድዋ እረፍት እስክታጣ ድረስ ክፍልዋን ሞልተው ...በሙቀት እና በትንፋሽ ቤቱ እስኪታፈን ድረስ አልጋዋን ከበው ይቆማሉ፡፡ ይሄ በፍጹም የዘመድ ወይንም የወገንነት ስራ አይደለም፡፡ ጭካኔ ነው፡፡ ለወለደችው ሴትም ሆነ ለተወለደው ልጅ ማሰብን ያላካተተ ነው። ስለዚህ ማንኛውም ጠያቂ ...ወላድዋም ሆነች ሕጻኑ ንጹህ አየር... በቂ እረፍት እንደሚያስፈልገው መገመት ይጠበቅበታል፡፡

Read 2649 times