Saturday, 11 January 2014 12:18

በፍቅር የወደቁ ገጣሚያን!

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(5 votes)

            ጀምስ ኢ.ሚለርና በርኒስ ሎቲ እንዲህ ይላሉ: “Poetry is simply a deep kind of pleasure – like roses, or music, or love” ገጣሚ ስንኝ ከመቋጠሩ በፊት ነፍሱ ከሆነ ነገር ጋር በፍቅር ወድቃ፣ በባህር መዋኘት፣ በአየር መንሣፈፍ አለባት፡፡ ቫዛር ሚላር የተሰኘችው አሜሪካዊ ገጣሚት ይህንን ሃሳብ ስታጎላ “poets have been in love with any number of things.” ትላለች፡፡ ለምሣሌ ቬሊ ከዘማሪዋ ወፍ ጋር በፍቅር እንደወደቀ ነው፡፡ የልቡ ኳስ በቅኔ የሚሞላው፤ የአይኑ ጉንጮች በእምባ የሚጠረዙት፣ የነፍሱ ዋሽንት የሚጠዘጠዘው እርሷን ሲያይ ነው፡፡ ጡቶችዋ ደረትዋ ላይ ዘውድ የደፋ ኮረዳ፣ አይኖችዋ እሣት የሚወረውሩ ሸጋ ከምታስደነግጠው ይልቅ በወፍዋ ሕይወት ይማረካል፡፡ ከአይኑ ሥር የሚፈስስ ፏፏቴ መዐዛና ውበታቸውን አንድ ላይ ከሚወረውሩት አበቦች ይልቅ ወፊቷ ታውረገርገዋለች፡፡ ቲ. ኤስ. ኢሊየት ደግሞ የካቶሊክ መነኮሳትን ሲያይ ይነዝረዋል፡፡ አይኖቹ ይፍለቀለቃሉ፣ ልቡ ቃላት ታዘንባለች፡፡ ሩፐርት ብሩክስ ራሱን “ታላቅ አፍቃሪ” የሚለውም ለዚህ ነው፡፡ ገጣሚ አፍቃሪ ነው፡፡ ስሜቱ እንደ ብይ የምትንከባለልበት የንፋስ ባሪያ ነው፡፡ ስለ ገጣሚ አፍቃሪነት ሳስብ የከበደች ተክለአብ ግጥም ትዝ አለኝ፡፡

“ጣት ወዳጁን ሲያጣ” ከሚለው ግጥሟ ጥቂት ስንኞችን እወስዳለሁ፡፡ ከበደች ጥልቅ ሃሳብ፣ ውብ ስንኞች በእርጋታ የሚያፈስስ ብዕር ያላት የግጥም እመቤት ናት፡፡ “ካንጀት ከወደደ ካደነቀ ዓለምን እንደ ቀሳሚ ንብ ባበባ እንዳረፈ ከቀሰመ ፍቅርን፣ ይጽፍ ነበር ብዕር የውበት ውዳሴን የተፈጥሮ ትንግርት የዓለም ቡራኬን የዓለም ሱታፌን፡፡ በጥዑመ ቃሉ ጣዕም እየሰጠ በኪነት ልሳኑ ልብ እየመሰጠ ወዶ እያስወደደ ቤተ ፍቅር አንፆ ጥቅረ - ላህይ ገልሶ የራሱን አፍቅሮት ባንባቢው አሥርፆ የውበት ዐይኑንም ለሌላው ለግሶ፣ እዩት ይል ነበር ያልታየውን ዳሶ እንዲህ እንዳሁኑ ብዕር እንደዋዛ ተዘንግቶ ሳይቀር ጣት ወዳጁን አጥቶ መሬት ሳይቆረቁር የብሶት ተካፋይ ንፁህ ብራና አጥቶ---” ከበደች የጥበብ ፍቅሯን የምትገልጥበትን ብዕር በሶማሊያ እሥር ቤት ተነጥቃ የፃፈችው ነው፤ የልብዋ ንዝረት፣ የውስጧ ስብራት ድምጽም በስንኞችዋ ይደመጣል፡፡ ኋላ ላይ በአሜሪካ ታዋቂ ገጣሚ የሆነው፣ ነገር ግን በአሥራ ሦስት ዓመቱ በኒውዮርክ ጐዳና የወደቀው ግሪጐሪ ኮርሶ፤ ከልጅነቱ ሶስቱን ዓመታት በእሥር ቤት ስላሳለፈ ፍቅሩ ለሰው ልጆች ይመስላል፡፡ ታዲያ የልቡ ክንፎች ለሰው ልጆች እየተርገበገቡ በሚከንፍበት የዓለም አድማስ ላይ ከሌሎች ነገሮች ጋር በፍቅር የወደቁ ገጣሚያንን ለመተቸት ይቃጣዋል፡፡

ከሰው ልጆች ይልቅ ከዛፍና ሌሎች ግኡዝ ነገሮች ጋር ፍቅር የወደቁ ገጣሚያን ለርሱ ፌዘኞች ናቸው፡፡ ግሪጐሪስ ኮርሶ፤ ግጥም የሰው ልጅ ፀሐይ ናት ባይ ነው፡፡ “The poets cries for a change in society, not for himself but for all peoples” ገጣሚ የሰው ልጆች ጠበቃ፣ የለውጥ ሃዋርያ ነው የሚል ይመስላል፡፡ ገብረክርስቶስ ደስታ ደግሞ በሀገር ፍቅር የተለከፈ ነው፡፡ ለእርሱ ግጥም ማለት የሀገር ሙዚቃ ነፍስና ውበት ነው፡፡ ገብሬ ሲጽፍ ትንሹን ያገዝፋል፣ ረቂቁን ያጎላል፡፡ ጠላውን፣ ሽሮውን ፣ በርበሬውን ፣ ጮማውን፣ ጠጁን ሲተርክ--- ሀገርን ለማስታወስ፣ ትዝታውን ለማቅለም አስቦ ነው፡፡ ስለ ፆታ ፍቅርም ይጽፋል፡፡ ግን እንደሀገር እየነደደ አይደለም፡፡ ለነገሩ ፍቅርስ ያለሀገር ምን ዋጋ አለው? እሣት ያለ ምድጃ ማለት አይደል! “ወጡ ቀለም ሆኖ እንጀራው ብራና ይድረሰኝ ደብዳቤ ተርቤያለሁና ይሽተተኝ ቁሌቱ የቅመም ሽንኩርቱ በርበሬው ይበተን ንፋስ ይዞት ይምጣ በዝናብ ላኩልን ጠላውን ልጠጣ ልስከር በፊልተሩ! ይረሳኝ ችግሩ…” የገብረክርስቶስ ግጥሞች ከሀገር ናፍቆት የተወለዱ ናቸው፡፡ የሀሣቡ ሀውልት ዞሮ ዞሮ ሀገር ላይ ነው፡፡ ልቡ የተሠረቀው በሀበሻዊ ባህሎች ነው - በምግቡ፣ መጠጡና የሙዚቃ መሣሪያዎቹ ጭምር፡፡

“እንደገና” የሚለው ግጥሙ እንዲህ ይላል: “ይናፍቀኝ ነበር … ዞሮ ዞሮ ከቤት ይላል የኛ ተረት፡፡ አቧራው ፀሐዩ ይናፍቀኝ ነበር፤ አፈሩ ጠጠሩ ይናፍቀኝ ነበር፡፡ የመንደር ጭስ ማታ … ይናፍቀኝ ነበር የሣር ቤት ጥቀርሻው መደቡ ምሰሶው፣ ማገሩ ግድግዳው፣ አጥሩና ጥሻው፡፡ የፈራረሰ ካብ … ቀጭን ጠባብ መንገድ በመንደር የሚሮጥ ቅጠል የሸፈነው፣ ሣር ያለባበሰው፤ እነዚህ፤ እነዚህ፤ ይናፍቁኝ ነበር፡፡ የተቆላ ቡና፤ የሚወቀጥ ቡና፤ የጐረቤት ሱፍ አልቦ ሁለተኛ፤ የተረጨ ቆሎ የሚያርቅ መጋኛ፤ የሚጨሰው ዕጣን … እንጀራ በመሶብ የፈሰሰበት ያገልግል እንጀራ የሚቧጠጥ ፍትፍት፣ የክክ ወጥ የሽሮ፣ የሥጋ የዶሮ፡፡ ሀገርን የሠራባቸው ጡቦች ይገርማሉ፡፡ ሳር ቤቱ ከነጥቀርሻው መደቡና ምሠሦው ፣ የድንጋዩ ካብ፤ የተቆላው ቡና፣ የአገልግሉ እንጀራ --- እነዚህ የተዳፈኑ ትዝታን የመፈንቀል አቅማቸው ብርቱ ነው፡፡ የነፍስን ምሠሦ ይነቀንቃል፡፡ እውነትም ቫዛር ሚለር እንዳለችው፤ ገብሬ ባንድ ነገር በፍቅር ወድቋል - በሀገር! ይሄን ሁሉ ያመጣነው ግጥም ያለ ፍቅር የሚፃፍ ጥበብ አይደለም ለማለት ነው፡፡

መጀመሪያ ስሜታችን መግለብለብ፣እንደ ባህር ዛፍ ቅጠል መንደድ፣ ከዚያም እንደ ግራር ከሠል ትርክክ ያለ ፍም መፍጠር አለበት፡፡ እንደ ገብረክርስቶስ ከሀገር ጋር ፍቅር የወደቅ፣ እንደ ቬሊ ከወፍ ጋር የሚበርሩ ያሉትን ያህል፣ ከተፈጥሮ ጋር የተሣሠሩ፣ ከባህርና ሀይቅ ጋር በልባቸው ተቃቅፈው የሚኖሩና የሚፅፉ ሞልተዋል፡፡ የተቃራኒ ፆታ ፍቅር እንደ ቤንዚን እሣት ቦግ እያለ ድንገት የሚጠፋባቸውም፣ የተሰጥዖው ሃይል ካላቸው አንዱ የፍቅር ወደብ ላይ አርፈው፣ ግጥም ማፍሰሳቸው አይቀርም፡፡ ግጥም በውስጡ ፍቅር ያቀፈ እንቁላል ነው፡፡ ፍቅር ማለት ጠንካራ ንፋስ፣ ጣፋጭ ዜማ፣ የማይቋረጥ ሣቅ … የሚያፍን ደስታ ሣይሆን ይቀራል? እንደየ ትርጉሙና እንደየዐውዱ ---- ማን ያውቃል? የመስቀል ወፍና የአደይ አበባ ቀጠሮ እንዳላቸው መስከረም ሲጠባ ማን ያውቃል? በጊዜ፣ በቦታና በሁኔታ የተከበበ የሰው ልጅ ከመልሱ ይልቅ ጥያቄው ላይ ተንጠልጥሎ እየተወዛወዘ አይደል የሚኖር? …

Read 5125 times