Saturday, 11 January 2014 11:40

ዋልያዎቹ ከቻን በኋላስ…

Written by 
Rate this item
(3 votes)

         3ኛው የአፍሪካ አገራት የእግር ኳስ ሻምፒዮንሺፕ ዛሬ በኬፕታውን ሲጀመር በምድብ 3 የመጀመርያ ጨዋታውን ሰኞ ከሊቢያ ጋር የሚያደርገው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ትናንት ወደ ደቡብ አፍሪካ አምርቷል፡፡ ኮንጎ ለውድድሩ በ2013 የመጨረሻ ቀን ደቡብ አፍሪካ በመግባት ከ15 እንግዳ ብሄራዊ ቡድኖች የመጀመርያዋ ስትሆን ሊቢያ በሳምንቱ አጋማሽ ላይ ገብታ እየተዘጋጀች ነው፡፡ ጋና ያለፈውን ሰሞን በናሚቢያ ስትዘጋጅ ቆይታለች፡፡ የቻን ውድድር ሁሉም ጨዋታዎች በዲኤስቲቪ “ሱፐር ስፖርት 4” እና በጎቲቪ “ሱፐር ሴሌክት” ቻናሎች የቀጥታ ስርጭት እንደሚኖራቸውም ሲታወቅ የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቭዥን ድርጅት በውድድሩ ላይ የዘገባ ሽፋን ከመስጠት ባሻገር የቀጥታ ስርጭት አይኖረውም፡፡ 3ኛው የቻን ውድድር የሚዘጋጅባቸው ኬፕታውን፤ ብሎምፎንቴንና ፖልክዋኔ ከተሞች በስታድዬም ትኬት ሽያጭ አልተሳካላቸውም፡፡ የመክፈቻው ስነስርዓት 54ሺ ተመልካች በሚይዘው የኬፕታውን ስታድዬም ላይ በዛሬው ዕለት ሲከናወን ለመጀመሪያዎቹ ሁለት ጨዋታዎች 10ሺ ትኬት መሸጡን ያመለከቱ ዘገባዎች በብሎምፎንቴንና ፖልክዋኔ ከተሞች የቻን ትኬቶች በቅናሽ ቢቀርቡም እንደተጠበቀው አልሆነም ተብሏል፡፡ አዘጋጆቹ በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ የኢትዮጵያ፤ ዲሪ ኮንጎ፤ ናይጄርያና ዚምባቡዌ ዜጎች ለውድድሩ ድምቀት ይፈጥራሉ በሚል ተስፋ አድርገዋል፡፡

የቻን ውድድር ለተሳታፊዎቹ ለ16ቱ ብሄራዊ ቡድኖች መጠናከር ከማገዙም በላይ አንዳንዶቹ የአህጉሪቱን ጠንካራ ቡድኖች በመግጠም ልምድ ያገኙበታል፡፡ በወዳጅነት ጨዋታ ደረጃ የሚፈረጀው ውድድሩ የፊፋ ወርሃዊ እግር ኳስ ደረጃን በውጤት በማሻሻል ከሁለት ወራት በኋላ ለ2015 የአፍሪካ ዋንጫ ለሚደረገው ድልድልም ወሳኝ ይሆናል፡፡ በአፍሪካ ትልልቅ ሊግ ውድድሮች ተሳታፊ ለሆኑ ክለቦች የሚሰሩ በርካታ የተጨዋች መልማዮች በቻን ውድድር ይኖራሉ፡፡ በቻን ውድድር ከኢትዮጵያ በጉጉት የተጠበቁት አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው ናቸው፡፡ ወደ ደቡብ አፍሪካ ከማቅናታቸው በፊት ዋና አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው በኢንተር ኮንትኔታል ሆቴል ልዩ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡ ‹‹አዲስ ነገር እንፈልግ፤ ለለውጥ ራሳችንን እናምጣ፤ ለብሄራዊ ቡድን ምን ይደረግ፤ ሰፋ ባለ ነገር ብንወያይ እመርጣለሁ፡፡ የእድገት አመላካች የሆኑ ጉዳዮች ላይ መስራት ያስፈልገናል፡፡ ይህ የናንተ ትውልድ ነው፡፡ በፊት የማናውቀው ታሪክ ውስጥ ነው ያለነው፡፡

ለአፍሪካ ዋንጫ ከ31 ዓመታት መራቅ በኋላ ተሳትፈናል፡፡ እስቲ በቀጣይ ተሳትፏችን እንዴት ማደግ አለበት በሚል እንጠያየቅ፡፡…. ይህ ቡድን የናንተ ነው፡፡ እኔ ከአሁን በኋላ 30 ዓመት ለመቆየት አልችልም፡፡ ከእንግዲህ ለኢንተርናሽናል ውድድሮች ማለፍ እና መሳተፍ አለብን፤ ለምን ውጤቱ የህዝብ ነው፡፡›› ብለው አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው በጋዜጣዊ መግለጫው ተናገሩ፡፡ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ከቻን በኋላ በ2015 በሞሮኮ ለሚደረገው 30ኛው የአፍሪካ ዋንጫ፤ በ2018 በራሽያ ለሚደረገው 21ኛው ዓለም ዋንጫና በቻን ውድድር እንዲያልፍ የሚያስፈልገውን ጥረት በመጠቆም ጥሪ ማቅረብ ዋና ትኩረታቸው ነበር፡፡ በተጨዋቾች ምርጫ፤ ዝግጅትና፤ ዲሲፕሊን ዋና አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው እንደገለፁት የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ለቻን ያደረገው ዝግጅት የተፈለገውን ያህል የተጨዋቾች ብዛት አካትቶ የተሰራበት አልነበረም። ከካፍ የተጨዋቾች ዝርዝር ማሳወቂያ መመርያ ቀነገደብ የመጀመርያው መጨናነቅ ነበር፡፡ ቀነገደቡ ያለፈባቸው አንዳንድ ተጨዋቾች የህክምና ምርመራውን ባለማድረጋቸው ሊሳተፉ አልቻሉም፡፡

በሌላ በኩል ባለፉት ሁለት ዓመታት በብሄራዊ ቡድኑ ቁልፍ ሚና የነበራቸው ወሳኝ ተጨዋቾችን ለመተካት የነበረው ሂደት ፈተና ነበር ፡፡ አስቀድመው የነበሩት ውጤታማ ተጨዋቾች ከአገር ውጭ ባሉ ክለቦች በመጫወታቸው በቡድኑ ሊያዙ አለመቻላቸው በዝግጅቱ ላይ ክፍተት ፈጥሮ እንደነበር የገለፁት አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው፤ በተጨዋች ምርጫቸው በተከላካይ፤ አማካይ እና አጥቂ መስመር በጎደሉ ተጨዋቾች የሚያስፈልጉ ተተኪዎችን ለቡድኑ ለማዘጋጀት እና ስብስቡን ለማስተካከል ስንጥር ጊዜ ወስዶብናል ሲሉ ተናግረው ዋናው ትኩረታቸው ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን የሚመጥኑ ተጨዋቾች ለማግኘት ነበር ብለዋል። በቻን ለሚሳተፈው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን የተመረጡት 3 በረኞች፤ 8 ተከላካዮች፤ 8 አማካዮችን እና አራት አጥቂዎች ናቸው፡፡ ዋና አሰልጣኙ ምርጫቸውን በጎደሉ ቦታዎች ላይ ትኩረት በማድረግ ያካሄዱት እንደሁኔታው አማካይ እና አጥቂ በማድረግ እያቀያየርን የምናሰለፋቸውን ተጨዋቾች ለማብዛት እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡ በሴካፋ ውድድር ተተኪ ተጨዋቾች ለማግኘት ሃሳብ ስለነበር ከየክለቡ ለብሄራዊ ቡድን ገብተው ያልተጫወቱ ልጆችን ለሴካፋ ይዘን በመሄድ አዳዲስ ልጆች ሞክረዋል፡፡ በአንድ ቀን ልምምድ በሴካፋ ባደረግናቸው ጨዋታዎች የአንዳንድ አዳዲስ ተጨዋቾችን ብቃት ተመልክቼ ነበር ያሉት አሰልጣኝ ሰውነት፤ ሙሉ ለሙሉ የነበሩትን ተጨዋቾች የሚተኩ ብቁ ተጨዋቾችን እንደፈለግነው አላገኘንም ብለዋል፡፡ ከሳምንት በፊት በናይጄርያ አቡጃ ከናይጄርያ የቻን ቡድን ጋር 2ለ1 ስለተሸነፉበት የአቋም መፈተሻ ግጥሚያ ሲናገሩ ደግሞ፤ በጨዋታው የናይጄርያ ቡድን የዓለም ሻምፒዮን ከሆነው የሀ 17 ቡድን በርካታ ተጨዋቾችን በስብስቡ በማካተት ሲቀርብ እኔ ከየት አሳድጌ ልቅረብ ብዬ ተከፍቻለሁ ብለዋል፡፡ የናይጄርያ ብሄራዊ ቡድን ባለው ጥንካሬ ለቡድናችን አቋም ጥሩ መፈተሻ ነበር ያሉት ዋና አሰልጣኙ፤ ስቴፈን ኬሺ በቡድናቸው አጨዋወት በመማረክ አድናቆቱን እንደገለፀላቸው ተናግረዋል፡፡ “በወዳጅነት ጨዋታው የተማርነው በመከላከል፤ በጎል ማስቆጠር ችግሮች አሁንምእንዳሉ ነው፡፡

በተከላካይ ተጨዋቾች በሚሰሩ ጥቃቅን ስህተቶች ጎሎች ይቆጠሩብናል፡፡ በአጥቂ መስመር ላይ ያሉን ተጨዋቾች ያገኙትን የግብ እድል መጠቀም እና የማግባት ችግርም እንዳለ ነው፡፡ ይህን ለማስተካከል አሁን ባሉ ተጨዋቾች ላይ የሚሆን አይደለም፡፡ ከታዳጊ ደረጃ ተነስቶ በመስራት የተጨዋች ብቃትን ማሻሻል ብቻ ይቻላል ብዬ አምናለሁ፡፡” በብሄራዊ ቡድን ተጨዋቾች ዲሲፕሊን ዙሪያ ዋና አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው ሲያስረዱ፤ አሁን የሚያሳስብ የዲስፕሊን ችግር ያለበት ተጨዋች የለም ሲሉ ተናግረው፤ የብሄራዊ ቡድን ተጨዋቾች የስነምግባር መመርያ በማስቀመጥ ተጨዋቾችን ለመቆጣጠር ለጊዜው የሚያግዝ አሰራር አይሆንም፤ ምክንያቱ በርካታ ተጨዋቾችን ከሌሎች ጋር አፎካክሮ፤ በዲስፕሊን እየቀረፁ ለማሰልጠን በበቂ ሁኔታ ተተኪ አለመኖሩ እክል ይፈጥራል ብለዋል፡፡ በአሁኑ የቻን ቡድን የሚሰክር ተጨዋች የለበትም ሲሉም በልበሙሉነት ተናግረዋል፡፡ በአጠቃላይ ግን ለቻን በመረጥነው ቡድን በየክለባቸው ጥሩ የሚንቀሳቀሱትን፤ በወቅታዊ ብቃታቸው ያመንባቸውን መርጠናል፡፡ ምርጥ ብቃት ኖሮት ሳልመርጠው የቀረ እና የምቆጭበት ተጨዋች የለም በማለት አሰልጣኙ ይናገራሉ፡፡ የተጨዋቾች አያያዝ በክለቦችና ብሄራዊ ቡድን የብሄራዊ ቡድን ተጨዋቾችን በማሰባሰብ ለአንድ አህጉራዊ ውድድር ለማዘጋጀት አንድ ሳምንት በቂ ነበር የሚሉት ዋና አሰልጣኝ ሰውነት፤ የፕሪሚዬር ሊግ ውድድር ጥንካሬ ስለሌለው ይህን ማድረግ አልተቻለም፡፡ ሁል ጊዜ በአሰልቺ ሁኔታ ለመስራት ግድ እየሆነብን መጥቷል ብለዋል፡፡ በአጠቃላይ ግን እስከ 3 ሳምንት እና አንድ ወር ተጨዋቾች በሆቴል ተቀምጠው መስራታቸው ግድ እንደነበር የሚያስረዱት አሰልጣኙ፣ ሁኔታው ተጨዋቾቹን በተለይ በተመጣጠነ ምግብ ተጠቃሚ ስለሚያደርጋቸው በዚሁ መሠረት ዝግጅቱ መከናወኑን አመልክተዋል፡፡

ለብሄራዊ ቡድን የሚያዙ ተጨዋቾች በክለቦች ሲቆዩ ወጥ ስልጠና፤ አመጋገብ እና የዲስፕሊን ስርዓት ስለማይኖራቸው ለሶስት እና ለ4 ሳምንት በብሄራዊ ቡድን ተይዘው መስራታቸው ይገባል ነው የአሰልጣኙ እምነት፡፡ አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው እንዳስታወቁት አንዳንድ ተጨዋቾች ከብሄራዊ ቡድን ወጥተው ወደ ክለባቸው ሲመለሱ ከጥቅም ውጭ ሆነውና ከስተው ነው፡፡ በብሄራዊ ቡድን ደረጃ እና በፕሪሚዬርሊግ የሚወዳደሩ ክለቦች ያለው የተጨዋቾች አመጋገብ ይለያያል፡፡ ‹‹ ምግብ፤ ልምምድ እና እረፍት ተጨዋችን ብቁ የሚያደርጉ ነገሮች ናቸው፡፡ ከሶስቱ አንዱን ማጣት አያስፈልግም፡፡ በየክለቡ ተጨዋቾች ቅቅል እና ጥሬ ስጋ እየበሉ እንዴት ብቁ ይሆናሉ፡፡ ክትፎ እና ቀይ ወጥ እየተበላ ይቻላል እንዴ፡፡ ተጨዋቾች ብሄራዊ ቡድን ሲገቡ እኮ አካል ብቃታቸውን የሚገነቡት በአመጋገባቸው በባለሙያ በተዘጋጀ ሜኑ መሰረት ነው፡፡›› በማለት ዋና አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው ለአህጉራዊ ውድድር በሚደረግ ዝግጅት ተጨዋቾች በብሄራዊ ቡድን ከ1 ሳምንት በላይ ተሰባስበው የመዘጋጀታቸውን ጥቅም ያስረዳሉ፡፡ በክለቦች የስልጠና መዋቅር ተጨዋቾች በበቂ ሁኔታ ዝግጁ ሆነው ቢገኙ ወደ ብሄራዊ ቡድን ገብተው ሲሰሩ ውጤታማ ለመሆን በተቻለ ነበር፡፡ ክለቦች ይህን የመሰለውን መሰረታዊ መዋቅር አለመከተላቸው ችግር እየፈጠረ ቆይቷል ብለዋል፡፡ “ተጨዋቾች እግር ኳስ ሙያቸው፤ የገቢ ማግኛቸው ህይወታቸው መሆኑን ማወቅ አለባቸው፡፡ ማንም ተጨዋች ራሱን ጠብቆ ለልምምድ የሚመጣበትን ሁኔታ መማር ማወቅ አለበት፡፡

ሆቴል ቁጭ ማድረግን እኛም አንፈልገውም። በማለት አሰልጣኝ ሰውነት የተናገሩት ክለቦች በስራቸው ከብሄራዊ ቡድን ጋር ተመጋጋቢ ሆነው የመስራታቸውን ጠቀሜታ ለማመልከት ነው፡፡ በቻን ስለሚጠበቅ ውጤት በደቡብ አፍሪካ በሚዘጋጀው 3ኛው የአፍሪካ አገራት ሻምፒዮንሺፕ ስንገባ የማናውቀውን ቻን ለማወቅ ነው ያሉት ዋና አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው፤ እንደማንኛውም ቡድን ቀዳሚ ግባችን ዋንጫውን ማምጣት፤ ካልሆነ አራት ውስጥ መግባት፤ ካልሆነ ሩብ ፍፃሜ መድረስ፤ ካልሆነ ተሸንፎ መምጣት ነው። ተሸንፎ መምጣት እንደ ውድቀት ሊቆጠር ይችላል ብለዋል። ብሄራዊ ቡድኑ በቻን ውድድር የመጀመርያ ተሳትፎውን በማድረጉ ብቻ ተጫውቶ ቢመለስ እንደ ስኬት መቁጠር ይገባል የሚሉት አሰልጣኙ፤ በማያውቀው ውድድር የገባ ስለሆነ በአሁኑ ወቅት የሚያደርጋቸው ነገሮች ሁሉ ስኬት ናቸው፡፡ ከዚያ በኋላ ብቻ ከተሳትፎ የዘለለ ውጤት መጠበቅ ይኖርበታል ሲሉ ተናግረዋል፡፡ ኢትዮጵያና ሊቢያ በቻን ውድድር የምድብ 3 የመጀመርያ ጨዋታ ላይ የሚገናኙት ለ8ኛ ጊዜ ነው፡፡ የሊቢያ ብሄራዊ ቡድን በአገር ውስጥ ክለቦች በሚገኙ ተጨዋቾች ለመገንባት ብዙም እንዳላደከመ ሲታወቅ በዘንድሮ ተሳትፎው እስከግማሽ ፍፃሜ ለመድረስ እቅድ ይዟል፡፡ ሊቢያ በቻን ውድድር የምትሳተፈው ለ2ኛ ጊዜ ሲሆን ለመጀመርያ ጊዜ በ2009 እኤአ ላይ በ1ኛው የአፍሪካ አገራት የእግር ኳስ ሻምፒዮንሺፕ ስትሳተፍ በምድቧ በሶስት ጨዋታ 2 ነጥብ አግኝታ ከጥሎ ማለፍ በፊት ከውድድሩ ተሰናብታለች፡፡

በታሪካቸው በሁሉም ውድድሮች 7 ጊዜ በተገናኙበት ወቅት እኩል ሶስት ጊዜ ሲሸናነፉ በ1 ጨዋታ አቻ ተለያይተዋል፡፡ ሁለቱ ቡድኖች ለመጀመርያ ጊዜ ሲገናኙ በ1969 እኤአ በዓለም ዋንጫ ማጣርያ የደርሶ መልስ ጨዋታዎች ነበር፡፡በመጀመርያው ጨዋታ ሊቢያ ሜዳዋ ላይ 2ለ0 ስታሸንፍ በመልሱ ጨዋታ ደግሞ ኢትዮጵያ 5ለ1 በሆነ ውጤት ለማሸነፍ በቅታለች፡፡ ሁለቱ ቡድኖች በ1979 እኤአ ላይ የተገናኙት በአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ የደርሶ መልስ ጨዋታዎች ነው፡፡ የመጀመርያውን ጨዋታ ሊቢያ 2ለ1 ስትረታ በመልሱ ጨዋታ በኢትዮጵያ ሜዳ አንድ እኩል አቻ ተለያይተዋል፡፡ በ1983 እኤአ ላይ ሁለቱ ቡድኖች ለአምስተኛ ጊዜ የተገናኙት በኢንተርናሽናል ጨዋታ ሲሆን ኢትዮጵያ ጨዋታውን በሜዳዋ በ1ለ0 አሸናፊነት ተወጥታለች፡፡ በ2006 እኤአ በአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ ተገናኝተው ኢትዮጵያ 1ለ0 ስታሸንፍ፤ በ2007 እኤአ ላይ ደግሞ በተመሳሳይ ውድድር 3ለ1 ያሸነፈችው ሊቢያ ነበረች፡፡ ታዋቂው የእግር ኳስ ዘጋቢ ድረገፅ ጎል ዶትኮም በሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ላይ አንባቢዎቹን አሳትፎ በሰራው የውጤት ትንበያ 19.05 በመቶ ኢትዮጵያ 3ለ1 እንደምታሸንፍ ሲገምቱ፤ ሌሎች 19.05 በመቶ ሊቢያ 2ለ0 እንደምታሸንፍ ሲገምቱ ቀሪዎቹ ገማቾች ሊቢያ 3ለ0 እንደምትረታ ጠብቀዋል፡፡ ቀዮቹ ሰይጣኖች ተብለው የሚጠራው የኮንጎ ኪንሻሳ ቡድን በ2000 እኤአ በአፍሪካ ዋንጫ ከተሳተፈ ወዲህ ወደ ትልልቅ ውድድሮች መመለስ ቸግሮት ቆይቷል፡፡ መካከለኛውን አፍሪካ በመወከል የብሄራዊ ቡድኑን ጥንካሬ ለመመለስ ተፎካካሪነቱ ተጠብቋል፡፡ ኮንጎ በቻን ውድድር ስትሳተፍ የመጀመርያዋ ሲሆን በካሜል ጃቡር የሚሰለጥነው ቡድኗ ያልተጠበቀ ብቃት እንደሚያሳይ ተገምቷል፡፡ ኮንጎ እንደ ኢትዮጵያ ሁሉ በዓለም ዋንጫ ማጣርያዎች አስገራሚ ውጤቶች ነበሯት፡፡

ኢትዮጵያ ከኮንጎ በሚያደርጉት ጨዋታ በጎል ዶት ኮም አንባቢዎች መቶ በመቶ የአሸናፊነት ግምቱ ለኢትዮጵያ ሲሆን ውጤቶቹ 3ለ1 እና 2ለ0 ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ ከኮንጎ ጋር በ3ኛው የቻን ውድድር ሲገናኙ በታሪክ ለ3ኛ ጊዜ ሲሆን፤ በ1967 እኤአ በኢንተርናሽናል ጨዋታ 1ለ0 እንዲሁ በ1968 በአፍሪካ ዋንጫ 3ለ2 ኮንጎ አሸንፋለች፡፡ በምድብ 3 ለኢትዮጵያ ከባድ ተጋጣሚ ትሆናለች የተባለችው ጋና በቻን ተሳትፏዋ ለማይክል ኤስዬን እና ለአንድሬ አየው ምትክ የሚሆኑ ወጣቶችን እንደምታገኝ ትጠብቃለች፡፡ ጋና በቻን ውድድር ምድቧን በቀላሉ ማለፍ እንደምትችል ግምት ከማግኘቷም በላይ ለዋንጫው ተፎካካሪነት እንደምትበቃም እየተነገረ ነው፡፡ በ2009 እኤአ ለመጀመርያ ጊዜ በቻን ውድድር ስትሳተፍ ሁለተኛ ደረጃ አግኝታ የነበረችውና በ2ኛው የቻን ውድድር ከምድብ ማጣርያ የተሰናበተችው ጋና ዘንድሮ ለዓለም ዋንጫ ዋናው ቡድኗ በማለፉ የቻን ቡድኗ ተጨዋቾች በከፍተኛ መነቃቃት አስገራሚ ብቃት ሊኖራቸው ይችላል፡፡ የቡድኑ አሰልጣኝ የሆኑት ማክስዌል ኮንዱ በስብስባቸው ከጋና ፕሪሚዬር ሊግ መሪ ክለብ አሻንቲ ኮቶኮ 8 ተጨዋቾች የያዙ ሲሆን በኳስ ቁጥጥር ያለውን ድክመት በመቅረፍ ውጤታማ ለመሆን አስበዋል፡፡ በጎል ዶት ኮም በኢትዮጵያ እና ጋና ጨዋታ ላይ በቀረቡት 3 የውጤት ግምቶች ኢትዮጵያ 3ለ1 እንደምታሸንፍ 33.33 በመቶ ሲገምቱ ጋና 2ለ0 33.33 በመቶ እና 3ለ1 33.33 በመቶ ውጤትን ተንብየዋል፡፡ኢትዮጵያ እና ጋና ሁለቴ ተጫውተው አንድ እኩል ተሸናንፈዋል፡፡ በ1963 እኤአ በአፍሪካ ዋንጫ ጋና 2ለ0 ስታሸንፍ፤ በ1996 እኤአ በኢንተርናሽናል ጨዋታ ኢትዮጵያ 2ለ0 ረታለች፡፡ በታዳጊና ወጣት ብሄራዊ ቡድኖች ተተኪዎችን ለማግኘት በአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን ሰሞኑን በ2015 እኤአ በታዳጊና ወጣት ብሄራዊ ቡድኖች በሚካሄዱ ውድድሮች ለመግባት የጥሎ ማለፍ ማጣርያዎችን የሚሳተፉ አገራት ተመርጠዋል፡፡

በሀ 20 ወጣት ብሄራዊ ቡድን ውድድሮች እንዲሳተፉ ከ54 የካፍ አባል አገራት 37 ሲመረጡ ፤በሀ 17 ታዳጊ ብሄራዊ ቡድን ውድድሮች የሚሳተፉት ደግሞ 40 ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ በሁለቱም የታዳጊና ወጣት ውድድሮች እንድትሳተፍ ብትመረጥምም ሁለቱም ብሄራዊ ቡድኖች አለመኖራቸው የሚያሳስብ ነው፡፡ ከቻን በኋላ የኢትዮጵያ እግር ኳስ አሁን ባለበት ሁኔታ መቀጠል የለበትም በማለት በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ በአፅንኦት ያሳሰቡት ዋና አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው ናቸው፡፡ በቀጣይ ለአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ፤ በዓለም ዋንጫ ማጣርያዎች ጠሩ ተፎካካሪ ሆኖ ለመቀጠል በቻን ውድድር ቋሚ ተሳትፎ ለማግኘት በመላው አገሪቱ በመዘዋወር የታዳጊ ተጨዋቾችን ፈልጎ በመመልመል መስራት እንደሚገባ፤ ከ20 ዓመት በታች ጀምሮ ተተኪ ቡድኖች በየደረጃው በአገር አቀፍ ደረጃ ተዋቅረው መሰራት እንደሚያስፈልግ፤ ለብሄራዊ ቡድኑ ቀጣይ የውጤታማነት ጉዞ ግብዓት ሊሆኑ የሚችሉ አሰራሮችን መተግበር እንደሚገባ ሃሳብ አቅርበዋል፡፡ በየክልለሉ ታዳጊ እና ወጣት ተጨዋቾችን የማሰባሰብ ፍላጎት አላቸው፡፡ ይህንንም ለፌደሬሽኑ ገልፀው ምላሹን እየተጠባበቁ ነው፡፡ ዋና አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው ለታዳጊ እና ወጣት ቡድኖች ልዩ ልዩ ውድድሮች ማዘጋጀት፤ ልምድ የሚቀስሙባቸውን ኢንተርናሽናል የውድድር ተሳትፎዎች በትኩረት ማግኘት እና የልምድ ጨዋታዎችን በማድረግ እየተሰራ እና መሰረታዊ ስልጠና በስፋት መተግበር ከተቻለ አሳሳቢው የተኪ ተጨዋቾችን ችግር መቅረፍ አይከብድም በማለትም መክረዋል፡፡ ‹‹እነ ናይጄርያ ተተኪ ተጨዋቾች አላቸው፡፡ ከብሄራዊ ቡድን በታች በየእድሜ ደረጃው ቡድኖች አሏቸው በየጊዜው ያሳድጋሉ፡፡ አሁን ለእኛ ብሄራዊ ቡድን ከየት ነው የማሳድገው፡፡ እቅዴ ከቻን በኋላ በመላው የኢትዮጵያ ምድር መዞር ነው፡፡ እግር ኳስ በሚዘወትርባቸው፤ በውድድሮች ላይ ወጣቶችን ማፈላለግ ቀጣይ ትኩረቴ ነው፡፡ ወጣት ተጨዋቾች በመላው አገሪቱ በብዛት ስለመኖራቸው ቶክ ጀምስ ምሳሌ ነው፡፡

በሁለት ዓመት ውስጥ ነው ለብሄራዊ ቡድን ደረጃ የበቃው፡፡ የቶክ ጀምስ አይነት በየጨዋታው ስፍራ አስር እና አስራ አምስት ታዳጊ ተጨዋች በየትም ቢገኝ ዞሬ ላመጣ እፈልጋለሁ፡፡ አሁን ያለው የተጨዋቾች ስብስብ በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት 50 በመቶው ላይኖር ይችላል፡፡ ክለቦች ይህን ስራ ቢሰሩ ነገሩ ይቃለል ነበር፡፡ እስከዛሬ ግን አልተሰራም፤ ወደፊትም የሚሰራበት አቅጣጫ አይመስልም፡፡ በርግጥ ተጨዋቾች የሚገኙት ከክለቦች ነው፡፡ ክለቦች በየቡድን መዋቅራቸው ወጣቶችን ማሳደግ ካልቻሉ፤ በተገቢው መንገድ ካልሰሩ የብሄራዊ ቡድኑ እጣ ፋንታ ምን ሊሆን ነው፡፡ ክለቦች ካልሰሩ ተብሎ ግን መቀመጥ አያስፈልግም፡፡ ስለዚህም እቅዴን ለብሄራዊ ፌደሬሽኑ በማቅረብ በዚህ የወጣቶች ምልመላ ስራ ዙርያ ለመስራት አስባለሁ” በማለትም ስለሁኔታው አስፈላጊነት አስረድተዋል፡፡ በየክለቡ ይካሄዳል የሚባለው ምልመላ በኢትዮጵያ ሁሉም ክልሎች ያሉ ታዳጊዎችን አፈላልጎ በማግኘት የሚሰራበት መሆኑ ያጠራጥረኛል የሚሉት ዋና አሰልጣኙ ችሎታ እያላቸው ክለብ ያጡ ወጣቶች መዓት መሆናቸውን ለወጣቶች እድል ለመስጠት ለብሄራዊ ቡድን ተስፋ የሚሆን ቡድን መፍጠር እንደሚቻል አስገንዝበው። “የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ተጨዋች ኢንዱራንስ 2200 ነው በዓለም አቀፍ ደረጃ ይሄው መለኪያ 3500 ደርሷል፡፡ የኛ ተጨዋቾች ያላቸው የጨዋታ ፅናት 40 ደቂቃ ተጫውቶ መቆም ነው፡፡

ይህን ማሳደግ ይጠበቅብናል፡፡ እግር ኳስ ትምህርት ነው፡፡ በሌላው ዓለም እግር ኳስን ልጆች ከስድስት እና ሰባት አመት ጀምሮ ነው የሚማሩት እና የሚሰለጥኑት፤ በእኛ አገር ይህ አይነቱ አሰራር መቼ ነው የሚፈጠረው ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል፡፡” ሲሉ ሃሳባቸውን አጠቃልለዋል፡፡ ይለቃሉ፤ ይቀጥላሉ አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው በብሄራዊ ቡድኑ ባላቸው ሃላፊነት ከፌደሬሽኑ ጋር የተፈራረሙት የኮንትራት ውል ካበቃ ወራት ተቆጥረዋል፡፡ የኮንትራት ውላቸው ስለመራዘሙ እና ስለመቋረጡ የማውቀው ነገር የለምም ብለዋል፡፡ በቅርቡ ከፌደሬሽኑ ጋር በመመካከር ኮንትራታቸውን በቀጣይ ለሁለት አመት የማራዘም ሁኔታ ሊፈጠር እንደሚቻልም ይገምታሉ። “ለአሰልጣኝነት ቅጥር የጠየቁኝ ብዙ ናቸው ምን መልስ አልሰጠሁም፡፡የውጭ አገር አሰልጣኝ ለመሆን በፍፁም ጥያቄ አላቀረብኩም፡፡ ከተጠየቅኩ ደግሞ እምቢም ሆነ እሽ ማለት የራሴው መብት ነው፡፡ ‹‹ብዙ አገራት እና ክለቦች ቡድኖቻቸውን እንዳሰለጥንላቸው በተደጋጋሚ ጠይቀውኛል፡፡ ቡድናችሁን ላሰልጥን ብዬ ለማንም አላመለከትኩም፡፡ ክለቦች ቢጠይቁኝ አገሮች ቢጠይቁኝ ምላሼ አገሬን ለቅቄ ልምንድነው የምሰደደው አልሄድም ነው፡፡ አገሬ ላይ መስራት እፈልጋለሁ፤ በአገሬ የምበላው አላጣው፤ የምኖርበት ቤት አለኝ፤ ብዙሺ ዶላር ሰጥተው የጠየቁኝ ቢኖሩም አልተቀበልኩም›› በማለት አሰልጣኝ ሰውነት ብሄራዊ ቡድኑን የመልቀቅ ምንም አይነት ፍላጎት እንደሌላቸው ሊያስረዱ ጥረት አድርገዋል፡፡ ማበረታቻ እና ስፖንሰርሺፕ ድጋፎች በቻን ውድድር ለምስታስመዘግቡት ውጤት ከፌዴሬሽኑ በኩል ቃል የተገባላችሁ ማበረታቻ አለወይ ተብለው የተጠየቁት አሰለጣኝ ሰውነት “ካሸነፍን ሽልማቱ ይመጣል፡፡ የእኛ መጦርያችን እሱ ነው፡፡ ጥቅማችን ተጫውተን ስናሸንፍ ሽልማታችን ነው፡፡

እግር ኳስ ፌደሬሽን ማበረታቻ ለመስጠት ሁሌም ቃል የገባል፡፡ እኛ ውጤት አስመዝግበን ሽልማቱን ለመውሰድ ተቸገርን እንጅ፡፡” ብለዋል፡፡ የሐረር ቢራ ፋብሪካን የገዛው ታዋቂው የአውሮፓ ቢራ ጠባቂ ኩባንያ ሄኒከን የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ እና ሌሎች ትልልቅ የስፖርት ውድድሮችን በስፖንሰርሺፕ በመደገፍ የሚታወቅ ሲሆን በበደሌ ስፔሻል ምርቱ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድንን አብይ ስፖንሰር ሆኖ ለሁለት ዓመታት 24 ሚሊዮን ብር ከፍሎ ነበር፡፡ የእግር ኳስ ፌደሬሽኑ የማርኬቲንግና ፕሮሞሽን ማናጀር አቶ ሳምሶን ጌታቸው እንደተናገሩት የበደሌ አብይ ስፖንሰርነት ከብሔራዊ ቡድኑ ጋር እንዳለ መሆኑን ጠቅሰው፤ የውል ስምምነቱ የሚያበቃበት ጊዜ እንዳልደረሰ እና ወደፊት ውሉን አድሶ በተሻለ የገንዘብ ድጋፍ ስፖንሰርሺፑን ለመቀጠል አቅሙ መኖሩን አስታውቀዋል፡፡

Read 2798 times