Saturday, 11 January 2014 11:35

ያልሰከነ ብዕር

Written by  ከሊቀ ኅሩያን ዘደብረ መዊእ
Rate this item
(3 votes)

“ቅኔን ሳያውቁ ቅኔን መፍታት ታላቅ ድፍረት”
በሚል ርእስ ለቀረበ ትችት የተሰጠ መልስ

 በሌላ የወረቀት ሥራ ብዙ ጊዜ ስለምጠመድ አልፎ አልፎ ካልሆነ በስተቀር ጋዜጣዎችን የማንበብ የዳበረ ልምድ የለኝም፡፡ ታኅሣሥ 19 ቀን 2006 ዓ. ም የወጣው አዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ ስምህ ተጠቅሷልና ተመልከተው ብሎ አንድ ወዳጄ በእጅ ስልኩ ሹክ አለኝና ተመለከትኩት፡፡ ትችቱ የቀረበው ገጣሚ ኤፍሬም ሥዩም “ተዋነይ ብሉይ የግዕዝ ቅኔያት ፍልስፍና ከቀደምት የኢትዮጵያ ነገሥታትና ሊቃውንት” በሚል ርእስ ባዘጋጀው መጽሐፍ ላይ ሲሆን፣ ትችት አቅራቢው ጽሑፉን ያቀረበው “ጵርስፎራ ዘዋሸራ” በሚል የብዕር ስም ነው፡፡ “ጵርስፎራ” የግዕዝ ቃል ነው፡፡ የቃሉ መሠረተ አመጣጥ (Etymology) “ፕርስፎራ” ከሚል የጽርዕ ቃል ሲሆን፣ መባአ ኅብስት፣ ሰንበቴ… ምእመናን የሚያቀርቡት ቁርባን (መክለፍት) ማለት ነው፡፡ ቀደም ባለው ጊዜ የብዕር ስም መጠቀም የተለመደ ቢሆንም በዘመናችን ግን ዘመን ያለፈበት ስልተ ሒስ እየሆነ የመጣ ይመስለኛል፡፡ የቀደሙት የሀገራችን ሐያስያን ለምን የብዕር ስም ተጠቀሙ? ብለን ጥያቄ ልናነሣ አንችልም፡፡ ምክንያቱም ያ ዘመን የራሱ የሆኑ ማኅበረሰባዊና ፖለቲካዊ መስፈርቶች ነበሩትና፡፡

ዛሬ ግን የሀገር መሪዎችንና የፖለቲካ ተሹዋሚዎችን ሳይቀር በቃልም ሆነ በጽሑፍ መተቸት እየተለማመድን ባለንበት ዘመን ግለሰቦችን (ያውም በሥነ ሒስ የሚያምኑ) በብዕር ስም ተደብቆ፣ በዋሸራ ስም አዲስ አበባ ሸምቆ ለመተቸት መሞከር ፍፁም ፈሪነት ወይም ዐቅመ-ቢስነት ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡ ጵርስፎራ ዘ…በግዕዝ ቅኔ እና ምናልባትም በሥነ ጽሑፍ ወይም ሥነ ልሳን ዕውቀት ያለው ሰው መሆኑን አልተጠራጠርኩም፡፡ የግዕዝ ቅኔ ያሰባሰቡ ባለሙያዎችና ተቋማትን በዝርዝር በማቅረቡም ጥሩ ነገር አድርጓል ብዬ አስባለሁ፡፡ ይህ ጸሐፊ ከዘመናዊው የሥነ ሒስ ጥበብ ጋር ግን ብዙም የተዋወቀ አይመስለኝም፡፡ ትችቱ ሚዛናዊ ካለ መሆኑም ባሻገር ኢ-ሥነ ምግባራዊ የሆኑ አገላለጾችን እየተጠቀመ ሥራቸውን ሳይሆን ባብዛኛው ግለሰቦችን ነው ለመተቸት የሞከረው፡፡ እንዲህ ዓይነቱ የትችት አቀራረብ ደግሞ ሚዛናዊና አስተማሪ የሆነ መልስ ሊሰጥበት ግድ ስለሚል የሚከተሉት መልሶች ተሰጥተውበታል፡፡ “በኢትዮጵያ እንደ አበባ ከፈኩት ጥበባት ውስጥ አንዱና በሌላው ዓለም የሌለው የግዕዝ ቅኔ መሆኑ ግልጽ ነው” ይላል ጽሑፉ፡፡ ግዕዝ እንደ አፍ መፍቻ ቋንቋ ይነገር የነበረ በኢትዮጵያ፤ አሁንም የቅኔ ድርሰት የሚደረስበትና የጽሑፍ ቋንቋ ሆኖ የሚያገለግል በኢትዮጵያ እንጂ የግዕዝ ቅኔ በሌላው ዓለም ሊኖር ይችላል ተብሎ ስለማይታሰብ የጵርስፎራ ብዥታ ገና በመጀመሪያው አንቀጽ ላይ ይጀምራል፡፡ “ስለ ተዋነይ ታሪክና ሥራ በጥቂቱም ቢሆን አለማተቱ ነው፡፡” የሚለው አስተያየት ተቀባይነት ያለው ነው፡፡ የተዋነይ ታሪክ በጥቂቱም ቢሆን መዳሰስ ነበረበት፡፡ “… አንባቢው ለዚህ መጽሐፍ 100 ብር የሚከፍለው ለባዶ ወረቀት ጭምር ነው” ብሎ ጽፏል፡፡ አንዳንድ የቃላት አጠቃቀሙን በማየት ይህ ሰው የሥነ ጽሑፍ ተማሪ ሳይሆን አይቀርም የሚል ግምት ነበረኝ፡፡ ነገር ግን የሥነ ግጥም መጻሕፍትን የአጻጻፍ ስልት አለመገንዘቡ ደግሞ እንድጠራጠረው አደረገኝ፡፡ የኤፍሬም አጻጻፍ ባዶ ወረቀት ለመሸጥ ታስቦ ሳይሆን የሥነ ግጥም አጻጻፍ ስልት/ስታይል ስለ ሆነ ነው፡፡ ጥቂት ምሳሌዎችን ላሳይ፡፡ 

ሰሎሞን ደሬሳ፤ (1991፡23)፤ ዘበት እልፊቱ ወለሎታት፡፡ ንዳል (ባለ ሁለት ስንኝ ወይም መንቶ ቤት)

አያልነህ ሙላቱ፤ (1985፡117)፤ ጥገት ላም። የበለዘ ጥፍር (ባለ ሁለት ስንኝ)

አበባው መላኩ፤ (1999፡38)፤ ከራድዮን፡፡ አንቺን ነበረ (ባለ ስድስት ስንኝ)፡፡

እንዳለጌታ ከበደ፤ (2001፡01)፤ ልብ ሲበርደው፡፡ መጅና ጥሬ (ባለ አራት ስንኝ)፡፡

ሜሮን ጌትነት፤ (1991፡9)፤ ዙረት፡፡ ያልገባው (ባለ ሁለት ስንኝ)፡፡

እነዚህ ሁሉ ግጥሞች ባንድ ዐምድ ላይ ነው የተከተቡ፡፡ ወዳጄ ጵርስፎራ እነዚህንና ሌሎችንም የግጥም መድበሎች ቢያያቸው ኖሮ ባዶ ወረቀት” የሚለውን ቃል ባልተጠቀመውም ነበር፡፡ “ኤፍሬም አንዷን ባለ ሁለት ቤት ጉባኤ ቃና ዘተዋነይ ከተዋነይ መንፈስና ዕሳቤ ውጪ በ3 ገጽ ግጥም ጽፎባታል” ብሎ አያ ጵርስፎራ ይተቻል፡፡ ይህ ኤፍሬምን የሚያስደንቀው እንጂ የሚያስተቸው አይመስለኝም፡፡ ባንድ ድንቅ ቅኔ መጽሐፍም ሊጻፍበት ይችላል፡፡ “ከተዋነይ ዕሳቤ ውጪ” የሚለው ደግሞ ልክ አይደለም፡፡ “በካፋ ኢትርሳዕ ዘተዋነይነ ክልኤነ” በካፋ ሁለታችን የተነጋገርነውን ምስጢር አትርሳ፡፡ ይህ ቀጥተኛ ትርጉም ነው፡፡ የቅኔው ምስጢር ያለ በሁለተኛው ስንኝ ነው፡፡ “እንዘ አበ አብርሃም አንተ” አንተ የአብርሃም አባት ሳለህ፤ እንዘስ፤ የአብርሃም አባት ታራ፤ አንተ+ስ+ታራ=ሀ “ወብእሲተ አብርሃም አነ” እኔ የአብርሃም ሚስት ሳለሁ፤ የአብርሃም ሚስት ሣራ፡፡ እኔ+ሣራ=ለ፡፡ በዚህም ተባለ በዚያ የተዋነይ ዕሳቤ ሁለቱም የቅኔ ተማሪዎች ሆነው የተነጋገሩትን ምስጢር ማስታወስ ነው፡፡ ይህን ደግሞ ኤፍሬም በውብ ቅኔያዊ ቃላት ገልጾታል-አይነኬውን (ጸያፍ) ቃል ላለመንካት ተጠንቅቆ፡፡ “ቅኔ በስማ በለው አይታወቅም፡፡ ይህ ቢሆን ኖሮ በቤተ ልሔም አካባቢ የሚንገላወደው ሰሞነኛና አማርኛ ግጥም መግጠምና ቃላት መደርደር፣ መደረት የቻለው ሁሉ ባለ ቅኔ ይሆን ነበር፡፡” አያ ጵርስፎራ (አያ የምል የቅኔ ቤቱን ዘየ ተጠቅሜ ነው፡፡) እዚህ ላይ በጣም ተሳሳተ፡፡ ብዙ ነገር ነው የተበላሸበት፡፡ “ቅኔ በስማ በለው አይታወቅም።

ለሚለው አዎ! ሁሉም ሙያ በቦታውና በዐውዱ ተገኝቶ ሲያጠኑት የልብ ይደርሳል፡፡ ነገር ግን ተሰጥዎውና ትጋቱ ካለ የማይቻል ነገር የለም፡፡ ቀደም ባለው ጊዜ በቤተ ክርስቲያን ዐውደ ምሕረት ለማስተማር ዕድሉ የሚሰጣቸው “አንድም” ብለው የትርጓሜ መጻሕፍት የተማሩ ሊቃውንት ብቻ ነበሩ። ዛሬ በዘመናችን እዚሁ አዲስ አበባ ተወልደው፤ በሰንበት ትምህርት ቤት ተምረው አድገው “ዲያቆን እገሌ፣ ቀሲስ እገሌ፣ መምህር እገሌ… ዛሬ በዚህ ቤተ ክርስቲያን ያስተምራል” ሲባል የቤተ ክርስቲያኑ ዐውደ ምሕረት ጠቦ የመንገድ ትልልፉ እስኪጉላላ ድረስ በሕዝብ የሚጨናነቅ በተሰጥዎና በትጋት በተገኘ ዕውቀት ነው እንጂ ከመጻሕፍት ትርጓሜ ቤት ሂደው ተምረው አይደለም፡፡ ከውጪ ሰዎች ብንጠቅስ ጀርመናዊው ኦገስት ዲልማን፤ በግዕዝ ቋንቋ ላይ ያን ሁሉ ጠቃሚ ሥራ ሲሠራ፤ ለአለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌና ለመምህር ክፍለ ጊዮርጊስ መዝገበ ቃላት መሠረት እንደ ሆነ የሚታመነውንና Lexicon Linguae Aethiopicae የተሰኘውን መዝገበ ቃላት ሲያዘጋጅ ወደ ኢትዮጵያ አልመጣም፤ ማንም መረጃ አቀባይ አልነበረውም። ወይም ኦገስት ዲልማን ዋሸራ፣ ወልፍ ሌስላው ጎንጅና ዋድላ ቅኔ ቤት ገብተው አልተማሩም፡፡ ሥራውን ግን ሠርተውታልና እናደንቃቸዋለን፡፡ “በቤተ ልሔም አካባቢ የሚንገላወደው ሰሞነኛ…” ሰሞነኛ የሳምንት ተረኛ ማለት ነው፡፡ “ጠባ ለኪዳን፣ መሸ ለቁርባን” ብሎ ቤተ ክርስቲያን የሚያገለግል ካህን፣ ቄስ ወይም ዲያቆን፡፡ እና ቤተ ልሔም ሥጋ ወደሙ የሚዘጋጅበት የተቀደሰ ሥፍራ ሲሆን፣ ዲያቆኑ ሥጋ ወደሙን ያዘጋጃል፤ ካህኑ ይቀድሳል ያቆርባል፡፡ በተቀደሰው ሥፍራና በባለ ሙያዎቹ መሳለቅ ከስህተትነት አልፎ ድፍረት ነው። “የጥበቡ አባ አጋር” ብሎ መጨረሻ ላይ ያቀረበልን ጉራማይሌ መወድስ ቅኔም ይህንኑ ስህተትና ድፍረት ነው ያሳየን፡፡ “አማርኛ ግጥም መግጠምና ቃላት መደርደር፣ መደረት የቻለው ሁሉ ባለ ቅኔ ይሆን ነበር፡፡”የወዳጄ ጵርስፎራ ስህተት ጎልቶ የወጣ ደግሞ እዚህ ላይ ነው፡፡ “የቅኔ ምስጢሩ እንጂ መንፈሱ አይወረስም” የሚለውን አገላለጹን በጣም ወድጀለት ነበር፡፡ ለካ እርሱ የሚያወራ ስለ ግዕዝ ቅኔ ብቻ ነው፡፡

ምስጢሩ የሚወረስ የአማርኛ ቅኔ መኖሩን አያውቅም። ከቀደምት ባለ ቅኔዎቻችን የጸጋዬ ገ/መድኅን፣ የመንግሥቱ ለማ፣ የዮሐንስ አድማሱ፣ የደበበ ሰይፉ፣ የገብረ ክርስቶስ ደስታ ወዘተ. ሥራዎችን፤ ከዘመናችን ገጣምያን የጌትነት እንየው፣ የበዕውቀቱ ሥዩም፣ የአበባው መላኩ፣ የኤፍሬም ሥዩም፣ የሜሮን ጌትነት፣ የፀሐይ መላኩ ወዘተ ሥራዎችን አላየም፤ አላነበበም ማለት ነው፡፡ ሳያነቡ መጻፍ ያሳዝናል!! ወዳጄ ጵርስፎራ እኔን ስትተች “ቀድሞ ነገር ራሱ ወደ ቅኔ ቤት ሄዶ ቅኔውን ቢያለዝብና ቢቀጥል ይሻላል፡፡… ወደ ዋሸራ ከመጣም እንቀበለዋለን” ብለሃል፡፡ አያ ጵርስፎራ! “ትንሽ አሻሮ ይዘህ ቆሎ ወዳለው ተጠጋ” የሚለውን የአማርኛ ብሂል መቸም ሳትሰማው አትቀርም፡፡ እና ወዴት ነው ጠጋ ጠጋው? ታሪካዊቷ ዋሸራ ማርያም ገዳም በዘመናችን ከምንጊዜውም በላይ ታሪኳ እየናኘ፤ በሀገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን በዓለም-አቀፍ ደረጃም በስሟ ብዙ ድርጅት፣ ብዙ ተቋም እየተከፈተ ስለ ሆነ ምናልባት አንተም ወጉ አይቅረኝ ብለህ “ዋሸራ” የሚል ሱቅ ከፍተህ ከሆነ ንገረን እንጂ አንተ ዋሸራ እንዳልሆንክ፣ ከዋሸራ ሊቃውንት ተራ እንደማትገባም እኛ ብቻ ሳንሆን አንተ ራስህ ታውቀዋለህ፡፡ ዋሸራን ዋሸራ ካሰኙዋት ቀደምት ሊቃውንት እነ መምህር ቀስሙ፣ መምህር ገብረ ማርያም፣ አለቃ ተክሌ፣ መምህር ወልደ ሚካኤል፣ መሪጌታ ፈንቴ (ማዕበል)፣ መሪጌታ ደለለ እና መሪጌታ ገድሉን በታሪካቸው፤ በዘመናችን ያሉትን ደግሞ በአካልም በስምም መሪጌታ ጥዑም፣ መሪጌታ ናሁ ሠናይ ዘዋሸራ፣ መሪጌታ መንክር (ተረክበ) ዘውኢፋት ብለን እናውቃቸዋለን፡፡ ወዳጄ ጵርስፎራ! አልዋሽህም፡፡

የግዕዝ ቅኔ ዕውቀት ያለህ ሰው መሆንህን ተረድቻለሁ፡፡ ግን ብዙ ይቀርሃል፡፡ ዋሸራዎች እኮ ግዕዝን ሲማሩትም ሆነ ሲያስተምሩት ፊደላቱን ጥንቅቅ አድርገው ነው። ለስሕተትህ ጥቂት ምሳሌዎችን ላሳይህ፡፡ “እመ ትሬዒ ደመና” [እመ ትሬኢ ደመና]። “ሲመተ ርእስ” [ሢመተ ርእስ፡፡ “ሊቀ ህሩያን [ሊቀ ኅሩያን] “ዕደ ማርያም” [እደ ማርያም]፡፡ “ግስ የገሠሡ” [ግስ የገሰሱ]፡፡ እና በነዚህ ምሳሌዎች በትንሹ እንዳሳየሁት አያ ጵርስፎራ “ንጉሡ ሠ” እና “እሳቱ ሰ”ን ሳትለይ እንዴት ነው ከዋሸሮች ተራ የምትሰለፍ? እንዲያውም ኤፍሬም ሥዩም “እሳቱ ሰ” በሚል ርእስ፣ ይኼው በጉብዝናም በፈቃድ ስተት ትርጓሜው አይለይም አንድ ነው በማለት እጽፋለሁ ጽፈት፣ እስታለሁ ስተት እሳት ስባል ንጉሥ፣ ንጉሥ ስባል እሳት፡፡ (ሶልያና ግጥም በሲዲ) ብሎ የጻፈውን ቅኔያዊ ግጥም ከመጀመሪያውም አድንቄዋለሁ፤ ዛሬ ደግሞ ለጵርስፎራ የተነገረ ትንቢት መስሎ ተሰምቶኛል፡፡ “በመጽሐፉ ውስጥ የምናገኘው ባለ ቅኔ ንጉሥ እስክንድር ብቻ ነው፡፡ ይኸውም ያው የተለመደው ከተዋነይ ጋር ገጥሞ የዘረፈው ሥላሴ ቅኔ ነው” ብለኸናል ጵርስፎራ፡፡ ይህ አባባልህ በጣም የሚያሳፍር ነው፡፡ ተዋነይ ዘጎንጅ መቼና የት እንደ ነበረ ሳይረዱ የተዋነይ ተቆርቋሪ መስሎ መቅረብ ትልቅ ጉድለት ነው፡፡ ዋሸራዎች ግን ተዋነይ የትና መቼ እንደ ነበረ ጠንቅቀው ያውቁታል፡፡ አያ ጵርስፎራ! ጎበዝ ተማሪ አንዳንዴ “መምህሩን” ይደጉማልና ስለ ተዋነይ ትንሽ ልደጉምህ፡፡ በ15ኛው ምእት ዓመት 2ኛ አጋማሽ፣ በሽዋ ሥርወ መንግሥት፣ ከዐፄ እስክንድር (1470-1486) ጋር ቅኔ የዘረፈ ደቀ እስጢፋ እንጂ ተዋነይ አይደለም፡፡

ቦታውም ሰሜን ሽዋ ነው፡፡ እርግጥ አልፈርድብህም፡፡ ይህን የተሳሳተ ታሪክ ሊቀ ሥልጣናት ሀብተ ማርያም ወርቅነህም መጽሐፍ ላይ አስፍረውታልና፡፡ የቅኔው ፈላስፋ ተዋነይ በዐፄ እስክንድር ዘመን አልነበረም። በግራኝ አሕመድ ወረራ ጊዜም የለም፡፡ ተዋነይ የነበረ በጎንደር ሥርወ መንግሥት በ18ኛው ምእት ዓመት መጀመሪያ ሲሆን፣ ቦታው ደብረ ጥበብ ጎንጅ ቴዎድሮስ ነው፡፡ ከዐፄ በካፋ (1713-1722) ጋር በፂማ አቡነ ዘርዐ ቡሩክ ገዳም (አዴት) ቅኔ አብረው ተምረዋል፡፡ ለነቀፋ ስትንደረደር አላስተዋልከውም እንጂ “ከተዋነይ ዕሳቤ ውጪ” 3 ገጽ ትርጉም ተሰጠው ብለህ የተቸኸውን ቅኔ፤ ብትመረምረው ኖሮ ያለብህ የታሪክ ዕውቀት እጥረት ይህን ያህል ጎልቶ አይወጣም ነበር፡፡ የወዳጄ ጵርስፎራ ትችት በጥናት ላይ ተመርኩዞ ሳይሆን በነሲብ የቀረበ መሆኑን ለማጠየቅ ከጽሑፉ አንድ ምሳሌ እንውሰድ፡፡ “ከጥንት ዘመን ጀምሮ ቅኔያት… ከትውልድ ወደ ትውልድ በቃል ሲተላለፉ ኖረዋል፡፡ የተወሰኑትም እየተንጠባጠቡና እየነጠቡ ጠፍተዋል” ይላል። ጵርስፎራ እያለን ያለው የተወሰኑት እየነጠቡ ሲጠፉ የግዕዝ ቅኔያት በቃል እየተላለፉ ለትውልዱ ደርሰዋል ለማለት የፈለገ ይመስላል፡፡ የኔና የኤፍሬም ሥዩም፤ የሌሎችም አስተሳሰብ ደግሞ ከዚህ የተለየ ነው፡፡

“የቅኔ ቋንጣ የለውም” በሚል አጉል ፈሊጥ ቅኔያቱ ብራና ላይ ሳይሰፍሩ አይደለም በሚሊዮን በትሪሊዮን የሚቈጠሩ የግዕዝ ቅኔያት ተረስተው ቀርተዋል፤ ለትውልዳችን አልደረሱም የሚል ነው፡፡ ለዚህም አንድ አስረጅ ማቅረብ ይቻላል፡፡ ሊቅተ ሊቃውንት እሜቴ ገላነሽ ሐዲስ፤ ለ50 ዓመታት የግዕዝ ቅኔን አስተምረዋል፡፡ በቅኔ ቤት ሥርዓት ከሰኞ እስከ ዓርብ ባሉት 5 ቀናት ቢያንስ በየቀኑ 7 ቅኔያት ይዘረፋሉ፡፡ የበዓላት ቀናትንና ዘራፊዎቻቸው የሚዘርፉበትን ቀን ሳይጨምር እሜቴ ገላነሽ በሳምንት በአማካይ 3 ቀን ቅኔ ይዘርፋሉ ብለን ብናስብ 52 ሳምንት× 3 =156 ቀናት። 156×7=1155 ቅኔያት በዓመት ዘርፈዋል ማለት ነው፡፡ የ50ውን ዓመት ብናስበው 1156×50=57800 ቅኔያት፡፡ እንግዲህ እሜቴ ለ50 ዓመታት ሲያስተምሩ በትንሹ 57800 ቅኔያትን ዘርፈው ነበር ማለት ነው፡፡ በኔ ጥናት እስካሁን በቃልም በጽሑፍም ሰፍረው ያገኘኋቸው የእሜቴ ቅኔያት ከ50 አይበልጡም፡፡ ይህን በመቶኛ ብናስቀምጠው 50×100÷57800=0.09% መሆኑ ነው፡፡ በዚህ ስሌት መሠረት ከዘጠና ዘጠኝ በመቶ በላይ የሚሆነው ቅኔያቸው ባየር ላይ ቀርቷል ማለት ነው። እና እውነታው የሚያሳየን ይህን ነው፡፡ ጵርስፎራ ዘ… ሚዛኑን በሳተና በተንሻፈፈ ትችት ስለ በላይ የጻፈው ተራ ጽርፈት በዓይነ ሕሊና ሳይሆን “በዓይነ ገመድ” የተለካ ይመስላል፡፡ በመሆኑም በዚህ ዐምድ ላይ ስለ ግለሰባዊ ሕይወት ማውራት ተገቢነት ባይኖረውም በተነሡት ነጥቦች ላይ አንድ ሁለት ብሎ መልስ መስጠት የግድ ስለሚል በ3ኛ መደብ የአጸጻፍ ስልት እንዲህ ቀረበ፡፡ 1.”ከመጠምጠም መማር ይቅደም” ጵርስፎራ ዘ… እንደ ተጠቀመበት ይህ ጥቅስ ለበላይ ይስማማው ይሆን? እስቲ የትምህርት ቤት ሕይወቱን እንቃኘው፡፡

በላይ በተወለደ በ4 ዓመት ከ4 ቀኑ በደብረ መዊእ ማርያም ገዳም ከነበሩት ታዋቂ የድጓ መምህር ጉባኤ ቤት ገብቶ ሀ ለ ሐ መ… ብሎ ፊደል rጠረ፡፡ የንባብ ትምህርቱን አጠናቆ ዳዊት ከደገመ በኋላ፣ ጾመ ድጓ ሦስት ጊዜ፣ የዘወትር ምዕራፍ ሁለት ጊዜ፣ የጾም ምዕራፍ እና ድጓውን አንድ አንድ ጊዜ ዘልቆ በተወለደ 13 ዓመቱ የዜማ ትምህርቱን አጠናቀቀ፡፡ በላይ የግዕዝ ቅኔን ለመማር ጊዜ አልወሰደበትም። በታኅሣሥ ወር ቅኔ ቤት ገብቶ በሐምሌ ወር (በስድስት ወሩ) ግዕዝና ዕዝል ዕጣነ ሞገር በደብረ መዊእ ተቀኝቷል፡፡ በዐሥር ወሩ የደብረ መዊእ ማርያም ገዳም ዓመታዊ በዓል በሚከበርበትና ብዙ ሊቃውንት በተገኙበት የበዓሉን ዕጣነ ሞገር ተቀኝቶ የቅኔ ተሰጥዎውንና ብቃቱን አስመስክሯል። በአጠቃላይ በሁለት ዓመታት ቆይታው ከሁለት የቅኔ መምህራን ማለትም መሪጌታ ግሩም ብንያም የጎማ ገብርኤል እና ከታዋቂው ሊቅ መሪጌታ ጥበቡ ደስታ ታች ጋፊት ገብርኤል የግዕዝ ቅኔ ዕውቀቱን አሸራሽቶ ወደ ዜማ ትምህርቱ ተመለሰ፡፡ ወደ ጎንደር ተሻግሮም በመካነ ሰማዕት ገላውዴዎስ ከታወቁት ሊቅ መልአከ ሕይወት አስናቀ ጸጋው ጉባኤ ቤት በነበረው ከአራት ዓመታት በላይ ቆይታ ዜማውን እየከለሰ፤ የራሱንና መምህሩ በማይኖሩበት ሰዓት የመምህሩን ደቀ መዛሙርት እያስተማረ ጭምር ብራና አውጥቶ፤ ቀለም በጥብጦና ብዕር ቀርጦ ምዕራፍ፣ ጾመ ድጓ እና ድጓ የተባሉትን የዜማ መጻሕፍት ጽፎ አጠናቋል፡፡

በጉራምባ ኪዳነ ምሕረት ደብር ከመሪጌታ ይትባረክ የጎንደርን አቋቋም ተምሯል፡፡ ወደ ቅድስት ቤተ ልሔም የዜማ ምስክር ቤት ገብቶም የቅዱስ ያሬድን ዜማ አመሉን፣ ሥርዓቱንና ባህሉን በሁለት ዓመታት ውስጥ አጠናቆ ዐውቆ በድጓ መምህርነት ተመርቋል፡፡ እንደ ገናም ወደ ጽርሐ አርያም ዙር አባ አረጋዊ የዝማሬና መዋስእት ምስክር ቤት ገብቶ ዝማሬና መዋስእት ተምሯል፡፡ እንግዲህ እነዚህን ነባርና ሀገር-በቀል ዕውቀቶች በተወለደ 23 ዓመቱ አጠናቆና የመምህሩን የመሪጌታ ዓለሙ ጎሹን ጉባኤ ቤት በቡራኬ ተረክቦ ማስተማር ሲጀምር እንደ ድንቅ ነገር ተቆጥሮ ነበርና .”ከመጠምጠም መማር ይቅደም” የሚለው ብሂል ለበላይ ሊጠቀስ የሚገባው አይደለም፡፡ 2. “ሲመተ ርእስ” [ሢመተ ርእስ] ለራስ የመዓርግ ስም መስጠት በላይ በድጓ መምህርነት ሲመረቅ “መሪጌታ” ተባለ፡፡ በ3ኛው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት “ርእሰ ደብር” ተሰኘ፡፡ እንዴትና በምን ምክንያት? በላይ ከግንቦት ወር 1971 እስከ ጥር 1974 ዓ.ም ድረስ የባሕር ዳር ወረዳ ቤተ ክህነት ኃላፊ ሆኖ ሠርቷል፡፡ በዚህ ወቅት በታኅሣሥ 1974 ዓ.ም 3ኛው ፓትርያርክ የባሕር ዳርን አውራጃ በይፋ ጎብኝተው ነበር፡፡ በጣና ደሴት የሚገኙት አራቱ ታሪካውያን ገዳማት ተጎብኝተው ለቅ/ፓትርያርኩ ባሕር ዳር ከተደረገው የእራት ግብዣ በኋላ፣ በላይ ከቅዱስ ያሬድ ዜማ “ውእቱ እግዚኣ ለቤተ ክርስቲያን አቡነ ተክለ ሃይማኖት ገሠፃ ለባሕር ከመ ያርምም ማዕበላ…” የሚለውን መዝሙር አዜመ፡፡ ቅኔዎችንም አቀረበ፡፡ የታወቁት ሊቃውንት ብፁዕ አቡነ አብርሃም ካልእ፣ ሊቀ ጳጳስ ዘሐረር፣ ብፁዕ አቡነ መርቆሬዎስ ሊቀ ጳጳስ ዘጎንደር፣ ብፁዕ አቡነ መቃርዮስ ሊቀ ጳጳስ ዘጎጃም፣ መጋቤ ካህናት ብርሃኑ መኰንን (በኋላ ሊቄ) እና ሌሎቹም “ይበል” አሉ፡፡ “ለመሆኑ የበላይ ሥራው ምንድን ነው?” ሲሉ ቅዱስ ፓትርያርኩ ጥያቄ አቀረቡ፡፡ “የባሕር ዳር ወረዳ ቤተ ክህነት ኃላፊ” ተብሎ ሲነገራቸው አልተደሰቱም፡፡ ወዲያው የራሳቸውን ውሳኔ ሰጡ።

“ትምህርቱን ሲጨርስ ወደ ውጪ እንልከዋለን። እስከዚያ ድረስ ግን በላይ ቢሮ ሰራተኛ መሆን የለበትም፡፡ ይህንን ሙያውን ለሌሎች ማስተላለፍ አለበት።” ብለው በባሕር ዳር ፈለገ ገነት ቅዱስ ጊዮርጊስ ገዳም የድጓ መምህር ሆኖ፣ በሚከፈለው ብር 85.00 ላይ ብር 35.00 ተጨምሮ ብር 120.00 የወር ደመወዝ እየተከፈለው እንዲያስተምር ወሰኑ። በዚህ አጋጣሚ ሊቄ ብርሃኑ “በላይ የመዓርግ ስም ይገባዋል” የሚል ሀሳብ አቀረቡ፡፡ “ማን እንበለው?” ብለው ቅ/ፓትርያርኩ መልሰው ሲጠይቋቸው “የታላቁ ሊቅ የሊቀ ኅሩያን ዘገየ የልጅ ልጅ ስለ ሆነ ሊቀ ኅሩያን ቢባል?” ብለው ሳይጨርሱ ሊቀ ጳጳሱ ከወንበራቸው ብድግ አሉና “ርእሰ ደብር ቢባል መልካም ነው” የሚል አማራጭ አቀረቡ፡፡ ቅ/ፓትርያርኩም ይህንኑ ተቀብለው “ርእሰ ደብር በላይ ብለንሃል” ሲሉ ተጨበጨበ፡፡ በላይም እጅ ነስቶ መስቀል ተሳለመ፡፡ ይሁን እንጂ የመዓርግ ስሙ ሳይሆን የሊቀ ጳጳሱ ሁኔታ ስላልተመቸው በላይ በዚህ ስም ብዙም አልተጠራበትም፡፡ ከየካቲት ወር 1974 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ታኅሣሥ ወር 1979 ዓ.ም ድረስ ግን በድጓ መምህርነት አገለገለ፡፡ “ሊቀ ኅሩያን” የሚል የመዓርግ ስም የተሰጠው በብፁዕ አቡነ በርናባስ ካልእ የምዕራብ ጎጃም ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ነው፡፡ ምክንያቱ እንዲህ ነው። በላይ “ለጸሎት ተነሡ” የተሰኘችውን የጸሎት መጽሐፍ አዘጋጅቶ በ1989 ዓ.ም ለማሳተም ሲንቀሳቀስ፣ ከቤተ ክህነት ፈቃድ ማምጣት እንዳለበት ከማተሚያ ቤቶች ተነገረውና፣ ይህን ፈቃድ ለማግኘት ለምዕራብ ጎጃም ሀገረ ስብከት መንበረ ጵጵስና አመለከተ፡፡

የመጽሐፍዋ ረቂቅ በሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ሰብሳቢነት በሊቃውንቱ ለሁለት ቀናት ከሰዓት በኋላ ምርመራ ከተደረገባት በኋላ የማሳተሚያ ፈቃዱ ተሰጥቶት መጽሐፍዋ ታተመች፡፡ በላይ በ1998 ዓ.ም “ሕያው ልሳን ግዕዝ-አማርኛ መዝገበ ቃላት” የተሰኘውን መጽሐፍ ለኅትመት ካዘጋጀ በኋላ ባጋጣሚ ወደ ባሕር ዳር ሄዶ ነበር። ብፁዕ አቡነ በርናባስን ለመገናኘት በማረፊያ ቤታቸው ተገኝቶ ሲነጋገሩ፣ ለኅትመት የተዘጋጀውን መጽሐፍ አሳያቸው፡፡ በዚህ ጊዜም፣ “እንደዚህ ዓይነት ጠቃሚ መጻሕፍትን ታዘጋጃለህ፤ ካህናትንና ምእመናንን እያስተባበርኽ ቤተ ክርስትያን ታሠራለህ (መካነ ሰላም በአታ፣ ፓዊ-መንደር 7)፤ ደብረ መዊእ ማርያምን ለማሳደስ ጥረት ታደርጋለህ፡፡ እና የመዓርግ ስም አያስፈልግህም?” “የብፁዕነትዎ ፈቃድ ከሆነ ደስ ይለኛል፡፡” ጥቂት አሰቡና “በአያትህ ስም ለምን ሊቀ ኅሩያን አትባልም?” “ብፁዕ አባታችን ይህን የመዓርግ ስም እኔ አልመጥነውም”ኮ” አለ በትሕትና፡፡ “እ… አዎ እንደ ድሮው ቢሆን ትክክል ነህ። ዛሬ ግን አፋሹ አጎንባሹ እየተጠራበት ስለሆነ አይበዛብህም።” ብለው የፕሮቶኮል ቁጥር ይዞ የተጻፈው ደብዳቤ፣ በብፁዕ አቡነ በርናባስ እና በሀገረ ስብከቱ ማኅተም ተረጋግጦ ለበላይ ተሰጥቶታል፡፡ በታላቁ የደብረ መዊእ ማርያም ዓመታዊ በዓል ላይም ብፁዕነታቸው ባሉበት ተነቦ፣ የበዓሉ ታዳሚ “ይደልዎ” ይገባዋል በሚል ስሜት ደስታውን በጭብጨባ ገልጾለታል፡፡

                                           ***

“ቅኔ በወረቀት ላይ እንደ ግጥም እየጻፈ..” ለሚለው፣ ቅኔያቱን በተዛማጅ ትርጉምና በግጥም ለታዳሚ ለማቅረብ ወይም አስተያየቶችን ለመስጠት ማስታወሻ መያዝ ካልሆነ በስተቀር በላይ የግዕዝ ቅኔያትን በወረቀት ጽፎ ያነባል የተባለው ፍጹም ስሕተት ነው፡፡ “ብሉይ የግዕዝ ቅኔያት ፍልስፍና…” በሚለው ሐረግ “ብሉይ” የሚለው ሥረይ ቃል ክላሲክ ወይም ዓይነተኛ የሚባለውን ተክቶ ፍልስፍናውን እንዲገልጽ እንጂ እነ ዮፍታሔ እነ መልአከ ብርሃን አድማሱ …የብሉይ ዘመን ሰዎች ናቸው ለማለት አለመሆኑን ጵርስፎራ ልትገነዘብ ይገባል፡፡ ኤፍሬም በሥራው ቀድሞናል፡፡ እኔም የቀደምቶቻችን ፍልስፍናና አስተሳሰብ የሚታይባቸውን ቅኔያት መሰብሰብ ከጀመርኩ ቆይቻለሁ፡፡ የአርትዖት ሥራ ለመሥራት ረቂቅ ጽሑፉን እንዳየሁት ኤፍሬም ሥዩምን ያልኩት ነገር ቢኖር “ቀደምከን” የሚል ነበር፡፡ በውስጤ ግን አንዳችም ቅናት የሚሉት ነገር እንዳልነበረ እርግጠኛ ነኝ፡፡ ቅናት መጥፎ ባህል ነው፡፡ ባንድ ሞያ ውስጥ ያሉ ባለ ሙያዎች ደግሞ መደጋገፍ እንጂ መነቃቀፍ የለባቸውም፡፡ “ኀጺን ለኀጺን ይትባላሕ፡፡” ብረትና ብረት በመፋጨት ስለት ያወጣል ይላልና መጽሐፍ፤ ሚዛናዊ በሆነ ሒስ ግን መጠራረብ አለባቸው፤ ያለ መፈራራት ያለ ድብብቆሽ፡፡ ወዳጄ ጵርስፎራ! አንድ ነገር ልምከርህ፡፡ ለወደፊቱ ዲያቆን፣ ሰሞነኛ፣ የቤተ ልሔም እንትን ስትል ሰው እንዳይሰማህ፡፡ ይህ ዓይነት አስተሳሰብ የነበራቸው፣ “ተምረው ያልተማሩ” አንዳንድ የአብነት መምህራን እንደ ነበሩ ዐውቃለሁ፡፡ በምሥራቅ አፍሪካ የሥልጣኔ ቀንድ የነበረችው ሀገራችን ኢትዮጵያ የዓለም ጭራ የሆነችው አንዱ የሌላውን ሙያ ሲያንቋሽሽ፤ አንዱ ሌላውን ሲንቅና ሲያንጓጥጥ ያሳለፈው የታሪካችን ዘመን ነው፡፡ እንደ ኤፍሬም ሥዩም፣ ያልተሄደባቸውን የጥበብ ሥራዎች ጥበባዊ በሆነ አተያይ ሠርቶ የሚያቀርብ ወጣት፤ አይዞህ በርታ ነው የሚባል፡፡ አብነት ትምህርት ቤት ገብተህ ግዕዝ አልተማርክም ተብሎ ሊወረፍ አይገባም፡፡ ሌላው ወጣት እንዳይከተል “ገበሬ አስደንግጥ” መሆን ነውና፡፡ ኤፍሬም ለዘመኑ ትውልድ በሚመቸው መልኩ ቅኔያቱን መተርጐሙ አርአያነት ይኖረዋል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ “ይታደሉታል እንጂ አይታገሉትም” እንደሚባለው ተሰጥዎና ትጋት ካለ ደግሞ ብዙ መሥራት ይቻላል፡፡ መተቸትህ ክፉ አይደለም። አፍሬምን ለመተቸት ምን ምን ሠርቷል? ምን ጠንካራ ጎን አለው? ድክመቱስ? በላይንም እንዲሁ ብትተች ጥሩ ነበር፡፡ በሥራው ላይ እንጂ በግለሰብ ላይ ማነጣጠር ደግሞ ግላዊ ጥላቻ ይመስላልና፣ ከሥነ ሒስ ሙያ አንጻርም ስለማይደገፍ ብዕርህ ቢሰክን መልካም ነው። እናም ወዳጄ ጵርስፎራ! ከግል ሥራዬ ብታናጥበኝም ይህም በራሱ ጥናት ስለሆነ ብዙ አልተከፋሁብህም። ለወደፊቱ በተሻለ የሒስ ሥራ እንገናኝ፡፡ በተለይ ደግሞ ዋሸራዎችን እንዳስታውሳቸው ስለ አደረግከኝ አመሰግንሃለሁ፡፡

Read 4217 times