Sunday, 05 January 2014 00:00

አፍሪካ በ20ኛው የዓለም ዋንጫ

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(2 votes)

        ብራዚል በምታስተናግደው 20ኛው የዓለም ዋንጫ ላይ አፍሪካን የሚወክሉት 5 ብሄራዊ ቡድኖች ምን ውጤት እንደሚኖራቸው በርካታ ዘገባዎችና ትንተናዎች  እየተሰሩ ናቸው፡፡  በዓለም ዋንጫው የአፍሪካ ቡድኖች እንደልማዳቸው በተሳትፎ ብቻ ተወስነው እንደሚቀሩ ብዙዎች ቢገልፁም፤ አዲስ የውጤት ክብረወሰን ሊመዘገብ እንደሚችል የገመቱም ይገኛሉ፡፡  የምድብ ፉክክሩን በማለፍ ወደ ጥሎ ማለፍ ምእራፍ ለመግባት እድል የሚኖራቸው የአፍሪካ ቡድኖች በታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ ከአንድ በላይ ሊሆን እንደሚችል ተተንብይዋል፡፡ በታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ ወደ ግማሽ ፍፃሜ የሚቀላቀል አፍሪካዊ ቡድንም ሊኖር እንደሚችልም ተገምቷል፡፡   
በዓለም ዋንጫ ታሪክ ለዋንጫ የተጫወቱ አገራት አውሮፓ እና ደቡብ አሜሪካን የወከሉ ብሄራዊ ቡድኖች ብቻ ናቸው፡፡ ለግማሽ ፍፃሜ በመድረስም አውሮፓ እና ደቡብ አሜሪካ ከሌሎቹ አህጉራት በከፍተኛ ሁኔታ ይበልጣሉ። ከሁለቱ አህጉራት ውጭ ለግማሽ ፍፃሜ መድረስ የቻሉት ሁለት ብሄራዊ ቡድኖች ብቻ ሲሆኑ ሰሜንና መካከለኛው አሜሪካን የወከለችው አሜሪካ እና ኤሽያን የወከለችው ደቡብ ኮርያ ነበሩ፡፡
በዓለም ዋንጫ  መድረክ አፍሪካዊ ቡድኖች አንዳንድ አስደናቂ ውጤቶች ከማስመዝገብ ባሻገር፤ በጎል ደስታ አገላለፅ መላው ዓለም ከማስደመም እና ትልልቅ ተጨዋቾች በሚያገኙት የሚዲያ ትኩረት ከማነጋገር በቀር የአውሮፓ እና የደቡብ አሜሪካ ቡድኖችን የመፎካከር አቅም ሳይኖራቸው ቆይተዋል፡፡ በዓለም ዋንጫ መድረክ አንድም አፍሪካዊ  ቡድን ግማሽ ፍፃሜ ደርሶ አያውቅም፡፡ የአህጉሪቱን ከፍተኛ የዓለም ዋንጫ ውጤት ለሩብ ፍፃሜ መድረስ ሲሆን ይህ  3 ብሄራዊ ቡድኖች አስመዝግበዋል፡፡  በ1990 እኤአ ላይ ጣሊያን ባስተናገደችው 14ኛው ዓለም ዋንጫ ካሜሮን፤ በ2002 እኤአ ላይ ደቡብ ኮርያ እና ጃፓን ባዘጋጁት 17ኛው ዓለም ዋንጫ ላይ ሴኔጋል እንዲሁም በ2010 እኤአ ላይ ደቡብ አፍሪካ ባስተናገደችው 19ኛው የዓለም ዋንጫ ላይ ጋና  እስከ ሩብ ፍፃሜ መጓዝ ችለዋል፡፡
የአምስቱ አፍሪካ ቡድኖች ታሪክ፤ ብቃትና ግምት
ባለፉት 19 ዓለም ዋንጫዎች በአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፈዴሬሽን አባል ከሆኑ 52 አገራት ለአንዴና ከዚያም በላይ 13 ብሄራዊ ቡድኖች ተሳትፎ አድርገዋል፡፡ ከሰሜን አፍሪካ 5፣  ከምዕራብ አፍሪካ 7 ፤ እንዲሁም ከደቡባዊ አፍሪካ አገራት ናቸው፡፡  በዓለም ዋንጫ  ብዙ ጊዜ በመሳተፍ አንደኛ ደረጃ የወሰደችው 7 ጊዜ የተሳተፈችው ካሜሮን ናት፡፡ ናይጄርያ ለ5 ጊዜያት በመሳተፍ ሁለተኛ ደረጃ ስትወስድ፤ የሰሜን አፍሪካዎቹ ሞሮኮ ፣ቱኒዚያ እና አልጄርያ እያንዳንዳቸው ለ4 ጊዜያት በመካፈል፤ አይቬሪኮስት፣ጋና እና ደቡብ አፍሪካ እያንዳንዳቸው ለ3 ጊዜያት፤ ግብፅ ለሁለት ጊዜያት እንዲሁም ዛየር፡ አንጎላ፣ ሴኔጋል እና ቶጎ እያንዳንዳቸው አንድ አንድ ጊዜ የዓለም ዋንጫ ተሳትፎ በማስመዝገብ በተከታታይ ደረጃ ይቀመጣሉ፡፡ የአፍሪካ ቡድኖች በ71 የዓለም ዋንጫ ጨዋታዎች ከአውሮፓ ቡድኖች ጋር ተገናኝተው 15 ጊዜ ድል፣ 20 ጊዜ አቻ እንዲሁም 36 ጊዜ ሽንፈት አስመዝግበዋል። ከደቡብ አሜሪካ ጋር ቡድኖች  በ22 ጨዋታዎች ጋር ተገናኝተው 3 ጊዜ ድል ፣ 5 ጊዜ አቻ እንዲሁም 14 ጊዜ ሽንፈት ገጥሟቸዋል፡፡ በ6 የዓለም ዋንጫ ጨዋታዎች ከሰሜንና መካከለኛው አፍሪካ ቡድኖች ጋር ሲገናኙ 3 ድል፣ 2 አቻ እንዲሁም 1 ሽንፈት ውጤት ሲመዘገብላቸው፤ በ7 የዓለም ዋንጫ  ጨዋታዎች ከኤሽያ ቡድኖች ጋር ተገናኝተው 3 ጊዜ ድል፤ 3 ጊዜ አቻ እንዲሁም አንድ  ጊዜ ሽንፈት ነበራቸው፡፡  
በ20ኛው የዓለም ዋንጫ የአፍሪካ ቡድኖች ያላቸው የፉክክር ደረጃ ከአውሮፓ እና ከደቡብ አሜሪካ በመቀጠል በሶስተኛ ደረጃ ግምት አግኝተዋል፡፡ በዚሁ ዓለም ዋንጫ አፍሪካዊ ቡድኖች የሌሉባቸው ሶስት ምድቦች ስፔን፣ ሆላንድ፣ ቺሊና አውስትራሊያ የሚገኙበት ምድብ 2፤ ኡራጋይ፣ ኮስታሪካ፣ እንግሊዝና ጣሊያን የሚገኙበት ምድብ 4 እንዲሁም ስዊዘርላንድ፣ ኤኳዶር፣ ፈረንሳይና እና ሆንዱራስ የሚገኙበት ምድብ 5 ናቸው፡፡ አንዳንድ መረጃዎች በደቡብ አሜሪካ የተዘጋጀ ዓለም ዋንጫን የአውሮፓ ቡድን አሸንፎ አያውቅም በሚል ምክያት የአውሮፓን ሃያላን ከግምት ውጭ ያደርጋሉ። በሌላ በኩል ደግሞ የደቡብ አሜሪካ የአየር ሁኔታ እና ባህል ከአፍሪካ ጋር ተቀራራቢ መሆኑን በመግለፅ አፍሪካን ከወከሉ አምስት ብሄራዊ ቡድኖች መካከል በታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ የሚመዘገቡ ውጤቶችን ሊያሳኩ እንደሚችሉ ገልፀዋል። የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን ናይጄርያ በአህጉሪቱ የዓለም ዋንጫ ተሳትፎ ታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ ለግማሽ ፍፃሜ የማለፍ እድል እንዳላት በሚል ተስፋ ማድረጉም አልቀረም። በአጠቃላይ ከአምስቱ የአፍሪካ ተወካዮች በ20ኛው ዓለም ዋንጫ ላይ ውጤታማ እንደሚሆኑ ግምት ያገኙት በምርጥ ፕሮፌሽናሎች የተገነቡትና በወቅታዊ ብቃታቸው ጥሩ ደረጃ ላይ ያሉት ጋና እና አይቬሪኮስት ናቸው፡፡ ካሜሮን እና አልጄርያ ከተሳትፎ የማይዘል ውጤት እንደሚያገኙ ተጠብቋል፡፡ ታዋቂው የፈረንሳይ ተጨዋች እና የዓለም ዋንጫ አሸናፊ ማርሴይ ዴሳይ አይቬሪኮስት ሩብ ፍፃሜ እንደምትደርስ ሲገምት፤ የናይጄርያ አሰልጣኝ ስቴፈን ኬሺ በበኩሉ የራሱ ቡድን በዓለም ዋንጫው ሩብ ፍፃሜ ለመድረስ ይታገላል ብሏል፡፡ የአፍሪካ ቡድኖች በዓለም ዋንጫ ባለድል እንደሚሆኑ ግምት በመስጠት ይታወቅ የነበረው የብራዚሉ ፔሌ ነው፡፡ ፔሌ አፍሪካዊ ቡድን ዓለም ዋንጫን ማሸነፍ ይችላል ያለበት ይግዜ ተመን ከ10 ዓመት በላይ አልፎታል። የአፍሪካ ቡድኖች በዓለም ዋንጫ በሚኖራቸው ተሳትፎ እንደ አውሮፓ እና ደቡብ አሜሪካ ቡድኖች ስኬት ለማግኘት የማይችሉባቸው በርካታ ምክንያቶች አሉ፡፡ የመጀመርያው የአፍሪካ ቡድኖች በዓለም ዋንጫ ያላቸው የተሳትፎ ኮታ ማነስ ነው፡፡ አንዳንድ የአፍሪካ እግርኳስ ሰዎች አህጉሪቱ በዓለም ዋንጫ የሚኖራት የተሳትፎ ኮታ ጭማሪ ሊደረግበት ይገባል በሚል በፊፋ ላይ ግፊት እያሳደሩ ናቸው፡፡ 52 አገራት የሚያቅፈው የአፍሪካ አህጉር በዓለም ዋንጫ ያለው የተሳትፎ ኮታ 5 ሲሆን 53 አገራትን የሚያስባስበው የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር 13 ተሳታፊዎች አሉት፡፡ ይህ የተሳትፎ ኮታ ሚዛናዊ አይደለም በሚል እነ ሳሚ ኩፎር፤ ሳሙኤል ኤቶ እና ሌሎች የአፍሪካ እውቅ እግር ኳሰኞች አስተያየት ሰጥተዋል። በብዙዎቹ አስተያየቶች የአፍሪካ ቡድኖች ተሳትፎ በዓለም ዋንጫ ከ5 ወደ ሰባት ማደግ አለበት ተብሏል፡፡ ይህንኑ ሃሳብ ከደገፉ መካከል የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር ፕሬዝዳንት የሆነው ሚሸል ፕላቲኒ ሲገኝበት በቀጣይ በ2018 እና በ2022 እኤአ ላይ በራሽያ እና በኳታር በሚደረጉት ዓለም ዋንጫዎች የአፍሪካ ኮታ ሊያድግ የሚችለው በ20ኛው ዓለም ዋንጫ በሚገኝ ውጤታማነት ነው፡፡ የአፍሪካ ቡድኖች በዓለም ዋንጫ ስኬታማ እንዳይሆኑ የሚያደርጉ ሌሎች ምክንያቶችም መዘርዘር ይቻላል፡፡  በዓለም ዋንጫ ከመሳተፋቸው በፊት ባለው ጊዜ በቂ ዝግጅት አያደርጉም፤ በአውሮፓ እና በአገር ውስጥ የሚጫወቱ ተጨዋቾችን አቀናጅቶ ምርጥ ቡድን ለመስራት ይቸገራሉ፤ በየአገሮቻቸው ፌደሬሽኖች በዓለም ዋንጫ በሚገኝ ውጤት የሚሰጡ የቦነስ ክፍያዎች አለመኖር እና ማነስ እንዲሁም ከዚሁ ጋር በተያያዘ በሚነሱ ውዝግቦች መጠመዳቸው ትኩረት ያሳጣቸዋል፤ የብሄራዊ ቡድኖቹ አሰልጣኞች አገር በቀል መሆናቸው እና ዓለም አቀፍ ልምድ እና ተፎካካሪነት የሌላቸው መሆኑም ፈተና ይሆንባቸዋል፡፡
የአረንጓዴዎቹ ንስሮች በረራ
የአፍሪካ ሻምፒዮን የሆነችው ናይጄርያ ብራዚል ላይ በታሪኳ ለ5ኛ ጊዜ ዓለም ዋንጫን ልትሳተፍ ነው፡፡ በ4 የዓለም ዋንጫዎች ላይ በነበራት የተሳትፎ ታሪክ 14 ጨዋታ አድርጋ 4 ድል፣ 2 አቻ 8 ሽንፈት የገጠማት ሲሆን 21 ጎሎች ተቆጥረውባት በተጋጣሚዎቿ ላይ 21 ጎሎችን አስመዝግባለች። በ4ቱ ዓለም ዋንጫዎች 14 ነጥብ በመሰብሰብ ከአፍሪካ በ3ኛ ደረጃ ከዓለም በ36ኛ ደረጃ ተቀምጣለች፡፡     የወቅቱ የአፍሪካ ሻምፒዮን በመሆን ዓለም ዋንጫውን የምትሳተፈው ናይጄርያ በፊፋ ወርሃዊ የእግር ኳስ  ደረጃ በዓለም 35ኛ በአፍሪካ 5ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች፡፡ የናይጄርያ ብሔራዊ ቡድን 362 ግጥሚያዎችን በኢንተርናሽናል ደረጃ በማድረግ ልምድ ሲኖረው የፕሮፌሽናል ተጨዋቾች ብዛት 18 ይደርሳል የናይጀሪያ ብሔራዊ ቡድን አማካይ እድሜ 24.10 ሲሆን በዝውውር ገበያ  ያለው ዋጋ ሲተመን 56 ሚሊዮን ፓውንድ ነው፡፡ ናይጄርያ በምድብ 6  ከአርጀንቲና፤ ቦስኒያ ሄርዞጎቪና እና ኢራን ጋር ስትድለደል አረንጓዴዎቹ ንስሮች በስብስባቸው ወጣትነት መልካም ውጤት ለማግኘት የተገመቱ ናቸው፡፡
የወርቃማዎቹ ዝሆኖች  መጨረሻ
አይቬሪኮስት በ2 የዓለም ዋንጫ ተሳትፎ 6 ጨዋታ አድርጋ 2 ድል፣ 1 አቻና 3 የሽንፈት ውጤት ሲኖራት 9 ጎል ገብቶባት በተጋጣሚዎቿ ላይ ያስቆጠራቸቸው 9 ጎሎች ተመዝግቦላታል፡፡ በሁለቱ አለም ዋንጫዎች 7 ነጥብ ማግኘት የቻለችው አይቬሪኮስት በዚህ ስኬት ከአፍሪካ 8ኛ ደረጃ ሲሰጣት ከዓለም በ49ኛ ደረጃ ላይ ናት፡፡ የዝሆኖቹ  ወርቃማ ትውልድ በተከታታይ በተሳተፈባቸው 2 ዓለም ዋንጫዎች ከፍተኛ ግምት እየተሰጠው ምድቡን ማለፍ እንኳን ሳይችል ቀርቷል፡፡ ብራዚል ላይ በዓለም ዋንጫ በታሪክ 3ኛ ተሳትፎውን ያገኘው የዝሆኖቹ ወርቃማ ትውልድ  ለስኬት የመጨረሻ እድሉ ነው፡፡ አይቬሪኮስት በፊፋ ወርሃዊ የእግር ኳስ  ደረጃ በዓለም 18ኛ በአፍሪካ 1ኛ ደረጃ ስትገኝ፤ 772 ግጥሚያዎችን በኢንተርናሽናል ደረጃ በማድረግ ልምድ አላት፡፡ በብሐራዊ ቡድኑ የፕሮፌሽናል ተጨዋቾች ብዛት 25 አማካይ እድሜ 25 እንደሆነና አጠቃላይ  ስብስቡ በዝውውር ገበያ  ያለው ዋጋ ሲተመን 135ሚሊዮን ፓውንድ ነው። የአይቬሪኮስት ብሄራዊ  ቡድን በምድብ 3 የተደለደለው ከኮሎምቢያ፤ ጃፓንና ግሪክ ጋር ነው፡፡
በተሳትፎ የማይበገሩት አንበሶች  
ካሜሮን በ20ኛው ዓለም ዋንጫ የምትሳተፈው ለ7ኛ ጊዜ ሲሆን የአህገሪቱ ከፍተኛ የተሳትፎ ክብረወሰን ነው። አስቀድማ በተሳተፈችባቸው 6 የዓለም ዋንጫዎች 20 ጨዋታዎች አድርጋ 4 ድል 7 አቻ እና 9 የሽንፈት ውጤት ሲመዘገብላት በተጋጣሚዎቿ ላይ 17 ጎል አግብታ 34 ተቆጥሮባታል፡፡ በ6 ዓለም ዋንጫዎች ካሜሮን 19 ነጥብ በመሰብሰቧ ከዓለም 29ኛ ደረጃ ስታገኝ በዓለም ዋንጫ ከፍተኛውን ነጥብ በመሰብሰብ አንደኛ ናት፡፡ ካሜሮን በ1990 እኤአ ላይ በጣሊያን ተደርጎ በነበረው ዓለም ዋንጫ ለሩብ ፍፃሜ በመድረስ የመጀመርያውን ከፍተኛ የአፍሪካ ቡድን የውጤት ክብረወሰን በማስመዝገብ ፈር ብትቀድም ይህን ስኬት መድገም ተስኗት ቆይቷል፡፡ በፊፋ ወርሃዊ የእግር ኳስ  ደረጃ በዓለም 51ኛ በአፍሪካ 8ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው የካሜሮን ቡድን ቡድን 498 ግጥሚያዎችን በኢንተርናሽናል ደረጃ በማድረግ ልምድ አለው፡፡ ካሜሮን ያሏት ፕሮፌሽናል ተጨዋቾች ብዛት 28 ሲሆን የቡድኑ  አማካይ እድሜው 26 እንደሆነና አጠቃላይ ስብስቡ በዝውውር ገበያ  ያለው ዋጋ ሲተመን 125 ሚሊዮን ፓውንድ ነው፡፡ የካሜሮን ብሄራዊ ቡድን  በምድብ 1 ከብራዚል፤ ሜክሲኮ እና ክሮሽያ ጋር ተመድቧል፡፡  ቡድኑ ከጡረታ በተመለሰው፤ ከዓለማችን ምርጥ አጥቂዎች አንዱ በሆነውና ለአራት ጊዜ የአፍሪካ ኮከብ ተጨዋች በነበረው ሳሙዔል ኤቶ የሚመራ ነው። የማይበገሩት አንበሶች በፈረንሳይ ሊግ በሚጫወቱ ምርጥ ተከላካዮች የተገነባ ቢሆንም በቡድኑ ተጨዋቾች መካከል ያለው መከፋፈል፤ ግጭት እና ከአቅም በታች የመጫወት አባዜ የ20ኛው ዓለም ዋንጫ ተሳትፎው ፈታኝ ሊሆንበት ይችላል፡፡
በሞት ምድብ ያሉት ጥቋቁር ክዋክብቶች
ጋና ባለፉት 2 የዓለም ዋንጫዎች ስታሳትፍ ባደረገቻቸው  9 ጨዋታዎች 4 ድል፣ 2 አቻ እና 3 ሽንፈት ውጤት ያስመዘገበች ሲሆን በተጋጣሚዎቿ ላይ 9 አግብታ 10 ጎሎች አስተናግዳለች፡፡ በሁለቱ ዓለም ዋንጫዎች 14 ነጥብ መሰብሰብ የቻለችው ጋና በዓለም ዋንጫ ውጤቷ በአፍሪካ ሁለተኛ ደረጃ ሲሰጣት በዓለም 35ኛ ነች፡፡ በፊፋ ወርሃዊ የእግር ኳስ  ደረጃ በዓለም 24ኛ በአፍሪካ 2ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው የጋና ብሄራዊ ቡድን 725 ግጥሚያዎችን በኢንተርናሽናል ደረጃ በማድረግ ልምድ አለው፡፡ 34 ምርጥ ፕሮፌሽናል ተጨዋቾች የሚያቅፈው ቡድኑ አማካይ እድሜ 25.20 ሲሆን አጠቃላይ ስብስቡ በዝውውር ገበያ  ያለው ዋጋ ሲተመን 77 ሚሊዮን ፓውንድ ነው፡፡ ከ4 ዓመት በፊት ደቡብ አፍሪካ አስተናግዳ በነበረው 19ኛው ዓለም ዋንጫ ወደ ግማሽ ፍፃሜ ለመግባት ከፍተኛ እድል ይዛ ነበረ፡፡ በ20ኛው ዓለም ዋንጫ ታሳካዋለች ተብሎ ይገመታል፡፡ በከሞት ምድብ በተፈረጀው ምድብ 7 ከጀርመን፣ፖርቱጋልና አሜሪካ መገናኘቷ ትኩረት አግኝቷል፡፡ የጋና ብሄራዊ ቡድን በወቅታዊ ብቃቱ የምርጥ አማካዮች እና አጥቂዎች ስብስቡ የተጠናከረ ነው፡፡
አልጄርያ ለሰሜን አፍሪካ ብቸኛ ተወካይ
ሰሜን አፍሪካን በብቸኛ የወከለችው አልጄርያ ከ20ኛው የዓለም ዋንጫ  በፊት አልጀሪያ በ3 የዓለም ዋንጫዎች ስትሳተፍ ባደረገቻቸው 9 ጨዋታዎች 2 ድል፣ 2 አቻ ና 5 የሽንፈት ውጤቶች ስታገኝ በተጋጣሚዎቿ ላይ 6 ጎል አግብታ በመረቧ ላይ 12 ጎሎች ተመዝግበዋል፡፡  አልጄርያ አስቀድሞ በተሳተፈችባቸው 3 ዓለም ዋንጫዎች በሰበሰበችው 8 ነጥብ ከአፍሪካ ሰባተኛ ደረጃ ስተወስድ ከዓለም 47ኛ ደረጃን ይዛለች፡፡ በፊፋ ወርሃዊ የእግር ኳስ  ደረጃ በዓለም 34ኛ በአፍሪካ 11ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው የአልጄርያ ቡድን 300 ግጥሚያዎችን በኢንተርናሽናል ደረጃ በማድረግ ልምድ ይዟል፡፡ የአልጄርያ ፕሮፌሽናል ተጨዋቾች ብዛት 19 ሲሆን አማካይ እድሜ 26.8 የሆነና ድረገፅ አጠቃላይ የቡድን ስብስብ በዝውውር ገበያ  ያለው ዋጋ ሲተመን 51.5 ሚሊዮን ፓውንድ ነው፡፡ በ20ኛው የዓለም ዋንጫ   ለ4ኛ ጊዜ ስትሳተፍ የተመደበችው ቀላል በተባለው ምድብ 8 ከቤልጅዬም፣ ደቡብ ኮርያ እና ራሽያ ጋር ነው፡፡ ከአራቱ የምዕራብ አፍሪካ ቡድኖች ለአልጄርያ ዝቅተኛ ግምት ተሰጥቷታል፡፡ ዋና ጥንካሬዋ ተቀማጭነታቸውን በፈረንሳይ ያደረጉ ተጨዋቾችን በብዛት ያሰባሰበ ቡድን መያዟ ነው፡፡





Read 2715 times