Sunday, 05 January 2014 00:00

ባሎች ለሚስቶች ሊሉት የማይገባ ነጥብ...

Written by 
Rate this item
(2 votes)

ባሎች ለሚሰቶቻቸው ሊሉት የማይገባቸው ነጥቦች ምንድናቸው? በእርግጥ ይህ ሁሉንም አስፈላጊ ነገር ያንትታል ባይባልም በመጠኑ ለጠቅላላ እውቀት ስለሚረዳ ለንባብ ብለነዋል፡፡ፀሐፊዋ ጂሊ ስሞክለር ትባላለች፡፡  
ጂሊ ስሞክለር እንደምትለው ከባለቤትዋ ጋር ከአስር አመት ላላነሰ ጊዜ አብራ ኖራለች፡፡
ነገር ግን ከዚህ ሁሉ አመታት በሁዋላም ባልዋ ባህርይዋን ስላልተረዳው እኔ ምን መስማት እንዳለብኝና እንደሌለብኝ ብነግረው ብነግረው ሊሰማኝ አልቻለም፡፡ የተከበርክ ባለቤቴ እባክህን እኔን በሚመለከት እነዚህን አስር ነጥቦች አትናገራቸው... አልወዳቸውም ብዬ በፍሪጅ ላይ በግድግዳ ላይ ሁሉ ቦታ ለጠፍኩዋቸው፡፡ ነገር ግን ትላለች ጂሊ... እሱ ምን በወጣው ዞር ብሎም አያያቸውም፡፡ ስለዚህ ሌሎች ሚስቶችም ልክ እንደእኔ ተበሳጭተው ሊሆን ስለሚችል ለንባብ ብያቸዋለሁ ብላለች፡፡ ሰዎች  በአለም ዙሪያ በብዙ ጎናቸው ይመሳሰላሉ፡፡ እናም  ትዳሩ ...ወልዶ ማሳደጉ ... ፍቅሩ...ጸቡ...ብቻ ብዙው ነገር ይመሳሰላል፡፡ምናልባትም የአንዱ ሀገር ህዝብ ከሌላው ጋር የሚለያይባቸው ነገሮች ቢኖሩም ሰው በመሆናቸው ብቻ የሚጋሩዋቸው ነገሮች ይኖራሉ፡፡ ለዚህም ነው መረጃዎች ከአለም አለም በተመሳሳይ ድህረ ገጽ ለንባብ የሚቀርቡት፡፡
                                                 -------////-------
ባሎች ለሚስቶች ወይንም ለፍቅረኞች ሊናገሩዋቸው የማይገባቸው ነጥቦች...
1/ መታጠቢያ ቤት አጠቃቀም፣
እኔ ወደ መታጠቢያ ቤት ስሔድ ትክክል ልሁን ወይንም አልሁን ባለቤቴ ሊነግረኝ አይገባም፡፡
የመታጠቢያ ቤት ጉዞ ለግለሰቡ የግል ጉዳይ ተደርጎ መተው ያለበት ጉዳይ ነው፡፡ ወደ መታጠቢያ ቤት  መሔድሽ ልክነው ወይንም ልክ አይደለም የሚለው አስተያየት በሌላው ሰው ወይንም በባል  ቢሰነዘር የተጠቃሚውን  ሞራል ሊነካ ይችላል፡፡ ይሄንን በሚመለከት በባልና በሚስት ብቻም ሳይሆን በማንኛውም ሰው ቢሆን አስተያየት ሊሰጥበት የማይገባ ነው ትላለች ፀሐፊዋ፡፡ ስለዚህ ባሎችም ሆኑ ሚስቶች በእንደዚህ ያለው የግል ጉዳይ ላይ አስተያየት እንዲሰጡ ካልተጋበዙ በስተቀር ጣልቃ በመግባት አስተያየት ባይሰጡ ይመከራል ትላለች ጂሊ።
እንደዚህ ያለው ጉዳይ ለዚህ አገር ሰዎች ይሆናል አይሆንም የሚባል ሳይሆን ለሁሉም የሰው ልጅ የሚሆን አስተያየት ነው፡፡
2/ ምግብ፣
እኔ ቀኑን ሙሉ ለፍቼ የሰራሁትን... ቀኑን ሙሉ የደከምኩበትን ምግብ ባሌ እንዲበላ ሳቀርብለት ... የምግብ ጠረኑን ማሽተት...ወይንም አሁን ይሄ ምግብ ነው? ብሎ መተቸት እጅግ ያማር ራል፡፡ በእርግጥ ምግቡ የጎደለው ነገር ቢኖር በግልጽ መነጋገር ይቻል ይሆናል። ነገር ግን በደፈናው መተቸት አይገባም ትላች ጂሊ... አንዳንድ ጊዜ ወንዶች ለቤት ወጪ የሚሰጡት ገንዘብ ምግብን አጣፍጦ ለመስራት አይበቃ ይሆናል ብለው ቢገምቱ ምናልባት አስከፊውን ነገር ያስወግድ ይሆናል፡፡
-------////-------
“...ባለቤቴ ለእኔ የሚሰጠው የቤት ወጪ እና እሱ በኪሱ የሚያስቀረው ገንዘብ አኩል ነው፡፡ ለቤት ወጪ የሚሰጠው ገንዘብ አራት ልጆችን እሱንና እኔን ጨምሮ የተተመነ ነው፡፡ በሱ ኪስ የሚቀረው ግን ለእሱ ብቻ ነው። እሱ ቁርሱን እራቱን ምሳውን የሚበላው ከቤቱ ነው፡፡ በኪሱ የሚቀረው ገንዘብ ግን ለመጠጥ ብቻ የሚሆን ነው፡፡ ታድያ ሁልጊዜ የሚናገረው ነገር ምግቡ እንደማይጣፍጥ ነው፡፡ አንድ ሊትር ዘይት ለአስራአምስት ቀን ካልበቃ ምን ኑሮ ነው? ይላል በሌላ በኩል ደግሞ ወጡ ዘይት የለውም አይጣፍጥም ይላል፡፡ ግራ የገባ ነገር ነው...”
    ኢትዮጵያዊት ሴት የሰጠችው አስተያየት
3/ የልጆች መስተንግዶ፣
ጂሊ እንደምትገልጸው...እኔ እናታቸው ቀኑን ሙሉ አብሬአቸው ውዬ ነገር ግን አመሻሹ ላይ እሱ ሲመጣ ሶስት ሴኮንድ ባልሞላ ጊዜ ውስጥ የእሱ አድናቂዎች እንዲሆኑ...እሱ እንደሚ ወዳቸው... አንዳንድ ቀለብ ወይንም ልብስ የማይሆኑ ነገሮችን ይዞ መጥቶ በማባበል... ወይንም በማታለል ከእኔ ጋር ጭቅጭቅ መፍጠር አይገባም፡፡ እኔ እናታቸው ምግባቸውን አብስዬ አቅርቤ ልብሳቸውን አጥቤ ትምህርት ቤት እንዲሄዱ አድርጌ… እነዚህንና የመሳሰሉትን መሰረታዊ ስራዎች ሰርቼ ስለማሳድጋቸው አባትየው የበለጠ ተወዳጅ ለመሆን የማያስፈልግ ጥረት ማድረግ አይገውባም፡፡ ነገር ግን አለች... ጂሊ ...በትክክለኛው መንገድ ከእናትየው ጋር በመተባበር ልጆችን ማስተናገድ ከአባትየው ይጠበቃል፡፡ እናትየው አባታቸውን እንዲጠሉ ወይንም አባትየው እናታቸ ውን እንዲጠሉ ማድረግ ትክክል አይደለም፡፡
4/ አጉዋገል ቀልዶች፣
አንዳንድ ጊዜ በስራ ቦታ የሚቀለዱ ደርቲ ጆክ የሚባሉ አጉዋጉል ቀልዶችን በቀጥታ ወደቤት ማምጣት እና ከሚስት ጋር ለመቀለድ መሞከር ደግ አይደለም፡፡  ለእንደዚህ ያለው ጨዋታ እነዚያኑ ጉዋደኞችህን ጥራቸው ብላለች ጂሊ ለባልዋ ...ይሄንን የሚያደምጡ ሁሉ ቀልዶቹ ምን አይነት እንደሆኑ መገመት አያቅታቸውም። እውነትም ከሚስት እና ከባል ጋር የሚቀለዱ ቀልዶችን መለየት ይገባል፡፡
5/ ቅያሬ ካልሲ ማጣት፣
ምነው ካልሲዎቼ በሙሉ ቆሸሹ? ይሄ ጥያቄ በጭራሽ ሊነሳ አይገባም፡፡ ምክንያቱም ባል ካልሲ እንኩዋን በማጠብ እራሱን አይረዳም እንዴ? ስትል ትጠይቃለች ጂሊ ስሞክለር፡፡  ካልሲውን ባጥብ... ባጥብ ...ሁልጊዜ ችግር መሆኑ አይቀርም፡፡ እኔ ከአቅሜ በላይ ስለሆነ ብትፈልግ አንዱን ካልሲ ከአንዱ አዛምደህ አድርግ ...አረ ብትፈልግ አታድርግ ብዬ መልስ ሰጠሁ፡፡ በዚህ ብቻም አላቆምኩም ትላለች ጂሊ፡፡ እንዲያውም ከዚያ በሁዋላ ወደካልሲ ፊቴን ማዞር ትቻለሁ፡፡ በገዛ እጁ በቅንነት ማገልገሌን እንድተው አድርጎኛል ትላለች፡፡
በእርግጥ ይህ ብዙ ወንዶችን አይመለከትም፡፡ በዛሬ ጊዜ ወንዶች ከዚህም ባለፈ ቤታቸውን ልጆቻቸውን ሲረዱ ስለሚታዩ ለሚስቶቻቸው እንዲህ ያለ ጥያቄ ያቀርባሉ ተብሎ አይጠበቅም፡፡ ከሆነም ይታረም ይላሉ ሚስቶች፡፡
6/ የሰውነትን ቅርጽ በሚመለከት ፣
ምነው በየቀኑ ትወፍሪያለሽ? ይህ ጥያቄ በጣም ነው የሚያበሳጨኝ፡፡ ምናልባት ወፍሬም ቢሆን እኔ እንዲነገረኝ አልፈልግም፡፡ ይልቁንም ይህ አይነት ቀለም ልብስ  አይስማማሽም ወይንም ይሄኛውን ለውጠሸ ልበሽ ብባል እወዳለሁ፡፡ ከዚህ ባለፈ ግን ስለውፍረቴ መስማት ያበሳጨኛል፡፡ እኔ ወድጄ ያደረግሁት ስላልሆነ ልወቀስበት አልፈልግም ትላለች ጂሊ፡፡  
7/ የሰውነት ጠረን፣
በስራ እና በተለያዩ ምክንያቶች ጊዜ አጥቼ ልብሴን ለሁለት ቀን ወይንም ከዚያ በላይ አልለወጥኩ ይሆናል። እንግዲህ ልብስ ካልተለወጠ ሰውነት ምን ምን ሊሸት እንደሚችል የታወቀ ነው፡፡ይህንን እኔም አላጣሁትም፡፡ ግን ጊዜ አጥቼ ወይንም ሳይመቸኝ ቀርቶ ነው፡፡
የተከበረው ባለቤቴ በፍቅር መንገድም ሳይሆን በማጥላላት ኡፍ… ምን ምን ትሸቺያለሽ? አትታጠቢም እንዴ ቢለኝ እና ቢያጥላላኝ በጣም ነው የሚከፋኝ። ቢታገሰኝ ግን እኔ እራሴ ጥሩውን ነገር ለማድረግ ጭንቅላቴ ዝግጁ ስለሚሆን አርመዋለሁ፡፡
8/ ኩርፊያ፣
አንተ የሚያስገርም ኩርፊያ እያኮረፍክ ጥሩ እንቅልፍ ትተኛለህ፡፡ እኔ ግን በአንተ ኩርፊያ ምክንያት ቁጭ ብዬ አድራለሁ፡፡ እስቲ ምን ይባላል? ኩርፊያን የሚያመጡ ነገሮችን ለማረም ምንም ዝግጁ አይደለህም፡፡ አመጋገብ አስተኛኘት የመሳሰሉት ነገሮች ላይ ግድ የለህም፡፡ ታዲያ እንደዚህ ያለውን ጥፋት ለማረም ካልቻልክ ምናለበት ወደዚያችው ወደምትችልህ እናትህ ብትሄድ ወይንም እሱዋን ወደ አንተ ብትጠራት የወለደ እንግዲህ እዳ አለበት አይደል? ትላለች ሚስት...
...በአገራችንም ይብላኝ ለወለደህ ያገባህስ ይፈታሀል ተብሎ የለ?
9/ ሙድ፣
አንተን ደስ ባለህ ወይንም ሙድህ በተስተካከለ ጊዜ የሚስትህን መደሰትና አለመደሰት ወይንም ሙድ ሳትገነዘብ ምንም ነገር አትጠይቅ፡፡ የስዋ ስሜት እስኪስተካከል ጠብቅ፡፡ አለበለዚያ እንደመጣልህ የምትገልጸው ወይንም ስሜትህን የምታሳይ ከሆነ ሚስትህ ልታስቀይምህ ትችላለች፡፡ ምክንያቱም አልተዘጋጀችበትማ...
10/ ልጆን ማዝናናት፣
ልጆችህን ከቤት ውጭ የማዝናናት ስራ እንዳለብህ አትዘንጋ... ወደሲኒማ ቤት ወይንም መታጠ ቢያ ቦታ፣ ስፖርት ቦታ፣ ዋና ቦታ ፣ከውጭ ምሳ መጋበዝ የመሳሰሉትን ከሚስትህ ጋር አብረህ ማድረግ አለብህ። ምናልባትም ሚስትህ በአንዳንድ ስራዎች እንኩዋን ብትያዝ መስተንግዶው እንዳይቋረጥባቸው ልጆችህን መንከባከብ ትልቁ ስራህ መሆኑን እንዳትረሳ፡፡

Read 3329 times