Sunday, 05 January 2014 00:00

ፅርሀ አርያማዊ የገና ዛፍ

Written by  ደራሲ፡- ፊዮዶር ዶስቶቨስኪ ተርጓሚ፡- ዮናስ ነማርያም
Rate this item
(7 votes)

         ደራሲ ነኝ፡፡ ይህ ታሪክ ከእኔው ምናብ የፈለቀ ይመስለኛል፡፡ ይመስለኛል ብልም እኔው እንደፈጠርኩት በእርግጠኝነት አውቃለሁ፡፡ ምናልባትም በሆነ ስፍራ ፣ ወቅት በገሃዱ ዓለም የተከሰተ ሊሆን ይችላል፡፡ ያውም በገና ዋዜማ …በአንድ ሞቅ ደመቅ ባለ ከተማ፡፡ ውርጩ እና ቁሩ በበረቱበት ወቅት፡፡…በእዝነ ሕሊናዬ አንድ ልጅ ይታየኛል፡፡ 6 ዓመት ያልበለጠው ብላቴና፡፡ እንደ በረዶ ከቀዘቀዘ የምድር ስር ቤት በማለዳ ከእንቅልፉ ነቃ፡፡ ብን ብላ የሳሳች ጨርቅ ቢጤ ትከሻው ላይ ጣል ቢያደርግም ብርዱ እያንዘፈዘፈው ነው፡፡ በዚያ ላይ ርሀብ እየሞረሞረው፡፡ የሳሳ ፍራሽ ላይ ከተኛችው በሽተኛ እናቱ ዘንድ መለስ ቀለስ አለ…ግን እናቱ እንዴት? ከየት? እዚህ መጣች፡፡ ከሌላ ቦታ መጥታ ድንገተኛ በሽታ ጥሏት ይሆን፡፡
አብዛኛዎቹ ተከራዮች ከበዓሉ ቀደም ብለው ቤቱን ለቀዋል፡፡ ቤቱ ውስጥ የቀሩት ለ2 ሰዓት ቀምቅሞ አቅሉን ስቶ የተዘረረ ሰካራም ሰውዬ እና አንዲት የጨረጨሱ አሮጊት፡፡ እኚህ የ80 ዓመት አሮጊት ቀድሞ ሞግዚት ነበሩ….ልጅ ጠባቂ…አሁን ግን ከሞት ሌላ የሚጠብቁት ምንም የለም…ያውም ያለ አስታዋሽ፡፡ በቁርጥማት በሽታ በፅኑ እያቃሰቱ ነው፡፡ ልጁ ላይ እያልጎመጎሙ በጥልቅ ጥላቻ አፍጥጠውበታል፡፡
ጨለማው እየበረታ ነው፡፡ ፍርሃት ህይወት ዘርግቶ ውስጡ ተላወሰ፡፡ በሽተኛ እናቱን ልቀስቅሳት አልቀስቅሳት በሚል ወላወለ፡፡ ከቆይታ በኋላ የእናቱን ፊት ሲነካ እንቅስቃሴ አልባ በድን የመሆኗ ነገር ገርሞት “እዚህ ይቀዘቅዛል” ሲል አሰበ፡፡ ሳያስበው እጆቹን የሟች እናቱ ትከሻ ላይ አሳረፈ፡፡
……ጣቶቹን እርስ በእርስ እየሰበቀ በትንፋሹ ሞቅ አድርጎ፣ ከዚያች የጨለማ ማኅፀን የምድር ስር አብራክ ወጣ፡፡ ወደ ጎዳናው አመራ፡፡ እንዴት ያለ የሞቀ የደመቀ ከተማ ነው! በፊት የነበረበት ከተማ ከመሸ በኋላ በጨለማ አዘቅት የሚዋጥ ነው፡፡ ደንገዝገዝ ሲል መንገድ ላይ ዝር የሚል ሰው የለም። ሁሉም ወደቤቱ ይገባል፡፡ ጎዳናው ሌሊቱን የውሾች ማላዘኛ ሆኖ ያርፈዋል፡፡ ቢሆንም እዚያ እንደዚህ አይበርድም፡፡ ሙቀት አለ፡፡ ምግብ አለ፡፡ እዚህ የሚላስ የሚቀመስ የለም፡፡ ትርምስና ግርግሩ ግን ሌላ ነው፡፡ ከአፉ የሚያኖረው የሚቀመስ ነገር ለማግኘት ተንሰፍስፏል፡፡ ጠኔ ሊጥለው ነው፡፡ በማለፍ ላይ የነበረ ፖሊስ መኮንን፣ ልጁን ላለማየት ፊቱን አዞረ፡፡
ወደ ሌላ ሰፊ ማራኪ ጎዳና አቀና፡፡ ሰው ሁሉ ይጯጯኃል፡፡ በዚያ ላይ ግርግሩ….በብርሃን የተሽቆጠቆጠ፡፡ በአንድ ሰፊ የመስታወት መስኮት፣ጣሪያ ሊነካ የደረሰ ድምቅ ያለ የገና ዛፍ ይታያል፡፡ ሙሉ በሙሉ በመብራት፣በወርቃማ ወረቀቶች፣በአሻንጉሊቶች ያሸበረቀ…..የገና ዛፍ። ፍፁም ፅዱ የሆኑ ልጆች ክፍሉ ውስጥ ላይ እታች ይራወጣሉ …… እየተሳሳቁ እየፈነደቁ….. እየበሉ እየጠጡ፡፡ አንዲት ትንሽዬ ውብ ልጅ ከአንዱ ጋር መደነስ ጀመረች፡፡ እንዴት የምታምር ውብ ልጅ ናት፡፡ ሙዚቃው ውጪ ድረስ ያስተጋባል፡፡ የእጅና የእግር ጣቶቹ በቆፈኑ ተቆራምደው ፅኑ ስቃይ ውስጥ ቢሆንም በተመለከተው ነገር በመደነቅ ከት ብሎ ይስቃል፡፡
የጣቶቹ ህመም በረታበትና ማልቀስ ጀመረ፣እንደ መሮጥም አለ…. ደግሞ ከሌላ የመስታወት መስኮት የገና ዛፍ ተመለከተ፡፡ ጠረጴዛው ላይ የኬክ አይነት በገፍ ተደርድሯል፡፡ ሶስት ሴቶችም ተቀምጠዋል፡፡ ለሚገባው ሁሉ ኬክ እያነሱ ይሰጣሉ፡፡ ልጁም በቀስታ ወደ በሩ ተጠጋ፡፡ በሩን ከፍቶ ሰተት ብሎ ወደ ውስጥ ዘለቀ፡፡ ውስጥ የነበሩት አንድ ላይ አምባረቁበት፣ አዋከቡት፡፡ አንዷ ወደ እሱ መጥታ ሳንቲም እጁ ላይ አኖረችና እንዲወጣ በሩን ከፈተችለት፡፡ እንዴት በፍርሃት እርዶ ነበር፡፡ የገነተሩ ቀይ ጣቶቹ በቅጡ ሳንቲሙን በቅጡ መጨበጥ ስላልቻሉ ወደቁበት፡፡ ወዴት እንደሚሄድ ባያውቅም ከዚያ ቦታ በፍጥነት ሸሸ፡፡
….አልቅስ አልቅስ ብሎታል፡፡ ደግሞም ፍርቷል። እናም እሮጠ…እሮጠ…የባይተዋርነት፣ የብቸኝነት ስሜት ተሰማውና በሀዘን ተዋጠ፡፡
ደግሞ ሌላ ባለ መስታወት መስኮት ውስጥ ሶስት አሻንጉሊቶች ተደርድረዋል፡፡ ቀይና አረንጓዴ የለበሱ፡፡ ሽማግሌው ትልቅ ቫዮሊን ይዞ ይጫወታል። ሁለቱ ደግሞ እራሳቸውን ነቅነቅ …ነቅነቅ…. እያደረጉ ከንፈራቸውን እያንቀሳቀሱ የሚያወሩ ይመስላሉ። ልጁ አሻንጉሊቶቹ ህይወት ያላቸው ፍጡራን መስለውት ነበር፡፡ ቆየት ብሎ ግዑዝ አሻንጉሊቶች መሆናቸውን ሲረዳ፣ ሳቁን መቆጣጠር አልቻለም…ከት ብሎ ሳቀ፡፡ እንዲህ አይነት አሻንጉሊቶች ይኖራሉ ብሎ አላሰበም፡፡
በድንገት አልቅስ አልቅስ አለው፡፡ አሻንጉሊቶቹ የፈጠሩበት ግርምት ግን አለቀቀውም፡፡ የሆነ ሰው ከኋላው ሲጎነትለው ተሰማው፡፡ አንድ እርኩስ ልጅ ነበር፡፡ በኩርኩም ብሎት ኮፍያውን ላፍ አድርጎ ገፈተረው፡፡ ልጁ ከመሬት ላይ ተዘረረ፡፡ ግርግር ሆነ፡፡ ዙሪያውን ሰዎች ከበቡት፡፡ ልጁ በፍርሀት ተብረከረከ። ከወደቀበት ተነስቶ እብስ አለ፡፡  የት እንደደረሰ ሳያውቀው አንድ ግቢ ጓሮ ገብቶ ከእንጨት ክምር ጀርባ ተደበቀ፡፡ “እዚህ በፍፁም ማንም አያገኘኝም፤ ደግሞ ጨለማ ነው”….
ኩርምት ብሎ ቁጢጥ አለ፡፡ በተፀናወተው ፍርሐት ትንፋሹ እየተቆራረጠ ከመቅፅበት የደስተኝነት ስሜት በውስጡ ናኘ፡፡ የእግርና የእጁ ህመም ለቀቀው፡፡ ፍፁም ፈውስ በውስጡ እንደ ጠል ፈሰሰ፡፡ ምድጃ ዳር እሳት እንደሚሞቅ ሰውነቱ ዘና አለ፡፡
በመሀል ብንን አለ….ተኝቶ ነበር ማለት ነው፡፡ “እዚህ መተኛት እንዴት አስደሳች ነው…ትንሽ ቆይቼ እንደገና አሻንጉሊቶቹን ሄጄ አያቸዋለሁ፡፡” ብሎ በውስጡ አብሰለሰለ እናም ስለ አሻንጉሊቶቹ አስቦ ሳቅ አለ፡፡ “ልክ የእውነት እኮ ነው የሚመስሉት”፡፡ ….እናቱ ከላይ ሆና ስታንጎራጉር ሰማት፡፡
“እማዬ ተኝቻለሁ፤ እዚህ ማንቀላፋት እንዴት ደስ ይላል”
“ና ወደ ገና ዛፌ …ማሙዬ” በርህራሔ የተነከረ ለስለስ ያለ ድምፅ አንሾካሾከበት፡፡ የእናቱ መስሎት ነበር፡፡ ግን አይደለም፡፡ ሊያየው አልቻለም፡፡ የሆነ ሰው ከጨለማው አብራክ ወጥቶ በርከክ ብሎ እቅፍ አደረገው፡፡ እሱም በደስታ ሲቃ እጁን ዘረጋለት…ሁሉም ነገር ከመቅፅበት ብርሀን በብርሃን ሆነ….አስደናቂ የገና ዛፍ፡፡ ብሩህ አንፀባራቂ ምትሀታዊ የገና ዛፍ…. የተለመደው የፅድ ዛፍ አልነበረም፡፡ እንዲህ ያለ የገና ዛፍ ፈፅሞ አይቶ አያውቅም፡፡ የት ነው ያለው? ምትሀታዊ የገና ዛፍ በአሻንጉሊቶቹ ተሽቆጥቁጦ…. የለም የለም አሻንጉሊቶች አይደሉም….አንፀባራቂ የሚያማምሩ ትናንሽ ልጆች ናቸው፡፡ እንደ መላዕክት እየበረሩ መጥተው በልጁ ዙሪያ ሾሩ፡፡ ሁሉም ሳሙት። ተሸክመው ይዘውት ነጎዱ፡፡ እርሱም እየበረረ ነበር፡፡
እርሱን እያየች በመሳቅ ላይ የነበረችው እናቱን አያትና “እማምዬ እንዴት ደስ ይላል እዚህ” …ልጆቹን በየተራ ሳመና ….በሱቁ መስኮት ስላያቸው አሻንጉሊቶች ሊነግራቸው አሰበ፡፡ “እነ ማሙሽ…እነ ሚሚ እነማን ናችሁ?” ግርም ብሎት ጠየቀ፡፡
“ይህ የክርስቶስ የገና ዛፍ ነው” ሲሉ መለሱለት፡፡ …. “ክርስቶስ በዛሬው እለት የገና ዛፍ ያዘጋጃል…የገና ዛፍ ለሌላቸው ምስኪን ልጆች…”
እነዚያ ሁሉ ልጆች ልክ የእርሱ ቢጤ ምንዱባን መሆናቸውን አወቀ…የግፍ ብካይ ሰለባዎች፡፡ አንዳንዶቹ በጨቅላነታቸው በቅርጫ ተደርገው ከሀብታሞቹ የፒተርስበርግ ነዋሪዎች ቤት ደጃፍ ተጥለው በረዶ ሆነው የቀሩ …በየማሳደሪያው በጭስ ታፍነው የሞቱ ወላጅ አልባ ህፃናት…አንዳንዶቹም ጠኔ ከያዛት እናታቸው ጡት ላይ የሞቱ…ሌሎቹም በተግማማው በሚቀረናው ሶስተኛ ማዕረግ ባቡር ውስጥ ታጅለው ታፍነው የሞቱ…እነሆ አሁን ግን ሁሉም እዚህ ናቸው፡፡ ኢየሱስን የከበቡ መላዕክት መስለው፡፡ ክርስቶስ መሀላቸው ሆኖ እጆቹን ዘርግቶላቸዋል፡፡ እጆቹን ከፍ አድርጎ ሀጥያተኛ እናቶቻቸውን ይቅር አላቸው፡፡ ባረካቸውም፡፡ የህፃናቱ እናቶች በአንድ በኩል ቆመዋል….እንባቸው ኩልል ብሎ እየፈሰሰ፡፡ ልጆቻቸውም ለይተው አውቀዋቸዋል፡፡ ህፃናቱም ወደእየ እናቶቻቸው በመሄድ ሳሟቸው፡፡ በሚጢጢዬ ፀአዳ እጆቻቸው የእናቶቻቸውን እንባ አበሱ፡፡ ዛሬ የሀሴት ቀን በመሆኑ እንዳያለቅሱ ተማፀኗቸው፡፡
ማለዳ የቤቱ ዘበኛ፤ እንደበረዶ የተጋገረውን የህፃኑን አስክሬን ከእንጨት ክምሩ ጋ አገኘው፡፡ እናቱ ከልጇ ቀደም ብላ ነበር የሞተችው…በሰማይ ግን በጌታ ፊት ተገናኙ፡፡
በምድር ቤቱ እና ከእንጨቱ ክምር ስር የሆነው በገሀዱ አለም ተከስቶ ሊሆን ይችላል…. የክርስቶስ የገና ዛፍ ተከስቶ ይሆናል ወይም አይሆንም የሚለውን ግን ለማወቅ አልችልም፡፡

Read 3270 times