Sunday, 05 January 2014 00:00

ቀጣዩ የምርጫ ቅስቀሳ ቤት ለቤት ሳይሆን በፌስቡክ!

Written by  ኤልያስ
Rate this item
(11 votes)

የጋዜጠኞች ማህበራት ደቡብ ሱዳንና ሶማሊያ ቢሞክሩ ያዋጣቸዋል!
ኤልፓ ለአርጀንቲና የኤሌክትሪክ ኃይል ለምን አይሸጥም?

ባለፈው ሳምንት ሁለት እምብዛም የማላውቃቸው የአገሬ የጋዜጠኞች ማህበራት ፕሬዚዳንቶች ለአዲስ አድማስ ጋዜጣ የሰጡትን ቃለምልልስ አንብቤ እንዴት እንደኮራሁ ልገልፅላችሁ አልችልም፡፡ የኩራቴ ምንጭ ግን በጋዜጠኞች ማህበር መሪነታቸው አይደለም። እኔ የኮራሁት በሌላ ነው፡፡ ለምሳሌ የአንደኛው ማህበር ፕሬዚዳንት ማህበሩ ከተቋቋመ ጀምሮ ምን እንደሰራ ሲጠየቅ “ታሪካችን መፅሃፍ ነው፤ተነብቦ አያልቅም” ሲል የመለሰው በእጅጉ ነው ያስደመመኝ፡፡ ይኸው ሳምንት ሙሉ እኮ ንግግሩ ከልቤ አልወጣም፡፡ (አንደበተ ርቱዕ አይጥፋ አቦ!)
የሌላኛው ማህበር መሪ ደግሞ በሽብርተኝነት ተከስሶ የታሰረውን ጋዜጠኛ ውብሸትን ለማስፈታት ማህበራቸው ከመንግስት ጋር ተደራድሮ ሁሉም ነገር ሊያልቅ ሲል፣ሲፒጄ ውብሸትን የተመለከተ ሪፖርት በማውጣቱ ጥረታቸውን እንዳስተጓጎለባቸው ለአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ገልጿል፡፡ ግን እንዴት--አልገባኝም። መንግስት ጋዜጠኛውን ለመፍታት ከተስማማ በኋላ፣ሲፒጄ ባወጣው መግለጫ እልህ ውስጥ ገብቶ  ሃሳቡን ቀየረ ማለት ነው፡፡ መቼም እውነቱ ይሄ ከሆነ ስቄም አላባራ! ይሄን ኩሩ ህዝብ የመምራት አደራ የተሰጠው መንግስት፣ እንዴት ከአንድ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ድርጅት ጋር እልህ ውስጥ ይገባል? (ማን ነበር “ለጠብም እኩያ ያስፈልጋል” ያለው?)  ከቃለምልልሱ ውስጥ ብዙ ጋዜጠኞችን ግራ ያጋባው ነገር ምን  መሰላችሁ? የአንደኛው ማህበር ፕሬዚዳንት ስንት አባላት እንዳላቸው ሲጠየቁ “700 አባላት አሉን” ያሉት ነገር ነው፡፡ (የህዝብ ግንኙነቶችም አባል ናቸው እንዴ?)
እኔ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ብሆን ኖሮ የማህበራቱን መሪዎች “ጋዜጠኛ ለሚለው ቃል ፍቺያችሁ ምንድነው?” ብዬ እጠይቃቸው ነበር፡፡ ልክ ነዋ --- በፍቺው ካልተስማማን እኮ አንግባባም፡፡ እኔ የምለው --- የማህበራቱ መሪዎች በቃለምልልሳቸው  “ኢትዮጵያ ውስጥ አንድም የታሰረ ጋዜጠኛ የለም” (ይቅርታ “በሙያው ሳቢያ ነው” ያሉት!) ብለዋል---አይደል? ባለፈው የአፍሪካ ሚዲያ ፎረም መጠናቀቂያ ላይ በሰጡት የጋራ  መግለጫ ደግሞ “የፕሬስ ነፃነት ከየትኛውም የአፍሪካ አገር በተሻለ መልኩ በአገራችን  ተከብሯል” ማለታቸው አይዘነጋም - ኢህአዴግ ቢስቅባቸውም፡፡ ግን ግዴለም እነሱ እንዳሉት ይሁንና “እሺ ተከብሯል!” እንበላቸው፡፡ ታዲያ እነሱ እዚህ አገር ምን ይሰራሉ? ምናልባት ኢህአዴግን አያምኑት ይሆናል፡፡ እንዴት አትሉም --- አሳቻ ጊዜ ጠብቆ  የፕሬስ ነፃነት  መልሶ እንዳይነጥቀን ይሰጉ ይሆናላ! (እንኳን እነሱ እኛም አንሰጋ!)
እናላችሁ --- ማህበራቱ ደጋግመው እንደነገሩን ----  ጦቢያ  ጋዜጠኛ የማይሰደድባት፣የማይዋከብባት፣ የማይታሰርባትና እንዳሻው በነፃነት የሚፅፍባት የዲሞክራሲ አገር ናት ብለን እንመንላቸው፡፡ እንዲያ ከሆነ ደግሞ ---- የጋዜጠኞች መብት “ተሟጋች ነን” ለሚሉ ማህበራት ብዙም ሥራ የለም ማለት ነው። (ለአንድም ጋዜጠኛ ተከራክረናል አላሉማ!) እናም ለእነዚህ ማህበራት ምን አሰብኩላቸው መሰላችሁ? እዚህ ሥራ ከሚፈቱ ለምን ወደ ጎረቤት አገራት --- ለምሳሌ ደቡብ ሱዳንና ሶማሊያ ተሻግረው የጀማሪዎቹን አገራት የጋዜጠኞች መብት አያስከብሩም  አልኩ፡፡ ተንኮል አስቤ ግን  እንዳይመስላችሁ፡፡ ለእነሱው አስቤ ነው (ለወገን ማሰብ አይቻልም እንዴ?) አያችሁ --- ወደ ጎረቤት አገር ሄደው ሲንቀሳቀሱ እግረመንገዳቸውንም የራሳቸውንና የማህበራቸውን ሲቪ ያበለፅጉታል - ከ“ሎካል” የጋዜጠኞች ማህበርነት ወደ አህጉራዊ የጋዜጠኞች ማህበርነት ያድጋሉ (“ያልተገላበጠ ያራል” አሉ!) ብልጥ ከሆኑና  ከበረቱ ደግሞ ዓለም አቀፍ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ከመሆን የሚያግዳቸው ነገር የለም፡፡ (“ዘ ስካይ ኢዝ ዘ ሊሚት” አለ ፈረንጅ!) እናም--- ቀስ በቀስ የኒውዮርኩን ሲፒጄ ሊገለብጡት ይችላሉ፡፡ (የጋዜጠኞች ማህበር ኩዴታ ተከልክሏል እንዴ?) ይሄ ከተሳካላቸው እኮ --- ኢህአዴግም ጋዜጠኞችን በማሰርና በማሰቃየት በእነሲፒጄ እና አምነስቲ ኢንተርናሽናል ከመወቀስና  ከመወንጀል ዳነ ማለት ነው፡፡ እዚያ ሳይደርሱ ግን  ሲፒጄ ስለኢትዮጵያ አያገባውም ማለት ብዙም ውሃ አያነሳም፡፡ አያችሁ ---- ማህበራቱ እንዲህ ቢዚ ከሆኑ  “ሲፒጄ የወሮበሎች ቡድን ነው” ምናምን እያሉ ለመዝለፍ ጊዜም አይኖራቸው። (“ዘለፋ ለአገር ገፅ ግንባታ ወሳኝ ነው” የሚል ጥናት ወጣ እንዴ?)  
አሁን ደግሞ እስቲ ወደ አውራው ፓርቲያችን እንመለስ (ዞሮ ዞሮ ወደ እናት ክፍል አሉ!) እኔ የምለው …ኢህአዴግ አልፎ አልፎ የሚያሳያቸው ድንገተኛ  ለውጦች አያስገርማችሁም? (“23 ዓመት ሙሉ የት ነበር”  ያስብላል እኮ!) ሆኖም ፈዝዞና ደንዝዞ ከመቅረት መነቃቃት ይሻላልና “ጐሽ … አበጀህ!” ነው የምንለው። እስቲ አስቡት ---- ቪኦኤንና የማይጥሙትን ድረ-ገፆች ይዘጋል ወይም ጃም ያደርጋል እየተባለ ሲታማ የከረመው አውራው ፓርቲ ድንገት ተነስቶ የሶሻል ሚዲያ አቀንቃኝ ሲሆን! የማይታመን ቢመስልም እውነት ነው። ኢህአዴግ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ፊቱን ወደ ድረገፆችና ፌስቡክ ያዞረ ይመስላል፡፡    (የግሎባላይዜሽን ተፅእኖ ነው ወይስ አማራጭ ማጣት?) የሆኖ ሆኖ በቅርቡ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ሃላፊ ሆነው የተሾሙት (በሚኒስትርነት ማዕረግ መሆኑን ልብ በሉ!) አቶ ሬድዋን ሁሴን ሰሞኑን እንደተናገሩት፤ የመንግስት መ/ቤቶች ስለሚያከናውኗቸው ስራዎች ትክክለኛውን መረጃ በድረገጾቻቸው ማሰራጨትና ወቅታዊ ማድረግ ይኖርባቸዋል (ሳይነገራቸው አይሰሩም ማለት ነው!) ሃላፊውም አክለውም መ/ቤቶቻቸውንና ሥራቸውን  ፌስ ቡክን በመሳሰሉ ሶሻል ሚዲያዎች ላይ በንቃት ማስተዋወቅ እንዳለባቸው አሳስበዋል (ሕዝብ ግንኙነቶች “ነብር አየኝ” ይበሉ!) ሚኒስትሮችም ቢሆኑ  እንደ ውጭ ጉዳይ ሚ/ሩ ቴዎድሮስ አድሃኖም፤ ንቁ የፌስቡክ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ኢህአዴግ “ግሪን ላይት” አሳይቷል የሚል መረጃ ደርሶኛል፡፡ ኢህአዴግ የቴክኖሎጂ “ጋግርቱ” ካልተነሳበትና በዚሁ “ሙድ” ከቀጠለ የ2007 አገራዊ ምርጫ ቅስቀሳ ቤት ለቤት ወይም በፈንዲሻ መሆኑ ቀርቶ በፌስቡክ ይሆናል ማለት ነው - በ21ኛው ክ/ዘመን ቴክኖሎጂ!  አንድ ወዳጄ --- የኢህአዴግ ወጣት አባላትም በፌስቡክ ፖለቲካዊ ሃሳባቸውን መግለፅና  በአንዳንድ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ላይ “ሙድ” መያዝ እንደጀመሩ ሲነግረኝ፣እንደ ሥልጣኔ ምልክት ቆጥሬው ደስ አለኝ፡፡ እሱ ግን ሃሳብ ሲያልቅባቸውና የተሸነፉ ሲመስላቸው “የባለቤቱ ልጅ ነን” በሚል ወደ ማስፈራራት እንዳይገቡ እፈራለሁ ሲል ስጋቱን ገለፀልኝ፡፡ ስጋቱን ብጋራውም እምብዛም የሚያሳስብ  አይመስለኝም፡፡ (ማስፈራራት የሰለጠነ ሰው ምግባር አይደለማ!)
እስቲ ለአፍታ ደግሞ ወደ ደቡብ አሜሪካ ልውሰዳችሁና--- በአርጀንቲና ለ15 ቀን በተከሰተ የኤሌክትሪክ ሃይል መቋረጥ ሳቢያ የተፈጠረውን ረብሻ፣ የጐዳና ላይ “ነውጥ”፣ ዝርፊያና ማህበራዊ ምስቅልቅል ላስቃኛችሁ፡፡ (የእኛ አገር መብራት ስንት ዓመት እንደተቋረጠ ቢሰሙ አርፈው ይቀመጡ ነበር!) ለነገሩ አርጀንቲናውያን በአሁኑ ወቅት ችግር ጓዙን ሁሉ ጠቅልሎ እላያቸው ላይ የከተመባቸው ነው የሚመስሉት፡፡ እስቲ አስቡት … የአገሪቱ የሙቀት መጠን ከ40 ዲግሪ ሴንቲግሬድ በላይ በመሆኑ ህዝቡን አላስቆም አላስቀምጥ ብሎታል፡፡ በዚያ ላይ ይሄን ሙቀት የሚያበርዱበት ውሃ የላቸውም፡፡ የውሃ ፓምፓቸው እንደኛ አገር በኤሌክትሪክ ሃይል የሚሰራ በመሆኑ ውሃውም ከመብራቱ ጋር ጠፍቷል፡፡
እናም በዚህ ሰበብ -- በአርጀንቲና መዲና ቦነስ አይረስና በግራን ቦነስ አይረስ ከተማ ረብሻ፣ ተቃውሞና በጠራራ ፀሃይ የሚፈፀም ዘረፋ --- የዕለት ተዕለት ተግባር ሆኗል፡፡ (ሙቀቱ ብቻውን እኮ አቅል ያስታል!) የሚገርማችሁ ደግሞ ለችግሩ መፍትሔ ከመዘየድ ይልቅ የአገሪቱ መሪዎች እርስ በእርስ መናቆር ይዘዋል። የኤሌክትሪክ መቋረጡን በተመለከተም የአርጀንቲና መንግስት በሃይል ማመንጨት ስራ ላይ የተሰማሩ ኩባንያዎችን ተጠያቂ ያደረገ ሲሆን ኩባንያዎቹ ደግሞ ጥፋቱ የመንግስት ነው ባይ ናቸው፡፡ (“የፉክክር ቤት ሳይዘጋ ያድራል” አሉ!) ኤድኖር እና ኤድሰር የተባሉት የኤሌክትሪክ ኃይል ኩባንያዎች እንደሚሉት፤ ባለፉት 20 ዓመታት መንግስት የኤሌክትሪክ መስመሮችን ባለማደሱና በአገሪቱ የኤሌክትሪክ ሃይል ላይ ኢንቨስት ባለማድረጉ የተከሰተ ችግር ነው፡፡ እኔ የምላችሁ … የአገራችን ኤልፓ ስለመብራት መቆራረጡ ሲደረድርልን የነበረውን ሰበብ ከውጭ አገር ነው እንዴ የቀዳው? (እንደ ፀረ-ሽብር ህጉ ማለቴ ነው!)  የኃይል መቋረጡን በተመለከተ የአርጀንቲና ኩባንያዎች ያሉትን ስሙልኝ -
“የሃይል እጥረት የለብንም፤ ችግሩ የውስጥ ለውስጥ መገናኛ መስመሮች ማርጀትና ከአገልግሎት ውጭ መሆን ነው” (ቁጭ የኤልፓ መግለጫ!) እንግዲህ ወይ አርጀንቲና ከእኛ ቀድታለች አሊያም  እኛ ከሆነ አገር “ቃል በቃል” ቀድተነዋል ማለት ነው (የራሳችንን ሰበብ እንኳ መፍጠር ያቅተን?)
ሌላው የሚያስገርመው ደግሞ ምን መሰላችሁ? የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ክርስቲና ፈርናንዲዝ ህዝባቸው በዚህ ሁሉ ችግር ውስጥ ሲዳክር ድምፃቸውን ማጥፋታቸው ነው፡፡ መረጃዎች እንደሚሉት፤ ፕሬዚዳንቷ እስካሁን በኃይል መቋረጡ ዙሪያ ትንፍሽ ያሉት ነገር የለም፡፡ (የእኛዎቹ እኮ እውነት አይናገሩም እንጂ ድምፃቸውን አጥፍተውብን አያውቁም!) ይገርማችኋል … የአርጀንቲናዋ መሪ ህዝባቸው ከ40 ድግሪ ሴንቲግሬድ በላይ በሆነ ሙቀት ሲነፍር፣ እሳቸው ግን ቀዝቀዝ ያለ አየር በሚነፍስባት የኢል ካላፋቴ ግዛት ውስጥ ከሃይቅ ዳርቻ በታነፀው መኖርያ ቤታቸው ውስጥ የሰላም እንቅልፋቸውን እያጣጣሙ ነው፡፡ (አላይም አልሰማም ብለው!)
ሌላው ቀርቶ የተለመደውን የገና በዓል “የእንኳን አደረሳችሁ” መልዕክት እንኳን ለህዝባቸው አላስተላለፉም (ይሄ ታዲያ ፍራቻ ነው ጥላቻ?) አርጀንቲናውያን ግን አሁንም ሻማና የታሸገ ውሃ ከሱቅ እየገዙ በረብሻ፣ በተቃውሞና በዘረፋ ኑሮአቸውን እየገፉ ነው ተብሏል፡፡ መብራትና ውሃ የሚመጡበት ጊዜ “እንደ ኢየሱስ መምጫ” አልታወቅም ተብሏል (አንድዬ ይሁናቸዋ!) እኔ የምለው ግን … የኢትዮጵያ መብራት ኃይል ኮርፖሬሽን ለአርጀንቲና የኤሌክትሪክ ኃይል ለመሸጥ አላሰበም እንዴ? (አያስብም አይባል እኮ!) መልካም የገና በዓል ይሁንላችሁ!

Read 3589 times