Sunday, 05 January 2014 00:00

“እንቆቅልሽ --- ጧት ታይቶ ከሰዓት በኋላ የሚጠፋ?”

Written by  ብዕር ጂ.
Rate this item
(6 votes)

          ከሁለት ሣምንት በፊት ከአንድ ወዳጄ ጋር ቀጠሮ ነበረኝ፡፡ ለወትሮው የቀጠሮ ሰዓት መሸራረፍ የማይወደው ወዳጄ፣ በ “የሀበሻ ቀጠሮ” ልማድ ላይ አዘውትሮ ጣቱን የሚቀስረው ባልንጀራዬ ከተቀጣጠርንበት ቦታ በሰዓቱ መድረስ አልቻለም፡፡
በርግጥ እኔም አሥር ደቂቃ አሣልፌ ነበር ከቦታው የደረስኩት፡፡ በቀጠሮ ሰዓት የማያወላዳው ባልንጀራዬ እንደዓመሉ፣ በኋላቀር የቀጠሮ ሰዓት ልማዴና አመለካከቴ እያላገጠ፣ የወግ መጀመሪያ ያደርገኛል ብዬ እራሴን እያዘጋጀሁ ብመጣም፣ ከቀጠሮው ቦታ አላገኘሁትም። ቀድሜ በመድረሴ ከፉተታው ብድንም ባልተለመደ መልኩ መኪናውን በአካባቢው ሳጣት ሃሳብ ውስጥ መግባቴ አልቀረም፡፡ ተንቀሳቃሽ ሥልኬን አውጥቼ ልደውልለት አልኩና “አሁን እየነዳ ሊሆን ይችላል” ብዬ ለተጨማሪ አሥር ደቂቃዎች መታገስ ግድ አለኝ፡፡
አስር ደቂቃዎች አለፉ፡፡ ስልክ ደወልኩ - አይነሣም። አሁን ትንሽ መደናገጥ ጀመርኩ፡፡ ባልንጀራዬ በጤናው ከግማሽ ሰዓት በላይ አይዘገይም፡፡ የስልኩ በተደጋጋሚ አለመነሳት ደግሞ ድንጋጤዬን እየጨመረው መጣ፡፡ ምንም እንኳ የትራፊኩ መጨናነቅ የመዲናችን የየዕለት ግብር ቢሆንም፣ ባልንጀራዬ ወደቀጠሮ ቦታው የመምጫ ጊዜውን አስረዝሞ፣ ቀድሞ ለመነሳት ይሞክራል እንጂ በምንም መልኩ የመዘግየት ልማድ የለውም፡፡ እርሱም፣ በቀጠሮ ሰዓት ላለመገኘት የሚቀርብን ምንም አይነት ሰበብ አይቀበልም፡፡
በትራፊክ መጨናነቅ፣ በታክሲ ወረፋ ወይም በሌሎች ማኅበራዊ እክሎች ጦስ ሳቢያ የሚፈጠር  የቀጠሮ መዘግየት እንዳለ ቢያምንም፣ “ቀድሞ በመነሳት ማካካስ ይቻላል” የሚል ቆራጥ “አብዮታዊ”ም በሉት “ልማታዊ” አቋም ነው የሚያራምደው፡፡ በተለያዩ የፊልም፣ የመጻሕፍት፣… … ምረቃ ላይ በተለይ የክብር እንግዳ በመጠበቅ የምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ከተባለው ጊዜ ሲዘገይ፣ አሥር ደቂቃ ጠብቆ ጥሎ ሲሄድ በተደጋጋሚ ስላየሁ፣ ይህን የቀጠሮ ሰዓት አስከባሪ አርበኛ  በድንገት ያውም ከግማሽ ሰዓት በላይ ሲዘገይ፣ ብደነግጥ ይፈረድብኛል?
ከክብደቴ ላይ ኪሎ ሥጋ ቀንሼ ከወዲያ ወዲህ ሥንቆራጠጥ፣ የባልንጀራዬን መኪና የምትመስል ተሽከርካሪ በርቀት ስትመጣ አየሁ፡፡ መኪናዋ እኔ ወዳለሁበት አካባቢ ስትቀርብ ሌላ እንደሆነች አረጋገጥኩ። ለአሥረኛ ጊዜ ይመስለኛል እየደወልኩ አልነሳ ያለው ስልክ፣ በመጨረሻ ተነሣና ምላሽ ሣይሰማ ተዘጋ። ባልንጀራዬ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እንደሆነ ወይም እየነዳ እንዳለ ጠረጠርኩ፡፡ ቀጠሮ የያዝንበት ጉዳይ ብርቱ መሆኑ ብቻ ሳይሆን፣ ባለ ጉዳዩም በዋናነት እርሱ ስለነበረ እንደማይቀር አውቃለሁ፡፡ የባልንጀራዬን  መጥፎ ዜና እንዳያሰማኝ ከአምላኬ ጋር መደራደሬ አልቀረም፡፡ በሰላም ያገናኘን እንጂ፣ ሥዘገይበት እርሡ የሚፈጥረውን ቡራከረዮ እኔ እንደማልደግመው፣ ለአምላኬም ለራሴም ቃል እስከመግባት ደረስኩ፡፡ “የጨነቀው እርጉዝ ያገባል” የሚባለው ምሣሌያዊ አነጋገር እንደዛሬ በተግባር ተተርጉሞብኝ የሚያውቅ አልመሰለኝም፡፡
በዚህ ሁኔታ ውስጥ እያለሁ፣ የባልንጀራዬ መኪና አጠገቤ መድረሷን ልብ ሳልል ብቀርም፣ ከኋላዬ ሲጠራኝ ግን አልደነገጥኩም፡፡ እንደውም ያላሰብኩት ንዴት ተናነቀኝ፡፡ “አንተ በአሥር ደቂቃ እያበድክ እንዴት ከአንድ ሰዓት በላይ ዘግይተህ ትመጣለህ? ለምንስ ስልክ አታነሣም?” እያልኩ ሳቅራራ፣ ባልንጀራዬ መኪናውን  ቦታ ለማስያዝ ወደ ኋላ እየነዳ ነበረ፡፡ እርሱ አይቶኛል ቦታ ይለቅልኛል ሲል፣ እኔም አይቶኛል ብዬ ዞሬ ስሳደብ መኪናዋ ለካ ወደ ቆምኩበት አቅጣጫ እየመጣች አጠገቤ ደርሳለች፤ በአካባቢው ያሉ ሰዎች ሲጮሁ፣ መኪናዋ እግሬ ሥር ስትቆም አንድ ሆነ፡፡
ከዚህ በኋላ ምን ሊፈጠር እንደሚችል የምትገምቱ ይመስለኛል፡፡ እኔ ከመበሳጨቴ የተነሣ የምናገረውን ሁሉ አላውቅም ነበረ፡፡ ባልንጀራዬ ከመዘግየቱ፣ ሊገጨኝ መቃተቱ የበለጠ አሳፈረው፤ ሲናደድና ሲደንግጥ ምንም መናገር የማይችል “ዝጋታም” የሚባል አይነት ሰው ነው፡፡ እንደምንም ተረጋግተን ስንነጋገር፣ ባልንጀራዬ ለመዘግየት ያበቃውን ምክንያት እየመረረውም ቢሆን ያስረዳኝ ጀመር። ምሣ ለመብላት መኪናውን ውጭ ላይ አቁሞ ወደ ሆቴል አመራ፡፡ ሰዓቱ 7፡30 ላይ እንደነበር ያስታውሳል፡፡ ሆቴሉ ከአንድ ዋና መንገድ ተገንጥሎ በሚገባ አገናኝ መንገድ ዳር የሚገኝ ቢሆንም፣ መንደር ውስጥ ሊባል የሚችል ነው፤ ሰፈሩ ደግሞ፤ ቦሌ ሩዋንዳ አካባቢ፡፡ ባልንጀራዬ 9፡00 ካዛንቺስ ላይ ቀጠሮ እንዳለው ስላወቀ፣ በእርሱ አገላለጽ ምሣውን፣ “ቷቷ…አድርጐ” ሒሣብ ከፍሎ፣ ከሆቴሉ ወጣና  ወደ መኪናው አመራ፡፡ መኪናውን ተዟዙሮ ገላመጣት፡፡ በሰላም ነበር የጠበቀችው፡፡ አስነስቶ ወደ ዋናው መንገድ የሚያወጣውን ብቸኛ የውስጥ ለውስጥ መንገድ ተያያዘው፡፡ ከዋናው መንገድ ጋ ሊደርስ ሲል ሰዓት ተመለከተ፡፡ ግማሽ ሰዓት ብቻ ነው የፈጀው፡፡ ኮራ ብሎ፣ ቀስ ብሎ እየነዳ 9፡00 ቀጠሮው ቦታ መድረስ እንደሚችል እያሰበ ወደፊት ሲመለከት፣  ብቸኛው የየውስጥ ለውስጥ መንገድ ጫፉ ላይ “በግሬደር” ገደል ሆኖ አገኘው፡፡  
መኪናውን ወደ ዳር አቁሞ፣ ምን እየተሠራ እንዳለ የሚመለከተውን ለማነጋገር በእግሩ ሄደ፡፡ ከፊት ለፊቱ ያለው ቱቦ ከተቀበረ በኋላ ጉዱጓዱ ተደፍኖ እንደሚያልፍ ተነገረው፡፡ “አሁን ሣልፍ እኮ ደህና ነበረ፤ ቢያንስ የመኪና ማለፊያ ከጫፍ በኩል ትንሽ ቦታ ለምን አልተዋችሁም?” ለሚለው አሳዛኝ ጥያቄ የቀረበለት የማስተዛዘኛ ማስመስል አልነበረም፡፡ አንድ በወጉ የማይናገር ሃላፊ ነገር፣ “ሰውዬ እንሥራበት አትረብሽ! ሁለት ሰዓት መታገሥ ያቅትሃል?...እንዴት እንደምንሠራ አንተ አትነግረንም…መኪናህን ትተሀት ሂድ፤ ያንተን መኪና ማን ይነካል…” የሚሉ የሚያበሣጩ የቃላት ጥይቶች አዘነበበት፡፡
ባልንጀራዬ በወጉ ከማያውቀው ሰፈር መኪናውን አቁሞ፣ ከግማሽ ሰዓት በላይ ሲከራከር ከቆየ በኋላ 8፡30 አካባቢ በታክሲ ወደ ቀጠሮው ለመምጣት እንደሞከረ ነገረኝ፡፡ ሁኔታውን ለማሳወቅ ተንቀሳቃሽ ሥልኩን ከኪሦቹ ውስጥ ሲፈልግ አጣው፡፡ መኪና ውስጥ አስቀምጦት መውረዱ ትዝ አለውና ወደ ቆመችው መኪናው አመራ፡፡ የመኪናው በር አልተዘጋም፤ ሣይዘጋው ይውረድ ወይም በአንዳች ተአምር ይከፈት እስከ ዛሬም አልታወቀም፡፡ ብቻ ተንቀሣቃሽ ስልኩ ከመኪናው ውስጥ ተሠወረ፡፡ ሲጨንቀው ወደ ሆቴሉ ሄደ፡፡ የእርሡን ሞባይል የበላ ጅብ እንዳላዩ አረዱት፡፡ ሥልኩ ላይ እንዲደውሉለት አደረገ፡፡ ሞባይሉ ይጠራል። ሞባይሉ ከጅብ አፍ እንዳልገባ ተሥፋ ተደረገ፡፡ መኪናውን አገለብጦ እንዲፈትሽም ተመከረ። የተባለውን ሁሉ አደረገ፡፡ ሞባይሉ ግን እስከ ዛሬም እንዳልተገኘ አውቃለሁ፡፡
ከአንድ ሰዓት በኋላ የተቆፈረው መንገድ ቱቦው ተቀብሮ ተጠናቀቀና በጐን በኩል እንዲያልፍ ተነገረው። መኪናው፣ አዲስ የተደፈነውን ጉድጓድ በማለፍ ታሪክ ብትሠራም፣ በቀጠሮው ሰዓት መድረስ አልቻለችም፡፡ ይኼን ሁሉ ጉድ አሣልፎ የመጣው ቀጠሮ አስከባሪው አርበኛ ባልንጀራዬ፣ ቀጠሮ ቦታው ከመድረሱ እኔንም ወደ ሞት አፋፍ ሊያደርሠኝ ነበር፡፡
በመጨረሻ፣ ጓደኛዬና እኔ ተረጋግተን ወሬ ሥንጀምር፣ ያጋጠመውን ነገር ከመጀመሪያው እስከ መጨረሻ ሣይደብቅ ሊነግረኝ ቃል ገባ፡፡ ወዲያው ትንሽ እረፍት ወሠደና ፈገግ አለ፡፡ የነበርንበትን ቀዝቃዛ ድባብ የቀየረው ግን በድንገት “እንቆቅልሽ?” ሲለኝ ነበረ፡፡ በሁኔታው ተገርሜ ሣቅሁ፡፡ እየሣቀ “እንቆቅልሽ?” አለኝ በድጋሚ፡፡ “የጨነቀው እርጉዝ ያገባል ማለትስ አሁን ነው … ምን አውቅልህ?” በማለት መለስኩለት፡፡ “ጧት ታይቶ ማታ የሚጠፋ ምንድን ነው?” አለኝ፤ ኮስተር ብዬ፡፡ “ቀሽም? አሪፍ እንቆቅልሽ እንኳን ብትጠይቀኝ ምን አለ?” ብዬ ከተኩራራሁ በኋላ፣ “ለመሆኑ ቀልዱን ብትተው ምን አለ? … ለማንኛውም ጤዛ” በማለት መለስኩለት፡፡ አገር እንድሠጠው ሲጠይቀኝ፣ “ምን አገር አለህን? አገር ቢኖረን መቼ እንዲህ እንሆን ነበረ …” ስለው ከትከት ብሎ ሣቀና፣ “ጧት ታይቶ ከሰዓት በኋላ የሚጠፋ … የአዲስ አበባ መንገድ ነው!” አለኝ፡፡
እውነትም ጧት ታይተው ከሰዓት የሚጠፉ መንገዶች…! የመንገዶች ባለሥልጣን በፊታውራሪነት፣ ቴሌኮም በቀኝ አዝማችነት፣ መብራት ኃይል በግራ አዝማችነት፣ ውኃና ፍሳሽ ደግሞ በደጅ አዝማችነት የአዲስ አበባን መንገዶች ወይም አስፋልቶች እንዳሻቸው ያሣርሷቸዋል፤ በፈረቃ ይቆፍሯቸዋል፤ በተናጠል ያፈርሷቸዋል … ለአዲስ አበባ መንገዶች ሠቆቃና ብሶት ሲባል፣ ፍሬ ሣይዘሩ የሚያርሷቸውን ተቋማት፣ ቅርስ ሣያውቁ የሚያፈርሷቸውን አካላት 1ለ4 “የሚያደራጃቸው” አርቆ አሣቢ መሪ እንዴት ይጥፋ!?

Read 3540 times