Sunday, 05 January 2014 00:00

ከሚመጣው ዓመት ዶሮ፣ ዕንቁላል ዘንድሮ!

Written by 
Rate this item
(9 votes)

አንዳንድ ተረቶች በሂደት የዕውነታ ትንቢት ይሆናሉ፡፡ ቻይናዎች ዛሬ የደረሱበት ሁኔታ በሚከተለው ተረታቸው ላይ የተመሠረተ ሳይሆን አልቀረም፡፡
እነሆ፡-  
አንድ የቻይና ሊቅ-አዋቂ፣ አንድ ቀን በተከሰተለት ራዕይ ላይ ተመሥርቶ እንዲህ የሚል ሀሳብ ለህ/ሰቡ ያቀርባል፡-  
“ጐበዝ በመጪው ዘመን የሚመጣው ውሃ የተበከለ ነው የሚሆነው፡፡ ስለዚህ ካሁኑ በእጃችሁ ያለውን ንፁህ ውሃ ብታከማቹ ደግ ነው፡፡ መጪው ውሃ ከቶም ጥራት ያለው ስለማይሆን በጊዜ ውሃችሁን አጠራቅሙ፡፡”
ይህን በየቦታው እየዞረ መስበኩን ቀጠለ፡፡
ከፊሉ፤
“አጭበርባሪ ነው፡፡ አዋቂ ነኝ በማለት አዲስ ነገር ለማስመሰል የቆመ ነው፡፡”
ግማሹ፤
“ጊዜው እያለፈ ሲሄድ ፈላስፋ ነን የሚሉ መምጣታቸው አይቀሬ ነው፤ ተውት አትስሙት” የሚል እሳቤ አቀረበ፡፡
አዋቂው ግን፤
“ግዴላችሁም እኔ እምላችሁን ስሙ፡፡ ስለ ውሃ የወደፊት ሁናቴ የሚጠቅማችሁ ይሄ እኔ የምላችሁ ነገር ነው” ማለቱን ቀጠሉ፡፡
ሰው ሁሉ አዋቂውን ናቀ፡፡ ዘለፈ፡፡
ስለሆነም፤ አሮጌውን ውሃ ትቶ አዲስ ውሃ መጠጣት ፈቀደ፡፡ ጠጣ ጠጣና ሰው ሁሉ አበደ!
ከማ/ሰቡ መካከል አንድ ሰው ግን፤ አዋቂው ያለውን ተቀብሎ ውሃ ማጠራቀም ጀመረ፡፡ ሆኖም፤ የሰው ሁሉ መሳቂያ መሳለቂያ ሆነ፡፡ “ዕብድ ነው!” ተባለ፡፡ ይብስ ብሎ ተቃዋሚ አፈራ፡፡ ተቃዋሚው በዛ በዛና አገሩ ሁሉ ተቃዋሚው ሆነ፡፡ በዚህም ምክንያት ሰው ሁሉ፤
“ይሄ ሰው ጤና ቢጐለው ነው እንጂ የዱሮ ውሃ አያጠራቅምም ነበር፤ እያለ ክፉኛ ወሬውን ነዛው”
ሰውዬው፤ ከነጭራሹ በህብረተሰቡ ተተፋ፡፡ ንክ ነው፣ ዕብድ ነው ተባለ! የሚጠጋውም ሆነ የሚያወራው ወዳጅ በማጣቱ ይጨነቅ፣ ይጠበብ ጀመር፡፡ ያበደ አገር፤ እሱን ዕብድ ነው እያለ አገለለው!
ስለዚህ ዋለ አደረና ተስፋ ሲቆርጥ ያጠራቀመውን ውሃ ሁሉ ደፋው፡፡ ከዚያም እንደሰው አዲሱን ውሃ መጠጣት ጀመረ፡፡ ይሄኔ አገሬው፤ “ይሄ ዕብድ ጤናው ተመለሰ፡፡ ደህና ሰው ሆነ!” እያለ እያወደሰው፣ ቀርቦ ያጫውተው ጀመር፡፡ ያ ዕብድ የተባለ ሰው ከአገር ተደባለቀ፡፡ ከዕድር ተዋሃደ፡፡ ካበደው አበደ፡፡ ነባሩን ጽዱ ውሃ ያጠራቀመ ሰው በአገሩ ባለመኖሩ፤ ሰው ሁሉ የተመረዘው፣ አዲስ ውሃ ሰለባ ሆነ!!
*    *    *
ከመንገደኝነት አስተሳሰብ ካልወጣን ንፁህ ውሃ አንጠጣም፡፡ በአንድ አሸንዳ የመፍሰስ አባዜ ለለውጥ አያዘጋጅም፡፡ የተለየ አስተሳሰብ ያላቸውን ወገኖች እህ ብለን ካላዳመጥን ለውጥ አናመጣም። ምክንያቱም፤ አንቻቻልምና ሰላም አይኖረንም፡፡ አንተራረምምና ከስህተት ክብ ቀለበት ለመውጣት አይቻለንም፡፡
ሀገራችን፤ ሁለመናቸው ዓይን ብቻ የሆኑ (እለ ኩለንታሆሙ መሉዐነ ዓእይንት እንዲል ግዕዙ) ሰዎች የሚያስፈልጓት ሰዓት ላይ ናት፡፡ ደራሲ ብርሃኑ ድንቄ በ “አልቦ ዘመድ” እንደገለፁት፤ “የኢትዮጵያን ታሪካዊ ባህል አስፋፍቶ ለማሳደግና መሠረቱንም ለማጠንከር የደከሙት፤ “እብነ ማዕዘንት” የሚባሉት አባቶች ሁሉ አልቀው፤ ዛሬ ኮረቶቹና ጠጠሮቹ መሠረት ነን እያሉ ሲፎክሩ መስማት ‘ትራጀዲ’ ብቻ አይባልም፡፡ ‘ኮሜዲም’ መሆን አለበት፡፡ ይህን ዝብርቅርቅ ሳስብ በማልቀስ ፈንታ አንዳንድ ጊዜ ያስቀኛል፡፡ ‘እንዳላለቅስ ብዬ በመፍራት ሁልጊዜ እስቃለሁ’ ብሎ የተናገረው ማነው?” ይሉናል። ጥቅሱ የፀሐፌ-ተውኔቱ የቦማርሼ ነው፡፡ አፍንጫችን ሥር ያለውንና የፊት የፊታችንን ብቻ ስንመለከት መሠረታችንን እንዳንስት በቅጡ ማስተዋል ይገባናል፡፡ መሠረቱ የላላ ህብረተሰብ የኋላ ኋላ፤ ራሱንም አጥቶ የሌላውንም መቀበል ሳይችል አየር ላይ ተንገዋሎ ይቀራል፡፡ ለጊዜው የሥልጣኔ የሚመስሉን፣ ከነስውር - ደባቸው ማንነታችንን ሊያጨነግፉ የሚባትቱ አያሌ መጤ የካፒታሊዝም ሳልባጅ አስተሳሰቦችን በጥንቃቄ ማየት አለብን፡፡ እነዚህን ትውልድ ሳንገነባ ልንታገላቸው አንችልም። የሚከተለው ቃል ትውልዳችንን ለማየት ይጠቅማልና እነሆ፡- “ያለፈውን ትውልድ የሚያደንቁበት፣ የዛሬውን ትውልድ የሚፈርዱበት ዋናው ምክንያት ምንድን ነው? …” ተብለው አንደኛው ገፀ - ባህሪ ይጠየቃሉ፡፡ ሌላው ሲመልስ -  
“በነዚህ ሁለት ቃላቶች ላይ የእኔን ምክንያቶች ተንጠልጥለው ያገኙዋቸዋል፡-
፩ መስዋዕትነት ፪ ራስን መውደድ፡፡ ያለፈው ትውልድ መስዋዕትነት ምን እንደሆነ ደህና አድርጎ ያውቃል፡፡ የዛሬው ትውልድ ደህና አድርጎ የተማረው ራስን መውደድ ነው!!” (አልቦ ዘመድ)
አንድ ትውልድ መስዋዕትን ሳያቅ ጥቅም እንደሚያገኝ ሲያስብ ሐሳቡ እንደጧት ጤዛ እየተነነ፣ የጨበጠው የመሰለውና ያዝኩት የሚለው ነገር ሁሉ እየበነነ፣ መንፈሰ - ባዶነት ስለሚያጠቃው፣ መቦዘን፣ መንገዋለልና የማናቸውም አዲስ ሀሳብ፣ አዲስ ግጭት ሰለባ የመሆን ዕድሉ ሰፊ ነው፡፡ ስለሆነም በብሔር-ብሔረሰቡም፣ በሃይማኖቱም፣ በፍልስፍናውም፣ በማህበራዊ ቀውሱም፣ እንዲያው ባገኘው ክስተት ውስጥ ሁሉ ጠብ-ያለሽ-በዳቦ ማለትን፣ ተንኳሽነትን፤ ሽፋጭነትን፣ ዘራፊነትን ያስተናግዳል። ሰከን፣ ጠንፈፍ ብሎ ስለማይቀመጥ ትግሉ ሁሉ ብትን ይሆናል፡፡ የመደራጀት፣ የመሰባሰብ የመወያየት፤ መላ ይጠፋበታል! ጊዜ ወስዶ የመብሰል ነገር ይሳነዋል፡፡ ኑሮ ያራውጠዋልና መንፈሱ እየባዘነ ያገኘውን ሁሉ ቀጨም የማድረግ ፈሊጥን ብቻ ያዘወትራል፡፡ የበለጠ ከሥሩ ይነቀላል። ንቀትን እንደዕውቀት ምንጭ ስለሚይዝ፤ ሁሉን ነገር በቅድመ-ፍርድ (bias) ወስኖ፤ አዕምሮውን ዘግቶ፣ ፋይሉን ወደ መዝገብ ቤት መልሶ፣ ስለሚቀመጥ የመለወጥ ዝግጁነት ከቶ ያጣል፡፡ ስለሆነም ከጥቅም ማጋበስ ውጪ የሚታየው ነገር አይኖርም፡፡ በአፉ ይራገማል፣ ድርጊቱን ግን ራሱ ሲፈፅመው ይታያል፡፡ የህ/ሰብ ዝቅጠት (degeneration) ምልክት ነው፡፡ የንቅዘት (decadence) መገለጫው ነው፡፡ ከዚህ ሁሉ ባሻገር ደግሞ የአንጎላችን ባዶነት ሳያንስ፣ በድህነታችን ጥልቀት ሳቢያ ሆዳችን ባዶ ሆኖ ሲጮህብን፣ ጉሮሮአችን ደርቆ ሲሰነጣጠቅብን ዓመት በዓል ሲመጣብን፣ ሌማታችን ባዶ ሲሆን፣ ህይወት የምሬት ሬት ወደመሆን ያመራና፤ ዕቅዱ፣ ራዕዩ፣ ስትራቴጂው፣ ታክቲኩ፣ ፖለቲኩ፣ ምርምሩ ሁሉ፤ ይቀርና ከልቡናችንም ይፋቅና፣ ይጠፋና፤ “ነገ ነዳጅ ሊወጣ ነው”፣ “ተቆፍሮ ወርቅ ሊፈልቅ ነው” ቢባል፣ “ከሚመጣው ዓመት ዶሮ፣ ዕንቁላል ዘንድሮ!” ማለት ብቻ ይሆናል ቋንቋችን! ለማንኛውም መልካም የገና (“ገ” ጠብቆም ላልቶም) በዓል ይሁንልን!!
እንኳን ለልደት በዓል አደረሳችሁ!

Read 3852 times