Sunday, 05 January 2014 00:00

ያለከልካይ በጦርነት የመፋጀት አፍሪካዊ ቱባ ባህል ተበርዟል

Written by 
Rate this item
(8 votes)

          የአፍሪካ ነባር ባህል፣ ባለፉት 25 አመታት ምን ያህል እንደተረዘ በግልፅ አየነው - በደቡብ ሱዳን። ተቀናቃኞቹ ወገኖች፣ ገና ተኩስ ከመጀመራቸው፣ በጦርነት የመቀጠል ፋታ አልተሰጣቸውም። በቃ፣ በድንበር መዋጋት ወይም እርስበርስ እንደልብ መፋጀት ከእንግዲህ ለአፍሪካዊያን አይፈቀድም ማለት ነው?
ድሮኮ እንዲህ አልነበረም። ግጭትን ከትውልድ ትውልድ ማውረስና ማሸጋገር የለመደ አህጉር፣ አሁን ጦርነት ተከልክሎ ምን ሊውጠው ነው? ቢያንስ ቢያንስ፣ አስር አመት ወይም ሃያ አመት መዋጋት ለአፍሪካ ብርቅ አልነበረም፡፡ ኢትዮጵያ፣ አንጎላ፣ ሞዛምቢክ፣ ደቡብ አፍሪካ... እና ሌሎች ከደርዘን የሚበልጡ የአፍሪካ አገራትን መጥቀስ ይቻላል። አይገርምም? ዛሬ ከሶማሊያና ከኮንጎ በስተቀር፣ የያኔዎቹ የጦርነት አውድማዎች ከሞላ ጎደል ሰላም አግኝተዋል። የብዙዎቹ አገራት የእርስ በርስ ጦርነት እየከሰመ ጠፍቷል ወይም ረግቧል። በአንዱ ወይም በሌላው አገር አዲስ ግጭት ስንለኩስም፣ በጦርነት በርካታ ወራትና አመታት ሳይቆጠሩ ፍጅቱን በአጭሩ ለመቅጨት መሯሯጥ ተለምዷል።
አሁን አሁንማ፣ ፈፅሞ ለጦርነት ጊዜ የሚሰጠን ሰው እየጠፋ ነው። ደቡብ ሱዳንን ተመልከቱ። ለአዲስ ጦርነት የተነሳሱት ባላንጣዎች፤ የአንድ ሳምንት የውጊያ ጊዜ እንኳ አላገኙም። ከግራና ከቀኝ፣ ከጎረቤትና ከሩቅ፣ ከጓዳና ከአደባባይ... አለም ሁሉ “ተረጋጉ፣ እረፉ፣ አደብ ግዙ” እያለ ዘመተባቸው። “ጦርነት ካልቆመ እመጣላችኋለሁ” የሚል ማስፈራሪያ ከሰነዘረችው ከኡጋንዳ ጀምሮ እስከ አሜሪካ፣ ከአፍሪካ ህብረት እስከ ዩኤን፣ ከኢትዮጵያ እስከ ቻይና፣ ከኢጋድ እስከ አውሮፓ፣ በግልና በቡድን ድምፁን ያላሰማ የለም ማለት ይቻላል። እንደየዝንባሌው፣ ገሚሱ ሸምጋይና አደራዳሪ፣ አንዳንዱ ተቆጪና መካሪ፣ ሌላኛው ገላጋይና ሰላም አስከባሪ እየሆነ፣  አለማቀፉ ማህበረሰብ (አዳሜ በሙሉ) ከየአቅጣጫው ሲያጣድፋቸው፣ ደቡብ ሱዳኖች ሳይደነግጡ አይቀሩም።
በቃ፣ “እንደልብ መዋጋትና እድሜ ልክ መፋጀት ድሮ ቀረ!” ልንል ነው? ድሮ ድሮኮ፣ አፍሪካዊያን እንዳሻቸው በጦርነት ቢፋጁ ከልካይ አልነበራቸውም። ደግሞም አይገርምም። በብዙ የአፍሪካ አገራት፣ የአንዱ ጎሳ ተወላጆች፣ በሌላ ጎሳ ተወላጆች ላይ እየዘመቱ፣ ከብት መዝረፍና መንደር ማቃጠል፣ አካል መቁረጥና በጅምላ መግደል፣ ከጥንት ጀምሮ የተለመደ ነባር ባህል ነው። ስሙን እናሳምረው ካልን፣ “ቱባ ባህል” ልንለው እንችላለን - ለረዥም ዘመን ዛይበረዝና ሳይከለስ የዘለቀ! ጥንታዊው የጎሳ ዘመቻ፣ በሃያኛው ክፍለዘመንም ቢሆን፣ ከዘመኑ አኗኗር ጋር መልኩ ቢቀየርም ጨርሶ አልቀነሰም። እንዲያውም ይበልጥ ሲጧጧፍና ዘግናኝነቱ ሲብስበት ነው ያየነው። በቋንቋና በብሄረሰብ ወይም በፖለቲካ ድርጅት ተቧድኖ መጨፋጨፍ፣ የአፍሪካ መለያ ባህርይ እስከመሆን የደረሰው በ20ኛው ክፍለዘመን አይደል?
ኢትዮጵያ ውስጥ በእርስበርስ ጦርነት ከ150 ሺ ሰው በላይ፣ በኢትዮኤርትራ የድንበር ጦርነትም ከ70 ሺ ሰው በላይ አልቋል። በላይቤሪያ የሰባት አመታት ጦርነትም እንዲሁ 150 ሺ ሰው ሞቷል። የአፍሪካውያን የጦርነት ሱስና የፍጅት ባህል ባይቀየርም፤ ፍጅቱ እየበዛ የመጣው አለምክንያት አይደለም። ዛሬ በዘመናችን፣ እንደጥንቱ በጎራዴና በጦር ሳይሆን፣ በክላሺንኮቭና በታንክ ነው የሚጨፋጨፉት። አንጎላዊያን ለሃያ አመታት ባካሄዱት የእርስ በርስ ጦርነት፣ የግማሽ ሚሊዮን ሰዎች ህይወት ጠፍቷል። በሱዳን የዳርፉር ግዛት፣ በሁለት አመታት ግጭት ሰበብ ሁለት መቶ ሺ ሰዎች ሞተዋል። በሴራሊዮንም እንዲሁ፣ ከሞተው ህዝብ የማይተናነስ ቁጥር ያላቸው ሰዎች፣ በጭካኔ እጃቸው ተቆርጧል።
ታዲያ፣ ያ ሁሉ ሰው ያለቀው፣ “ሕዝቡን ከቅኝ ግዛት ነፃ አውጥተናል” በሚሉ ሶሻሊስት መሪ፣ ወይም “ሕዝቡን ከአምባገነን መሪዎች ነፃ እናወጣለን” በሚሉ ሶሻሊስት አማፂዎችና አገር ወዳድ አርበኞች አማካኝነት ነው። እርስ በርስ ሲጨፋጨፉ፣ “አለማቀፉ ማህበረሰብ” ምን ይሰራ ነበር ትሉ ይሆናል። አንዳንዱ፣ በእሳት ላይ ቤንዚን በማርከፍከፍ ጦርነቱን ያባብሳል። አንዳንዱ፣ “እንደፍጥርጥራቸው” ብሎ አይቶ እንዳላየ ኑሮውን ይቀጥላል። ነገር ግን፣ ተግሳፅና ምክር ለመለገስ የተጣጣሩ አልነበሩም ማለት አይደለም። ገላጋይና አስታራቂ ለመሆን የሞከሩ አልጠፉም። ቢሆንም ሰሚ አላገኙም። እንዲያውም ስድብ ነው የተረፋቸው። “በውስጥ ጉዳያችን ላይ ጣልቃ አትግቡብን፤ የእጅ አዙር ቅኝ ገዢዎች ናችሁ” ተብለው ይዘለፋሉ። የአፍሪካ አንድነት ድርጅት፣ ዋነኛ መርህ “በአገራት የውስጥ ጉዳይ ላይ ጣልቃ አለመግባት” የሚል እንደነበረ አታስታውሱም? አፍሪካዊያን “ጣልቃ አትግቡብን” እያሉ የሚከራከሩት፤ እያንዳንዱ አገር የውስጥ ጉዳዩን በራሱ ምርጫ እየመራ ተከባብሮ ለመኖር በማሰብ እንዳይመስላችሁ። ያለከልካይ እርስ በርስ ለመተላለቅ ነው።
የአፍሪካዊያን እልቂት ከጣሪያ በላይ አልፎ አለምን ለማስደንገጥ የበቃው ግን፣ በሩዋንዳ ከዚያም በኮንጎ በተከሰቱ ዘግናኝ ጦርነቶችና ግጭቶች ነው። በአንድ አመት የእርስ በርስ ፍጅት ነው፣ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሩዋንዳዊያን የረገፉት። የኮንጎ ደግሞ የባሰ ነው። ጦርነትና ረሃብ ተደማምሮ፣ በአስር አመታት ውስጥ፣ 5.4 ሚሊዮን የኮንጎ ሰዎች መሞታቸውን አለማቀፉ የቀይመስቀል ድርጅት ገልጿል።
ደግነቱ፣ ከቅርብ አመታት ወዲህ፣ አፍሪካዊያን ጥንታዊ የጦርነት ሱሳቸውንና የፍጅት ባህላቸውን የሙጢኝ ይዘው መቀጠል አልቻሉም። ምክንያቱ ሚስጥር አይደለም፡፡ የጥንቱ የፍጅት ባህል እና ዘመናዊ የጦር መሳሪያ ሲቀላቀሉ ነው፤ አህጉሪቱ በደም የታጠበችው። በጥንቱ ዘመን፣ አፍሪካዊያን ብዙ ሰውዎችን የመግደል ፍላጎት እንጂ ብዙ ሰዎችን የመግደል አቅም አልነበራቸው። ሹል እንጨት ቀስሮ ለጦርነት የሚዘምት ተዋጊ፣ አገር ምድሩን የመጨፍጨፍ እድል አያገኝም። እንጨቱ ይዶለዱማል ወይም ይሰበራል። አልያም እያሳደደ ሲገድል ውሎ፣ አመሻሹ ላይ ደክሞት ይዝለፈለፋል። ባደክመው እንኳ ጊዜ አይበቃውም - እያንዳንዱን ሰው ማሳደድና በእንጨት መውጋት ከባድ ፈተና ነው። ክላሺንኮቭ ታጥቆ በእሩምታ ደርዘኖችን መረፍረፍ፣ በታንክ መንደሮችን ማረስ የቻለ ጊዜ ነው፤ ጥንታዊ የፍጅት ባህል ምን ያህል ዘግናኝ እንደሆነ ጎልቶ መታየት የጀመረው። ጥንታዊ ባህልን ይዞ ዘመናዊ የጦር መሳሪያ የታጠቀው የአፍሪካ ሕዝብ፣ ብዙም በሕይወት የመቆየት እድል እንደሌለው በአህጉሪቱ ከተከሰቱ እልቂቶች መረዳት ይቻላል።
እናስ ምን ተሻለ? ያለከልካይ የመጨፋጨፍ ቱባ ባህል የግድ ተወግዶ፣ በምትኩ ተከባብሮ የመኖር ባህል መፈጠር አለበት። በዚህ ምክንያት፣ “ወግና ልማድ ተሻረ፤ ቱባ ባህል ተበረዘ” የሚል ቁጭት የሚያድርባቸው ሰዎች ይኖሩ ይሆን? የሚኖሩ ከሆነ፤ “ነገር የተበላሸው በ1980ዎቹ መጀመሪያ ነው” ማለታቸው አይቀርም። እውነትም፤ ኢትዮጵያንና ጎረቤቶቻችንን ጨምሮ፣ በአህጉሪቱ አራት አቅጣጫዎች፣ የጥንቱን ባህል የሚቃረን የለውጥ አየር ከዳር እስከ ዳር የነፈሰው፣ ያኔ ነው። የለውጡ መጠንና የነፋሱ ጉልበት፣ እንደየአገሩ ሁኔታ ይለያያል። የአንዳንዶቹ ፈጣን ሲሆን፣ የሌሎቹ ዘገምተኛ ነው። ገሚሶቹ፣ በእመርታ ሲራመዱ፤ ገሚሶቹ ይንፏቀቃሉ። ከፊሎቹ ያለማቋረጥ ሲሻሻሉ፤ ከፊሎቹ መነሳትና መውደቅ ያበዛሉ። ጠንካራ መሠረት የተከሉ እንዳሉ ሁሉ፣ ከአፍታ እልልታ በኋላ ወደ ዋይታ የተመለሱም አሉ። ከጦርነት ለመላቀቅ ጊዜያዊ መፍትሄ ማበጀትና የተኩስ አቁም ስምምነት መፈረም ብቻውን በቂ አይደለማ፤ ተከባብሮ ለመኖር ዘላቂ መላ መፍጠር ያስፈልጋል።
የሆነ ሆኖ፣ መጠኑና ደረጃው ቢለያይም፤ በ80ዎቹ ዓ.ም መግቢያ ግድም፣ በአዲስ የለውጥ ነፋስ ያልተነካ የአፍሪካ አገር የለም ማለት ይቻላል። በአፍሪካ የለውጥ አየር የነፈሰው፤ በራሺያ መሪነት አለምን ሲያተራምስ የነበረው የሶሻሊዝም ስርዓት በተፈረካከሰ ማግስት መሆኑ አይገርምም። ያው እንደምታውቁት፣ በሶሻሊዝም ስርዓት ተከባብሮ መኖር አይቻልም።
ሶሻሊዝም ማለት የአንድ ፓርቲ፣ የአንድ ቡድን ወይም የአንድ ግለሰብ አምባገነንነት ስለሆነ፤ የፈላጭ ቆራጭነትን ስልጣን ለመያዝ፣ የግድ መጠፋፋትና መፋጀት ያስፈልጋል። ብዙዎቹ የአፍሪካ መንግስታትና አማፂ ሃይሎች፣ ሶሻሊስት ለመሆን የተሯሯጡት ለምን ሆነና! ሶሻሊዝም ከጥንታዊው አፍሪካዊ የፍጅትና የጦርነት ባህል ጋር ይጣጣማላ። ደግነቱ፣ በ1980 ዓ.ም መፍረክረክ የጀመረው የሶሻሊዝም ስርዓት፣ በ1983 ዓ.ም ሶቭየት ዩኔን ስትበታተን ነው ተፈረካክሶ አበቃለት። ይሄው የለውጥ ነፋስ፣ አፍሪካን ለማዳረስ ጊዜ አልፈጀበትም። እንዴት በሉ።
ከዚያን ጊዜ በፊት፣ በአፍሪካ ለስም ያህል፣ የፓርቲዎች ፉክክርና የምርጫ ውድድር የሚያካሂዱ አገራት ከሁለትና ከሶስት አይበልጡም ነበር። አንዷ ቦትስዋና ናት። በተወሰነ ደረጃ ደግሞ፣ ሴኔጋል ትጠቀሳለች።
ሌሎቹ አገራት በሙሉ ማለት ይቻላል፤ የአንድ ፓርቲ አገዛዝ የነገሰባቸውና፣ “ተቃዋሚ ፓርቲ ማቋቋም በእስር ወይም በሞት የሚያስቀጣ ወንጀል ነው” የሚል ህግ ያወጁ፤ ከዚህም ጋር ተያይዞ፣ ለበርካታ አመታት በእርስ በርስ ጦርነት የሚታመሱ አገራት ነበሩ። አማፂው ሃይል፣ በጦርነት አሸንፎ ስልጣን ሲቆናጠጥም፣ በተራው የአንድ ፓርቲ አምባገነንነትን ስለሚያሰፍን ሌላ ዙር ጦርነት ይቀጣጠላል። ማብቂያ በሌለው የአምባገነንነትና የፍጅት አዙሪት ውስጥ በነበረችው አህጉር ላይ፣ አዲስ የለውጥ አየር ሲነፍስ ይታያችሁ። በጦርነት ብዛትና በአንድ ፓርቲ አገዛዝ የተጥለቀለቀችው አህጉር፣ በሰላም ድርድርና በአዳዲስ የህገመንግስት ረቂቆች ተጥለቀለቀች።
ለምሳሌ ለረዥም አመታት በአንጎላ፣ በሞዛምቢክና በኢትዮጵያ ሲካሄዱ የነበሩ ጦርነቶች እልባት ያገኙት በተመሳሳይ ጊዜ ነው። እነዚህ ሶስት የጦርነት አገራትን ጨምሮ፣ ኬንያና ደቡብ አፍሪካ፣ ጋና እና ናይጄሪያ፣ ኒጀር እና ዛምቢያ፣ ታንዛኒያና ኬኒያን…ምን አለፋችሁ? ከሰሃራ በታች፣ 25 ገደማ አገራት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ለማቋቋም የሚፈቅድ ህገመንግስት ያዘጋጁትና ፓርቲዎች የሚፎካከሩበት ምርጫ ማካሄድ የጀመሩት ከ1982 እስከ 1987 ዓ.ም ባሉት አምስት አመታት ነው። በቃ፤ ከዚያን ጊዜ ወዲህ ነው፣ የነፃነት ሜዳው ሰፊም ሆነ ጠባብ፣ የፖለቲካ ምርጫ የማያካሂድ አገር እንደ ነውረኛ መታየት የጀመረው። አሁን እንደ ኤርትራና ሱዋዚላድ ከአለም የተገለሉ አገራት ካልሆኑ በቀር፤ የአንድ ፓርቲና የአንድ ግለሰው አምባገነንነትን በአዋጅ የሚያሰፍን የአፍሪካ አገር የለም ማለት ይቻላል። ከዚሁ ጎንም ነው፤ “ያለከልካይ እንደልብ በእርስበርስ ጦርነት የመፋጀት ባህል” የተበረዘው።
የምታስታውሱ ከሆነ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ለሃያ አመታት ያህል፣ የእርስ በርስ ጦርነት ሲካሄድ፣ አለም “እሪ” አላለብንም። ሊያስቆመን አስቦ እጁን ያስገባ ማንም የለም። የሰላም አስከባሪ ሃይል ማሰማራትማ ጨርሶ አይታሰብም ነበር። ያለገላጋይ እስኪለይለት ድረስ መፋጀት ነው። ከ1980ዎቹ ዓ.ም ወዲህ፣ በተለይ ከርዋንዳው እልቂት በኋላ ግን፣ አዲስ ጦርነት በተቀሰቀሰ ቁጥር፣ አለም እሪ ይላል። ሳምንት ሳይሞላው፣ ጎረቤት አገራት አደራዳሪ ቡድን ያቋቁማሉ። የአፍሪካ ህብረት የአቋም መግለጫና ውሳኔ ያስተላልፋል። ዩኤን በበኩሉ፣ በኬንያና በሱዳን፣ በላይቤሪያና በርዋንዳ እንደታየው፣ የጅምላ ጭፍጨፋ ያካሄዱ መሪዎች ላይ ምርመራ ለማካሄድና ወደ አለማቀፉ የወንጀል ፍ/ቤት ለመውሰድ ይዝታል፡፡ አሜሪካና አውሮፓ በፊናቸው የዲፕሎማሲ ዘመቻ ይከፍታሉ።
በዚህ መሃል፣ “አልደራደርም፤ እንዳሻኝ እዋጋለሁ፤ በውስጥ ጉዳይ ጣልቃ አትግቡብኝ” ለማለት የሚደፍር ማን ነው? ዋጋውን ያገኛታላ። ጎረቤት አገራት ጦር ይልካሉ። የምዕራብ አፍሪካ አገራት ወታደሮቻቸውን ወደ ላይቤሪያ አዝምተው አልነበር? ኢትዮጵያና ኬንያም፣ ጦራቸውን ወደ ሶማሊያ አስገብተዋል። አሜሪካና አውሮፓም፣ እንደሁኔታው፣ ሊቢያ ላይ እንዳደረጉት የጦር አውሮፕላን ይልካሉ። ወይም እንደ ፈረንሳይ እግረኛና ኮማንዶ ጦር ያዘምታሉ። የተባበሩት መንግስታት እንኳ፣ እንደድሮው፣ ሰላምን የሚጠብቅ (Peace Keeping) ታዛቢ ሃይልን አይደለም የሚያሰማራው። በእርግጥ ስሙ አልተለወጠም። ተግባሩ ሲታይ ግን፤ “ሰላም አስከባሪ ተዋጊ ሃይል” ብለን ልንጠራው እንችላለን። በኮንጎ፣ በሴራሊዮንና በላይቤሪያ እንዳየነው፤ የተባበሩት መንግስታት ጦር፣ ለእርቅ እምቢተኛ ሆነዋል የተባሉ አማፂ ቡድኖችን እያሳደደ ወግቷል። አንዳንዳችን አስሮ ለፍርድ አቅርቧል፡፡ በተባበሩት መንግስታት ድጋፍ ወደ ሶማሊያ የዘመተው የአፍሪካ ህብረት ጦርም፣ ከአልሸባብ ጋር ይዋጋል።
በአጭሩ፣ ጊዜው ተለውጧል። እንደ ድሮ አይደለም፣ ዛሬ “አለከልካይ መፋጀት ለአፍሪካዊያን አይፈቀድም” የሚል ስሜት በርክቷል። ይሄውና የደቡብ ሱዳን ተቀናቃኝ ወገኖች፤ ገና ወደ ጦርነት በገቡ ሳምንት፣ በሰላም ጥሪ መውጪያ መግቢያ አጥተዋል።

Read 3515 times