Saturday, 28 December 2013 11:03

የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የደብር ሃላፊዎችና ሠራተኞች አዲሱን መዋቅር ተቃወሙ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(5 votes)


“ዲግሪ ያላቸው በየአስተዳደሩ እንዲገቡ መደረጉ አግባብ አይደለም” በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የአዲስ አበባ ሃገረ ስብከት፣ ካለፈው ህዳር ወር ጀምሮ እያካሄደ ያለውን አዲስ የመተዳደሪያ ደንብ የማፅደቅ ሂደት እና መዋቅራዊ ለውጥ አጥብቀው እንደሚቃወሙ የሃገረ ስብከቱ የአድባራትና ገዳማት አስተዳዳሪዎችና ሠራተኞች ለቅዱስ ፓትሪያርኩና ለጠቅላይ ሚኒስትር ፅ/ቤት አስታወቁ፡፡ ቅሬታ አቅራቢዎቹ ለፅ/ቤቶቹ ባስገቡት ደብዳቤ፤ የሃገረ ስብከቱ አዲስ መተዳደሪያ ደንብ ሁሉም የቤተክርስቲያኒቱ ሊቃውንት ሳይሳተፉበት በጥቂት አመራሮች ብቻ የተቀረፀና በውይይት ያልዳበረ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡ መተዳደሪያ ደንቡ ከነባሩ ህገ ቤተ ክርስቲያንና ከቃለ-አዋዲ ደንብ ጋር የሚጋጭና የሚጣረስ ነው ያሉት ቅሬታ አቅራቢዎቹ፤ “ደንቡ፤ ነባሩን የቤተክርስቲያኒቱን ሠራተኛ በማፈናቀል በምትኩ ስለቤተ ክርስቲያን ትምህርት ምንም እውቀት የሌላቸውን ግለሠቦች በስመ ድግሪና ዲፕሎማ በመሠግሠግ የቤተክርስቲያኗን ሙሉ አስተዳደራዊ መዋቅር ለመቆጣጠር ያለመ ነው” ሲሉ ተቃውመዋል፡፡

አዲሱን መዋቅር ያዘጋጁት አካላት ማንነታቸው በግልፅ እንደማይታወቅ በደብዳቤያቸው የጠቀሡት ቅሬታ አቅራቢዎቹ፤ የቤተክርስቲያኗ የመጨረሻ ስልጣን ያለውን ቅዱስ ፓትርያርክ ስልጣንን በመገደብ፣ ቤተክርስቲያኗ የእነዚህ አካላት ሠለባ እንዳትሆን ስጋት አለን ብለዋል፡፡ የቤተክርስቲያኒቱን ቃለ አዋዲ ያልጠበቀ ነው ያሉትን አዲሱን መተዳደሪያ ደንብ እንደማይቀበሉትም አስተዳዳሪዎቹ ገልፀዋል፡፡ ለቅሬታው መነሻ የሆነው ደንብ፣ ህግ በማርቀቅና በማዘጋጀት ከፍተኛ ልምድና እውቀት ባላቸው ገለልተኛ ምሁራንና የቤተክርስቲያኗ ሊቀ ሊቃውንት እንዲሰናዳ የጠየቁት ቅሬታ አቅራቢዎቹ፤ ህጉን አርቅቋል የተባለውን ማንነቱ ማህበር ፓትሪያርኩ እንዲያጣሩ ተጠይቀዋል፡፡ “አዲሱ ደንብ የካህናት ቅነሣ መርሃ ግብርም እንዳካተተ በግልፅ ተረድተናል” ያሉት ቅሬታ አቅራቢዎቹ፤ “ድርጊቱ መንግስት ስራ አጥን ለመቀነስ የሚያደርገውን ጥረት የሚፃረር ነው” ሲሉ ያጣላሉት ሲሆን ብዙ ሊቃውንትን ከስራ በማፈናቀል ለችግር እና ለእንግልት የሚዳረግ በመሆኑ ህጉ መፅደቅ እንደሌለበት አሳስበዋል፡፡ በጉዳዩ ዙሪያ ማብራሪያ የጠየቅናቸው የፓትርያርኩ ልዩ ፅ/ቤት ሃላፊ አቶ ታምሩ አበራ የቅሬታ አቅራቢዎቹ ደብዳቤ ወደ ፅ/ቤት ሳይገባ በቀጥታ ለፓትርያሪኩ የደረሰ በመሆኑ በጉዳዩ ላይ ምላሽም ሆነ አስተያየት ለመስጠት እንደሚቸግራቸው ተናግረዋል፡፡ ቅሬታ አለን የሚሉ ወገኖች በተናጥል ከሚቀርቡ፣ ለቤተክርስቲያኗ ይጠቅማል የሚሉትን ኮሚቴ መርጠው ሃሣባቸውን በማደራጀት ቢያቀርቡ እንደሚሻል የጠቆሙት ሃላፊው፤ የእነሡ ሃሣብ ተቀባይነት ባያገኝም እንኳ በውይይት ለመተማመን ዝግጁ መሆን እንዳለባቸው ገልፀዋል፡፡

Read 4459 times