Saturday, 28 December 2013 10:45

ገዳማትና አድባራት የልማት ፈንድ ሊያቋቁሙ ነው

Written by 
Rate this item
(0 votes)

•    የልማት ሥራዎች ለብዝሐ ሕይወት አስተዋፅኦ ሊኖራቸዋል ይገባል ተብሏል
•    የተከማቸውን አገልጋይ ለማቀፍ የሚያስችል መዋቅርና አደረጃጀት ተዘርግቷል

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት አድባራትና ገዳማት ልማትን በማስፋፋት

ሐዋርያዊ አገልግሎትን በዘላቂነት ለማከናወን የሚያስችል ሀብትና ንብረት የሚያፈሩበት የልማት ፈንድ ሊያቋቁሙ መኾኑ

ተገለጸ፡፡ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት በሰበካ ጉባኤ ከሚሰበስቡት አስተዋፅኦ ጋራ በልማት መስኮች ለሚያገኙት ገቢ

ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ አቅጣጫ መቀመጡን ለአዲስ አድማስ ያስታወቁት የሀ/ስብከቱ ምንጮች÷ ገዳማትና

አድባራት በአንድ የበጀት ዓመት መጨረሻ ለመደበኛ አገልግሎት ከሚመደበው በጀትና መጠባበቂያው ከሚተርፈው

ገንዘብ ስድሳ በመቶውን (60%) የልማት ፈንድ እንዲያቋቁሙበት የሚያስችል ጥናት መቅረቡን ገልጸዋል፡፡  

ገዳማቱና አድባራቱ በልማት ሥራዎች የሚያገኙት ገቢ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን  ያስረዱት ምንጮቹ÷ በሒሳብ

አያያዝ ፖሊሲውና ዝርዝር የአፈጻጸሙ መመሪያው መሠረት የሚመሠርቱት የልማት ፈንድ የልማት ተቋማትን

በማቋቋምና በማስፋፋት አብያተ ክርስቲያናቱን ከልመና ለማውጣት፣ የካህናትንና ሊቃውንትን የኑሮ ኹኔታ ለማሻሻልና

የገጠር አብያተ ክርስቲያናትን በዘላቂነት ከመደገፍ ጀምሮ የምግባረ ሠናይ ተግባራትን በስፋት ለማከናወን

እንደሚያገለግል ተናግረዋል፡፡

በልማት ፈንዱ የሚቋቋሙና የሚስፋፋፉ ነባርና አዲስ የልማት ሥራዎችና የምግባረ ሠናይ ተግባራት የሚመሩበት

ፖሊሲና መመሪያም ስለመረቀቁ በምንጮቹ ገለጻ ተጠቁሟል፡፡ የልማት ተቋማቱ የቤተ ክርስቲያኒቱ ዋነኛ ተልእኮ

የኾነውን ሐዋርያዊ አገልግሎትዋን በከተማና በገጠር የማፋጠንና የመደገፍ፣ የምግባረ ሠናይ ድርጅቶቿን በቋሚ የገንዘብ

ምንጭነት የማገልገል አስፈላጊነት እንዳላቸው በፖሊሲው ተዘርዝሯል፡፡
ፖሊሲው ለልማት ተቋማቱ ባስቀመጣቸው መርሖዎች መሠረት÷ በምሥረታና ማስፋፋት ወቅት ለቤተ ክርስቲያን

ምስጢራዊ አገልግሎት እንደ ግብዓት የሚያገልግሉ ዕቃዎችን ለማምረትና ለማከፋፈል ቅድሚያ መስጠት የሚጠበቅባቸው

ሲኾን ተቋማቱ የሚያመርቷቸውና የሚያከፋፍሏቸው ንዋያተ ቅድሳት፣ የኅትመት ውጤቶች፣ የምስል ወድምፅ ሥራዎችና

የመሳሰሉት ከቤተ ክርስቲያኒቱ ዶግማና ሥርዐት፣ ከማኅበረሰቡ ኢትዮጵያዊ ማንነትና ትውፊት አንጻር ታሳቢ

መደረጋቸው መፈተሽና መረጋገጥ እንደሚኖርበት ተመልክቷል፡፡
ፖሊሲው የተፈቀዱ ናቸው የሚላቸው የልማት ተቋማት ለብዝኃ ሕይወት አዎንታዊ አስተዋፅኦ ሊኖራቸው እንደሚገባ፣

በዕውቀቱ የበለጸገ፣ በሥነ ምግባሩ የታነጸ ትውልድ ለማፍራት ትኩረት ሰጥተው መሥራት እንደሚያስፈልጋቸው

በመርሖው አስቀምጧል፡፡ ከተቋማቱ ዝርዝር ውስጥም ኮሌጆችና ማሠልጠኛዎች፣ ማተሚያ ቤቶች፣ የጉዞና አስጎብኚ

ድርጅት በማቋቋም የሆቴልና ቱሪዝም አገልግሎት መስጠት፣ ክሊኒኮችን፣ ሆስፒታሎችንና ፋርሚሲዎችን በማቋቋም

የሕክምና የሕክምና አገልግሎት መስጠትና መድኃኒቶችን ማከፋፈል፣ የግንባታ ቁሳቁሶችን ማቅረብ፣ ለአገልግሎትና ኪራይ

የሚውሉ ሕንጻዎችን መገንባትና ማከራየት፣ ከውጭ የሚገቡ ንዋያተ ቅድሳትን በመተካት የውጭ ምንዛሬ ማዳንና ወደ

ውጭ በመላክ የውጭ ምንዛሬ ማስገኘት፣ የግብርና ውጤቶችን ለሀገር ውስጥና ለውጭ ገበያ ማቅረብ፣ የፋይናንስ ተቋም

አክስዮን መግዛት፣ የመንግሥት የግምጃ ቤት ሰነድና ቦንድ መግዛት ይገኙበታል፡፡
ገዳማትና አድባራት በራሳቸው አልያም በመቀናጀት ተቋማቱን መመሥረት እንደሚችሉ በመርሖው የተገለጸ ሲኾን

ቅንጅቱም አጥቢያ አብያተ ክርስቲያኒቱ ከሌሎች አጥቢያዎች ጋራ፣ አጥቢያዎች ከአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ጋራ እንዲሁም

ሀ/ስብከቱና አጥቢያዎቹ ከሌሎች አህጉረ ስብከትና አጥቢያዎቻቸው ጋራ ሊከናወን የሚችልበት የፕሮጀክት አጸዳደቅና

አተገባበር ሥርዐት ማካተቱ ተገልጧል፡፡
በልማት ፈንዱ የሚቋቋሙና የሚስፋፉ ተቋማት ካህናትና ሊቃውንት ከመደበኛ ተግባራቸው  በተጨማሪ

እንደየዝንባሌያቸው በተለያዩ ክሂሎቶች እየሠለጠኑ እንዲሠማሩ በማስቻል የሥራ ዕድል እንደሚፈጥሩላቸው፣

በአገልግሎታቸውም እንዲበረቱ ተገቢውን በማሟላት አስተዋፅኦ እንደሚያደርጉላቸው ታምኖባቸዋል፡፡ የልማት ተቋማቱ

ወደፊት በሀ/ስብከቱ እንደአስፈላጊነቱ ከሚተከሉት አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ጋራም ተነጻጻሪ መስፋፋት

እንደሚኖራቸው ተጠቁሟል፡፡

የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት 169 በሚደርሱት አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናቱ ባሰራጨው ቅጽ እየሰበሰበው የሚገኘው

የአገልጋዮች ጠቅላላ መረጃ፣ በአሁኑ ወቅት አድባራቱና ገዳማቱ ልዩ ልዩ ክህሎትና ልምድ ያላቸው አገልጋዮች

እንዳሉባቸው የሚያመላክቱ ናቸው ያሉት ምንጮቹ÷ ይህም ለልማት ተቋማቱ ከሚፈጥረው የሰው ኃይል አቅም ባሻገር

የቤተ ክርስቲያኒቱን ትምህርት ከዘመናዊው ሞያ ጋራ በአቻ ግመታ በማስቀመጥ በአምስቱ የአጥቢያ አብያተ ቤተ

ክርስቲያናት መዋቅርና አደረጃጀት ውስጥ በሚሠራው የሰው ኃይል ትመናና ምደባ በርካታ የአገልጋይ ቁጥር ለማስተናገድ

እንደሚያስችል ተመልክቷል፡፡

Read 1471 times