Print this page
Saturday, 28 December 2013 10:27

ጥቂቶች ሊመነደጉ፤ ብዙዎች አሽቆልቁለዋል Featured

Written by 
Rate this item
(14 votes)

ከአዲሱ ጠ/ሚኒስትር አዲስ ራዕይ እንፈልጋለን

“የራበው ሥራ ፈልጐ ማግኘት የማይችልና ልጆቹን ለማስተማር አቅም ያጣ ሰው ከባርነት ነፃ ነው ማለት አይቻልም፡፡” የሚለው የአሜሪካዊው ፕሬዚዳንት ሊንደን ቢ. ጆንሰን ንግግር እውነትነት አሁን አሁን በጆሮዬ መደወሉ ራሴን እያስገረመኝ መጥቷል፡፡ የዛሬ አምስትና ስድስት ዓመት ገደማ ደራሲና ጋዜጠኛ አለማየሁ ገላጋይ፤ ስለኑሮ ውድነት ሲጽፍ ብዙዎቻችን እያነበብን ፈገግ ከማለት በቀር ብዙ ልባችን አልተነካም ነበር፡፡ ምናልባትም በጣም አልፎ አልፎ ከምናነባቸው መጣጥፎች ይልቅ መንግስት ስለ ልማት የሚነፋው ጥሩንባ አደናቁሮን ይሆናል፡፡ አሁን አሁን የመንግሥት መዝገበ ቃላት “ልማት” የሚለው ትርጓሜ ግራ እያጋባን መጥቶ ጭራሽ ወደ ብስጭት የተመነዘረብን ብዙ ነን ብዬ አስባለሁ፡፡ መንግስት ልማት የሚለው ከእኛ አፍ “ቫት” እያለ የሚነጥቃትን ገንዘብ ሰብስቦ ለሌቦች ካጠገበ በኋላ፣ በፍርፋሪዋ የሚሠራትን መንገድና ጤና ጣቢያ ወይም ትምህርት ቤት ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ “ኮንደሚኒየም”እየተባሉ የተሠሩት ቤቶች አካባቢ ያለውን ግድየለሽነት ተመልከቱ፡፡ የውሃ መፍሰሻ ቦዮቹ ገና ተሠርተው ሳያልቁ ይፈርሣሉ። ሕንፃው ውስጥ ያሉትን የግብር ይውጣ ሥራዎች ተውአቸው፡፡ ለመሆኑ ልማትና ዕድገት ምንድነው? ወረቀት ላይ የሃሰት ሪፖርቶችን ከምሮ መቀለድ ነው። ቀልድና ውሸትስ እስከ የት ያዘልቀናል? ከወር ወደ ወር ሰዎች በልተው የማደር አቅማቸውን እያጡ፣ ልጆቻቸውን ማስተማር ተራራ መቧጠጥ እየሆነባቸው ሲመጣ --- እንዴት ስለ ዕድገት ይወራል? ጋዜጠኛ መሳይ ካድሬዎች ስለልማትና እድገት ብዙ ቢለፈልፉም ከሕዝቡ የበለጠ ጓዳውን የሚያውቅ ማንም ሊኖር አይችልም፡፡ አለ ቢባልም ከተራ ቀልድነት አያልፍም፡፡ እርግጥ ነው፤ ባለፉት ሃያ ዓመታት ጥቂት ሰዎች በኑሯቸው አድገው ይሆናል፤ ለስላሳ መጠጣት የማይችሉ ዛሬ ቤታቸው ውስኪ ደርድረው የሚመርጡበት ዕድል ደርሷቸው ይሆናል፡፡ያ ግን ዕድገት አይደለም፡፡ የማሕበረሰብ ሳይንስ ምሁራን የዕድገትና ልማትን ዓላማዎች እንዲህ ያስቀምጡታል - የሕዝቡን የገቢ መጠን በፍጥነት ማሳደግ ለዜጐች የሥራ ዕድልን መፍጠር መሠረታዊ የሆኑ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፍላጐቶችን ማርካት፤ ማህበራዊ ፍትህን ማስፈን ሥራንና የቁጠባ ባህልን በሕብረተሰቡ ማስረጽ መልካም አስተዳደርና አሣታፊ የሆነ የፖለቲካ
ምህዳር መፍጠር ከላይ የተጠቀሱትና ሌሎችም ተጨማሪ ነጥቦች የአንዲት ሀገርንና ሕዝብን ዕድገት መንገድ የሚያሳዩ ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ በሀገራችን ያለው ተጨባጭ ሁኔታ ከዚህ በተቃራኒ የቆመ ይመስላል፡፡ ምናልባት የማይካድ ለውጥ አምጥቷል ብለን የምንወስደው ሕብረተሰቡ በሥራ ላይ ያለውን አመለካከት በመጠኑ መቀየር መቻሉ ነው፡፡ ቁጠባውንም በውድም ሆነ በግድ በየሰበቡ ለማስለመድ የሚደረገው ጥረት የሚናቅ አይደለም፡፡ የፖለቲካው አሣታፊነት ጉዳይ የሕፃን ልጅ ዕቃ ዕቃን የመሰለ ቀልድ ስለሆነ ጉዳዩ ለሰለቸው አንባቢ ይህን አንስቶ እንዲህና እንዲያ ማለት እንደ ደንቆሮ መቁጠር ሊመስልብኝ ይችላል፡፡ ጠቃሚ ባህሎችን ማሳደግ በሚለውም መሥመር እያንዳንዱ ብሔር ብሔረሰብና ሕዝብ (በመንግስት መሠረት) ሥነ ጽሑፉንና ባህሉን ማሳደጉን እኔ በግሌ እደግፈዋለሁ፡፡ ልክ ነው ብዬም አምናለሁ፡፡ አንዱ በባህሉ እየኮራ፣ ሌላው እያፈረ የሚደበቅባት ሀገር አሁንም እኩልነት የጐደላት ስለሆነች ያንን ሕልም ማለም ጠባብነት ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡ የሚያሣዝነው ግን በዚህ በጐሣ በተከፋፈለ ከለላና አስተዳደር ምክንያት የተፈጠሩት
ጥላቻዎች ማርከሻ መድሃኒት ማጣታቸው ነው፡፡ መሪዎቻችን በወጣትነት መንፈስ በስሜታዊነት ያደረጉትን ነገር ምራቅ ሲውጡ እንኳን ለማስተካከል ያለመቅናታቸው የሚገርም ነው፡፡ ለዚህ ሃሳብ ዋቢ የሚሆነኝን አንድ ሃሳብ ወደኋላ መለስ ብዬ ሕዳር 18 ቀን፣ አንድ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ በዶክተር እሸቱ ጮሌ አዳራሽ፣ ለዶ/ር ፋሲል ናሆም (ለጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪ) ያቀረበውን ጥያቄ ልጥቀስ፡፡ተማሪው የተወለደበትን ክልል ጠቅሶ፣ በክልሉ ዋና ከተማ የሚኖሩ የሌላ ብሔር ተወላጆች ሀገራቸው እስከማይመስላቸው ድረስ በደል እየተፈፀመባቸው እንደሆነ ገልፆ፣ መንግስት ለ “minority” ምን መፍትሔ አለው ሲል ጠይቆ ነበር፡፡ በሌላ አንፃር ደግሞ ያ ተማሪ እኖርበታለሁ ወይም ተወልጄበት ግን የዜግነት መብት አላገኘሁም የሚልበት ክልል ተወላጅ የሆነ ሌላ ተማሪ ተነስቶ፣ ችግሩ የሚታየው የቀደመው ተማሪ በጠየቀበት ክልል ብቻ ሣይሆን በሁሉም የሀገሪቱ ክልሎች መሆኑን ጠቅሶ፣ ሥራ ለመቀጠርም ሆነ ለሌላ ጉዳይ ዘር መቁጠር ግድ ስለሆነ፣ ችግሩን መፍታት ያለብን ሁላችንም ነን ብሎ ደመደመ፡፡ እኔ ግን በሁለተኛው ተማሪ ሃሳብ አልስማማም፤ ችግሩን ለመፍታት እኛ ድርሻ ቢኖረንም የአንበሳው ድርሻ ግን የመንግስት ነው፡፡ ስለዚህ መንግስት ለዚህ ነቀርሣ መፍትሔ መፈለግ አለበት፤ ሰው በገዛ ሀገሩ ባዕድ እየሆነና እየተገፋ መኖሩ የሚያመጣው ልማት ፈፅሞ ግልጽ አይደለም፡፡ ለመሆኑ መንግስት ማለትስ የሰዎች ስብስብ አይደለም እንዴ? እንዴት ይህንን ነገር ማሰብ ያቅተዋል? ባለሥልጣን ሲኮን ተከትሎ የሚመጣው አጃቢ ወታደር፣ ያበጠ ወንበር--- የነገን ጉዳይ ያዘናጋልና መሪዎቻችንም ሊያስቡበት የሚገባ ይመስለኛል። አብዛኛው ሕዝባችን ከእጅ ወደ አፍ እንኳን ኑሮ እያቃተው ከመጣ፤ የመኖር ዕድሉ እየጠበበ ከሄደ ሊፈጠር የሚችለው ነገር ምንድነው ብሎም ማሰብ ደግ ይመስለኛል፡፡ የኢሕአዴግ አማካሪዎች ምናልባት እውነት የማይናገሩ አሸርጋጆች እንዳይሆኑ እሠጋለሁ። ሕዝቡ እየተራበ

“ጠግቧል”፣ እየተማረረ “ደስተኛ ነው” እያሉ ከሆነ ፍፃሜው አያምርም። በርግጥ እኛ ሥልጣን የሌለን አስበን ምንም አናመጣም፣ ሥልጣን ያላቸው ናቸው ለችግሩ መቋጫ መፍትሄ ሊያበጁለት የሚገባቸው፡፡አዲሱም ጠቅላይ ሚኒስትር ቢሆኑ ሁልጊዜ የታላቁ መሪያችንን መዝሙር ከመዘመር ይልቅ አዲስ መዝሙርና ራዕይ ለመፍጠር መሞከር ይጠበቅባቸዋል፡፡ ቶማስ ጀፈርሰን፤ ሁሉም ሰው የየራሱ ዘመን አለው፣ በሕይወት የሌለ ሰው በሕያው ሰው ዘመን ሊወስን አይችልም እንደሚል፣ አሁን ያለውን ኑሮና ሕይወት የማያዩት የቀድሞው መሪያችን ራዕይ ሊያዘልቀን ይችላል ብሎ ማመን ያስቸግራል፡፡ ርግጥ ነው ያስጀመሩትን ግድብ ማጠናቀቅ፣ የባቡሩን ሥራ መፈፀም፣ ወዘተ ጥሩ ነው። ግን በጤፍ ዋጋ፣ በስኳርና በትራንስፖርት ጉዳይ ያለውን ጣጣ ዛሬ ቢያዩ፣ እሳቸውም ደንግጠው ጭንቅላታቸውን ይይዙ ነበር፡፡ በዓመት ውስጥ ለአንድ የሆቴል ተመጋቢ ቢያንስ ሦስቴና አራቴ ዋጋ ይጨምርበታል፡፡ ታዲያ ሆዱ ባልጠገበ ሲቪል ሠራተኛ ተሠርቶ፣ ሀገርን ማሳደግ ይቻላል እንዴ? ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ አዲስ ሕልም ያልሙ እንጂ --- አዲስ ራዕይ ያምጡ! የስነ አመራር ምሁሩ

ጆን ሲ ማክስዌል እንደፃፉት፤ በየዓመቱ ዶሮዎቹን የክረምት ጐርፍ የሚወስድበት ዶሮ አርቢ፣ ሁልጊዜ በዶሮ ላይ የሙጢኝ ማለት የለበትም፤ ይልቅስ ጐርፉ ላይ ዋኝቶ አልፎ ሀብት የሚሆን ዳክዬ የማርባት ጥበብና ዘዴ ሊኖረው ይገባል። መቼም መንግስታችን ሁልጊዜ በሕይወት በሌሉት የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ላይ መንጠልጠል ያለበት አይመስለኝም፤ እሳቸው በጊዜያቸው የሚሰሩትን ሰርተው አልፈዋል፡፡ አሁን ተራው የሥልጣን ወንበሩ የተሰየሙት ሰውዬ ነው፡፡ ፕሬዚዳንት ሊንደን ቢ. ጆንሰን እንዳሉት፤ ድሀና ሀብታም በጠብደል ግድግዳ ሲለይ ጥሩ አይደለም። ይልቅስ ግድግዳው የመስተዋት ነውና በኋላ የሚያመጣው መዘዝ መጥፎ ነው፡፡ ከፊሉ በሌብነት እየበለፀገ፣ ሌላው በጨዋነት እየተራበ - ለዘላለም - አይኖርምና መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡ ዶክተር መረራ ጉዲና እንደሚሉት፤ የራበው ሕዝብ - መሪውን ለመብላት እንዳይነሣ - ካሁኑ ማሰብ የግድ ይላል፡፡ ጆንሰን - “There are two courses open to us. We can master the problem, or we can leave it to master us” ብለዋል - የኛም ምርጫ ይኸው ነው። አዲዮስ!

Read 2989 times Last modified on Monday, 28 November 2016 07:26
Administrator

Latest from Administrator