Saturday, 28 December 2013 10:25

“ለመብላት የጠፋ ቅቤ፤ ስሞት ባፍንጫዬ ይፈስሳል፤” ይላል ዶሮ

Written by 
Rate this item
(8 votes)

ከዕለታት አንድ ቀን አንዲት ዳንሴ የምትባል ወተት - አላቢ ሴት ራኘ ያለ ቦታ ወዳለው የላሞች በረት ሄዳ ወተቷን ታልብና በቅል ሞልታ,ኧ እንደተለመደው ጭንቅላቷ ላይ አድርጋ ወደ ቤቷ መንገድ ትጀምራለች፡፡ በመንገዷ ላይ የምታገኛቸው የሠፈሩ ሰዎች፤ “ከየት ትመጫለሽ?” ይሏታል፡፡ “ወተቴን አልቤ መመለሴ ነው” ትላለች፡፡ “ላሟ እንዴት ናት፣ ብዙ ወተት ሰጠች?” “በጣም ብዙ፡፡ ጭንቅላቴ ላይ ያሰቀመጥኩትን ቅል አታዩም፡፡ በሱ ሙሉ አልቤያለሁ” “ታድለሻል!” ይሏታል፡፡ መንገዷን ትቀጥላለች፡፡ ያገኘቻቸው ሰዎች ሁሉ አድናቆታቸውን ሲገለፁላት፣ በጣም ደስታ እየተሰማት በሀሳብ ስምጥ ትልና ለራሱዋ እንዲህ ትላለች፡- “ይሄን በቅል የሞላሁትን ወተት እንጥና፤ ቅቤ አወጣለሁ፡፡ ያንን ቅቤ ወደ ገበያ ወስጄ በደህና ዋጋ እሸጣለሁ፡፡ በዚያ ገንዘብ መዓት ዕንቁላል እገዛለሁ፡፡ ዕንቁላሉ ሲፈለፈል መዓት ጫጩት ይፈለፈሉልኛል፡፡ ጫጩቶቹ ያድጉና ብዙ ዶሮዎች ይሆኑልኛል። ከዚያ በጣም ሰፊ የዶሮ እርባታ አቋቁማለሁ፡፡ ግቢዬ ዶሮ በዶሮ ይሆናል፡፡ ከነዚያ ዶሮዎች ውስጥ በየጊዜው ጥቂቶቹን እየወሰድኩ ገበያ እቸበችባለሁ! ባለ ብዙ ብር እመቤት እሆናለሁ፡፡ ቀጥዬ በጣም ቆንጆ ቆንጆ የተባሉ ቀሚሶችና ጫማዎች እገዛለሁ፡፡ ያኔ እንግዲህ ያገሩ ሰው ሁሉ ሠርግ የሚጠራው፣ ግብዣ እሚጠራው እኔን ብቻ ይሆናል፡፡ ያገሩ ጐረምሳ ዐይንም እኔኑ ብቻ ማየት ይጀምራል፡፡ አንዱ ጐረምሣ ይመጣና “ዳንሴ እንዴት አምሮብሻል? ከእኔ ጋር ለምን አትሄጂም?” ሲለኝ፤ ደሞ ያም ሎጋ ይመጣና “ዳንሴ የኔ ቆንጆ! ዛሬ በምንም ዓይነት ከእኔ ጋር መሄድ አለብሽ” ሲለኝ፤ እኔ ግን እራሴን እየነቀነቅኩኝ፤ እየተምነቀነቅሁ ጥያቸው እሄዳለሁ!” ስትል፤ ለካ ራሷን ስትነቀነቅ ያ ጭንቅላቷ ላይ አስቀምጣው የነበረ የወተት ቅል ውሉን ስቶ ኖሮ፤ መሬት ወርዶ ተከሰከሰ፡፡ ያም ወተት ይፈስና አገር ምድሩን ይሞላዋል፡፡ በሀሳቧ የገነባችው ሀብት ንብረትና ቁንጅናም መሬት ፈስሶ ይቀራል! “ጫጩቶቹ ሳይፈለፈሉ በፊት፤ መቁጠር አትጀምር” የሚለው የፈረንጆች ተረት አመጣጥ ይሄ ነው! እኛ እናውርቸው እነሱ ያውርሱን አይታወቅም፡፡

                                                               * * *

ፈረንጆች፤ “Building a castle in the air” የሚሉት ይሄንኑ ነው፡፡ ማቀድና በባዶ ሜዳ መመኘት እጅግ የተራራቁ ጉዳዮች ናቸው፡፡ ማቀድ፤ በዝርዝር ያቀድኩትን ለመፈፀም ምን ምን አደርጋለሁ ማለትን፣ ያንንም ማስፈፀሚያ ፋይዳ ያለው ቁሳቁስንና አጋዥ የሰው ኃይልን፤ እንዴት እቀዳጀዋለሁ ማለትን፤ በመጨረሻም ቀን በቀን ሥራ ላይ ማዋልን ይጠይቃል፡፡ በዚህ ማህል ባይሳካስ ብሎ ማውጠንጠንን፣ ሁለተኛ ዘዴ መዘየድን (Plan B እንዲሉ) የግድ ማሰብን ይሻል፡፡ ካልሆነና አማራጭ ሁሉ ከተሟጠጠም በጊዜ ሀሳብን ለውጦ ወደ ሌላ ዕቅድ መሸጋገር ነው፡፡ ከዚህ ቀላልና ግልፅ መንገድ ውጪ በጉልበት ልሥራህ ቢሉት ሀብትንም ማባከን፣ የሰው ኃይልንም በአጓጉል መንገድ ሜዳ ማፍሰስ ነው፡፡ እግርህን በአልጋህ ልክ ዘርጋ፤ እንደማለት ነው፡፡ ይህን በአገር ደረጃ መንዝሮ ማየት ነው እንግዲህ አገርን ለማሳደግ መጣጣር፡፡ ከምንጨብጠው በላይ መጀመሪያ እጃችን ረዥም መሆኑን ማረጋገጥ ያስፈልጋል /a man’s reach should exceed his grasp ይላል ሮበርት ብራውኒንግ/ እጃችንን ዘርግተን የማንደርስበትን ነገር ለመጨበጥ መሞከር፤ በር ከፍተን ለዘራፊ እንደመተው ነው፡፡ የሰላም ትልቁ ጠላት ከአቅም በላይ መመኘት ነው፡፡ አሊያም የክቡር እምክቡራን ዕብደት ነው። “ከአቅም በላይ መኖር የዕድገት ፀር ነው” ይሉ ነበር ያለፈው ሥርዓት ነገረ-ሠሪዎች! ኮከብ እነካለሁ ብሎ ሠምበሌጥ ላይ መወድቅ ይከተላል፡፡ ለራስ ጥቅም ሲሉ የአገር ዕቅድ አወጣሁ ማለት መዘዙ ብዙ ነው፡፡ ድህነት ባጠጠበት፣ ችጋር በተንሠራፋበት አገር እንደ ህንድ እጉልላቱ አናት ላይ ጥቂት ባለ ፀጋ ሰዎች ብቻ ተቀምጠው፣ የበለፀገች ኢትዮጵያን መመኘት ከንቱ መገበዝ ነው፡፡ የሥራ መንፈስ ከብዙሃኑ የልብ ፍቅርና የአገር መውደድ ስሜት ጋር በፅኑ መቆራኘት አለበት፡፡ ላገር አሳቢ እየመሰለ ውስጥ ውስጡን እንደሚቦጠቡጥ ሹም ባለበት ቦታ ዕቅድ ሲታቀድ ቢውል ፍሬ-ቢስ ነው የሚሆነው። ነባር ነባር በላተኛ አባርረን ትኩስ ትኩስ፣ ልጅ-እግር በላተኛ ካመጣን፤ የበላተኞች መተካካት እንጂ የአዲስ ደም - ቅያሪ (New – Blood - Injection) አይሆንልንም፡፡ “ይህንንማ ማን ያጣዋል ይሄንን ማንም ያውቀዋል፡፡ ዝቅተኝነት’ኮ፣ የለጋ ምኞት መሰላል ነው ጠዋቱን ሥልጣን የጠማው:- ደረጃውን ሲያያዘው፣ ሽቅብ ሽቅብ ያንጋጥጣል ጫፉ ላይ ሲደርስ ግና፣ ጀርባውን ለመስጠት ይሻል ጧት የበላበትን ወጪት፣ ማታ ሰባሪ ይሆናል ቀና ብሎ ወደ ሰማይ፣ ደመናውን ብቻ ያያል እላይ ያወጣውን ታች ሰው፣ ቁልቁል ረግጦ ይሳደባል” ይላል የሺክስፒሩ ብሩተስ፡፡ ዞሮ ዞሮ ዕቅድ እንደ አቃጁ፣ ዕቅዱ እንደ ከዋኙ ነው፡፡ የሸር ዕቅድም፣ የአውቆ-አበድ ዕቅድም አለና ጠንቅቆ ማየት ይገባል፡፡ ታዋቂው ፀሀፌ-ተውኔት ፀጋዬ ገብረ መድህን በሚኒልክ ተውኔት፣ በኢልግ አፍ፣ እንዲህ ይላል፡- “ኮንቲ ኦሊኒ ግን ጭምት፣ ቀዝቃዛ፣ ነገር ለማሻከር ሆን ብሎ በዕቅድ የሚቆጣ፣ ሆን ብሎ በዕቅድ እንዳስፈላጊው ሁኔታ የሚያብድ፣ አንድ ነፃ መንግሥት ያለኔ ፈቃድ ለምን ሰንደቅ ዓላማ ተከለ ብሎ በነገረ-ቀደም አቅዶ እሚጮህ፤ … አቅዶ የሚያብድ ሥውር አደገኛ ሕሊና፣ ቁም - ነገር - አልባ ሰው ነው!” ከዚህ ይሰውረን፡፡ ዕቅዶች ይከወናሉ፡፡ ፓርቲዎች ይለመልማሉ፡፡ አገር ታድጋለች፡፡ የዕለት ጉርሥ የዓመት ልብስ ይኖረናል ማለት ያባት ነው፡፡ ሆኖም ያ እስኪሳካ ድህነት አንድያውን እንዳያደቀን ሁሉን በወግና በቅጡ ማስተካከል፣ መቆጣጠር፣ መተግበር ያስፈልጋል፡፡ አለበለዚያ “ለመብላት የጠፋ ቅቤ፣ ስሞት ባፍንጫዬ ይፈስሳል” ይላል ዶሮ፤ እንደተባለው ይሆናል!

Read 6343 times