Monday, 23 December 2013 10:16

የአውሮጳ ፈላስፋዎችን የሚተቸው ኢትዮጵያዊው ፈላስፋ!

Written by  ደረጀ ኅብስቱ derejehibistu@gmail.com
Rate this item
(4 votes)

አፍሪካዊያን በሕይወት ጉዞ ውስጥ ያለፉበትን ሂደት በመመርመር ፍልስፍናዊ ትንታኔዎችን በመጻፍ የሚታወቀው የሞርጋን ዩኒቨርሲቲ ተባባሪ ፕሮፌሰሩ ፀናይ ሠረቀ ብርሃን፤ የአውሮጳ ፈላስፋዎች ለቀሪው የዓለም ክፍል ያላቸውን እይታ ይተቻል። የአውሮጳ አዙሪት ማለት ፣ድንበር አልባ የሆነ በዘመናዊነት አስተሳሰብ ውስጥ ስር የሰደደ የተሳሳተ የራስ ግምት ነው። “አውሮፓዊነት ከማንኛውም የሌላ አካባቢ ሰው የተለየ ፍጡር ነው  ብለን ስናስብ የአውሮፓ አዙሪት ውስጥ ነን ። ገና ካፈጣጠራችን ጀምሮ ከቀሪው ዓለም የላቅን ነን የሚል አመለካከት ላይ የተመሰረተ ሰብእና ነው የአውሮፓ አዙሪት ማለት” ይለናል ፀናይ። የአፍሪካ ፍልስፍና በምንለው ዘርፍ ውስጥ አንድ ብለን ልንቆጥረው የምንችለው አበሻ ፈላስፋ ፀናይ ሠረቀ ብርሃን ነው።
ይህ የአውሮፓ አዙሪት እንደ ፀናይ ገለጻ ከሆነ፣ እንዲሁ በቀላሉ በየሰፈሩ የሚወራ ብቻ ሳይሆን ደንበኛ ፍልስፍናዊ መሰረት ተሰጥቶት ፈላስፎች ሲሰብኩት የኖሩት ጉዳይ ነው። የአውሮጳዊውን ዘር ከፍ ከፍ የሚያደርግና ሌላውን የሰው ዘር የሚያንቋሽሽ ፍልስፍናዊ ጽሑፎች በስፋት ተሰርተዋል። አውሮጳዊ ሐሳቦችን እና የሐሳብ ቅርጾችን ማደናነቅና የሌላውን ማህበረሰብ እሳቤዎች ትቢያ ማድረግ የቅድመ ሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን አባዜ ነበረ። አፍሪካዊያን፣ህንዳዊያን፣እስያዊያን እና የአሜሪካ የጥንት ባለርስቶች /ቀይ ህንዶች/ እነዚህ ሁሉም የአውሮፓዊ ፍልስፍና መሳለቂያ ከመሆን አላመለጡም። መሳለቂያ የሚያደርጓቸውም ዛሬም ድረስ በፍልስፍና ሐሳቦቻቸው የምናደንቃቸውና የምንፈራቸው ታላላቅ ሰዎች ናቸው። ፀናይ እነዚህን ዋርካዎች ነው የሚገነዳድሳቸው (የጦቢያቱ  ልጅ ማንን ይፈራል!)
ፍልስፍና “ይህን ዓለም የሚመራው አዕምሮ ነው” በሚል እሳቤ ላይ ተመስርታ፤ ለራሷ የሰጠችው ዓለማቀፋዊ ተልዕኮ አላት። እናም ፈላስፎች ለሰው ልጅ የሚበጅ ታላቅ ነገር እንደ ሚሰሩ ያስባሉ፤ ነገር ግን “ችሎት አምባ” የምናቀርብበት ሰዓት  አሁን ነው ይለናል፤ ፀናይ ሠረቀ ብርሃን። ባንድ ጎን አለማቀፋዊ ተልዕኳችን ለሰው ልጅ እርባና ያለው ስራ ማቅረብ ነው እያሉ፣ በሌላ በኩል ደግሞ አውሮጳዊነትን ብቻ ከፍ ከፍ ማድረጋቸው ፍርደ−ገምድልነት ነውና ካሁን በኋላ ይህንን እንዲሰሩ መፍቀድ የለብንም ባይ ነው። የአውሮፓ አዙሪት የተጠናወታቸውን ጽሑፎች ከተደበቁበት ስርቻ እየፈለስን እያወጣን፣ የአውሮጳዊን የተሳሳተ የኅላዌ ግንዛቤ በማጋለጥ የአፍሪካን ፍልስፍና እንጠብቅ/እንከላከል።
አማኑኤል ካንት፤ በታሪክ ነክ ፖለቲካዊ ጽሑፎቹ ውስጥ፤ሔግል “በመብት ፍልስፍና” እና “በታሪክ ፍልስፍና” ስራዎቹ እንዲሁም ካርል ማርክስ በኮሚኒስት ማኒፌስቶ ስራው የአውሮፓን “ዘመናዊነት” እውነተኛው የሰው ልጅ ዘመናዊነት አድርገው ሲያቀርቡት፤ የሌላውን ክፍለ ዓለም ዘመናዊነት ግን ግልብ፣መሰረት የለሽ ያደርጉታል። ለፈላስፎቹ ዘመናዊነት ማለት ግዛትን ማስፋት ወይም ኮሎኒያሊዝም ማለት ነው፤ይለናል ፀናይ። ዘመናዊነት በሚከሰትበት ወቅት ሁሉ ነባር እምነትን ሳይንድ መከሰት አይችልም፤ በሃቅ ውስጥ ያለን የሃቅ እጦት ያጋልጣል፤ የሌሎችን እውነታ መውረር/ማስገዛት ስራው ነው። የአውሮፓው ዘመናዊነት ዓለምን በአምሳሉና በአርያው ለመፍጠር የተቀረውን ዓለም ማህበራዊ ስሪት እንኩትኩቱን አውጥቶ አስገዝቶታል። የሌሎችን የህይወት እውነታዎች አርሳ፣ገልብጣ፣አበስብሳ የእራሷን የአውሮፓን እውነታዎች በመትከል አውሮፓዊነት በዓለም ለመሰራጨት ችላለች።
ኢምፔሪያሊዝም ኅልዮት ሲሆን ኮሎኒያሊዝም ደግሞ የተግባር መገለጫው ነው፤ በዚህም መሰረት ጥቅም  ላይ ያልዋለ ያልተገዛን ድንበር ሁሉ ወደ አውሮፓዊ ከተሜ ማህበረሰብነት በመለወጥ ጥቅም እንዲሰጥ ማድረግ። አንዳንዱን ቀደምት ነዋሪዎች አስወግዶ ሌሎችን ግን በተከለለ ቦታ እንዲኖሩ ማድረግ አሊያም ከገጠር እንዳይወጡ ማገድ አሊያም ከተማ እንዳይመጡ መከልከል። ይህንን እና መሰል የአገዛዝ እርምጃዎችን በመውሰድ ለቆጠራም፣ለግብር ስብሰባም፣ለብዝበዛም እንዲመቹ ማድረግ። በዚህ መልኩ አውሮፓ እራሷን በዓለም ላይ እያስፋፋች አፍሪካን፣እስያን፣አሜሪካን መቆጣጠር ችላለች። በዚህም ስራዋ ምንም ጥፋት እንዳልተከናወነ ማሳመኛ ፍልስፍናዎችን መደርደር ተያያዘችው። የሳይንስ፣የግብረገብ እና የጠቅላላ ፍልስፍና ሙግቶች ሁሉ እየተዘረዘሩ የአውሮፓን የጉልበት እንቅስቃሴ እንደ መደበኛ ጉዳይ እንድንቆጥረው ወተወቱ።
አውሮፓ የተቀረውን ዓለም  የማሰልጠን ኃላፊነትን ለራሷ አሸክማ፣የሌሎችን ነጻነት እና ሉዓላዊነት እንደልቧ ለመገርሰስ ያመቻት ዘንድ ስልጣኔን አስፋፋለሁ ትላለች። “ስልጣኔን የማስፋፋት ተልዕኳችን ብቻ የቅኝ ግዛትን ለማስፋፋት ማሳመኛ ነጥብ ይሆነናል” ይሉ ነበር እንደነ ፕላሲት ቴምፕል ያሉት ሚሲዮኖች። ሬድዮናችን፣ጽሑፋችን፣ትምህርታችን ሁሉም ደጋግመው አፍሪካን ማሰልጠን እንዳለብን ይሰብካሉ። ከህዝቡም መካከል ስልጣኔ ማለት የቁሳቁስ ቁጥር መብዛት፣የሙያ መስክ ክህሎት፣የቤት ግንባታ፣ንጽህና እና ትምህርት ሥርዓት የሚመስላቸው በብዛት አሉ፤ይሉናል አውሮፓዊያን። ይህ ሁሉ መልካም እሴት ነው፤ ነገር ግን ስልጣኔ ማለት ይህ ብቻ ነው? የሰው ልጅ መንሰራፋት እና መስፋፋት ማለት አይደለም እንዴ? ፀናይ መልሶ ይጠይቃል።
ኪፕሊንግ በጣፈጠ ቋንቋ እንዳስቀመጠው፤ “የአውሮፓ ቅኝ ግዛት ተልዕኮ ግማሽ አውሬ ግማሽ ሰው የሆነውን ገጠሬ ማህበረሰብ ‘ሰው ሰው እንዲሸት’ ማድረግ ላይ ያተኮረ ነበረ።” አውሮፓ እራሷን የሁሉም ነገር መለኪያ አድርጋ በመቁጠር፣ የሌሎች እውነታ አልታያት ብሎ “በእውነታ ውስጥ እውነታ ጎድሏል” ትል ነበር - ‘lack of reality in reality’። ጽድቅን ማስፋፋት፣ስልጣኔን ማዳረስ፣መላውን ዓለም በአውሮፓ መስፈርት አውሮፓዊ ማስመሰል የቅድመ ሃያ አንደኛው የአውሮፓ ፍልስፍና ነበረ። አውሮፓ ከነግሳንግሷ እራሷን በዓለም ላይ ቅኝ ግዛት እንድትጭን ፍልስፍና ከፍተኛ ሚና ተጫውታለች። የካንት “ከድንቁርና መንጻት” እና “በእውቀትና በእኩልነት መፈወስ” ትርክት፤ እንዲሁም የሔግል “አለማቀፋዊ እሳቤዎችን መከወን”፤ እናም የማርክስ “በማህበረሰባዊ ስራ ከጭቆናና ከባይተዋርነት ነጻ መውጣት” ትምህርቶች ለዚያ ዘመኗ አውሮፓ፣ እንደ ጉሽ ጠጅ በኃይል ላይ ኃይል እየሰጧት ዓለምን ወረረች።
አለማቀፋዊ ነጻነት፣ የሰው ልጅ ምልዑነት፣የሰው ልጅ መንሰራፋት የሚሉት ሐሳቦች አውሮፓን የታሪክ ባለቤት ለማድረግ የሚቀርቡ በፍልስፍና ውስጥ ያሉ ቅድመ ጽሑፎች ናቸው /the text that comes before the text of humanity/(ወይም ደግሞ በለመድነው አማርኛ “ስውር ደባዎች” ናቸው ማለት እንችላለን)። እንዲህ ያሉ ድብቅ አጀንዳዎችን በማምረት ደግሞ አማኑኤል ካንትን የሚያክለው የለም። ይህንን ሐሳብ ፍሬድሪክ ኒቼ እና ሚሼል ፉኮ ይጋሩታል፤ “የሰው ልጅ” ሲል ካንት ምን ለማለት ፈልጎ ነው ይለናል ፉኮ (እንደ ዛሬዎቹ የቋንቋ (ደንቆሮ) መምህር ነን ባዮች ሳይሆን፤የቋንቋ ፈላስፋው ፉኮ ከፈረስ ጭራ የቀጠኑ ሐሳቦችን የሚረዳ ፈላስፋ ነበረ)። የሰው ልጅ በዘመነ አብርሆት ውስጥ ነው እያለ ካንት የሚያውጀው የትኛውን የሰው ልጅ ነው? የካንት የሰው ልጅ የሚለው ብያኔ አውሮፓን ብቻ የሚወክል ስለሆነ ችግር ያለበት ብያኔ ነው ይለናል ኢትዮጵያዊው  ፀናይ። ይህ አልበቃው ብሎ እንደውም እቅጩን ሲነግረን “የአፍሪካ ጥቁሮች በተፈጥሯቸው ከእንጭጭ ስሜት ውጭ ምንም የላቸውም” ይለናል ካንት። ተራ ግርድፍ ስራዎችን/ሐሳቦችን መከወን ይችሉ እንደሆነ እንጅ የረቀቀና የጠራ ስራ/ሐሳብ መከወን የሚችሉ አይደሉም ጥቁሮች፣ እንደማለት ነው - የካንት ሐሳብ።
አቶ ሔግልም በተራው ከአፍሪካዊያን/ኒግሮ መካከል አንድ ተሰጥዖ ያለው ቢገኝ አሊያም ስነ ጥበብ፣ሳይንስ፣ሌላም ዋጋ ያለው ችሎታ ያለው ቢገኝ “ጸጉር ከምላሴ ይነቀል” ይለናል። “ብዙ ነጮች ከታችኛው ማህበረሰብ ተነስተው እራሳቸውን ሲለውጡ እናስተውላለን፣ ነገር ግን ነጻ ከወጡት ጥቁሮች ውስጥ እንኳን አንድም ኒግሮ ሲሻሻል አይተን አናውቅም፤ ነጩ ግን በተለየ ክህሎቱ በዓለም ክብር ሲያገኝ እያየነው ነውና አዕምሮው ብቻ ሳይሆን የቆዳ ቀለሙም የተከበረ ነው” ይላል ሔግል። ጉድና ጅራት ከወደ ኋላ ነው ይባላል፤ ይኸውላችሁ ቀስ እያሉ ልክ ልካችንን እየነገሩን ነው የተከበሩት ፈላስፎቻችን። የሔግል ድምዳሜ ደግሞ የባሰበት ነው (ጽንፍ የያዘ )፤ የሰው ደረጃው እንደ የቆዳው ቀለም ጥቁረትና ንጣት መጠን  ይለያያል ሊለን ትንሽ ነው የቀረው (ኧረ እንደውም ከዚህ በላይ ሳይሆን አቀርም አባባሉ)። ነጭ ሰው ቢወድቅም ተፍጨርጭሮ ይነሳል፤ እራሱንም ከትላልቆች እኩል እስኪያደርስ ይጥራል። ጥቁር የሆነ እንደሆነ ግን በባርነት ቢሸጥም ያው ባሪያ ነው፤ ከባርነት ነጻ ብንለቀውም ከባርነት ዘመኑ የተሻለ ምንም ነገር አይሰራም። የነጭንና የጥቁርን ሰው የተፈጥሮ ልዩነት በዚህ ማየት እንችላለን እንደ ማለት ነው፣ ጋሽ ሔግል የሚለን።
አብርሆት ምንድን ነው? (‘What is Enlightenment?’) በሚለው የካንት ስራ ውስጥ እራሳችንን ከገባንበት ድቀት እና ባዶነት ነጻ ማውጣት ማለት ነው ይለናል። ነጻ ለመውጣት ደግሞ እራስን መገምገም/መተቸት፣እራስን መጠየቅና መልሱን መፈለግ ወሳኝ እርምጃዎች ናቸው። አመክንዮ እና ተጠየቅ ላይ ተመስርተን ያለንበትን ዘመን መገምገም ነጻ ለመውጣት መተኪያ የሌላቸው መፍትሄዎች ናቸው ይለናል - ካንት። ችግሩ የሚፈጠረው እነዚህን  ክህሎቶች እና ጸጋዎች አውሮፓዊ ማድረጉ ነው። ለካንት ጥቁር ማለት እንጭጭ ስሜቶችን ከማስተናገድ ባለፈ፤ የአመክንዮና የተጠየቅ ስልቶችን የመጠቀም ተፈጥሯዊ ብቃት የለውም፤ስለሆነም ወደ ብርሃን ዘመን መምጣት የሚችለው ነጭ እንጅ ጥቁርማ ስንኩል ነው ይለናል።
ፀናይ ሠረቀ ብርሃን፤ እነዚህን የተከበሩ ፈላስፎች ሐሳቦቻቸውን ከፍ ዝቅ እያደረገ  እያብጠረጠረ የአፍሪካ ፍልስፍና ብለን ስናስብ ያለፉ ደባዎችን ግምት ውስጥ በማስገባት መሆን እንዳለበት የሚያሳስበን፤ እንዳንዶቹ  አበሾች ለሆዱ ማደር ተስኖት እንዳልሆነ መገንዘብ ይቻላል። አውሮጳ እና ፈላስፎቿ በመስመር መካከል በቀጫጭኑ፣ እንዲሁም በእብሪት ባደባባይ የጻፉብን የሞት መልእክቶች ይዘውን ገደል እንዳይገቡ፤ በማንገዋለያ  እያንገዋለልን ምርቱን ከግርዱ መለየት የኛ የቤት ሥራችን መሆን አለበት። አንድ ዘመን ላይ አውሮፓ በራሷ ፍቅር አዙሪት ውስጥ ገብታ ያስመለሳት ቅርሻት፣ ለዛሬ ህይወታችን ጥላሸት እንዳይሆነን መጠንቀቁ የሚበጅ ምክር ይመስላል። ለፀናይ ግን ይህ ብቻ አይበቃውም፣ ለቀጣዩ ቸር ያሰንብተን።

Read 4309 times