Saturday, 14 December 2013 13:24

ጦጣ፤ ጠዋት ነጭ ሽንኩርት ተክላ፣ ማታ ወደ ቤት ስትመለስ ነቅላ፤ “አይ የመሬት ነገር፤ ይገርማል!” ትላለች - የወላይታ ተረት

Written by 
Rate this item
(20 votes)

አንድ ዝነኛ ዕዳና ነጋዴን የሚያሳይ ወግ አለ፡፡  ሲቆይ ተረት ይመስላል እንጂ ዕውነተኛ መሰረት አለው፡፡
ከዕለታት አንድ ቀን በአንድ ከተማ፣ አንድ ባለፀጋ ቱሪስት፣ ወደ አንድ ሆቴል ይመጣል፡፡ በዚህ ወቅት በዚያ ከተማ ዝናብ በጣም ይዘንባል፡፡ከተማው የተወረረ ይመስላል፡፡ ሰው በመንገድ አይታይም።  ጊዜው ክፉ ጊዜ ነው፡፡ ሰው ገንዘብ ስለሌለው አንዱ ከአንዱ እየተበደረ ነው የሚኖረው፡፡ ብድር የሌለበት ሰው የለም፡፡ ዕዳ በዕዳ ሆኗል ከተማው፡፡
ባለፀጋው ቱሪስት እንግዲህ የመጣው ይሄን ሰዓት ነው፡፡ ጥሩ መኝታ ያለው ትልቅ ሆቴል ፍለጋ ላይ ነው፡፡ ብዙ ሆቴሎች አይቶ የተመቸ አይነት ክፍል አላገኘም፡፡ ይሄኛውን ሆቴል በዐይኑ ወዶታል፡፡
“ጤና ይስጥልኝ” አለ ወደ ሆቴሉ ባለቤት ቀርቦ፡፡
“እንኳን ደህና መጡ ጌታዬ”
“ጥሩ ክፍል አላችሁ - ለመኝታ?”
“አዎ ጌታዬ፤በጣም በርካታ ክፍሎች አሉን፡፡ ቢፈልጉ ምድር ቤት፣ቢፈልጉ ፎቅ ላይ፡፡ ብዙ ዓይነት ክፍሎች አሉን”
“መልካም፤ የሚያሳየኝ ልጅ መድብና ክፍሎቹን ልያቸው፤ከተስማማኝ ልጁን እልከዋለሁ - ትመዘግበኛለህ፡፡ ካልተስማማኝ ራሴ እመጣለሁ፡፡ ይኸው ይሄንን መቶ ዶላር ያዝ” ብሎ ባንኮኒው ላይ ብሩን አስቀምጦ ወደ ፎቁ ወደ ሚያወጣው ደረጃ ሄደ፡፡
የሆቴሉ ባለቤት ፈጠን ብሎ መቶ ዶላሩን ወስዶ አጠገቡ ለሚገኘው ባለልኳንዳ ዕዳውን ከፈለ፡፡
ባለልኳንዳው ደግሞ ወዲያው፤ በሬ ለሚያመጣለት በሬ - አድላቢ - ነጋዴ ዕዳውን ሊከፍል በረረ፡፡ በሬ አድላቢው - ነጋዴ በበኩሉ፤ መኖና አትክልት ወደሚያቀርብለት ነጋዴ በፍጥነት ሄደና “እንካ ዕዳዬን አወራርድ” አለው፡፡
መኖና አትክልት አቅራቢው ነጋዴ ደግሞ እየበረረ በከተማው ወደታወቀችው ሴተኛ አዳሪ ሄዶ፤ በክፉ ጊዜ በዱቤ ስላሳደረችው አመስግኖ 100 ዶላሩን ሰጥቶ ከዕዳ ነፃ ሆነ፡፡
ሴተኛ አዳሪዋ በጣም ፈጥና ወደዚያ ሆቴል ሄደች፡፡ ከዚያም፤ ደምበኞቿን እያመጣች በተከታታይ በዱቤ የተኛችበትን የክፍል ሂሳብ ለባለ ሆቴሉ ዕዳዋን ከፈለች፡፡
ባለሆቴሉ ያንን መቶ ዶላር ባንኮኒው ላይ አስቀመጠው፡፡ ቱሪስቱ እንዳይጠረጥርም፤ በትክክል ባስቀመጠበት ቦታ ነው ያኖረለት፡፡ ባለፀጋው ቱሪስት የፎቁን የመኝታ ክፍሎች ሁሉ ሲያይ ቆይቶ፣ አንዱም ሳይስማማው ስለቀረ፤ ከፎቁ ወርዶ፣ወደ ባለቤቱ መጣ፡፡ ከዚያም “የሆቴሉን መኝታ ክፍሎች፣ በሙሉ ለማለት እችላለሁ፤አየሁዋቸው፡፡አንድም ክፍል እኔ የምወደው ዓይነት አልሆነልኝም፡፡ ስለዚህ 100 ዶላሩን ስጠኝና  ሌላ ቦታ ልፈልግ” አለ፡፡
“በጣም እናመሰግናለን ጌታዬ” አለ ባለሆቴሉ፤ በትህትና ገንዘቡን እየሰጠ፡፡
ባለፀጋው ቱሪስት ገንዘቡን ተቀብሎ ሄደ፡፡
በዚህ የመቶ ዶላር ታሪክ ውስጥ፤ ማንም ምንም ገንዘብ አላገኘም፡፡ ያም ሆኖ የከተማው ነጋዴዎች አሁን ዕዳቸውን አቃለዋል፡፡ ወደፊት ያልፍልናል ብለው በተስፋ ተሞልተው ተቀምጠዋል፡፡
*     *     *
የትኛውም ባንክና ኢንሹራንስ በዚህ ህግ እንደሚሰሩ ልብ እንበል!
ዕዳ ስንፈራረም የነገ እጣችንን እናስብ፡፡ ማ እየተጠቀመብን እንደሆነ እናስብ፡፡ ስልጣኔ ብዙው እጁ ከቀናን መበዝበዝ ካልቀናን መበዝበዝ ነው፡፡ “ዕዳ ይሻግታል እንጂ አይበሰብስም (a debt may get moldy but it never decays) ይላል፤ ናይጄሪያዊው ደራሲ ቺኑዋ አቼቤ፡፡
“ሰርቼ እከፍላለሁ” ብሎ መበደር የያያዋጣበት ጊዜ አለ፡፡ ግን ሁል ጊዜ አያዋጣም፡፡ በተለይ ደሀ አገሮች የሚያስይዙት ንብረት ወይም ቅድመ - ሁኔታ (conditionality) ስለሚኖር መቼ እጃቸውን ተጠምዝዘው አንዳች ግዳጅ ውስጥ እንደሚገቡ ማስተዋል ይገባቸዋል፡፡ “አሁን እየተበደርን ባለንበት ፍጥነት በሶስት አመት ጊዜ ውስጥ ከ2ኛው ዓለም ጦርነት ጀምረን የገነባናቸው ህንፃዎች በሙሉ የኛ አይደሉም ማለት ነው” ይላል አሜሪካዊው ኢኮኖሚስት ፖል ቮልከር፡፡ ይህን አጥብቆ ልብ - ማለት ይገባል! ብድር እንዲህ ከሆነ እግዚሃር ያውጣን፡፡ ነገን ሳናጤን የምንጓዝበት መንገድ ትውልድን የማይችለው ጣጣ ውስጥ መክተት ነው፡፡ “ያባት ዕዳ ለልጅ” የሚለውን ስሜት በአግባቡ መመርመር ግዴታ ነው! “የኑሮ ደረጃችን እየተጠገነ ያለው በምርታማነት! ወይም በደሞዛችን አይደለም፡፡ በውጪ አገር ካፒታል እንጂ”  የሚለውን የጄፍሬይ ሳችስ (ታይም) አስተሳሰብ ጠለቅ ብሎ ማየት ያባት ነው! የሀገር ዕዳ ከነእንድምታው መጤን ይኖርበታል፡፡ ብድር የኢኮኖሚ ጉዳይ ብቻ ነው ብለን ካሰብን ቢያንስ የዋህነት አጥቅቶናል፡፡
“በሃገር ደረጃ ያለ ዕዳ ጥሩ ነገር ነው፡፡ አደገኛው ነገር ግን መልሰን እንዳንከፍል የፖለቲካል ኢኮኖሚ ጣጣ መኖሩ ነው” ይላል የብሪታኒያው ስላቅ ፀሃፊ ደብሊው ሴላር፡፡
ዕዳ አባዜው ብዙ ነው፡፡ የዕዳ ማስወገድን ችሎታና ጥበብ ከላይ የጠቀስነው፤ ተረት - መሰል ዕውቀት ይነግረናል! “ለኗሪዎች አክብሮትን፣ ለሟቾች ዕውቀትን የመስጠት ዕዳ አለብን”
የሚለው የፈላስፋው ቮልቴር አባባል ደግሞ፤ የራሳችንን ሰዎች እንዴት እንደምናከብር ይጠቁመናል።
የአገራችን ትላልቅ አበዳሪ ነጋዴዎች ስናይ ተበዳሪዎች ጤና መሆናቸውን ለማረጋገጥ በየሆቴል ጅምናስቲክ መስሪያ ቦታ ማለዳ እየሄዱ ያረጋግጣሉ፤ይባላል፡፡
“ዕመነኝ አበዳሪዎችህ፤ በቆራጥነት አምላክ ዕድሜህን እንዲያረዝምላቸው ይፀልያሉ፡፡ ከአንተ ሞት የበለጠ የሚያስፈራቸው ነገር የለምና!” ይለናል ፈረንሳዊው ምፅታዊ ደራሲ ፍራንሷ ራቤሌ፡፡ እናስብበት!
አገር በዱቤ መተዳደሯ፤መጨረሻው አሰቃቂ ነው!
“በመበደርና በእዳ ላይ የተመሰረተ ቤተሰብ አንድም ነፃነትን፣ አንድም ውበትን ያጣ ይሆናል” የሚሉትን ፈረንጆች፤ “በሽታ የሌለበት ክሳትና እዳ የሌለበት ድህነት አያሳስብም” በማለት ያጠናክረዋል፤ የወላይታ ተረት፡፡ አገርን በብድር ማስተዳደር አዳጋች የመሆኑን ያህል፤ ብድርን ለመክፈል፤ በጥድፊያ አገር እናለማለን ብሎ ማለምም አደጋ አለው፡፡ ሆነ ራሳችንን የምናይበት የሀብት ማፍራት መንገድ፤ በቅጡ የተፈተሸና በተግባር የተፈተነ መሆን ይኖርበታል፡፡ ምርታማነታችንና አልሚነታችን መፈክርና ዲስኩር ላይ የተንጠለጠለ ሳይሆን፤ በእርግጥ የኢኮኖሚ መስፈርቶችን ቁቤ ያለ ቢሆን አግባብነትና አስተማማኝነት ይኖረዋል፡፡ አለበለዚያ “ጦጣ፤ ጠዋት ነጭ ሽንኩርት ተክላ፣ ማታ ወደቤት ስትመለስ ነቅላ፤ “አይ የመሬት ነገር፤ ይገርማል!” ትላለች፤ የተባለው የወላይታ ተረት ይመጣል፡፡

Read 8767 times