Saturday, 03 December 2011 08:24

ሩሲያና ቻይና ፀረ-ምዕራባዊያን አቋም በመያዝ ወዳጅነታቸው አጠናክረዋል

Written by  ጥላሁን አክሊሉ
Rate this item
(2 votes)

እ.ኤ.አ በ1941 ዓ.ም የኮሚኒስት ሥርዓት መንኮታኮትን ተከትሎ የቀድሞዋ ሶቭየት ሕብረት ከፈራረሰች በኋላ፣ የዓለምን የፖለቲካና የኢኮኖሚ ሥርዓት በበላይነት ለሁለት አስርት አመታት ስትቆጣጠር የነበረችው አሜሪካ፤ በአብዛኛው የዓለም ክፍል ተጽዕኖ አሳድራለች፡፡ በፖለቲካ አቋማቸው ዲሞክራሲያዊ እንደሆኑ ከምትገልጻቸው አገሮች ጋር መልካም የዲፕሎማሲ እና የንግድ ግንኙነት ስትመሰረት፣ ዲሞክራሲያዊ ያልሆነ ሥርዓትን የሚያራምዱ አገራትን ደግሞ ከመተቸትና ከመንቀፍ ባሻገር፣ አምባገነን መሪዎችንም ከስልጣናቸው አሰናብታለች፡፡ ባለፉት 20 ዓመታት ብቻ በርካታ መሪዎች በአሜሪካ ጣልቃ ገብነት ወይ ተገድለዋል አሊያም ከስልጣናቸው ተወግደዋል፡፡

ለአካባቢውና ለዓለም ስጋት ናቸው የምትላቸውን አገራት ደግም ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እንዲገለሉ በኢኮኖሚ ማዕቀብና በቃላት ውግዘቶች ተጽዕኖዋን አሳርፋለች፡፡ በተለይም እንደ ኢራን እና ሰሜን ኮሪያ ያሉ አገራት እያካሄዱ ካሉት የኒውክሊየር ግንባታ ጋር በተያያዘ ተደጋጋሚ ውንጀላዎችን ሰንዝራባቸዋለች፡፡ 
በርካታ አገራት ከልዕለ ሀያሏ አገር የሚደርስባቸውን ጫና በመፍራት፣ ሳይወዱ በግድ ከፀረ-ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ወደ የይስሙላ ዲሞክራሲ (Pesudo democracy) እንዲሁም ከፍፁማዊ አምባገነንነት (absolute dictatorship) ወደ ከፊል አምባገነንነት (Partial dictatorship) ተቀይረዋል፡፡ ለአብነት መሀመድ ጋዳፊ በምዕራባዊያን በተለይም በአሜሪካና በእንግሊዝ ላይ ከሶስት አስርት አመታት በላይ ሲደነፉና ሲያቅራሩ ከቆዩ በኋላ፣ የሳዳም ሁሴን መገደልን ተከትሎ፣ (ምናልባት ቀጣዩ እኔ ልሆን እችላለሁ በሚል ስጋት) ለዘብተኛ አምባገነን መሆን ጀምረው ነበር፡፡ እ.ኤ.አ ከ2003 ጀምሮም ከምዕራቡ ዓለም ጋር በሁሉም ነገር እንደሚተባበሩ በመግለጽ ወዳጅነትን መስርተዋል፡፡ ነገር ግን መጋቢት ወር ላይ ሕዝባዊ አመጽ ሲነሳ እርሳቸውም ወደ ፍፁማዊ አምባገነንነታቸው ተመልሰዋል፡፡ ቀድሞ ጠላቶቻቸው ከዚያም ወዳጆቻቸው የነበሩት ምዕራባዊያንም እንደገና ጠላታቸው ሆነው አሰናበቷቸው፡፡
ዩናይትድ ስቴትስ በፖለቲካው መስክ የበላይነትን እንደተቀዳጀች ሁሉ፣ የዓለም ኢኮኖሚንም በመምራት ረገድ ከፍተኛ ሚና ተጫውታለች፡፡ ራሷን የዓለም የኢኮኖሚ ማዕከል በማድረግ ከበርካታ አገራት ጋር ጠንካራ የንግድ ትስስር መስርታለች፡፡ በ2007/08 የፋይናንስ ተቋማት መናጋትን ተከትሎ የምጣኔ ሀብት ቀውስና የበጀት እጥረት ውስጥ ብትገባም፣ የዓለም የኢኮኖሚ የበላይነት አሁንም በእሷ እጅ ነው፡፡ ከአሜሪካ ቀጥላ ኢኮኖሚዋ በሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ቻይናን ጨምሮ የብዙ አገሮች (ያደጉና በማደግ ላይ የሚገኙ አገሮች) ኢኮኖሚ የተገነባውም ከአሜሪካ ጋር ባላቸው የንግድ ግንኙነት ነው፡፡
በቅርቡ በአሜሪካ የደረሰውን የኢኮኖሚ መዋዠቅ አስመልክቶ የቻይና የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ሲናገሩ፣ “የአሜሪካ ኢኮኖሚ ከወደቀ የቻይና ኢኮኖሚም አደጋ ላይ ይወድቃል” ብለዋል፡፡
አሜሪካ ባላት ግዙፍ ኢኮኖሚና ፈርጣማ ወታደራዊ ጡንቻዋ ተጽዕኖ ያላሳደረችበት አገር የለም ለማለት ይቻላል፡፡ በብዙ የደቡብ አሜሪካ አገራት የማትፈልጋቸውን መሪዎች በማስወገድ የፈለገችውን አስቀምጣለች፡፡ ነገር ግን እ.ኤ.አ በ1994 ዓ.ም በሱማሊያ 25ሺ ወታደሮችን አሰማርታ፣ ሶማሊያዊያን በወታደሮቿ ላይ ካደረሱት አስከፊ ጥቃት በኋላ ለቃ መውጣቷ የሚታወቅ ሲሆን፣ ከዚያ በኋላ ግን በአገሮች የውስጥ ጉዳይ ብቻዋን ጣልቃ ከመግባት ይልቅ ምዕራባዊያን አጋሮቿን ይዛ ለመግባት ተገዳለች፡፡
ከመስከረም 11,2001 የአሸባሪዎች ጥቃት በኋላ፣ አሜሪካ ከእንግሊዝ ጋር በመሆን በአፍጋኒስታን የታሊባንን አስተዳደር ሲያስወግዱ የአልቃይዳን አከርካሪ ሰብረዋል - ቢንላደንን አድኖ በመግደል፡፡ በተመሳሳይ በ2003 ዓ.ም ሁለቱ አገራት የሳዳምን አገዛዝ ገርስሰዋል፡፡
በዓረቡ ዓለም ሕዝባዊ አመጽ እንደተነሣ መሪዎቹ ለሕዝቡ ጥያቄ ምላሽ እንዲሠጡ፣ አንዳንዶቹ ስልጣን እንዲለቁ አሜሪካና ምዕራባዊያን ጠይቀዋል፡፡ አሜሪካ የ30 ዓመት ወዳጇ በሆኑት በሙባረክ ላይ ሕዝባዊ አመጹ ሲነሣባቸውም ስልጣን እንዲለቁ አሳስባ ነበር፡፡ በፖለቲካ ቋንቋ “ዘላቂ ጥቅም እንጂ ዘላቂ ወዳጅነት የሚባል የለም” የሚለው አገላለጽ በሙባረክና በአሜሪካ በግልጽ ታይቷል፡፡ ሙባረክ በሕዝብ ጥያቄ ከወረዱ በኋላ፣ በጋዳፊ ላይ ነፍጥ ይዘው የተነሱትን ተቃዋሚዎች ለመደገፍ አሜሪካ፣ እንግሊዝና ፈረንሣይ፣ ኔቶ መራሹን ጦር ወደ ሊቢያ በማዝመት ለጋዳፊ አገዛዝ መውደቅ ትልቁን ሚና ተጫውተዋል፡፡
ከሊቢያ በኋላም ትኩረታቸውን በሶሪያ ላይ ያደረጉት አሜሪካና ምዕራባዊያን የበሽር አል-አሳድ አስተዳደር በተቃዋሚዎቹ ላይ የሚወስደውን የኃይል እርምጃ በተደጋጋሚ ከማውገዛቸው በላይ በሶሪያ ላይ የኢኮኖሚ ማዕቀብ ተደርጓል፡፡ እስካሁን በሶሪያ ላይ ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት እንደሚያደርጉ ባይታወቅም በሽር አል-አሳድ ስልጣን እንዲለቁ ጠንካራ ጫና እያደረጉባቸው ይገኛሉ፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ አሜሪካና ምዕራባዊያን በአረቡ ዓለም የሚያደርጉትን ጣልቃ ገብነት ከሊቢያ ጀምሮ መቃወም የጀመሩት ሩሲያና ቻይና፤ በሶሪያ ላይ የሚደረገውን ጫና አጥብቀው እየተቃወሙ ይገኛሉ፡፡ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ኢኮኖሚዋ ፈጣን ዕድገት እያሳየ የመጣው ቻይናና ሩሲያ ሁለቱም ኃያላን አገሮች ሲሆኑ፣ ከምዕራባዊያን በተቃራኒ መሰለፋቸውን በይፋ ማሳየት ጀምረዋል፡፡ “ፎሬን ፖሊሲ” የተባለው መጽሔት ሰሞኑን The Axis of No! በሚል ርዕስ ባወጣው ዘገባ፣ ቻይና እና ሩሲያ ፀረ ምዕራባዊያን አቋምን በስፋት እያንፀባረቁ እንደሆነ ጽፏል፡፡
ቻይናና ሩሲያ ወዳጅነታቸውን በማጠናከር ወደ ዓለም መድረክ መምጣታቸውን የገለፁት የፎሬን ፖሊሲ ፀሀፊ ሩሲያዊው ዲሚትሪ ትሬኒን፤ ሁለቱም አገራት በፀጥታው ምክር ቤት ድምጽን በድምጽ የመሻር መብታቸውን ተጠቅመው የአሜሪካንና የምዕራባዊያንን ዓለም አቀፍ የፖለቲካ የበላይነትና ጣልቃ ገብነት እየተቃወሙ ናቸው ብለዋል፡፡
አሜሪካና ምዕራባዊያን ከፖለቲካ አስተዳደር እና ከኢኮኖሚ ስርዓት ተመሣሣይነት በተጨማሪ በብዙ ነገሮች አንድነት ያላቸው ሲሆን፣ ቻይናና ሩሲያ ግን ልዩነት አላቸው፡፡ ቻይና ማኦኢዝምን እንደተወች ብትገልጽም አሁንም ድረስ ሶሻሊስት ነች፡፡ ሩሲያ ደግሞ ከ20 ዓመት በፊት ሶሻሊዝምን እርግፍ አድርጋ ትታለች፡፡ በሁለቱም አገራት እንደ ምዕራቡ ዓለም ነፃና ፍትሃዊ ምርጫ ብሎ ነገር የለም፡፡ የሁለቱ አገራት መንግስታት ፈላጭ ቆራጭ ናቸው፡፡ ኢኮኖሚያዊ ግንኙነታቸውም እንደምዕራቡ ዓለም መጠቃቀምን ብቻ ሳይሆን መፎካከርንም ይጨምራል፡፡ በዚህ አይነት ልዩነት ውስጥ ሆነውም ግን ወዳጅነት መመስረት አላዳገታቸውም፡፡
ቻይናና ሩሲያ በመካከለኛው ምስራቅ የኢኮኖሚ ተጠቃሚ ሲሆኑ፣ የምዕራባዊያንን ጣልቃ ገብነትንም የሚኮንኑትም ከኢኮኖሚ ተጠቃሚነታቸው በመነሣት እንደሆነ የሚገልጹት ጸሀፊው፣ ቻይና 25 በመቶ ነዳጅ የምታገኘው ከኢራን ሲሆን፣ አሜሪካ በኢራን ላይ እያሳደረች ያለውን ጫናም አጥብቃ ትቃወማለች ብለዋል፡፡
በሊቢያ የጋዳፊ አስተዳደር ዘመንም ቢሆን፣ ቻይና ተጠቃሚ ነበረች፡፡ 20ሺህ የሚጠጉ ቻይናዊያን ሠራተኞች በሊቢያ በኮንስትራክሽንና በመንገድ ሥራ ተሠማርተው ይገኙ የነበረ ሲሆን፣ ጦርነቱ ሲነሣም ሊቢያን ለቀው ለመውጣት ተገደዋል፡፡ በግብጽ የሙባረክ አስተዳደር ዘመን ደግሞ፤ ሩሲያ ለግብጽ የኒውክሊየር ኢነርጂ ገንብታ ነበር፡፡ አሁን ግን ሩሲያዊያን ቱሪስቶች እንኳን በተፈጠረው የፖለቲካ አለመረጋጋት ምክንያት ወደ ግብጽ ለመሄድ አለመቻላቸውን የጠቆመው ፀሐፊው፤ ሙባረክ የአሜሪካ ወዳጅ መሆናቸው ቢታወቅም ከሩሲያም ጋር ግንኙነት መስርተው እንደነበር ጽፏል፡፡
በሌላ በኩል ሩሲያ እ.ኤ.አ ከ1960 ዓ.ም ጀምሮ ከሶሪያ ጋር በፈጠረችው ግንኙነት ሳቢያ በበሽር አል-አሳድ አስተዳደር ላይ የሚደረገውን ጫና አትቀበለውም፡፡ የሶሪያ ወታደራዊ ኃይል በሩሲያ የሰለጠነ ሲሆን፣ በተጨማሪም ታርቱስ የተባለው የሶሪያ ወደብ ላይ የሩሲያ ባህር ኃይል ሠፍሯል፡፡ ምናልባት ምዕራባዊያን በሶሪያ ላይ የኃይል እርምጃ የሚወስዱ ከሆነ፣ የሩሲያው ባህር ኃይል ለመከላከል መንቀሳቀሱ እንደማይቀር ተገልጿል፡፡
ሩሲያ በተነሣባቸው ሕዝባዊ አመጽ አጣብቂኝ ውስጥ የገቡትን በሽር አል አሳድን ለመርዳት ደፋ ቀና እያለችም ነው፡፡ በሽር አል-አሳድ ሕዝባዊ አመጹን በኃይል ለመጨፍለቅ ከሚሞክሩ የፖለቲካ ተሃድሶ እንዲያደርጉም እየገፋፋች ትገኛለች፡፡ በተጨማሪም ተቃዋሚዎቹንና መንግስትን በተናጠል አነጋግራለች፡፡ በተመሣሣይ ቻይናም የሩሲያን አቋም በመጋራት በሽር አል-አሳድ አንዳንድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች እንዲያደርጉ ምክሯን ለግሳለች፡፡ ሁለቱም ኃያላን አገራት አሜሪካና ምዕራባዊያን በበሽር አል-አሳድ ላይ ከሚያሳድሩት ተጽዕኖ በተቃራኒ ድጋፋቸውን ለሶሪያ መንግስት እየሰጡ ይገኛሉ፡፡
የቻይና ባለስልጣናት ምዕራባዊያን የዲሞክራሲና ሰብዓዊ መብት መጣስን እንደ ምክንያት በማቅረብ የሶሪያን ሕዝብ ለመርዳት በሚል የሚያደርጉት ጣልቃ ገብነት ተቀባይነት የለውም ብለዋል፡፡ ባለስልጣናቱ አያይዘውም አንድ መንግስት በዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲወርድ በማስፈራራትና ጫና በማሳደር እንዲሁም ወታደራዊ ኃይል ተጠቅሞ ማውረድ በጠቅላላው ጣልቃ ገብነት በመሆኑ የቻይና መንግስት አይቀበለውም ብለዋል፡፡
የፎሬን ፖሊሲ መጽሔት ፀሐፊ በጽሑፋቸው ላይ የሩሲያንና የቻይናን አቋም ክፉኛ ተችተዋል፡፡ ሞስኮና ቤጂንግ እንዳሉት በሊቢያ የኔቶ ጦር ባይገባ ኖሮ፣ ሊቢያዊያን ከጋዳፊ አገዛዝ እንዴት አድርገው ነው ነፃ ሊወጡ የሚችሉት ያሉት ፀሐፊው፤ ምናልባትም ኔቶ ባይገባ ኖሮ የጋዳፊ ጦር ተቃዋሚዎቹን ድምጥማጣቸውን አጥፍቶ ነበር ብለዋል፡፡ “የሊቢያን ሕዝብ ውጭ ሆኖ በመደገፍ ብቻ ጋዳፊን የሚያክል ግትር አምባገነን መሪን ማስወገድ እንደማይቻል እንኳን ሩሲያንና ቻይናን የሚያህል ታላቅ አገራት ይቅርና መላው ዓለም የሚያውቀው ነው፡፡”
በተመሳሳይ የበሽር አል-አሳድ አስተዳደር፣ በሶሪያዊያን ላይ የሚወስደው የጭካኔ እርምጃ እየጨመረ በመጣበት በዚህ ጊዜ ሁለቱም አገራት ከሶሪያውያን እልቂት ይልቅ ለሶሪያ መንግስት ጥብቅና ቆመዋል፡፡ ከሶሪያ መንግስት ጋር የረጅም ጊዜ ግንኙነት ያላት ቱርክ፣ በሽር አል አሳድ ስልጣን እንዲለቁ ስታሳስብ ሩሲያና ቻይና ግን አሁንም ድረስ ለበሽር አል-አሳድን ጠንካራ ድጋፋቸውን እየሰጡ ይገኛሉ፡፡
በመካከለኛው ምስራቅ ጠንካራ ስትራቴጂ በመዘርጋት የኢኮኖሚ ጥቅም የሚጋሩት ሩሲያና ቻይና፣ በሶሪያ በስልጣን ላይ የሚገኘውን የበሽር አል-አሳድ አስተዳደር ከፖለቲካ ገጽታው የበለጠ ሃይማኖታዊ ቀውስ ሊያስከትል እንደሚችል አልጠፋቸውም፡፡ ሶሪያ የሱኒ፣ የሺአይት እና የአላዊት ሙስሊሞች መኖሪያ ስትሆን በይበልጥ ሱኒዎች ይኖሩባታል፡፡ በስልጣን ላይ የሚገኘው የበሽር አል አሳድ አስተዳደር ደግሞ አለዊትስ የተባሉ ሙስሊሞች ናቸው፡፡
እነዚህ ሙስሊሞች ደግሞ ከሱኒዎች ይልቅ ለሺአይቶች በጣም ይቀርባሉ፡፡ ብዙሃን ሺአይቶች የሚገኙባት ኢራንና መንግስቷም ጭምር የሺአይት ሙስሊሞች ናቸው፡፡ ሺአይት የሆነው የፕሬዚዳንት አህመዲን ኒጃድ መንግስትም አለዊትስ ከሆነው ከበሽር አል አሳድ አስተዳደር ጋር የጠበቀ ወዳጅነት አለው፡፡
አሜሪካና ምዕራባዊያን የሶሪያ መንግስት እያደረሰ ካለው ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት በተጨማሪም ከኢራን ጋር ባለው ግንኙነት የተነሳም እንዲወገድ ይፈልጋሉ፡፡ በመካከለኛው ምስራቅ ራሷን ኃያል አገር አድርጋ የምትቆጥረው ኢራን፤ በሜድትራኒያን አካባቢ የበለጠ በመጠናከር የእስራኤልን ኃያልነት ለማዳከም ለረጅም ጊዜ የወጠነችው ስትራቴጂያዊ ዕቅድ ሲሆን፣ እቅዷን ተግባራዊ ለማድረግም ብዙሀን የሱኒ ሙስሊም መንግስታት ከበዙበት የአረብ አገራት ይልቅ የአለዊትስ ሙስሊም ከሆነው ከሶሪያ ጋር መተባበር ነበረባት፡፡
በመካከለኛው ምስራቅ የኢራን መንግስት ብቸኛ ወዳጅ ሶሪያ ስትሆን፣ በሶሪያ ላይ ከተነሳው ሕዝባዊ አመጽ በኋላ የበሽር አል አሳድን መንግስት ከሩሲያና ቻይና ሌላ የምትደግፈውም ኢራን ነች፡፡ ምናልባት የበሽ አል አሳድ አስተዳደር ቢወድቅ በሶሪያ ስልጣን የሚይዘው የሱኒ ሙስሊሞች መንግስት በመሆኑ ከሺአይቱ ኢራን ጋር ሆድና ጀርባ እንደሚሆኑ ጥርጥር የለውም፡፡
የኢራን መንግስት ይህንን በማወቁም በሶሪያ የተቀሰቀሰውን ሕዝባዊ አመጽ በኃይል ለመደምሰስ ለሶሪያ ወታደሮች ተጨማሪ ስልጠናና የጦር መሣሪያ ድጋፍ አድርጓል፡፡
“Assad’s Hope for survival” በሚል ርዕስ ለንባብ የበቃው The Middle East መጽሔት ደግሞ፣ የኢራን እስላሚክ አብዮት ጋርድ ኮርፕስ (Isalmic Revolutionary Guard corps) እና አል ቅዱስ (Al Quds) የተባለው የኢራን ጦር፤ ሕዝባዊ አመጹን ለመበተን በሶሪያ መሰማራቱን ገልጿል፡፡ በሕዝባዊ አመጽ ሰልፈኞቹ ላይም ጠንካራ እርምጃ የወሰደው ከኢራን የመጣው ጠንካራው ጦር እንደሆነ መጽሔቱ ገልጿል፡፡
ሶሪያ ከኢራን ወታደራዊ ድጋፍ ማግኘቷን ሶሪያም ሆነች ኢራን ቢያስተባብሉም፣ የአሜሪካና የእስራኤል የደህንነት ምንጮች ግን ከኢራን ጦር ሌላ መቀመጫውን በሊባኖስ በማድረግ በኢራን እየተደገፈ በእስራኤል ላይ ጥቃት የሚፈጽመው ሂዝቦላም በሽር አል አሳድን ለመርዳት ወደ ሶሪያ መግባቱን አረጋግጠዋል፡፡ በሶሪያ ሕዝባዊ አመጽ እየተደረገ ባለበት ሁኔታ ሶሪያውያን፣ ኢራን መንግስታቸውን እየደገፈ መሆኑን በመገንዘብ የኢራንን ባንዲራ በደማስቆ አደባባይ አቃጥለዋል፡፡
የሕዝባዊ ሰልፈኞቹ ድርጊት የኢራን ባለስልጣናትን ያሸማቀቀ ቢሆንም፤ ዓለምአቀፉ ማኅበረሰብ ከሶሪያ ጀርባ ኢራን እንዳለች ተረድተዋል፡፡ የ”ፎሬን ፖሊሲ” ፀሐፊው ዲሚትሪ፤ የሶሪያ መንግስት ጠንካራ ደጋፊ የሆኑት ሩሲያና ቻይና የሶሪያ መንግስት ከወደቀ የወዳጃቸው የኢራንን የረጅም ጊዜ ስትራቴጂካዊ እቅድ ባዶ ቅዠት ሊያስቀርባቸው እንደሆነ በመገንዘብ አሁንም ድረስ አፋፍ ላይ የሚገኘውን የበሽር አል አሳድ አስተዳደር ምዕራባዊያን ከሚያሳድሩበት ጫና እየተከላከሉ ይገኛሉ፡፡ ፀሐፊው ሲያጠቃልሉም፤ ሩሲያና ቻይና ለመካከለኛው ምስራቅ የተሻለ መፍትሔ ከማቅረብ ይልቅ “No!” በሚል ማውገዝ ብቻውን አይሠራም በማለት አብራርተዋል፡፡

 

Read 6223 times Last modified on Saturday, 03 December 2011 08:27